Friday, March 25, 2011

አዲስ አበባንና ባህር ዛፍን ያስገኘልን መዘዝና አንድምታው

(ጌታቸው አሰፋ) ጊዜው 1981 ዓ।ም। ነበር ። እኔም 11ኛ ክፍል ነበርኩ። መኝታ ቤታችን ውስጥ ከነበረው ቁም ሳጥን ላይ የእጅ መዳፍ የምታህል ላስቲካማ ወረቀት ተለጥፋለች። ውሃ ሰማያዊ መደብ፤ ቀይ ጠርዝ መሐል ላይ ቢጫ አበባ። ቁም ሳጥኑ ላይ ከተለጠፈች ሁለት ዓመት ሆኗታል። የአዲስ አበባን መቶኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀች ነበረች። በ1979 ዓ।ም। መሆኑ ነው። ዛሬ አዲስ አበባ የ124 ዓመት “ጎልማሳ” ነች። የአክሱም፤የጎንደር፤የላሊበላ፤የአንኮበር፤ የእድሜ የታናሽ ታናሽ - አዲስ አበባ። ከአዲስ አበባ መቆርቆር ጀርባ የነበረው መነሻ በጎ የሚባል አይነት አልነበረም። የማገዶ እና የቤት መሥርያ እንጨት እጥረት ጋር የተያያዘ መዘዝ ነው አዲስ አበባን ያስገኘልን።

ለብዙ የጥንት ስልጣኔዎች መንገራገጭ ምክንያት የሆነ መዘዝ። ለአንዳንድ ከተሞች መቆርቆዝ ለሌሎች ደግሞ መቆርቆር ምክንያት ሆኗል። በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በቻይና በጃፓን የደን መጨፍጨፍና መመናመን ሰዎች የሚኖሩባቸውን ቦታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲቀያይሩ አድርጓል።

ቀደም ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት መቀመጫ የነበረው የሰሜኑ ክፍል የደን ሀብት ለረጅም ዘመን ከመጨፍጨፉ የተነሳ ክፉኛ የተጎዳ አፈርና የተቦረቦረ ሜዳና ሸንተረር፤ ዛፍ ቀርቶ ቁጥቋጦ ከዛም ብሶ ሣር የማያበቅልበት ደረጃ የደረሰ መሬት ያለበት ሆኗል።


ቦረቦረ ሜዳና ሸንተረር፤ ዛፍ ቀርቶ ቁጥቋጦ ከዛም ብሶ ሣር የማያበቅልበት ደረጃ የደረሰ መሬት ያለበት ሆኗል። ወደ 1000 ዓ.ም. ገደማ ጉዳቱ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ከመድረሱ የተነሳ የሰሜኑ ክፍል የመንግሥት ማእከልነት ወደ ደቡብ እንዲዛወርና አዲስ የመናገሻ ከተማም እንዲመሠረት አስተዋጽኦ አድርጓል። ሂደቱም ቀጠለ። ደኖች ተጨፈጨፉ። ከተሞች ቆረቆዙ። ከተሞች ተቆረቆሩ።
የአጼ ምኒልክ መናገሻ ከተማ ከአንኮበር ወደ እንጦጦ ተዛወረ። አንድ ሁለት አብያተ ክርስቲያን ተሠሩ - በእንጦጦ። ወደ በኃላ እንጦጦ የሃምሳ ሺህ ሰዎች መኖሪያ ሆና ነበር። ከዛ እቴጌ ከእንጦጦ በስተ ደቡብ ወዳለው የፊንፍኔ ሜዳ አቀኑ። ፍል ውሃን እየታጠቡ የሚያርፉበት ቤትም ሠሩ። ከዛም ሌሎች ንጉሣውያን ሰዎች ተከተሉ። መጀመሪያ የተሠራችው ቤትም እየሰፋች ሄዳ ዛሬ ድረስ ቤተ መንግሥት ሆና እያገለገለች ነው። አዲስ አበባ ተወለደች።
አዲስ አበባም ከተቆረቆረች ሃያ ዓመት ሳይሞላት በአከባቢው የነበረውን የዛፍ ዘር ሙልጭ አድርጋ ጨረሰችው። ንጉሡም በወቅቱ አዲስ አለም አካባቢ ወደ ነበረው የጥድ ዛፍ ደን ጠጋ ብለው አዲስ ቤተ መንግሥት መሥራት ጀምረው ነበር። ይሁንና አጼው ለማገዶና ለሌላ ሥራ የሚውለውን እንጨት ካለበት እየተከተሉ በመጓዝ ፈንታ ማገዶው እኛ ወዳለንበት ይምጣ ብለው የወስኑ በሚያስመስል መልኩ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ባህር ዛፎች ቅድመ አያቶች ያን ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ገቡ። እናም የአካባቢ መጎሳቆል መዘዝ አዲስ አበባን ብቻ ሳይሆን ባህር ዛፍንም ከአሥር ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ከሚገኘው ትውልድ አገሩ ከአውስትራልያ መዝዞ አምጣልን። በቤተ መንግሥታቸው ውስጥ በሚገኝ ችግኝ ማፍያ ለሙከራ መፍላት ሲጀምር ከሌሎች ከጣልያን፤ከፖርቹጋልና ከግሪክ ከገቡት የዛፍ አይነቶች ይበልጥ ልቆ ተገኘ - አዲሱ ባህር ዛፍ። ከአውስትራልያ ወደ ቤተ መንግስት የገቡት እነዚህ ባህር ዛፎች ለህዝቡ በነጻ በሚታደሉ ችግኞች ምክንያት በየጊዜው እየተባዙ ሄደው ሄደው ሄደው እነሆ የአፍሪካ ዋና ከተማ አዲስ አለም ሳትሆን አዲስ አበባ እንድትሆን አስተዋጽኦ አደረጉ። እንዲያውም አዲስ አበባ ከባህር ዛፍ ጋር መርፌና ክር መሆንዋን በማየት ስሟ ወደ ኢካላፕቶፖሊስ (በአሜሪካ ሚንያፖሊስና ኢንዲያናፖሊስ ተብለው በሚጠሩት ከተሞች ስም አይነት) እንዲቀየር ሃሳብ ያቀረቡም ነበሩ ተብሎ ተጽፏለ። በተግባር ባይሠራበትም እንኳ በ1936 እ.ኤ.አ አቆጣጠር የመጀመሪያዉን ማስተር ፕላን እስክታገኝ ድረስ አዲስ አበባ በማስተር ፕላን ሳይሆን በ”ባህር ዛፍ ፕላን” ስትመራ የቆየች ከተማ ነች ብንላት ራሷ አዲስ አበባም ብትሆን “አትቀልዱ” አትለንም።
ከጊዜ በኋላ ባህር ዛፍ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይወሰን በስፋት በየመንደሩ የሚገኝ ዛፍ ሆነ። በገጠርም አለ። በከተማም እንዲሁ። ከከተሞች ውጪ ባሉ አንዳንድ አውራ ጎዳናዎች በየመንገዱ ዳርቻ ተተከለ - በስፋት - ባህር ዛፍ። በአምቦ መንገድ፤ በጅማ መንገድ የባህር ዛፍ ዘንካታዎች የአውራ ጎዳና አጥር ሆነው ተሰለፉ።
ስለ ባህር ዛፍ ጥቅምና ጉዳት የተለያዩ ሰዎች የተለያየ እይታ እንዳላቸው ይታወቃል። በመሆኑም ሚዛኑ የሚደፋው ወደ ጥቅሙ ነው ወይስ ወደ ጉዳቱ ብሎ መጠየቅ የግድ ይላል።
የባህር ዛፍ ከ700 በላይ ዝርያዎች አሉት። ብዙዎቹ በአውስትራልያ ይገኛሉ። በጣም ጥቂት የሚባሉት ደግሞ በኒው ጊኒ እና ኢንዶንዥያ ሲገኙ ለአንዱ ዝርያ ደግሞ ፊሊፒንስ እና ታይዋን አካባቢ ቀዬው ነው። አሥራ አምስት ዝርያዎች ብቻ ከአውስትራልያ ውጪ የሚገኙ ናቸው። ይህችን አገር የመገኛ አገራቸው ያላደረጉ የባህር ዛፍ ዝርያዎች ዘጠኝ ብቻ ናቸው። የባህር ዛፍ ከጊዜ ብዛት ከመገኛው ተወስዶ በመልመድ በአፍሪካ፤ በሰሜንና በደቡብ አሜሪካ፤ በአውሮፓ፤ በሜድትራኒያን ተፋሰስ፤ በመካከለኛው ምሥራቅ፤ በቻይናና በህንድ ንኡስ አህጉር ውስጥ እየለማ የሚገኝ ዛፍ ነው።
የባህር ዛፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ የልማት ተመራማሪዎችና የአካባቢ ጠበብቶችን ትኩረት የሳበ ዛፍ ነውና ኢትዮጵያ ውስጥም የባህር ዛፍ ነገር አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ መቆየቱ የግድ ነው። ቶሎ ለአቅመ-እንጨት በመድረስ ሲፈልግ ለማገዶ፤ካስፈለገ ለቤት መሥሪያነት አልያም ለኢንዱስትሪ እንደሚውል ይታወቃል (የማይጨው የቺፕዉድ ፋብሪካ ወደ ሦስት መቶ ኪዩቢክ ሜትር የሚጠጋ የጥሬ እቃ ግብአት እያገኘ ያለው ከባህር ዛፍ ነው)። የተፈላጊ ዘይት ምንጭም ሆኖ ለመድኃኒትነት፤ለጽዳትና ለተፈጥሮአዊ ጸረ ተባይ ማምረቻነት አገልግሎት ይውላል። በአገራችን ጉንፋን ስንታመም በነጭ ባህር ዛፍ እንታጠናለን ወይም ሌሎች ሲታመሙ ሲታጠኑ አይተን እንሆናለን። ቢያንስ ሰምተናል። ከመታጠናችን ጀርባ ያለው የዚህ የባህር ዛፍ ዘይት ፈዋሽነት መሆኑ ነው። ባህር ዛፍ የወባ በሽታን ለማጥፋትም በተዘዋዋሪ ያገለግላል፡፡ የወባ ትንኝ መራቢይ የሆኑ ረግረጋማ ቦታዎች ላይ በመትከል ረግረጉን ማድረቅ ይችላል - ባህር ዛፍ።
በድህነት የሚኖር ህዝብ በበዛበት አካባቢ የዚህ ዛፍ ምጣኔ ሀብታዉ ጠቀሜታው የጐላ ነው። በአንድ ሄክታር ካለ ባህር ዛፍ በየዓመቱ 18 ኩንታል ውዳቂ ቅጠላ ቅጠሎች ማግኘት ይቻላል - አዲስ አበባና ዙሪያዋ እንደዚህ አይነት ውዳቂ ቅጠሎችን በመስብሰብና በመሸጥ የሚተዳደሩ በርካታ ወገኖች አሉ።
በሌላ በኩል ግን መጠነ ሰፊ ውኃን በመምጠጥ ችግር ፈጣሪ ሆኗል መባሉ አልቀረም። ከባህር ዛፍ አንድ ኪሎ ግራም ሕያው ቁስ (ባዮ ማስ) ለማግኘት በአማካይ ከሁለት ሺህ ሁለት መቶ የኮካ ኮላ ጠርሙስ በላይ ውሃ ይጠይቃል።
ባህር ዛፍ ወደ ኢትዮጵያ በአጼ ምኒልክ ዘመን ሲገባ ምናልባት ዘመኑ 1894 ወይም 1895 እ.ኤ.አ. ነበር ምናልባት በፈረንሳዊው የባቡር ሃዲድ መሐንዲስ በሞንዶ ቪዳሌ ወይም በእንግሊዛዊው ካፕቴን ኦብራያን ነው የገባው። አዲስ አበባ ለማገዶ እንጨት ሲባል የተጨፈጨፈው ደን ለመተካትና ለቀጣይ አቅርቦት ሲባል ባህር ዛፍ እነሆ ወደኛ መጣ። እንደ ሪቻርድ ፓንክረስት አባባል ባህር ዛፍ አገራችን ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የተሳካለት ዛፍ ሆናል። ምክንያት - በፍጥነት ስለሚያድግ፤ እኔ ነኝ ያለ እንክብካቤ ስለማይጠይቅ እንዲሁም ተቆርጦ ሲያበቃ ከቀረው ጉቶ እንደገና በቀላሉ ስለሚያድግ እና በየአሥር ዓመቱ ተፈላጊውን ምርት ለመስጠት ስለሚደርስ። እናም ከአዲስ አበባ ወጥቶም እንደ ደብረ ማርቆስ ወደ መሳሰሉት ሌሎች ከተሞች ተስፋፋ። እነ ደሴ፤ ጅማ፤ ነቀምት፤ አሰላ፤ ሀረር፤ ሃማሬሳ፤ አለማያ ወዘተ ባህር ዛፍን አስተናገዱ። በ1960ቹ አጋማሽ በአዲስ አበባ የሚገኘው የባህር ዛፍ ዋና ዝርያ ኢ.ግልቡለስ ሲሆን ኢ.ሜልዮዶራና ኢ.ሮስትራታም በርከት ብለው ይገኙ እንደነበር አዛውንቱ የታሪክ ምሁር ሪቻርድ ፓንክረስት ይናገራሉ።
ዴቪድ ብክስቶን በ1940ቹ አጋማሽ ስለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ሲጽፍ ባህር ዛፍ ከሸዋ መልክዐ ምድር ጋር የተጣማረና የደስ ደስ ያለው አካል ሆኖ እንዳየውና ቀስ እያለ የሚያድገውን ባላገሩን ጥድን በስፋት እየተካው እንደሄደ መመልከቱን አትቷትል።
የባህር ዛፍ የውኃ ጥም ወንዞችንና ምንጮችን ያደርቃል ተብሎ ከመታመኑ ጋር በተያያዘ ባህር-ዛፍ-ተኮር ተቃውሞ ተነሳ። በአዋጅ መልክም ተገለጸ። የነበሩት ባህር ዛፎች በከፊል እንዲነቀሉና በምታክቸው ቱት ወይም የሐር ትል ዛፍ እንዲተከል ተነገረ - በአዋጁ። ባህር ዛፍን አገር ልመድ ብለው ባመጡት በአጼ ምኒልክ መጨረሻ ዘመን በነበረው የእርሻና የመስሪያ ሚኒስቴር በኩል ወጥቶ የነበረው የዚህ አዋጅ መግለጫ እንደሚከተለው ይነበባል።
የኢትዮጵያ፡መንግሥት፡
“ሞአ፡አንበሳ፡ማህተም”፡
የርሻና፡የመስሪያ ሚኒስቴር
ማስታወቂያ።
በመጀመሪያ፡ጃንሆይ፡ይህንን፡ያዲስ፡አበባን፡ከተማ፡ለመስራት፡የቆረቆሩ፡ጊዜ፡መሬቱ፡ባዶ፡ምናምን፡ዛፍ፡የሌለበት፡ነበር።ነገር፡ግን፡ለጊዜው፡ እንዲደምቅና፡እንዲያምር፡፡ላይን፡ማረፊያ፡እንዲሆን፡ተብሎ፡በቶሎ፡እሚያድግ፡ይህንን፡እካሊብቶስ፡አስመጡ፡እንጂ።
የጃንሆይ፡አሣብ፡ግን፡ላገራችን፡ለሕዝቡ፡የሚጠቅም፡ፍሬው፡የሚበላ፡እንጨቱም፡ሥራ፡የሚይዝ፡ጥቅም፡ያለውን፡ሁሉ፡እያስመጡ፡ለማስከተል፡ነበረ።ይኸውም፡ይታወቅ፡ዘንድ፡በያይነቱ፡አስመጥተው፡መፈተናቸው፡አልቀረም። ከተፈተነውም፡ሁሉ፡አንድ፡ዓይነት፡አልጠፋም።ሁሉም፡ጥንት፡ከተገኘበት፡ ከሀገሩ፡የበለጠ፡እየሆነ፡በቅሏል፡ለምቷል፡እንጂ።
ይህንኑም፡በትልቁ፡ኮክ፡በቱት፡በሐሩ፡ዛፍ፡በጽጌ፡ረዳ፡በሲጥሬ፡ተረዱት።፡እነዚህንም፡የመሰሉ፡ብዙ፡ዛፎችና፡ተክሎች፡አሉ።እኛም፡ይህንን፡ዓይተን፡ነው፡ጥቅም፡የሌለውን፡ዛፍ፡አሳንሰን፡ጥቅም፡ያለባቸውን፡እናብዛ፡ማለታችን።ቱትም፡የሚባለው፡የሐር፡ዛፍ፡ፍሬው፡ይበላል።ቅጠሉም፡የሐር፡ትል፡ማርባት፡ለወደደ፡ሰው፡ዋና፡ነገር፡ነው።፡ይህም፡ባይሆን፡ደግሞ፡ቅጠሉን፡ለላምና፡ለበሬ፡ለበግና፡ለፍየል፡ ቢያበሉት፡እጅግ፡ያወፍራል።ግንዱም፡በያመቱ፡ሲቆረጥ፡ለሥራ፡ይሆናል።ብዙ፡ገንዘብ፡ያወጣል።፡ቁመቱም፡በልክ፡ነው።
እንደዚህ፡ያለውን፡ጥቅም፡ያለበትን፡ዛፍ፡ለማልማት፡ነው፡ልዑል፡ያልጋ፡ወራሹም፡ያሰቡት።፡ይህ፡ እካሊብቶስ፡ግን፡የሚበላውን፡አታክልትና፡መሬት፡ከማጥፋት፡በቀር፡ምንም፡ምን፡ጥቅም፡የለውም።፡ባጠገቡ፡ምንጭ፡ያለ፡እንደሆነ፡ያደርቀዋል።የጉድጓዱንም፡ወሀ፡ሁሉ፡ሥሩ፡እየሳበ፡እየጠጣ፡አደረቀው።እንጨቱም፡ሥራ፡አይይዝ፡ፍሬውም፡አይበላ።አሁንም፡በየቦታው፡እካሊብቶስ፡ያለው፡ ሁለት፡እጁን፡ይንቀል።አንዱ፡እጅ፡ይቆይ።በተነቀለው፡ፈንታ፡ጥቅም፡የሚገኝበትን፡የዛፍ፡ግልግል፡እንሰጣለን።
መጋቢት፡፲፪፡ቀን፡፲፱፻፭፡ዓመተ፡ምሕረት፡አዲስ፡አበባ፡ከተማ፡ተጻፈ።
ይህ ባህር ዛፍ ላይ ያነጣጠረ ጅምላ-ጨራሽ አዋጅ ከወጣ እነሆ መቶ ዓመት ሊሆነው ነው። ይሁንና ዛሬም ድረስ ባህር ዛፍ ከአገሬው ዛፍ በላይ ገጠርም ከተማም የራሱ አድርጎታል።
ሪቻርድ ፓንክረስት እንደሚሉት አዋጁ መና ሆኖ የቀረ ይመስላል። የባህር ዛፍ በአዋጁ መሠረት ለመነቀሉ መረጃ የለም። ቱት በስፋት ለመተከሉም እንዲሁ። እናም አሁንም ምናልባትም ወደፊትም አዲስ አበባ ብሎም ኢትዮጵያ ከባህር ዛፍ ጋር እጅና ጓንት እንደሆኑ አሉ፤ ምናልባትም ይኖራሉ።
ማንኛውም በአካባቢና በማኅበራዊ ኑሮ ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር የሚችል ፕሮጄክት የተጽእኖውን መጠንና ስፋት መገምገምያ ስልት የአካባቢ ተጽእኖ ግምገማ ተብሎ ይጠራል። በዓለም የዕድሜ ባለጸጋ የሆነው የአካባቢ ተጽእኖ ግምገማ ሥርዓት የአሜሪካው ሲሆን ይህም በመንግሥት ደረጃ ተቋማዊ ቅርጽ ከያዘ ወደ አርባ ዓመታት አካባቢ ይሆነዋል።
ከላይ ያነበብነውና በ1905 ዓ.ም. የወጣው አዋጅ በአገራችን በተለያየ መልኩ የአካባቢ ተጽእኖ ግምገማ አሠራር ምልክቶችን በመንግሥት ሚኒስቴር መ/ቤት ደረጃ እንደነበር የሚያሳየን ነገር አለው።
የዚህ ግምገማ ውጤትም የባህር ዛፍ ከአውስትራልያ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባና በአዲስ አበባ አካባቢ እንዲተከል ከተደረገ ወዲህ መስፋፋቱን ለማገድ የተደረገ መንግሥታዊ ጥረት ነበር። የባህር ዛፍ በተተከለበት አካባቢ የሚያሳድረው ተጽእኖ - ለምሳሌ አካባቢውን በማድረቅ - አሁን ድረስ እየተነገረ ያለ ነው። አዋጁ ባህር ዛፍ የሚያመጣው የአካባቢ ተጽእኖ ብቻ ሳይሆን በምጣኔ ሀብትና በማኅበራዊ ኑሮ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ዝርዝርና መወሰድ ስላለበት እርምጃም ጭምር የሚያትት ነበር።
ከአጼ ምኒልክ መሞት በኃላ የባህር ዛፍም ሆነ የሌላ ደን ልማት የተጎዳበት ጊዜ ነበር። ልጅ ኢያሱም፤ ዘውዲቱም ተፈሪ መኰንንም የተጠመዱት ትኩርታቸውን የበለጠ ሊስብ የሚችለው የፓለቲካ ነገር ላይ ነበር። አገራችን መንግሥት ቢቀየርም ባይቀየርም የሚቀጥልና ተቋማዊ ቅርጽ የያዘ ውጤታማ የሆነ የደን ልማት እንቅስቃሴ ዛሬም ድረስ ትናፍቃለች። እንከን የለሽ ተአምራዊ ዛፍ እስካላገኘን ድረስ ጠንቁ ያነስ ጥቅሙ የባሰ የዛፍ አይነት እየመረጥን ማልማት የግድ ይላል። ዛሬ ዛሬ ችግራችን መትከል እንዳልሆነ መቼም ግልጽ ነው። ማጽደቅ ግን አልቻልንም። በአገር ደረጃ ከተከልናቸው ዛፎች ምን ያህሉ እንደጸደቁ መናገር እንድንችል የሚያደርገን መረጃ የለንም። ለዕሥራ ምእቱ የየመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች በየከተማው ሲተክሉ የነበሩት የችግኝ ብዛት ለማወቅ ስንትና የት እንደተከሉ በየብዙኃን መገናኛው ሲነገር የነበረውን ቁጥር መደመር ብቻ ይሆናል የሚጠይቀው። እነዚሁ አካላት የተክሏችውን ችግኞች በየጊዜው እየጎበኙ ቢያንስ ምን ያህሉ እንደጸደቁ ምን ያህሉ እንደደረቁ አውቀው ቢያሳውቁን መልካም ነበር። እንደዚህ አይነት መረጃ በተከታታይ ለመሰብሰብም ይሁን ለማሳወቅ አሁንስ ቢሆን መቼ ዘገየ?
ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ባህር ዛፍ ውሃ ቢመጥም ባይመጥም አንዴ መጥቷል። የመቶ ዓመት ቤተኛም ሆኗል። ይህ ዛፍ አገራችን ከገባ እስካሁን በኢትዮጵያ ለስድስት ቀናት ብቻ ሥልጣን ላይ የቆዩት ጄነራል ተስፋዬ ገብረ ኪዳንን ጨምሮ አሥራ አንድ ርዕሳነ ብሔር እንዲሁም ለአርባ ቀናት በሥራ ላይ የቆዩት ሚካኤል እምሩን ጨምሮ አሥር መራሕያነ መንግሥት ተፈራርቀዋል። ከባህር ዛፍ የሚገኘውን ጥቅማ ጥቅም - ዘይት - እንጨት - ወዘተ ከፍ ማድረግ መቻል ይጠበቅብናል። ውሃን የሚያደርቀው በምን አይነት ሁኔታና ቦታ እንደሆነ የሚታወቅ ነገር አለ። የደን ልማት ተመራማሪዎቻችን ከመሠረታዊ ምርምር አልፈው ወደ ተግባራዊ ምርምር ቢገቡ መልካም ነው። መንግሥትም የምርምር ውጤቶችን እያደነ ወደ መስክ ትግበራ የሚያውልና የሚያስፋፋ የአእምሮና የገንዘብ አቅም ያለው ድርጅት ማቋቋምና ማጎልበት አለበት።
___
መጋቢት 10 ቀን 2003 ዓ।ም. አዲስ አበባ ላይ ታትሞ የወጣው “አዲስ ጉዳይ” መጽሔት ላይ መደበኛው “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምድ ላይ ለወጣው ጽሁፍ መነሻ የሆነ:: www.akababi.orgNo comments: