Tuesday, May 15, 2012

ኢል-ቆሻሻ

(ጌታቸው አሰፋ፤ ሚያዝያ 27 ቀን  2004 ዓ.ም.) እጅ ስልክ፤ ቴሌቪዥን፤ የጠረጴዛ ኮምፒዩተር፤ የጭን ኮምፒዩተር፤ የስሌት ማሽን፤ አታሚ ማሽን ወዘተና ሌሎች በኤሌክትሮኒክ የሚሰሩ የቢሮና የቤት እቃዎች ሲያረጁ ወይም ከጥቅም ውጪ ሆነው ሲወገዱ ስለሚፈጥሩት ቆሻሻ ነው ዛሬ የምናነሳው። ኢል-ቆሻሻ እንበለው - የእንግሊዝኛውን በቀጥታ ወስደን ‘ኢቆሻሻ’ (ቆሻሻ ያልሆነ) ብለን ጥሩ ስም ከምንሰጠው።
የኤሌክትሮኒክ እቃዎች በዘመናችን በሰው ሕይወት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ በእነሱ መጠቀም የጀመረ ሰው ከእነሱ ውጪ ሕይወት የሌለ እስኪመስለው ድረስ ጠባቃ ኑሮ እንደሚኖር ይታወቃል። አገራችን የእነዚህ ኤሌክትሮኒክ እቃዎች ለእያንዳንዱ ዜጋ ማዳረስ ቀርቶ በንጽጽር ከብዙ የአፍሪካ አገሮችም ባነሰ ደረጀ እንደሆነች ቢነገርም የኢል-ቆሻሻ መዘዝ ለማንሳት ግን ጊዜው አሁን ነው።
ማድረግ ያለብን ነገር ለነገ የሚቆይ አይደለምና ዛሬ እናነሳዋለን።
የኢል-ቆሻሻ አደገኛነት የሚመነጨው እቃዎቹ የሚሰጡትን ጥቅምና አገልግሎት ለማስቻል የዋሉት በርካታ የተፈጥሮም ሆኑ ሰው ሰራሽ ጥሬ ነገሮች ነው። በጥሬ ነገርነት ጥቅም ላይ የዋሉት የተለያዩ የፕላሳቲክ አይነቶች ፤መደበኛ ብረት-ነክ ነገሮችና ከባድ ብረቶች በኢል-ቆሻሻነት ወደ ተለያየው የአካባቢ ክፍል ሲቀላቀሉ ጠንቃቸው ትውልድም ድንበርም ዘለል ነው። በተለይ ከባድ ብረቶች የምንላቸው እንደ እርሳስ(ሌድ)፤ ዚንክ፤ ካድሚየም፤ ሜርኩሪ፤አርሰኒክ፤  ሰለኒየም፤ ክሮሚየም፤ ኮባልት ወዘተ ከየት ተነስተው የት እንደሚሄዱ ስንመለከት ጠንቁ ምን ያህል እንደሆነ የበለጠ ግልጽ ይሆናል። ለምሳሌ ሜርኩሪ በእነዚህ እቃዎች ጉዞ ጀምሮ፤ በተለያየ ሁኔታ ወደ አየርም ወደ ውኃም ተቀላቅሎ፤ በጊዜ ሂደት ጠረጴዛችን ላይ ልንበላው ያቀረብነው አሳ በኩል ወደ ሰውነታችን ይቀላቀላል። እናቶች በሚያጠቡበት ጊዜ ደግሞ በወተቱ በኩል ወደ ልጆች እንደሚተላለፍ የሚያሳዩ ሪፖርቶች አሉ። ሜርኩሪ ሕጻናት ጊዜያቸውን ጠብቀው መናገርም መሄድም እንዳይጀምሩና በአጠቃላይ የአእምሮአቸው  እድገት ዘገምተኛ እንዲሆን ያደርጋል። እርሳስም እንዲሁ የህጻናት የአእምሮ እድገትና ብስለት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያመጣል። ከኢል-ቆሻሻ ጋር አያያዝና አወጋገድ ጋር በተቆራኘ የሚለቀቁት ሌሎች ኬሚካሎች ደግሞ ካንሰርን ጨምሮ ለሌሎች የጤና ጠንቆች ዋነኛ መንስኤ ናቸው። ከከባድ ብረቶች ሌላ እሳት አዘግዪ የሆኑና ብሮሚን-ሰር ኬሚካሎችም ከኢል-ቆሻሻዎች ጋር አብረው የሚፈጠሩት መዘዛቸው ራሱ ተጠንቶ ያላለቀላቸው ኬሚካሎች ናቸው።
ቆሻሻን ከውጪ ማስገባት
የኤሌክትሮኒክ እቃዎች ኢትዮጵያ የሚከሰቱት ሙሉ በሙሉ ከውጪ አገር ተመርተው ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገር ውስጥ የሚገጠሙትም ቢሆኑ ዋናው ክፍለ-አካላቸው በተለያየ አገር ተሰርቶ የሚመጣ ነው። እቃዎች ስንል ግን ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት እቃዎች አዳዲስ ብቻ ናቸው ብለን ከወሰድን ነው። የኤሌክትሮኒክ እቃዎች ዘመናቸውን መጀመሪያ የነበሩበት አገር የጨረሱ ከሆነ የምናስገባው ኢል-ቆሻሻ መሆኑ ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ እሺ በጄ ብለን መቀበል ያለብን ነገር ባይሆንም ሰበር ዜና ግን ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም በአውሮፓም በሰሜን አሜሪካም ጥቅም ላይ የዋሉ አሮጌ ኮምፒዩተሮችና የመሳሰሉት የኢል-ቆሻሻዎች በየዓመቱ ወደ ቻይና፤ ህንድና እንደ ናይጄሪያ ወደ መሳሰሉት የአፍሪካ አገሮች እንደሚላኩ በስፋት ይታወቃል። በበለጸጉት አገሮች እነዚህ ቆሻሻዎች አያያዝና አወጋገድ  በተመለከተ ጥብቅ ህግና ብቁ ቴክኖሎጂዎች ያሉ ቢሆንም ህጎችን መከተልና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ቆሻሻውን ወደሌሎች ህጉ ጥብቅ ወደልሆነባቸው አገሮች በህጋዊም በህገወጥ መንገድም መላክ ርካሽ ስለሆነ ስለሚያዋጣ እንደጉድ እየላኩት ይገኛሉ። ‘ካዋጣቸው’ ምን የማያደርጉት ነገር አለ? በአውሮፓ ብዙ አገሮች እንደዚህ አይነት ቆሻሻን በስርአት ወደማይወገድባቸው አገሮች እንዳይሻግሩ የሚያገድ ህግ/አሰራር አለ። ይሁንና ለምሳሌ ከእንግሊዝ አገር ኢል-ቆሻሻዎች ምንነታቸው ሳይገለጽ ወደውጪ የተላኩበት ጊዜም አለ።
በዓለም አቀፍ ደረጃም የባዘል ስምምነት የሚባለው ድንበር ተሻግረው ስለሚጓጓዙ አደገኛ ቆሻሻዎች ላይ እግድ የሚጥል ስምምነት አለ። ይህ ስምምነት በስራ ላይ ዋለ ከዋለ እነሆ በዚህ ሳምንት ሃያ አመት ሞላው። ኢትዮጵያ ራሷ ይህን ህግ ካጸደቀች እነሆ አስራ ሁለት ዓመት አለፋት።  በዚህ ስምምነት ውስጥ ከተካተቱት የአደገኛ ቆሻሻዎች መካከል የኢል-ቆሻሻዎች ይገኙበታል። እንደዚህ አይነት ቆሻሻዎች ከምንጫቸው ብዙም ሳይርቁ ህጋዊና ቴክኒካዊ አቅሙ በከፍተኛ ደረጃ በሚገኝባቸው በበለጸጉት አገሮች እንዲወገዱ ለማድረግ ያለመ ነበር - ስምምነቱ። ምን ዋጋ አለው አሜሪካ ያህል አገር በህግ አውጪ አካልዋ እስካሁን ያላጸደቀችው ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ከአሜሪካ ወደላደጉት አገሮች የሚደረግ የኢል-ቆሻሻዎችም ሆነ የሌሎች አደገኛ ቆሻሻዎች መላክ በአገራቸው ህግ ህገወጥ አይደለም።  በአሜሪካ እዚሁ መልሰን እንጠቀማለን የሚሉ ዋሾ አትራፊዎች ከሚሰበስቡት የኢል-ቆሻሻ ወደ ሰማንያ ፐርሰንቱ ወደ ታዳጊ አገሮች የሚላክ ነው። ጥሩና ጥብቅ ህግ አላቸው ከሚባሉት አገሮችም ቢሆን በህገወጥ መንገድ መጓጓዙ አልቀረም።
እድሜና እድሜ
በአገራችን የነበረው እቃን ቶሎ ያለመጣል ልማድ ቢያንስ ማድረግ በሚችለው የኅብረተሰብ ክፍል ዘንድ እየተወወ መምጣቱ የኢል-ቆሻሻን መጠን በእጅጉ እየጨመረ እንዲመጣ ማድረጉ አይቀሬ ነው። ለጊዜው አሮጌ የኤሌክትሮኒክ እቃዎች የሚገኙት በየቤቱ ስርቻና ጓዳ ጎድጓዳ ውስጥ ሊሆን ይችላል። ለዓመታትም እንደዛ ሊቀጥል ይችል ይሆናል። ጊዜው አጠረም ረዘመም ግን አሮጌ የእጅ ስልክ፤ አሮጌ ኮምፒዩተር፤ አሮጌው ቲቪ ከየቤቱ እየወጣ በመጀመሪያ ወደ ጠጋኞችና መልሶ ሻጮች እንዲሁም ወደ በላቾች መሄዱ አይቀርም። እድሜያቸው በራሱ ጊዜ አጥሮ ወይም እንዲያጥር ተደርጎ ወደ በላቾች ይላካሉ። አምና ሐምሌ ወር ላይ በዚህ ዓምድ ላይ ወጥቶ በነበረው ጽሑፌ እንደተመለከትነው የእቃዎች እድሜ የጎላ የተረዳ  የምንለው መደበኛ እድሜያቸውና ‘ሃሳባዊ’ እድሜ ተብሎ የሚጠራውንም ነው (በጣም የሚሰራው ለኤሌክትሮኒክ ነክ እቃዎች ነው) ። ሆን ተብሎ ከእቃው ጋር አብሮ የተሸመነው እድሜ ሲደርስ የእቃው እጣ ውሎ አድሮም ቢሆን ቦታ መልቀቅ ይሆናል።  መደበኛ እድሜው ሲደርስ ተበላሽቶ ሲያበቃ የማይጠገን ሆኖ እርፍ ሲል። ወይም እንዲሰራ የሚያደርገው አዲስ መለዋወጫ ወይም ገባር እቃ  ከነባሩ እቃ ጋር የማይገጥም ሆኖ  ቁጭ ሲል። ይህን እድሜ የሚወስነው በአምራች ኩባንያው ውስጥ ያለው እቃውን ዲዛይን የሚያደርገው ክፍል ነው። ዓላማው - ተጠቃሚው የገዛው እቃ እድሜ ያጥርና እንደገና አዲስ ይገዛል፤ የዚህም ያጥራል፤ አዲስ ይገዛል… እንዲህ እንዲህ እያለ ይቀጥላል። “ሃሳባዊ እድሜ” ደግሞ እያጠረ ከመጣውና ከእቃው ጋር ከተሸመነውና ከተሰፋው  ከመደበኛው እድሜ የባሰ ያጠረ ነው። ሃሳባዊ እድሜ በእቃው ላይ ሳይሆን በተጠቃሚዎች አእምሮ አንዲሳል ብሎም እንዲሰፋና እንዲሸመን የተደረገ የአሻሻጮች ስልትና የብጤዎች ፉክክር ውጤት ነው ልንለው እንችላለን። ተጠቃሚዎች እርስ በርሳቸው እየተያዩ በ“የኔ ይበልጥ ፤ የእኔ አዲስ ነው”  ፉክክር በደንብ የሚሰሩ እቃዎችን ወደ ማይሰሩት እቃዎች ዓለም ለማቀላቀል ከመጣደፋቸው ጋር የተያያዘ እድሜ መሆኑ ነው (አንዳንድ የሞባይል ሞዴሎች በአዲስ አበባ የዚህ ክስተት ገፈት ቀማሽ ሳይሆኑ ይቀራሉ?)።
በአዳሾችም በበላቾችም የማይፈለጉ ሲሆን ደግሞ በየመንገዱና በየወንዙ ይጣሉ ይሆናል። አንዳንዱም ያቃጥላቸው ይሆናል። በላቾች እጅ የማይገቡትና ከነሱም የተረፉትን ክፍለ-አካሎች ወይ ወደ መጣያ ቦታ ወይም ወደ መቃጠያ ቦታ ነው የሚያመሩት። ይህ ደግሞ ከላይ እንዳየነው ወደ አፈር ወደ ውኃና ወደ አየር የሚጓዘውን መርዛማ በካይ መጠን ይጨምረዋል።
ስለዚህ ሲጀመር እቃዎችን ለረጅም ጊዜ መጠቀም (እያስጠገኑም ቢሆን) ኋላ ቀርነት አለመሆኑን በተግባር የሚያሳይ የአርአያነት እንቅስቃሴ ያስፈልጋል - በአገራችን። አንድ ሰው የሚሰራ - እንከን ቢኖርበት እንኳን ተጠግኖ  ጥቅም መስጠት የሚችል የኤሌክትሮኒክ እቃን እስከተቻለው ድረስ ከተጠቀመ ኃላፊነቱን እንደተወጣ የሚያሳምን አርአያነት።
ማዕከላዊ መበለቻ
ማዕከላዊ መበለቻ ማዕከል ወሳኝ ነው። በአቃቂ የሚገኘው አዲስ የኮምፒዩተር የእድሳትና ስልጠና ማዕከል አንዲሁም የኤሌክትሮኒክስ መፈታቻ ትክል ጥሩ ጅምር ነው። ስራ ከጀመረ ብዙ ጊዜ ያልሆነው ይህ ማዕከል በዓለም ባንክና በዓለም የቢዝነስ መሪዎች መድረክ ድጋፍ የተቋቋመ ነው። በዚህ ማዕከል መቋቋም ፕሮጄክት ወቅት ተሳትፈን ነበር እንደሚሉት የውጪ ዜጎች አባባል ከሆነ በእድሳትና ስልጠናው ማዕከል ከውጪ በተለይ ከአሜሪካ የመጣ አሮጌ ኮምፒዩተር ተገቢው ፍተሻ ይደረግለታል፤ ሲያስፈልግ እድሳትም ይደረግለትና አስፈላጊ ሶፍትዌሮች ተጭነውለት ወደሚሄድበት ይሄዳል። የአገልግሎት ጊዜው ሲጨርስ ከሄደበት ወደ መፈታቻው ትክል እንዲመለስ ይደረግና በአይነት በአይነቱ ይበለታል። ብረታ ብረቱ በአቅራቢያው ወደሚገኘው የብረታ ብረት ማቅለጫ ይወሰድና ለምሳሌ ለግንባታ ስራ የሚውል ፌሮዎች ይመረቱበታል። ሌሎች ሽቦዎችም እንደገና ሌሎች ሞተሮች ወዘተ ለመስራት ጥቅም ላይ ይውላሉ። በካይና መርዛማ የሆኑት ከባድ በረት አዘል የመሳሰሉትና በአገር ውስጥ በስርአት መወገድ የማይችሉት ክፍለ-አካሎች ደግሞ በበቂ ሁኔታ ከተጠራቀሙ በኋላ ወደ አውሮፓና ወደ መሳሰሉት አገሮች ይላካሉ። አሮጌዎቹን ኮምፒዩተሮችን ከያሉበት ለመሰብሰብም ሆነ አደገኛ ክፍለ-አካሎችን ወደ ውጪ ለመላክ የሚያስፈልገው ወጪ የሚሸፈነው የታደሰ ኮምፒዩተር ከማዕከሉ በመቶ አስር ዶላር ሲሸጥ ከጠቅላላ መሸጫ ዋጋ ውስጥ በአስር ዶላሯ ነው - እንደነዚህ ሰዎች አባባል። በተግባር የሚደረግ ከሆነ ይሄ ሁሉ እጅግ ግሩም ነገር ነበር። ይሁንና በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ አንዲት ኮምፒዩተር ከአቃቂ ወደ በቆጂ፤ ወይም ወደ እንትጮ፤ ወይም ወደ መተከል ወይም ወደ ገለምሶ ከሄደች በኋላ በየትኛው የአሰራር ስርዓት ነው እንደገና ተመልሳ ጎጂ የኢል-ቆሻሻ ሆና የወደፊቶቹን የበቆጂ፤ የእንትጮ፤ የመተከል ወይም የገለምሶ ህጻናትን ጤና ሳታበላሽ ወደ አቃቂ መበለቻ የምትገባው? ለዚያውም በአስር ዶላር ሂሳብ። የትኛው የተዘረጋ ስርዓት ነው ይሄን ሰንሰለት የሚያስችለው? ለማወቅ እጓጓለሁ። የአሜሪካ መንግሥት እደገፍዋለሁ ያለው የዚህ አይነት ማዕከል በኢትዮጵያና መሰል አገሮች መቋቋም አሜሪካ ወደ ውጪ የምትልከውን ኢል-ቆሻሻ ያለምንም እንቅፋት በበጎ ነገር ስም በመላክ ከመቀጠል ጋር የሚያያዙት በአሜሪካ የሚገኙ ተቆርቋሪዎች አሉ። እነሱን ሐሰተኛ ማድረግ የሚቻለው በአገራችን ያለውን ማዕከል የተነገረለትን በጎ ተጽእኖ በተግባርና በዘላቂነት ስናሳይ ብቻ ነው።
ብትን ጥገናና ብለታ
በአሁኑ ሰዓት በተበታተነ መልኩ በየሰፈሩ የሚሰጠው የጥገናና ብለታ ሥራ የጠጋኞችንና የበላቾችን ጤናና ደኅንነት ለአደጋ ማጋላጡ አይቀርም። የኬሚካል ብናኞች በአፍ አፍንጫቸው በኩል በቀላሉ የሚገቡበት እድል ሰፊ ነው። ወዲያው የሚታይ ችግር ባያመጣባቸው በጊዜ ርዝመትና በጥርቃሜ የሚከሰት መዘዝ እንዳለው ግን ማወቅ አለብን።
ተደራሽ ግን ማዕከላዊ መልሶ የመጠቀሚያ ማዕከሎች በየቦታው ከተከፈቱ  ግን ኅብረተሰቡ ኢል-ቆሻሻዎች በቀላሉ የትም እንዳይወድቁ ለማድረግ የድርሻውን ይወጣ ዘንድ ይረዱታል። ረጅም ርቀት ሄዶ ይሰጣል ማለት ቀላል ስላልሆነ በተቻለ መጠን አበራታችን ርቀቶች ላይ በስርአት የሚያዙ እንዲህ አይነት መሰብሰቢያዎች ቢኖሩ መልካም ነው።
አቃቂ ያለው ማዕከል ኮምፒዩተሮች ላይ ብቻ ያተኮረ ነው የሚመስለው። ሌሎች ኢል-ቆሻሻዎችም ተገቢው ትኩረት ያስፈልጋቸዋል።  መንግሥት ቢያንስ ምን ያህልና ምን አይነት ኢል-ቆሻሻዎች እየተፈጠሩ መሆኑ ጥራት ያለውና በየጊዜው የሚታደስ ወቅታዊ የመረጃ ቋት ማበጀት ይጠበቅበታል።
በኢትዮጵያ በተለየ በኢል-ቆሻሻ ላይ የሚያተኩር ህግ የለም። የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ (ቁጥር ፫፻/፲፱፻፺፭ ) ላይ ስለ አደገኛ ቆሻሻ የሚናገረው ክፍል የኢል-ቆሻሻን ያጠቃልላል ብሎ መወሰድ ይቻላል። ይሁንና ከዚህ አዋጅ በኋላ አራት አመት ዘግይቶ የወጣው የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ አዋጅ (ቁጥር ፭፻፲፫ /፲፱፻፺፱) ላይ ጭራሽኑ አልተነሳም - ቢያንስ በማንሳት ደረጃ። ከችግሩ አሳሳቢነት አንጻር ራሱን ችሎ ኃላፊነትንና ምዝገባን እንዲሁም አወጋገድን በተመለከተ የሚዘረዝር አዋጅ ያስፈልገዋል ባይ ነኝ። እርግጥ ብሔራዊ ስልት ለመንደፍ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመሆን የሚሰራ ኃይለ-ግብር ተቋቁሟል።በስልቱም ሆነ ሊወጣ በሚችለው አዋጁ (ከወጣ)  በአገር ውስጥ የሚገጣጥሙትም ሆኑ ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቡት (በተለይ ከፍተኛ አቅም ያላቸው ትልልቅ ኩባንያዎች ከሆኑ) መልሶ የመሰብሰብና በስርአት የማስወገድ ኃላፊነት መውሰድ እንዳለባቸው በግልጽ መቀመጥ ይኖርበታል። አምስት ኪሎ የዛሬ ሃያ ዓመት አካባቢ ፎርትራን ፕሮግራሚንግ ኮርስ ስወስድ ለመጀመሪያ ጊዜ በጣቶቼ የተነካኩት ኮምፒዩተሮች አሁን የት ይሆን ያሉት? ስንት ነገር በክለው ይሆን? ለስንት ሰው ጤና ሰበብ ሆነው ይሆን? ወደፊትስ?
=======

አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

1 comment:

Unknown said...

This is an excellent article. It brings to light the need to be responsible in using and deposing electronics products. Though at present the benefit that we get from technological devices are indisputable, a great concern should lay in there potential harm. While having a regulation policy is important, I also think encouraging our culture, which is to use a product for long time, is also important. Creating awareness, like this article, about the pollution that can occur is also critical!