Sunday, November 25, 2012

አረንጓዴ አብሪዎች


(ጌታቸው አሰፋ፤ ግንቦት 25 ቀን  2004 ዓ.ም.)  አገራችን ኢትዮጵያ የሚሰሩትን የሚያውቁ አብሪዎች በየመስኩ ያስፈልጋታል። የሚሰሩትን የሚያውቁ በዚህ አገባብ የፈለገው ነገር ቢመጣ፤ ምንም እንቅፋት ቢመጣ፤ ሰው ቢሰማም ባይሰማም፤ በመረጡት ጉዳይ ላይና ዙሪያ ከልብ በልብ ለመስራት ልባቸውን ከአእምሮአቸው ጋር አዋህደው የሚሰሩ ተብሎ ይተርጎም። እንደነዚህ አይነት ሰዎች ወይም ድርጅቶች ውሎ አድሮ ቢያንስ አይን ላላቸውና ብርሃንን ለሚወዱ ሁሉ የሚያበሩ አብሪዎች ናቸው። በአካባቢና በኃይል ጉዳይ ዙሪያም ብዙ ናቸው ባይባሉም አረንጓዴ አብሪዎች አሉ። የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ የምር አቀንቃኞችን ከሞላ ጎደል እንደ በጎ ሚና ተጫዋችነት ማየት ቀላል ባልሆነባቸው የእኛ አይነት አገሮች ውስጥ እንደዚህ አይነት አረንጓዴ አብሪዎች ብርቅ ናቸው። ለዛሬ ሁለት ድርጅቶችን በአረንጓዴ አብሪነታቸው ብርሃናቸውን እንዘክራለን።
የአካባቢ ጉዳይ ተቆርቋሪዎች መድረክ
መድረኩ በአካባቢና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ጥናቶች ያካሂዳል። ራሱ ወይም በሰራተኞቹ በቀጥታ የሚያሰራቸው  እንዳሉ ሆነው ሌሎች ክፍሎችን ከፍሎ በማሰራት የሚያስጠናቸው ጥናቶችም በርካታ ናቸው። በአበባ ልማት ፤ በባዮፊዩል፤ በጎርፍ መጥለቅለቅ ስጋት ወዘተ የተጠኑት በዚህ በኩል ለምሳሌ ያህል ጥቂት ተጠቃሾች ናቸው።
የብዙሃን መገናኛዎች በአካባቢና ኃይል ጉዳዮች ዙሪያ የዘገቡትን ዳሰሳ አጠር አድርጎ በማሰባሰብ በመደበኛነት በኢሜይል ያሰራጫል። የአረንጓዴ ጀግና ሽልማትን ያስተዳድራል። ላለፉት ስድስት ዓመታት ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ለአካባቢ ጉዳይ ላደረጉት አስተዋጽኦ እውቅናን የሚሰጥ ይህ ሽልማት ከገጠር እስከ ከተማ፤ ከገበሬ እስከ ተመራማሪዎች ለተለያዩ ሰዎች ተሰጥቷል። የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ያዘጋጃል። ወቅታዊ በሆኑ እንዲሁም በተለያዩ ባለድርሻዎች ዘንድ የግንዛቤ እጥረት ሊኖራቸው በሚችሉ ጉዳዮች ላይ በተለያዩ ርእሶች ላይ በተለያየ መልኩ መድረኮችን ይፈጥራል። 
የፖሊሲ ሃሳቦችን ያመነጫል። ፓሊሲ አውጪዎች ወደፊት ሊያወጡዋቸው በሚችሉ ወይም ማውጣት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ለፓሊሲ የሚሆኑ ሃሳቦችን አፍልቆ ለውይይት ያቀርባል።
የአካባቢ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ነባራዊ ሁኔታዎች ዙሪያ ወቅታዊ ግምገማ(ሪቪው) ያቀርባል። በዚህ በኩል የዛሬ ሁለት ዓመት የተዘጋጀውና ባለ 232 ገጾችና በስምንት አበይት ጉዳዮች ላይ ግምገማ የሚሰጠው የመጀመሪያው እትም ለቀጣይ እትሞች መነሻ የሚሆን ጥሩ ይዘት ያለው ነው።
በሌላ በኩል የአካባቢ ጉዳይ ተቆርቋሪዎች መድረክ በይነ-ድርጅቶችን በማስተባበርና በመምራት አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሚናውን እየተጫወተ የሚገኝ ነው። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለአየር ንብረት ለውጥ ኔት ወርክ ተጠቃሽ ነው። አዳዲስ ሃሳቦች ላይ ቅድሚያ በመስጠት ወደ ተግባር የማሻገር ስራ ይሰራል - መድረኩ። በምርጫ ዘጠና ሰባት ወቅት የተለያዩ ፓርቲዎች ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ  በተመረጡ ርእሶች ላይ በቀጥታ የሚተላለፉ የምረጡኝ ክርክር መድረኮች ይሳተፉ እንደነበር ይታወሳል። በዛን ወቅት በቀጥታ እንደ ሌሎች የክርክር መድረኮች በመንግሥት ራዲዮም ሆነ ቴሌቭዥን ለመተላለፍ ባይችልም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ቢመረጡ በአካባቢ ጉዳዮች ዙሪያ ምን ምን ለመስራት እንዳሰቡ የሚገልጹበትና የሚከራከሩበት መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር። አዘጋጁም የአካባቢ ጉዳይ ተቆርቋሪዎች መድረክ ነበር። ኢህአዲግ ቅንጅትና ህብረት በዋናነት የተገኙበት ይህ አጋጣሚ በዚህ ዘርፍ ፋና ወጊ ነበር ብዬ የማምንበት ነው።
የኅትመት ውጤቶችን ያዘጋጃል ያሰራጫል። አክርማ የተባለችውን መጽሔት እንደምሳሌ  ማንሳት ይቻላል።
በአካባቢ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች አድራሻና የሚሰሩት ስራ ዙሪያ አስጠንቶ የመረጃ ቋት አዘጋጅቶ ጥቅም ላይ እንዲውል አድርጓል።
ይህን ሁሉ ስራ የሚሰራ ድርጅት ያለው ገጸ ድር ለሱ የሚመጥን ነው ብዬ አላምንም። ከላይ የጠቀስኳቸው ስራዎች ለመስራቱና እየሰራ ለመሆኑ እንኳን የሚገልጽ አይደለም  ገጸ ድሩ - አሁን ባለበት ሁኔታ።
የአካባቢ ጉዳይ ተቆርቋሪዎች መድረክ የተመሰረተው የዛሬ አስራ አምስት ዓመት ገደማ ነው። በደናን ለጥበቃ የተከለሉ ቦታዎች፤ በውኃማ አካላት፤ በታዳሽ ኃይል፤ በብክለትና በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ላይ የተግባቦት፤የማስተማርና የጥብቅና ስራ ላይ የሚሰራ ነው - መድረክ። በጠንካራ መልዕክት አሰተላላፊነቱ ቀልብ በሚስበውና በአሜሪካ ወደሚገኘው ታዋቂው የየል ዩኒቨርስቲ በዓለም ፌለውነት የሄደውና በቅርቡ ደግሞ የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ ልማት መምሪያ የአየር ንብረት ለውጥ አማካሪ በሆነው በንጉሡ አክሊሉ ሲመራ ነበር።

መልካ ማኅበር
ከአካባቢ ጉዳይ ተቆርቋሪዎች መድረክ አንጻር ሲታይ በዕድሜ ለጋ ነው ሊባል የሚችል ማኅበር ነው - መልካ ማኅበር። የተመሰረተው  የዛሬ ስምንት ዓመት ገደማ ነው። መልካ ማኅበር ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራበት ጉዳይ ሰብሰብ ያለ ከመሆኑ አኳያ ለየት ያለ ነው - በብዙ ጉዳዮች ውስጥ እጁን እንደሚያስገባው የአካባቢ ጉዳይ ተቆርቋሪዎች መድረክ ሳይሆን።
ከተፈጥሮ እንክብካቤ ጋር አብሮ የሚሄድ ባህላዊ የሆነ አገር በቀል እውቀትና ክህሎት ላይ የተመሰረቱ አሰራሮችን መጠበቅና ማበልጸግ ነው የመልካ ትኩረት።
ይህን አገር በቀል እውቀትና ክህሎት የራሱ የሆነ ኅብረተሰባዊ ምንጭ ያለው የማንነት ወንዝ ነው ብሎ ያምናል መልካ። የማኅበሩ ስም የወንዙ ማዶና ማዶ በሰዎች ዘንድ በአጥቢያ ማኅበረሰቦችና እነሱ ባላቸው ስነምህዳራዊ እውቀት ዙሪያ ያለው ሁለት አይነት ግንዛቤ ይወክላል ከሚል እሳቤ ጋር ይገናኛል። አንደኛው አይነት ትክክለኛ ያልሆነ ግንዛቤ ሌላኛው አይነት ደግሞ ትክክለኛ የሆነ ግንዛቤን። ማኅበሩ ሰዎችን ወደ ትክክለኛው ዳርቻ የማሻገር ስራ ላይ ለመሰማራቱ አመላካች ይሆን ዘንድ የ’ወንዝ መሻገሪያ’ የሚል ትርጉም ያለው ‘መልካ’ የተሰኘው የአማርኛና የአፋን ኦሮሞ ቃልን ወስዶ ስሙን አድርጓል። እንደ ማኀበሩ ድረ ገጽ መልካ ሦስት የደን ቦታዎች ላይ ስራ በመስራት ላይ  ይገኛል። እነዚህም በኦሮሚያ ክልል በሚገኙት የባሌ ተራሮች ደንና የሰበታ ሱባ ደን እንዲሁም በደቡብ ክልል የሚገኘው የሼካ ደን ናቸው። መልካ ማኅበር ከአዲስ አበባ ውጪ በዲንሾና በማሻ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች አሉት።
ማኅበሩ ራዕዩንና ተልዕኮውን የሚያስፈጽምባቸው መርሐ ግብሮች አሉት። አንደኛው የስነምህዳራዊ እውቀትን ለአዲሱ ትውልድ ለማስተላለፍ የሚጠቀምበት የአካባቢ ትምህርት መርሐ ግብር ነው። በዚህ መርሐ ግብር ስር ወደ ፓርኮች የሚደረግ ጉብኝት፤ በአካባቢው የአገር ሽማግሌዎች የሚመሩ የአካባቢህን እወቅ የውሎና የአዳር ጉዞዎችና ውይይቶች የሚካተቱ ሲሆን የተለያዩ ዕጽዋት ባህላዊ ጥቅሞች ወዘተ የሚነሱበት ነው።
ሌላው እኔ እስከማውቀው ድረስ በአገሪቱ የመጀመሪያ የሆነው አሳታፊ የማኅበረሰብ-ሰራሽ ካርታዎች መርሐ ግብር ነው። በመንደርና በአጥቢያ ደረጃ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በቀያቸው ስላለው አካባቢ ያላቸውን ስነምህዳራዊ እውቀት በባለሦስት አውታር ካርታ ላይ በመመካከር እንዲያሰፍሩ እድል የሚያገኙበት ነው። ይህ ስራ ለሚሳተፉት ብቻ ሳይሆን ለአሁንም ለመጪውም ተጠቃሚ በርካታ ጥቅሞችን የሚሰጥ ትልቅ ጅማሮ ነው።
በተግባር የውኃና የአፈር እቀባ፤ የችግኝ ማፍላትና የአገር በቀል ዛፎች ተከላ ላይም ይሳተፋል - መልካ።
በፌዴራልም በክልል ደረጃም ከፓሊሲ አውጪዎች ጋርና ከተለያዩ የዘርፍ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቶች እንዲሁም ከተለያዩ የአካባቢ ተቆርቋሪ ስብስቦች ጋር የምክክር መድረኮች ያዘጋጃል።
መልካ ብዙ ጊዜ ከማትጊያ እጥረት ጋር በተያያዘ ከስኬት ሳይደርሱ በአጭሩ የሚቀሩ ጥበቃ-ተኮር የደንና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራዎች የሚያጋጥማቸውን ችግር ለመቅረፍ በደን ልማትና ጥበቃ የሚሳተፉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን አማራጭ የገቢ ምንጮች ላይ እንዲሰሩ በማገዝ ይረዳል። በዚህ መርሐ ግብር ስር የንብና ድሮ እርባታ፤ ከብት ማደለብና የመሳሰሉትን ስራዎች ይደግፋል።
እነዚህን ስራዎች የሚዘረዝርበት ማራኪና መረጃ-ጠገብ ገጸ ድር አለው - መልካ። የምነቅፍበት ነገር ቢኖር ማንነት፤ ባህልና አገር በቀል እውቀትን እንዲሁም የአካባቢ ቋንቋን መጠቀም በየመርሐ ግብሮቹ ላይ የሚያስቀድመው መልካ የራሱ ገጸ ድር ቢያንስ የአማርኛም ክፍል እንዲኖረው አለማድረጉን ነው። ለነገሩ ይህ ድክመት የአካባቢ ጉዳይ ተቆርቋሪዎች መድረክም የሚጋራው ድክመት ነው። እነዚህ ድርጅቶች የሚሰሩት ትልቅ ስራ ዋናው ተጠቃሚ መሆን ያለበት የአገሬው ሰው ስለሆነ የሚቀርበው መረጃ (በኢንተርኔትም ጭምር) በአገር ውስጥ ቋንቋ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ። 
በተወሰነ መልኩ የእነዚህ አይነት ድርጅቶች ተጠያቂነት ለረጂዎች ወይም ለውጪ አካላት መሆኑ ይታወቃልና በውጪ ቋንቋ መጻፉ ሊጠቅማቸው ይችላል። በተግባርም መረጃዎችን በአማርኛም ሆነ በሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ከማቀናበር ይልቅ በእንግሊዝኛ ይቀል ይሆናል። እንደዛም ሆኖ ግን የተወሰነ ጥረት ተደርጎ ቢያንስ የተወሰነው የገጸ ድሮቹ ክፍል በአገሬው ቋንቋ መደረግ አለበት።
ስለአካባቢ ጉዳይ ተቆርቋሪዎች መድረክና ስለመልካ ማኅበር አረንጓዴ አብሪነት የጻፍኩት በርቀት ከተከታተልኩትና ከታየኝ የብርሃን ነጸብራቅ አንጻር ነው።
በአገር ውስጥ ያሉ የትምህርት ተቋማት ስለነዚህና መሰል ድርጅቶች ብርሃናዊ አስተዋጽኦና የብርሃናቸው መጠንና ጥራት ከማጎልበት አንጻር ማሻሻል ስላለባቸው ነገሮች ጠቋሚ ጥናቶች ማድረግ አለባቸው እላለሁ - በገጠርም በከተማም በየዘርፉና በየመስኩ ብርሃናቸው ምን ያህል በጎ ተጽእኖ እየፈጠረ እንደሆነ ማወቅ ስለሚያስፈልግ።
ወደ ግለሰብ አብሪዎች ደግሞ በሚቀጥለው እትም እንመለሳለን። 

 =======

አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: