Sunday, November 25, 2012

አፕል እና አካባቢ


(ጌታቸው አሰፋ፤ መስከረም 25  ቀን  2004 ዓ.ም.) እነሆ አዲሱ ትውልደ-አይፎን iPhone 5 ገበያ ላይ ውሏል። በየአገሩ በየከተማው ከሰው ሁሉ አስቀድሞ ለመግዛት የነበረው ወረፋ በአንዳንድ የምግብ እጥረት ባለባቸው አገሮች ለምግብ ነው እንዴ ያስብል ነበር። በምእራቡ ዓለም ደግሞ በነጻ የሚታደል ነገር አለ እንዴ (መቼም እንደ ፈረንጅ በነጻ የሚታደል ነገርን ለመቀበል በነጻነት የሚሰለፍ አይቼ አላቅም)። 

በዚህ ዘመን በዊኪፒዲያ ዘመን፤ በዩትዩብ ጊዜ፤ በፌስቡክና በቲዊተር ዘመን፤ በጉግል ዘመን መኖር ከሌሎች ዘመኖች ጋር አንድ ሊሆን አይችልም። እነዚህ ቴኮኖሎጂዎች የተፈጠሩትም ዘመኑን ከአዝማናት ሁሉ ልዩ ለማድረግ ነውና። ይህ ዘመንም የአፕል ዘመን ነው።  በአፕል ምርቶች አለመመሰጥ አይቻልም ማለት ማጋነን ነው እንዳይባል ይከብዳል በሚል ላቃልለው።  የምርቶቹ ዲዛይን ‘ጸዳ ያለ’ መሆን፤ ማማራቸው፤ ዘርፈ ብዙ ጥቅም መስጠታቸው አፕልን ልዩ ያደርገዋል።የአፕል ተጠቃሚዎች ቁጥር እየበዛ መሄድ አፕል በጎ ሚና ለመጫወት ያለውን እድል ሰፋ ያደርገዋል። ለዚህ ምክንያቱም አፕል የሚታወቅባቸው የመረጃ ወተግባቦት ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ ለማዋል የምንጠቀምባቸው ቁሶች ስብስብ ከፍተኛ የኃይል መጠን ፍጆታ መጨመርን አስከትለዋል - በተለያየ ደረጃ። በብዙ ታዳሽ ኃይል በማይጠቀሙ አገሮች ይህ የኃይል ፍጆታ መጠን መጨመር ከአካባቢ ተጽእኖ ጋር አብሮ የሚመጣ ጣጣ ነው። ታዳሽ ኃይል ባላቸው አገሮችም (በተለይ በታዳጊ አገሮች) ቢሆን ለሌላ ቁም ነገር ሊውል ይችል የነበረ ኃይል የመረጃና ተግባቦት ቴክኖሎጂ ተሸካሚ ዘባተሎዎች መዋሉ ጥቅም ሊሆን አይችልም።
እነዚህ መጠቀም አሁን ባለንበት ሁኔታ እየቀነሰ ይመጣል ተብሎ አይጠበቀም። በተለይ የአፕልን የመሰሉን ቀልብ ሳቢና አማላይ ምርቶች አዳዲስ እትሞች በየዓመቱ ቢመጡ እንኳን ያለፈውን እትም ገዝቻለሁ ብሎ አርፎ የሚቀመጥ ሰው ቁጥር እያነሰ ነው እየመጣ ያለው።  የነዚህ አይነት ምርቶች በቁጥርና በአይነት መጨመር በአጭር ጊዜ ደግሞ በሌላ ቀጣይ ትውልደ-እቃ መተካት ከአሁን በፊት በዚህ ዓምድ እንዳየነው መዘዛቸውን እንኳን በደንብ የማናውቃቸው የቆሻሻ አይነቶች ወደ ተፈጥሮ ማኅጸን፤ ገጽ፤ ልብና ሳንባ እየጨመሩ ይሄዳሉ። እቃዎቹን ለማምረት ኃይል ያስፈልጋል። እቃዎችን ለመጠቀም ኃይል ያስፈልጋል። እቃዎችን በስርአት ከገበያና ከጥቅም ለማስወገድም ኃይል ያስፈልጋል።
ኩባንያዎች ትርፋቸውን ብቻ ስለሚያዩ ትርፍ የሚያስገኝ ነገር እስካልመሰላቸው ድረስ የምርታቸው አካባቢያዊ ተጽእኖ ለመቀነስ የሚወስዱት እርምጃ ይኖራል ብሎ መጠበቅ ከቀልድ የዘለለ ትርጉም አይኖረውም። ይህ ማለት በህግ ካልተገደዱ በስተቀር ወደውና ፈቅደው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከቁም ነገር የሚጣፍ አይደለም ማለት ነው - በአብዛኛው።በሌላ በኩል ዛሬ ዛሬ በምእራቡ ዓለም ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ የመጣው የተጠቃሚዎች ግንዛቤ ከዋጋና ከቴኪኒካዊ ጥቅም በተጨማሪ ወይም ጎን ለጎን ምርቶች በአካባቢ ላይ የሚያደርሱትን ተጽእኖ ሰሚ ጆሮዎችና ተመልካች አይኖች ትኩረት እየያገኘ እንዲሄድ አድርጓል። ለወትረው ይህ ትኩረት በተናጋሪ አፎች ደረጃ ብቻ ተወስኖ የነበረ መሆኑ ይታወሳል።ይህ ለውጥ በኩባንያዎች ትንሽና ትልቅ ስራዎች በኩል በሚገለጽ መልኩ ብቅ ብቅ ማለት እየጀመረ ነው። አሁንም መጠኑና ጥራቱ ያን ያህል የሚያስቦርቅ ባይሆንም።
የiPhone 5 ባለፈው ሳምንት በገበያ ላይ መውጣት ጋር በተያያዘ የአፕል ምርቶች ከአካባቢ አኳያ እያሳዩት ያለውን መሻሻል ወይም አለመሻሻል በአጠቃላይ ለውጥ በጥቂቱ እናያለን ለዛሬ። 
የታላቁ ዲዛይነር የስራ ፈጠራና የስራ አመራር ጠቢብ ስቲፍ ጆብስ የአእምሮ ልጅ የሆነው አፕል ኩባንያ ስለሚሰራው ምርት ብቻ ሳይሆን ስለሚሰጠው መረጃ ትኩረት ሰጥቶ የሚያቀርብ አይነት ነው።
በምርቶቹ ምን ምን አይነትና መጠን ጥሬ እቃዎችን እንደሚጠቀም፤ ምን ያህል ኡደታዊ የካርቦን አሻራ እንደሚያስከትሉ እና ምን ያህል የአደገኛ ቁሶች መጠን እንደቀነሱ ብሎም ምን ያህል የኃይል መጠን እንደሚጠቀሙ በገጸ ድሩ ዘርዝሯል - አፕል።
ለምሳሌ ያህል ከአፕል በርካታ ምርቶች መካከል የአይፎንና የአይፓድ ምርቶችን እስቲ እንመልከት።
መጀመሪያ የወጣው አይፎን iPhone 3GS  ነበር። ከዛ ቀጥሎ iPhone 4 ሲሆን የተወሰነ ማሻሻያ የተደረጉበት iPhone 4S ወጣ። አሁን ደግሞ iPhone 5 ነው። iPhone 3GS  135 ግራም፤ iPhone 4 137 ግራም፤ iPhone 4S 140 ግራም ይመዝናሉ። አዲሱ  iPhone 5 ደግሞ 115 ግራም ብቻ። ክብደቱ እየቀነሰ መምጣቱ ለተጠቃሚው ሸክም መቀነስ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢም ጥሩ ነው። የሚጠቀመው ጥሬ እቃ ስለሚያንስና እና እሱን ከማመርቻ ወደ ገበያ እንዲሁም በተለያዩ ሂደቶች ለማጓጓዝ የሚያስፈልገው ነዳጅና ስለሚያንስ ተከትሎት የሚከሰተው ብክለትም ይቀንሳል። የመጀመሪውያዎች ሶስት የአይፎን ትውልዶች የክብደት መቀነስ አላሳዩም። በካርቦን አቻ አሻራም የምናይው መቀነሱን አይደለም።  iPhone 3GS  135 እና iPhone 4  55 ኪሎ ግራም ብክለት ሲያስከትሉ፤ iPhone 4S  ለ70  ኪሎግራም የካርቦን አቻ ብክለት ምክንያት ሆኗል። ከአይፎኖቹ ክብደት ጋር በንጽጽር ሲታይ ከ iPhone 3GS  ወደ iPhone 4  በተደረገው ሽግግር  የነበረው ትንሽ ማሻሻያ  iPhone 4S ይዞት የመጣው ግን የባሰ የብክለት መጠን ጭማሪ ነው። iPhone 5 ክብደቱ በደንብ ከመቀነሱ አኳያ የብክለት መጠኑንም በዛው መጠን ይቀንሳል ብዬ እጠብቅ ነበር። ይሁንና በራሱ በአፕል በቁጥር የተቀመጠውን  ጥናት ስናይ አሁንም የቀነሰበት ሁኔታ አናይም። iPhone 5 በሕይወቱ ዘመኑ የ65 ኪሎ ግራም ካርቦን አቻ ብክለት ምንጭ ይሆናል።የአራቱ አይፎኖች የብክለት ምንጭ ቅንብር ከጊዜ ወደጊዜ እየተቀየረ መጥቷል። የማምረቻ ሂደት፤ የመጠቀም ሂደት፤ የመጓጓዝ ሂደትና የመልሶ መጠቀም ሂደት ድምር ውጤት ለሆነው ሙሉ ሂደት እያንዳንዱ ክፍለ-ሂደት የሚኖረው ድርሻን  የሚያመለክት ቅንብር ማለት ነው። ስራ ላይ ሲውሉ የኃይል አጠቃቀማቸው ከፍተኛ የሆኑ ምርቶች የመጠቀም ሂደታቸው ድርሻ ቀላል አይደለም። ይሁንና ይህ የኃይል አጠቃቀም እየቀነሰ እንዲመጣ ሲደረግ የማምረቻ ሂደቱ ድርሻ እየጎላ ይመጣል።
በአይፎኖቹም የታየው ሂደት ተመሳሳይ ነው። በአይፎንቹ አራት እትሞች የማምረቻው ሂደት ድርሻ ከ 45 ፕርሰንት 65 ፐርሰንት 69 ፐርሰንት ወደ 76 ፐርሰንት ጨምሯል።
በዛው ልክ ደግም የመጠቀም ሂደቱ ድርሻ ከ49 ፐርሰንት ወደ 26 ፐርሰንት ከዛ 23 ፐርሰንት በiPhone 5  ደግሞ ወደ 18 ፐርሰንት ወርዷል። ሌላው የአፕል ተወዳጁ ምርት አይፓድ ነው።
አይፓድ እስካሁን ሁለት እትሞች ያሉት ሲሆን የመጀመሪያው iPad 2 የሚባለው ሲሆን አዲሱ ደግሞ The New iPad ተብሎ የሚታወቀው ነው። በሁለቱ አይፓዶች መካከል ያለው የአካባቢ ተጽእኖ ልዩነት ከክብደታቸው ጋር የሚያያዝ ነው። 613 ግራም የሚመዝነ iPad 2 ከThe New iPad  የሚያንሰው በ49 ግራም ብቻ ነው።  የካርቦን አሻራውም በግማሽ ኩንታል ነው። ያም ማለት በሁለት አይፓዶች መካከል ያለው የካርቦን አቻ ስሌት የአይፎን iPhone 3GS ወይም  iPhone 4  የካርቦን አሻራ ያህል ሊሆን የሚቀረው አምስት ኪሎ ያክል ብቻ ነው። የማምረቻ ሂደትና የመጠቀም ሂደች ያላቸው ድርሻ ከiPad 2 ወደ The New iPad የተደረገው ሽግግር ያን ያህል ለውጥ ያመጣ አይደለም። ሦስት እጁን የማምራቻ ሂደቱ የያዘ ሲሆን መጠቀም ሂደት የጠቅላላ አካባቢያዊ ተጽእኖ ሩብ ያህሉን ይወስዳል።
እርግጥ አፕል እነዚህን ቁጥሮች ለማስላት የተጠቀመባቸው ግብአቶችና ጥቅም ላይ ያዋለው ዘዴ በይፋ ግልጽ በሆነ መልኩ የተቀመጡ ስላልሆነ በዛ በኩል በጎም ሆነ ደካማ ጎን ለመንቀስ አመቺ አልሆነን። እንደዛም ሆኖ የምንጠቀምበት ምርት አካባቢያዊ ተጽእኖው በንጽጽር ምን ያህል እንደሆነ እንኳን ለማወቅ እንድንችል አፕል እድል ለተጠቃሚዎች ስለሰጠን ምስጋና ይገባዋል።
በመጨረሻም - በዚህ ሳምንት የተመድ 67ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ተጀምሯል። በጠቅላላ ጉባኤው ከተነሱት ቁም ነገሮች መካከል አንዱ ‘✓’ የሚገባው የ“አዛላቂ ኃይል ለሁሉም” ጅማሮ ስብሰባ ነው። ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ።

=======

አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: