Sunday, November 25, 2012

ኦባማና የእጅ ነሺዎች አሜሪካ


(ጌታቸው አሰፋ፤ ኅዳር 7  ቀን  2004 ዓ.ም.)የአሜሪካው ምርጫ እነሆ ተጠናቀቀ። ፕሬዚደንት ኦባማ ለሁለተኛ ጊዜ ተመርጠዋል። አንቱ የተባሉ ተንታኞች፤ ዋና ዋና የቅድሚያ ግምቶች የሚሰጡ ክፍሎች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚቻልበት ደረጃ ምርጫውን ማን እንደሚያሸንፍ ለመተንበይ አለመቻላቸው ግልጽ ነበር (ከናቲ ሲልቨር በስተቀር)። መጨረሻ ላይ አሸናፊ ሲታወቅም በጣም በትንሽ ልዩነት እንደሚሆን ሲናገሩ ነበር።
እንዲያውም አልጎርና ፕሪዚደንት ቡሽ የተፎካከሩበት ምርጫ አይነት ‘ለመጭበርበር’ የተጋለጠ እስኪሆን ድረስ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ተገምቶ ነበር። በባራክ ኦባማና በሚት ሮምኒ ካምፕም ይህንን ግምት ግምት ውስጥ በማስገባታቸው ሳይሆን አይቀርም በጉጉት በሚጠበቁትና በቀጥታ በቴሌቭዥን በሚተላለፉት የክርክር መድረኮች ላይ ማንሳት ይጠበቅባቸው የነበሩ ነገሮችን ሳያነሱ ቀርተዋል። በተለይ በፕሪዜደንት ኦባማ በኩል የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ በአጠቃላይ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይን በተለይ ሳያነሱት ቀርተዋል። ጨዋታው ሁሉ በስራ አጦች ቁጥር መቀነስ ላይ ያተኮረ እንዲሆን ተደርጎ ቅኝቱ በሪፐብሊካኖች ተቃኝቶ ነበር።
የምርጫ ድምጽ ዋጋ
ለባራክ ኦባማ ለሁለተኛ ጊዜ መመረጥ መቻል ራሱ አስቸጋሪ ሊሆን የሚችል ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የመጀመሪያው አራት ዓመት የስልጣን ዘመናቸው የሚፈልጉትንና የሚያምኑበትን ነገር ሙሉ በሙሉ እንዳያደርጉ አስሯቸው ነበር።
የሚሰርዋቸው ስራዎችና የሚወስኗቸው ውሳኔዎች በምርጫ ካርድ በኩል ተጽእኖ ሊያሳድር በሚችለው  የኅብረተሰብ ክፍል ዘንድ በመልካም ሁኔታ የማይተረጎሙ እንዳይሆኑ ስጋት ስለሚይዛቸው በይደር ያቆይዋቸው ነገሮች ነበሩ። ለውሳኔያቸውና ለስራቸው የሚከፍሉት ዋጋ ለሁለተኛ ጊዜ ከመመረጥ የሚያግዳቸው የምርጫ ድምጽ ማጣት እንዲሆን አለመፈለጋቸው ለአንዳንድ ውሳኔዎች አለመወሰንና ለአንዳንድ ድርጊቶች አለመፈጸም ምክንያት ሆነዋል። ይህ በአንደኛው ዙር የነገሰው ለስለስ ያለ አካሄድ በምርጫ ዘመቻውም የተንጸባረቀ ነበር - በፕሬዚደንቱ በኩል። ከዚህ አኳያ የባራክ ኦባማ ለሁለተኛ ጊዜ መመረጥ በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው ጊዜ ድምጹ እንዲቀነስ ወይም እንዲጠፋ የተደረገው ጉዳይ ሁሉ፤ በምርጫ ዘመቻው ወቅት ከጠረጴዛ ወደ መደርደሪያ የተላከው አጀንዳ ሁሉ እንደገና ጉዳይ ሆኖ እንደገና ሕይወት ያለው አጀንዳ እንዲሆን ይደረጋል የሚል ተስፋ አለ። ለሦስተኛ ጊዜ ያስመርጠኛል አያስመርጠኝም የሚል ጥያቄ ስለማያሳስባቸው ጉዳዩ ‘መደረግ አለበት የለበትም?’ ከሚል አኳያ ብቻ የሚያዩት ይሆናል። ከነዚህ ጉዳዮች መካከል የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ አንዱ ነው። በወሳኞቹ የክርክር መድረኮች ላይ አንድም ጊዜ ያላነሱት ባራክ በምርጫ ማሸነፋቸው በታወቀ በደቂቃዎች ልዩነት ውስጥ በቀጥታ በቴሌቬዥን በተላለፈ የድል ንግግራቸው ላይ “በመሞቅ ላይ ያለች ፕላኔት አውዳሚ ኃይል” በማለት የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ አጀንዳቸው መሆኑን ማሳየታቸው አዲስ ተስፋን አጭሯል። ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የተለያዩ የአካባቢ ጉዳይ ተቆርቋሪዎች ፕሬዚደንቱ ቃላቸውን ወደ ስራ እንዲቀይሩ እየተማጸኑና እየገፉ ነው - ካሁኑ። በቅርቡ በዶሃ በሚደረገው የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ ወሳኝ ሚና መጫወት ይጠበቅባቸዋል። የአገሪቱ የቅሪታዊና የታዳሽ ኃይል ምጣኔ ጉዳይ ላይ የሚሰሩት ስራም ምን ሊሆን እንደሚችል የሚጠበቅ ነው።
የነዳጅ ዘይት ሱስ
ሱሰኛዋ አሜሪካ ወደ ሰባ ፐርሰንት የሚሆነው ኃይልዋን የምታገኘው ከቅሪታዊ ነዳጆች ማለትም ከነዳጅ ዘይት፤ ከከሰል ድንጋይና ከተፈጥሮ ጋዝ ነው። ለምሳሌ ነዳጅ ዘይትን ብቻ ብናይ አርባ አምስት ፐርሰንት የሚሆነው የአሜሪካ ፍጆታ የሚሸፈነው ከውጪ በማስገባት ነው። ድፍድፍ ነዳጅና የነዳጅ ዘይት ውጤቶቿም የሚገቡት በቅደም ተከተል ከካናዳ፤ከሳውዲ አረቢያ ፤ከቬንዝዌላ፤ ከናይጀሪያና ከሜክሲኮ ነው። ከካናዳ ውጪ ያሉት አገሮች ከጸጥታም ከርቀትና ከመሳሰሉት መስፈርቶች አንጻር የአሜሪካ የኃይል አቅርቦት ደህንነት ጋር በተያያዘ ሁሌም ጥያቄ የሚነሳባቸው ናቸው። የካናዳው ደግሞ ለየት ባለ መልኩ በአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ተቆርቋሪዎች መሪነት ተቃውሞ የሚቀርበት ነው። ካናዳ እኔ ከምገኝበት የአልበርታ ግዛት የምታወጣው የነዳጅ ዘይት በሌሎች አገሮች እንዳለውና እንደተለመደው የጥልቅ ጉድጓድ ነዳጅ አይደለም። በንጽጽር ከላይ ካለ ዘይት-ጠገብ አሸዋ ታጥቦ የሚገኝ ነው - በቀላሉ ለመግለጽ። ይህ ከፍተኛ ውኃና እንፋሎት ጥቅም ላይ በማዋል የሚገኘው ድፍድፍ ዘይት ከፍተኛ መጠን ያለው በካይ እጣቢን ያስከትላል። ይህ ደግሞ ለአካባቢ ደህንነት ጠንቅ ይሆናል ተብሎ ይሰጋል። የዚህ አይነት ድፍድፍ ዘይትም ሆነ የተጣራ የነዳጅ ዘይት በየቦታው ለማዳረስ አዋጪ ማጓጓዣ አንዳች አንዳች የሚያህሉ ቱቦዎች በመገጣጠም የሚዘረጉ ድፍድፍ ወይም ነዳጅ ዘይት ተሸካሚ መስመሮች ናቸው። እነዚህ መስመሮች ደግሞ የሆነ አደጋ አጋጥሞ የያዙትን ካፈሰሱ በአካባቢ የሚያደርሱት ጉዳት ጋር ተያይዞ የሚነሳባቸው ጥያቄ አለ።
በሌላ በኩል እነዚህ ዘይት-ጠገብ አሸዋማ ሀብቶች ለአልበርታ ብሎም ለካናዳ የሚያበረክቱት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በዚህ ምክንያት ነው በአልበርታ ከሌሎች የካናዳ ግዛቶች በበለጠ ከፍተኛ የስራ እድል ያለው። የኢኮኖሚ ድቀት ተጽእኖም ያን ያህል ያልታየበት ግዛት የሆነውም ለዚህ ነው። ለአሜሪካም ቢሆን ካለ ስጋት በአስተማማኝ ሁኔታ የምታገኘው የነዳጅ ምንጭ የቅርቧና ሰላማዊዋ ጎረቤት ካናዳ መሆኗ ራሱ ዶላራዊ በረከት ነው። ከዚህ አንጻር ነው እንግዲህ በ’እከክልኝ ልከክልህ’ ብሂል ካናዳ ከአልበርታ እስከ የአሜሪካው የቴክሳስ ግዛት ድረስ የሚሄድ የድፍድፍ ነዳጅ ተሸካሚ የቱቦ መስመር ለመዘርጋት ከፍተኛ ፕሮጄክት ቀርጻ የምትንቀሳቀሰው። የአሜሪካ ፕሬዚደንታዊ ፈቃድ የሚያስፈልገው ይህ ፕሮጄክት ኦባማ ውሳኔ በሚጠብቅበት ወቅት ኦባማ ‘ውሳኔዬን ለከምርጫው በኋላ አስተላልፌዋለሁ’ አሉና በይደር ቆየ። እነሆ አሁን በካናዳና በአሜሪካ በኩል ፕሮጄክቱን ከኢኮኖሚ አንጻር በሚሰጠው ጥቅም አይን የሚያዩት ሁሉ ኦባማ ያጸድቁታል ብለው እየጠበቁ ይገኛሉ። የአካባቢ ጉዳይ ተቆርቋሪዎች ደግሞ ኦባማ ለአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ያላቸውን ወገንተኝነት ከምር ለማሳየት ለዚህ ፕሮጄክት ይሁንታቸውን ባለመስጠት ማሳየት ይጠበቅባቸዋል እያሉ ይገኛሉ። አሁን በስራ ላይ ያለና በቀን ወደ 590 000 በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ለተለያዩ የአሜሪካ ነዳጅ ማጣሪያዎች የሚያስተላልፍ  3460 ኪሎሜትር ርዝመት ያለው መስመር አለ። አዲሱና የፕሬዚደንት ኦባማ ፈቃድ የሚጠይቀው ደግሞ አሜሪካን ከላይ ወደ ታች አቋርጦ የሚያልፈውና ድፍድፍ ነዳጅ አንዶቅዷቂ ባለ1897 ኪሎሜትር ርዝመት መስመር ነው። በርካታ ማጣሪያዎች የአስራ ሰባትና የአስራ ስምንት ዓመት የድፍድፍ ግዢ ውል የተፈራረሙበት ከመሆኑ አኳያ ፕሬዚደንት ኦባማ የአካባቢ ጉዳይን ‘ይለፈኝ’ ብለው ለፕሮጄክቱ ፈቃዳቸውን በመጪው የምዕራባዊያን አዲስ ዓመት በመጀመሪያው ሩብ ውስጥ ሳይሰጡ እንደማይቀሩ እየተገመተ ነው። ግምትን ማመን ጊዜው ሲደርስ ነውና ጊዜው ይድረስና እናየዋለን።
ላለው  የሚጨምሩ እጅ ተነሺዎች
በሌላ በኩል የታዳሽ ኃይል አልሚዎች ለምሳሌ የነፋስ ኃይል ኢንዱስትሪው እያገኘ የነበረው በጊዜ የተገደበ የታክስ ጥቅም እንዲራዘም ማድረግ ይጠበቅበቸዋል። ጊዜው አሁን ከአንድ ወር በኋላ የሚያልቅ ከመሆኑ ጋራ ተያይዞ አዛላቂ የመዋእል ንዋይ ፍሰት እንዳይኖር አድርጓል። ለቅሪታዊ ነዳጅ የሚደረገው ድጎማም ሌላው ወሳኝ ጥያቄ ነው። በዓመት እስከ 52 ቢልዮን ዶላር (ከሳንዲ የ50 ቢልዮን ዶላር የጥፋት መጠን መብለጡን ያስተውሏል!)  የሚደርሰው ለቅሪታዊ ነዳጅ ኩባንያዎች የሚሰጠው ድጎማ በአንድ አሰረኛ ደረጃ እንኳን ለመቀነስና ለታዳሽ ኃይል ልማት ለማዋል የተደረገው ጥረት ከንቱ ሆኖ ቀርቷል። የሚያሳዝነው የሚደጎመው ነገር ለአየር ንብረት ለውጥ ጠንቅ የሆነ፤ የሚደጎሙት ደግሞ በትርፍ ላይ ትርፍ የሚያግበሰብሱ ኩባንያዎች መሆናቸው ነው። የአሜሪካ የእጅ መንሻ ፓለቲካ ነድጃ ዘይትና መንግሥት (ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት እንዲል) መቼም እንዳይለያዩ አድርጓቸዋል። ኦባማ በዓመት ከድጎማው አራት ቢልዮን ዶላር ያህል ብቻ ቅነሳ ለማድረግ የሚያስችል የበጀት ሀሳብ በየዓመቱ ቢያቀርቡም በነዳጅ ዘይት ኩባንያዎች እጅ መንሻ የሚደርግላቸው የኮንግረስ አባላት የበዙበት ወሳኝ ኮሚቴ ዞር ብሎ እንኳን አላየውም። በዚህ ጉዳይ ላይ ፕሬዝደንቱ የሆነ እጅ ጠምዛዥ አካሄድ ይጠቀማሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በሁለተኛው ዙር የሥልጣን ዘመን በኃይል ጉዳይ፤ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያና በመሳሰሉት እንዲሰሩ  የሚሾምዋቸው የቅርብ ሰዎቻቸውና አማካሪዎቻቸው ማንነትም ላይ የሚጠበቁ  ስራዎች ይኖራሉ። በሰኔቱም ሆነ በኮንግረስ የተመረጡት ዴሞክራቶች ከአካባቢ ተቆርቋሪዎች ድጋፍ የተሰጣቸውና “አረንጓዴ” ሊባሉ የሚችሉ መሆናቸው ተስፋ ነገር ሰጥቷል። ኮንግረሱ በሪፐብሊካን ቁጥጥር ስር መውደቁ ፕሬዚደንቱ ወሳኝ ጉዳዮች እንዳይወስኑ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ያለው ስጋት እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው።

 =======

አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: