Thursday, May 5, 2011

የ”ጉ” ቤት ለግብጾች


(ጌታቸው አሰፋ)ወደ ጀልባው የገባሁት ዘግይቼ ነበር። ያልተያዘ ወንበር ያለበት ጠረጴዛ ስፈልግ አንድ ብቻውን የተቀመጠ ሰው አየሁና ሄጄ ተቀላቀልኩ። ተዋወቅኩት። ይህ የሆነው የዛሬ ሰባት ዓመት ካናዳ ቶሮንቶ ነው። ከየአገሩ የተሰባሰብን የኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ማብቂያ ላይ በኦንታሪዮ ሐይቅ እየተዟዟርን ለምንበላው እራት ነው ጀልባው ውስጥ የተገኘነው። “ከየት ነህ?” አልኩት። “ከዚሁ ከካናዳ ነኝ። ቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ ነው የማስተምረው” አለኝ። እኔም ተጠየቅኩ። “ከኢትዮጵያ ነኝ። አሁን ግን ስዊድን ነው ያለሁት” ብዬ የነበርኩበትን ዩኒቨርሲቲ ነገርኩት። ጠይምነቱ “መሠረትህ ግን ከየት ነው?” እንድለው ገፋፋኝ። ገና “ከግብጽ” ከማለቱ ሌላ ጥያቄ አስከተልኩ። “በጣም ጥሩ አጋጣሚ….. በመንግሥት ደረጃ ሳይሆን በተራ ግብጻዊ ደረጃ ስለአባይ የሚሰማችሁን ነገር እስቲ ንገረኝ።” የፊቱ  ቀለም ተቀያየረ።
የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መንግሥት ሆን ብሎ ለግብጽ ጥፋት የሚሠራ መሆኑን ከአባይ ጋር በተያያዘም ጉልበቱን ለግብጽ ለማሳየት በኤርትራና በሱማሊያ ጦርነት እንደጫረም ነገረኝ - በስሜት። ውይይታችን ቀጠለ። ቁጣው እየጋለ ነው። እኔም መቆጣት ጀመርኩ (መቆጣት ይነሰኝ?)። “ለበርካታ መቶ ዓመታት እየተራብን እናንተን በማጥገብማ አንቀጥልም”-ነገር አልኩት። ከዛ ረጋ ባለ መንፈስ ስናወራ የማልረሳቸውን ዝርዝር ጥያቄዎች ጠየቀኝ። “ስትገድቡ ምን ያህል ስፋት ያለው መሬት ነው ለማልማት የምታስቡት? የት የት ቦታ የሚገኙ መሬቶች? ውኃውን እስከ ኦጋዴን ድረስ ለመውሰድ ታስባላችሁ?”… አጣደፈኝ። እየፈጠርኩም ቢሆን መለስኩለት። ዛሬም ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ውስጥ የ15 ሺህ ስዎች መኖሪያ በሆነችው የጉባ ወረዳ ላይ ቁፋሮ የተጀመረለትን የአባይን ግድብ ሳስብ የሚመጣብኝ ያ ገጠመኝ ነው።
አሠራሩ ይለያይ እንጂ የሰው ልጅ በዘመናዊ መልክ ወራጅ ውኃን እንዲንዶቆዶቅ የሚያደርገውን ኃይል ነጥቆ ሥራ ላይ ማዋል ከጀመረ ቆይቷል።  ውኃን በግድብ መልክ በአንድ ቦታ በመሰብሰብ ለኃይል ማመንጫነት ሲውል የሚገኘውን ኃይል “ውኃዊ ኃይል” ብለን ሰይመን እንቀጥል። ግድቡ ውኃን አጠራቀመ ማለት ከግድቡ የውኃ መጠንና ከፍታ ጋር የሚመጣጠን ኃይል አጠራቀመ ወይም የኃይል መጋዘን ሆነ ማለት ነው። በግድቡ የተጠራቀመው እምቅ ኃይል ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚቀየረው  ውኃው በአግባቡ በተሰራ ማስተንፈሻ በኩል ተመጥኖ ሲለቀቅ በሚፈጥረው ግፊት ተሽከርካሪ የኃይል ማመንጫ አካላትን ሲመታ ማግኔታዊ ቁሶችና ኤሌክትሪክ አስተላላፊ ገመዶች በሚፈጥሩት ቅንጅት አማካኝነት ነው። 
የውኃዊ ኃይል በዓለም ዙሪያና በኢትዮጵያ 
በዓለም እየመነጨ ከሚገኘው የውኃዊ ኃይል መጠን ቻይና ካናዳና ብራዚል የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ። እንደነ ኖርዌይ፤ ካናዳ፤ ብራዚልና ፓራጓይ ያሉ አገሮች ከአጠቃላይ የኃይል ምንጭ ስብጥራቸው መካከል ውኃዊ ኃይል ዋናው ነው። ለምሳሌ ኖርዌይ 98–99% የኤሌክትሪክ ኃይልዋን የምታገኘው ከውኃዊ ኃይል ነው።
በተለያየ የዓለማችን ክፍሎች በመገንባት  ላይ ካሉት ትልልቅ የውኃዊ ኃይል ማመንጫዎች ከሁለት ሦስተኛው እጅ በላይ የሚሆኑት የሚገኙት በቻይና ሲሆን በብራዚል በህንድና በራሺያም እንዲሁ የሚካሄዱ ግንባታዎች አሉ።
አንዳንድ አገሮች የትልልቅ ግድቦች መገንባት የሚቃወሙ አካላትን ይሁንታ በሚያገኙባቸው ትንንሽና ጥቃቅን የውኃዊ ኃይል ግድቦች ላይ ትኩረት እየሰጡ ይገኛሉ። 
በአህጉራችን ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ የዓለማችን ትልቁና የቻይናውን የስሪ ጎርጅ ግድብን የሚያስንቅ ግድብ ለመገንባት በዝግጅት ላይ ትገኛለች። ይህች አገር ነች በአፍሪካ በብቸኝነት አገራችንን በውኃዊ ኃይል የማመንጫ እምቅ አቅም የምትበልጠው።  በአገራችን ከ113 ዓመታት በፊት የአዲስ አበባው ቤተ መንግሥት የኤሌክትሪክ መብራት ተጠቃሚ ሆነ። ይህ ከሆነ ከ33 ዓመታት በኋላ አቃቂ ወንዝ ላይ የመጀመሪያው ውኃዊ የኃይል ማመንጫ ተገነባ። ይህ ባለ 6.6 ሜጋ ዋት ማመንጫ የጥቂት መኖሪያ ቤቶችና መንገዶች ጨለማን ገፈፈ። ለ30 አንድ ፈሪ ዓመታት ቆይቶ ባለ 43.2 ሜጋ ዋት  ማመንጫ አዋሽ ወንዝ ቆቃ ላይ ተተከለ።  ባለፉት አሥር ዓመታት ደግሞ አበራታች የማስፋፋት ሥራዎች እየተሠሩ ነው። 
ውኃዊ ኃይል - የሚቆሙበትና የሚቆሙለት
በምጣኔ ሀብታዊ አይን ካየነው አንዴ ከተሰራ ኃይል ለማመንጨት ቀጣይ የነዳጅም ሆነ የሌላ ግብአት  የማይፈልግ አማራጭ ስለሆነ የኃይል ማመንጫ ወጪው ዝቅተኛ ነው። በመሆኑም አገራችን አንዴ የተገነባ የኃይል ማመንጫ በቀጣይነት እንዲሠራ ለማድረግ ከውጪ የምታስገባው ግብአት አይኖርም - ከሞላ ጎደል። በአካባቢያዊ ተጽእኖ በኩል ከነፋስ ኃይል፤ ከኑክሌርና ከጸሐያዊ ኃይል ማመንጫዎች የተሻለ የአየር ንብረት ለዋጭ ጋዞች ልቀት መጠኑና ጠቅላላ ዑደታዊ ተጽእኖው ዝቅተኛ ነው። ማሽኖቹ ሲመረቱና በግንባታ ሂደት ወቅት ላይ የሚከሰተው ልቀት ከሌሎች አማራጮች ጋር ሲነጻጸር ልዩነቱ ትልቅ ነው። ይሁንና በምድር ወገብ አካባቢ የሚገኙ አገሮች ላይ ያሉና የሚያመነጩት የኃይል መጠን ከግድቡ ስፋት ጋር ሲነጻጸር አነስ ያለባቸው ቦታዎች አካባቢ በግድቡ ወለል ላይ የነበሩ እጽዋቶች በአየር-አልባ የመበስበስ ሂደት ምክንያት ሲበሰብሱ ከካርቦን ዳይኦክሳድ ከሃያ እጅ በላይ የአየር ንብረትን የሚለውጥ ሚቴን የተባለ ጋዝ ይፈጠራል። በሌላም በኩል የየብስና የውኃማ ስነ-ምኅዳራዊ ተጽእኖው ቀላል የማይባል ሊሆን ይችላል - እንደ ቦታውና እንደ ግንባታው አይነት ቢለያይም። ብዙ ጊዜ የውኃዊ ኃይል ግድቦች የውኃ መጋዝናቸው የሚሸፍነው የመሬት ስፋት ትልቅ በመሆኑ በአካባቢው ያለውን ብዝኃ ሕይወታዊ አካላትን የመዋጥ ጉዳት ያመጣል።  በተጨማሪም መጋዝኑቹ ወጥ የሆነውና መሆንም ያለበትን ቤተ ስነ ምህዳርን ይቆራርጡታል። ይህ የብስን በተመለከተ ሲሆን በውኃዊ ስነ ምህዳር በኩልም ከመጋዝኑ ራስጌና ግርጌ ላይም ተጽእኖ ያሳድራል። ለምሳሌ መጋዝኑና የኃይል ማመንጫው አካል በአካባቢው ላሉ አሳዎች ተፈጥሮአዊ የእንቅስቃሴ ፍኖትና አቅጣጫ ላይ ደንቃራ በመፍጠር በመደበኛ የርቢ ስርአታቸው ላይ ተጽእኖ ያሳድራል። በተለይ የመራቢያ መካናቸው ከግድቡ ራስጌ የሆነባቸው የአሳ ዝሪያዎች የበለጠ ይጎዳሉ። በአትላንቲካና በፓስፊክ የሰሜን አሜሪካ ዳርቻዎች የሳልመን ቁጥር መቀነስ ከዚሁ ጋር እንደሚገናኝ የሚጠቁሙ ጥናቶች አሉ። አሜሪካ ኦሪገን ግዛት ይገኝ የነበረው የማርሞት ግድብ እንዲፈርስ የተደረገው በአሳዎች ላይ ካሳደረው ከፍተኛ ተጽእኖ የተነሳ ነው። 
የግንባታ ሂደቱ በአካባቢው የሚገኙና በዙሪያቸው ካለ የተፈጥሮ ሀብት ጋር የቀጥታም ይሁን ተዘዋዋሪ ቁርኝት ያላቸው ወገኖችን የማያፈናቅል እንዲሆን ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። በዓለማችን ከግድብ ግንባታዎች ጋር በተያያዘ የተፈናቀለው ህዝብ ብዛት የኢትዮጵያን ጠቅላላ የህዝብ ብዛት እንደሚያክል ይገመታል።
ውኃዊ የኃይል ማመንጫ ግድቦች  የቅድመ-መከላከል እርምጃን የሚጠይቁ ሌሎች አሉታዊ ገጽታዎች አሏቸው። ለምሳሌ በደለል መሞላትና የመደርመስ አደጋ። በደለል መሞላቱ የማመንጫውን አቅም ከመቀነስ ጀምሮ እድሜውን እስከማሳጠር ድርስ መዘዝ አለው። መደርመስ ጥራቱን ያልጠበቀ ግንባታ ወይም ቦታው ለርዕደ መሬትና ለመሬት መንሸራተት የተጋለጠ ከመሆኑ የተነሳ ሊከሰት ይችላል። እንደ አገራችን ባሉ ለጦርነትና ለሽብር ጥቃት የተጋለጡ ቦታዎች ላይ ደግሞ በተለይ ታላላቅ ግድቦች የጠላት ቀላል ኢላማዎች ናቸው። የግድቦች መደርመስ ሲከሰት የሚከተለው ጉዳት ቀላል አይሆንም። በደቡብ ቻይና የተከሰተ የአንድ ግድብ መደርመስ  ለ26 ሺህ ሰዎች ሞት በቀጥታ፤ ለሌሎች 145 ሺህ ሰዎች ሞት ደግሞ በተዘዋዋሪ ምክንያት ሆኖ ነበር። ቤት-አልባ የሆኑትን ሚልዮኖችን ሳንቆጥር። 
ሜጋ-ዋቶቻችንና መደረግ ያለበት
የማመንጨት አቅም በሜጋ-ዋት ይገለጻል። ለምሳሌ ለዚህ ጽሁፍ መነሻና የአገራችን ሰናይም ሆነ እኩይ የሚመኙ ሰዎች ሁሉ ቀልብ የሳበው ግድብ 5250 ሜጋ-ዋት ኃይል ማመንጨት የሚችል ነው። ለተጠቃሚው የሚጠቅመው  ከአንድ የውኃዊ ኃይል ማመንጫ ሜጋ-ዋት በላይ ሜጋ-ዋት-አወሩ (ጊጋዋት-አወር ወዘተም ሊሆን ይችላል) ነው። እስቲ የመጠጥ ውኃን ምሳሌ  አድርገን እንየው።  ከለገዳዲ ተጣርቶ ወደ ተጠቃሚው የሚላክ ውኃ የፍሰት መጠን በሊትር በሰከንድ መናገር ይቻላል። ይህ የፍሰት መጠን የሚወሰነው ለገዳዲ ባለው የውኃ መጠን፤ በሚለቀቅበት የቧንቧ ስፋት ብሎም ግፊትና በመሳሰሉት ነው። እዚህ ድረስ ሜጋ-ዋት ነው። በዓመት ወደ ተጠቃሚው የሚደርሰው የውኃ መጠን የሚወሰነው ግን ከላይ ካልኩት በተጨማሪ ለገዳዲ በሙሉ አቅም ያለምንም እንከን የሚሰራበት የጊዜ ርዝማኔም ጭምር ነው። እየተንጠባጠበ ለተወሰኑ ወራት በመሥራትና እንደ ጉድ እየወረደ ዓመቱን ሙሉ በመሥራት መካከል ያለውን ልዩነት ማሰብ ማለት ስለ ሜጋ-ዋት አወር ማሰብ ማለት ነው።  እንግዲህ ግድቦቻችን ከፍተኛ የሜጋ-ዋት አወር መጠን እንዲያመነጩ ለማድረግ አስፈላጊው ነገር ሁሉ ማድረግ ይጠበቃል። 
ወደ ጎረቤት አገሮች ልንሸጠው የምናስበውን ኃይል የመሸጫ ዋጋ  ለግድቡ ግንባታ የምናወጣው ወጪ የምንመልስበት ጊዜ ማጠርና መርዘም ላይ ሚና ይጫወታል። በተለይ ጥቅመ-ብዙ ግድቦች የግንባታ ውጪያቸውን በቀላሉ የመመለስ አቅም አላቸው።
 ከስሌቶች  እንደታየው የቻይናው የስሪ ጎርጅ ግድብ ከ5 እስከ 8 ዓመት በሙሉ አቅሙ ከሰራ የኃይል ሽያጭ ገቢው የግንባታ ወጪውን ይሸፍናል (የውኃዊ ኃይል ማመንጫዎች ከሃምሳ እስከ መቶ ዓመት ይሠራሉ)። አገራችን ግድቦችን አዋጪና ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ በስፋት መገንባትና ጥሩ ዋጋም ማግኘት ከቻለች የኤሌክትሪክ ኃይል የውጪ ምንዛሬ ማስገኛ መንገዶችን ቁጥር የሚጨምር ይሆንልናል። ፓራጓይ  መቶ በመቶ የኤሌክትሪክ ኃይልዋ በውኃዊ ኃይል ላይ የተመሠረተ ሲሆን  ከምታመነጨው  90% ያህሉ ደግሞ ወደ ብራዝልና አርጀንቲና የሚሸጥ ነው። 
አዲሱ ግድብ ልዩ ፋይዳ ያለው ከመሆኑ የተነሳ የውኃ ላይ ስፖርት ማዕከል ያለው፤ለአገር ውስጥ ጎብኚዎች መስህብ የሚሆን እንዲሁም የውኃ ላይ ግብርናን ያካተተ ሆኖ መልማት አለበት። ከማኅበረሰባዊና ከምጣኔ ሀብታዊ አውታሮች አንጻር ስናየው በውሃ-አጠር ወቅቶችና ዓመታት ሊታደጉን የሚችሉ ሌሎች ተጠባባቂ  አማራጭ የኃይል ምንጮችን አብሮ ጎን ለጎን ማልማት የግድ ይላል።
ታላቁን ግድብ ለመገንባት ገና ከመነሳታችን ግብጽ እየተቆጣች ነው። ከዚህ ቀደም ግብጽ ጉንደትና ጉራዕ ድረስ መጥታ ነበር - ከዛሬ 136 ዓመታት በፊት። በወቅቱ በአጼ ዮሐንስና በአሉላ አባ ነጋ ተመልሳለች። ዘንድሮ ጉባ ድረስ የሚያስመጣ ነገር የላትም። ይልቅ አርፋ ኤሌክትሪክ ከጉባ ወደ ደቡብ ግብጽ የሚሄድበትን ቀን ትጠብቅ። እስከዛው የግብጽ ሕጻናት ፊደል ሲቆጥሩ ‘ “ጉ” …ጉንደት ጉራዕና ጉባ’ ይበሉ።   
 -------------
ሚያዝያ 22 ቀን 2003 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለውአዲስ ጉዳይመጽሔት ላይ መደበኛውየአረንጓዴ ጉዳይዓምዴ ላይ የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: