Sunday, November 25, 2012

ቆሻሻን ከመጋራት ጽዳትን መጋራት


(ጌታቸው አሰፋ፤ ሐምሌ 14  ቀን  2004 ዓ.ም.)በቅርቡ በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ የተመራና ከአዲስ አበባ መስተዳድር የሥራ ኃላፊዎችም አባል የሆኑበት የልኡካን ቡድን ወደ ሩዋንዳ ኪጋሊ አምርቶ ነበር። ኢቲቪ እንደዘገበው ሚኒስትሩ በኪጋሊ ከተማ ጽዳት ተገርመዋል - ‘ለውርርድ ያህል መንገድ ላይ የተጣለ ቆሻሻ አይታይም’ እስኪሉ ድረስ። ኢቲቪ ያሳየን የከተማዋ ጸዳ ያሉና አረንጓዴ አደባባዮች ምስልም ሚኒስትሩና ዘጋቢው በቃል የገ ልጹትን የሚደግፉ ነበሩ። በአላማው ውስጥ ‘ኪጋሊ እንዴት እንዲህ ጸዳች?’ ‘አዲስ አበባን እንዴት ብናደርጋት ነው ጸዳ ያለች ሆና የምትዘልቀው?’ የሚሉትን ጥያቄዎች መመለስን ያካተተው ተልእኮ ‘አሁን ገብቶናል!’  በሚል ድምዳሜ የተጠቃለለ ይመስላል - እንደ ኢቲቪ ዘገባ። ምን እንደገባቸው ወይም የሩዋንዳ አቻዎቻቸው ምን አይነት ጠንቋይ እየቀለቡ ኪጋሊን እንደዛ እንዳደርጓት ዘገባው አልነገረንም። በአጠቃላይ ከቅርብም ከሩቅም የልምድ ልውውጥ ማድረጉ ጥሩ ነው። አዲስ አበባ ግን ‘ኪጋሊ ድረስ ሳይኬድ መደረግ ያለበት ነገርም ነበር አለም!’ ትላለች - እነሆ እንስማት።

ሸገር-በቀል ጅምሮች
ጋሽ አበራ ሞላ አያስቀርቤ አያስጠጌ የነበሩትን የከተማዋን ቦታዎችና አደባባዮችን አጽድቶና አስውቦ አሳይቷል። ለአይን የሚቀፉ ለአፍንጫ የሚከረፉ የነበሩ በሽተኛ ስፍራዎችን አክሞ በላያቸው ላይ ሻይ ቤትና ምግብ ቤት መሰራት እስኪቻል አድርሷቸዋል። ‘እንዴት ሆነልህ?’ መባል አለበት - እሱ። ‘በትንሹ የተሰራውን በትልቁ እንዴት እንሂድበት?’ ‘በአጭር ጊዜ ውስጥ የተቻለውን እንዴት ለዘለቄታው እናስቀጥለው?’ ‘በሰራኸው ስራ ውስጥ የተሳተፉት የተከፈላቸውም ያልተከፈላቸውም ወጣቶችና ሌሎች ሰዎች አይነት እንቅስቃሴ ተቋማዊ ቅርጽ አስይዞ ማስቀጠል የሚቻለው ምን ቢደረግ ነው?’ ለእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች ቢያንስ ከፊል መልስ ለመስጠት ጋሽ አበራ ሞላ ልምድ አለው።
በየቦታው የቆሻሻ መጣያ ቋቶች አሉ - ሲሞሉ ወይም ችግር ሲያጋጥም ተደውሎ የሚነገርበት ስልክ ቁጥርም በላያቸው ላይ የተጻፈባቸው። ሰሞኑን በየቦታው በእግር ስዞር የታለመት አላማ የሚፈጽም አንድም ቋት አላገኘሁም - ብሳሳት ደስ ይለኛል።  አንዷ ቋት አጠገብ ቆሜ ‘አሁን በዚህ ስልክ ቁጥር ብደውልና ስልኩ ቢነሳ ምን ብዬ ልናገር እችላለሁ’ ስል አሰብኩ። ሲጀመር አላማው ‘በዚህ አካባቢ ከሚገኙት ቋቶች ከላይ ወደታች ሦስተኛው ወይም አራተኛው ቋት በጣም ሞልቶ ቆሻሻው ወደውጪ እየፈሰሰ ነው’ ወይም ‘ስድስተኛው ቋት በአንድ ጎኑ ተነቅሏል’ ተብሎ እንዲደወል ነው። አሁን ሁሉም በማይሰሩበት ሁኔታ ምን ተብሎ ነው የሚደወለው? ‘አዲስ አበባ በቆሻሻ ሞልታ ወደውጪ እያፈሰሰች ነው’ ወይስ  ‘የአዲስ አበባ የቆሻሻ ማስወገጃ ስርአት በደንብ ሳይሰራ ተነቃቅሏል’?
የቋቶቹ ስራ ከዲዛይን ጀምሮ በጥናት ላይ ለመመስረታቸው ምልክት የለም። ላስቲክ እላያቸው ላይ ተገጥሞ በመደበኛነት በየሃያ አራት ወይም አርባ ስምንት ሰዓቱ ቆሻሻ የያዘውን ላስቲክ አንስቶ ሌላ አዲስ ላስቲክ በመተካት የሚያሰራ መሆን ነበረበት። የጽዳት ስራው ጥሩ የሚሄደው የአዲስ አበባ ኗሪ የሚጣል ቆሻሻን ቋት ውስጥ እንጂ ከቋት ውጪ ያለመጣል ባህል ሲኖረው ነው።  ይስሩም አይስሩም ቋቶቹ ሞልተው አይታዩም - አልተጣለባቸውማ! ያልተጣለባቸው ደግሞ ስለማይሰሩ ወይም ቶሎ ቶሎ ስለማይጋቡ አይደለም። የትም መጣል የፋራ ማድረግ ካልቻልን ከባድ ነው። የትም የሚሸናውንና የሚጥለውን ሰው ካልተጸየፍን አዲስ አበባን ማጽዳት ቀላል አይሆንም። የምንውልበትና የምናድርበት አካባቢን ማቆሸሽ የነውሮች ነውር ያላደረገ ኅብረተሰብ ይዘን  ጽድት ያለች አዲስን ማየት እንዴት ይቻለናል? ጎዳና ላይ ያሉት ወገኖቻችን በቀንም በሌትም በሚውሉበት አካባቢ ቆሻሻ ሲጥል የሚያዩትን ሰው ‘አይደላንምና ተው’ ካላሉት ጸዳ ያለች ሸገርን የኛ የማድረግ ምኞታችን እንዴት እውን ይሆናል? 
የጽዳት ጓዶች
እያንዳንዷ የአዲስ አበባ መንገድና ስፍራ ተሸንሽና በጽዳት ጓድ ስር መዋል አለባት። የጽዳት ጓዱ ስራ በመከላከል ላይ ያተኮረ የማንቃትና የማስተማር ስራን ከተግባራዊ የማጽዳት ስራ ጋር አቀናጅቶ የሚያስኬድ ሊሆን ይችላል። ቋቶችን የሚያጋቡና  ከቋት ውጪ የተጣለውን የሚያነሱት የተለያዩ ቢሆኑ ይመረጣል። ከቋት ውጪ የተጣለውን የሚያነሱት ከእዝ ቦታቸው የማይጠፉ መሆን አለባቸው። የተጣለ ቆሻሻ እስካሁን እንዳለው በተጣለበት ቦታ ተደላድሎ እንዲቀመጥ እድሜ ሊሰጠው ስለማይገባ ብዙም ሳይቆይ በማንሳት እድሜውን እንዲያሳጥሩ። በተግባር ስናየው ቆሻሻ ቆሻሻን የሚጠራ እስኪመስል ድረስ ያለውን ሂደት በአጭሩ በመቅጨት ስራ በተከታታይነትና በመደበኛነት ሲመታ ከቋት ውጪ ለመጣል ‘የሚጎመዥ’ ሰው ቁጥር እየቀነሰ ይመጣል። በየአካባቢው የጽዳት ጓዶች በሚታዩበት ወቅት ደፍሮ የሚጥል ሰውም ላይኖር ይችላል።
ልኬትና ክትትል
ሂደቱ ያለምንም እንከን መሄድ አለመሄዱን የሚቆጣጠር ለምሳሌ የሃምሳ ወይም መቶ ቋቶች አለቆች ሊኖሩ ይገባል። ከቋት ውጪና ከቋት ውስጥ የሚሰበሰበው ቆሻሻ መጠንም በቦታና በጊዜ (ለምሳሌ በቀን ወይም በሳምንት) ተለክቶ ተሰፍሮ የሚታወቅ መሆን አለበት።  የሁለቱም መጠን ለብቻ እንዲሁም ድምራቸው ለመነሻ ያህል ከታወቀ የምንዘረጋው ስርአት ውጤታማ መሆን አለመሆኑ ለመከታተል እንችላለን። ከየቦታው ለምሳሌ በየሳምንቱ የሚሰበሰበው አፍአ-ቋት(ከቋት ውጪ) ቆሻሻ መጠን ወደ ዜሮ እስኪጠጋ ድረስ እየቀነሰ መምጣቱን ማረጋገጥ አለብን። በዛው መጠን የቋቱ ቆሻሻ መጠን ደግሞ መጨመር አለበት።  በጊዜ ሂደት ሌሎች ተገቢ የፓሊሲና አመቺ የአኗኗር ዘይቤ ስርአቶች ሲኖሩን ደግሞ አጠቃላይ የቆሻሻ መጠናችን ወደ መቀነስ የሚያመራ ‘ከምንጩ የማድረቅ’ ስራ መስራት ይገባናል (ሌላ ቀን እመለስበት ይሆናል)።
ይህ አሰራር ኀብረተሰቡ ዳግም ላያንቀላፋ እስኪነቃና ከሕይወቱ ጋር እስኪዋሃድ ድረስ የሚቀጥል እንጂ በዘመቻ መልክ በአንዴ ጮኾ ወዲያው እንደሚጠፋ የአጨብጫቢዎች ድምጽ መሆን አይገባውም።ቆሻሻን የትም የሚጥል ሰው ብርቅ ወደመሆን ደረጃ ማድረስ የሚቻለን ከቁርጠኝነት ጋር በርካታ የሰው ኃይል ሲኖረን ነው። ተከፍሏቸው ወይም ተቀጥረው ከሚሰሩት በተጨማሪ የመንግስትና የልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ክፍል አደረጃጀት አባላት የየራሳቸውን ድርሻ አላቸው - የማንቃት፤ የማስተማርና ተግባራዊ የቆሻሻ ማንሳት ስራን መስራት ጨምሮ። አሰራሩን ለመዘርጋትም ሆነ ያለምን እንከን ለማስኬድ ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል። ይህ ወጪ ደግሞ በመደበኛ በጀትና የበጀት ምንጮች ሊሸፈን አይችልም። እንደ አገር ወይም እንደመንግሥት ዛሬ ከባድ የምንለው ወጪ አውጥተን ልክ ማስገባት የምንችለውን ጉዳይ ከወጪው ከፍተኛ መሆን አንጻር በይደር በማቆየታችን ወደፊት የፈለገውን ያህል ወጪ ብናወጣ የማንፈታው ችግር ውስጥ ሊያስገባንና ዘርፈ ብዙ ዋጋ ሊያስከፍለን ይችላል። የምንከፍለው ዋጋም በገንዘብ ከመተመን በላይ ነው። ነገም ሆነ ዛሬ የሚወጣው ወጪ የአገሪቱ ሀብት በመሆኑ ዛሬ ማውጣት ያለብን ወጪ ላይ ከተማመንን ከመደበኛ የበጀት ጣራ በላይ አንገቱን የሚያስረዝመው ወጪን እንዴት እንሸፍነው የሚለውን እናንሳ።   
በዋና ዋና አደባባዮችና መንገዶች ላይና ዙሪያ የሚኖሩ ቋቶችና በቋቶች መካከል ያለውን ቦታ ጽዳት ለመጠበቅና ለማስጠበቅ በነዚህ አደባባዮችና መንገዶች ዙሪያ ያሉ የንግድ ተቋማት፤ ኩባንያዎችና መስሪያ ቤቶች የጽዳት ወጪውን መጋራት አለባቸው። ወደዱም ጠሉም በዙሪያቸውና በደጃፋቸው የሚጣለውን ቆሻሻ እየተጋሩት ነው። የቆሻሻውን አስቀያሚ ገጽታ ከመጋራት ደግሞ የጽዳት ስራውን መጋራት ይሻላቸዋል። አዲስ አበባን ማጽዳት ማለት የውጪ ዜጎች የሚያይዋቸው አደባባዮችና ዋና ዋና መንገዶችን ብቻ በማጽዳት ብቻ መወሰን ማለት አይደለም። ከተማችን መጽዳት ያለባት በዋናነት ለእኛና ለእኛ ተብሎ መሆን አለበት።  በመሆኑም ጽዳቱና የቋት ሰንሰለት ዝርጋታው ወደ ከተማችን የውስጥ ገላም ዘልቆ መግባት አለበት።  በነዚህ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችና መንደሮች የሚሰራው ጽዳትን የመጠበቅ ስራ በየመንደሩ በሚገኙ የእድርና መሰል ማኅበራት ዋና ተዋናይ የሚሆኑበት ሊሆን ይገባል። እድሮች ከተለመደው አላማና አሰራራቸው ወጥተው ሟች ቀባሪና ለቋሚ ከፋይ ከመሆን አልፈው አካባቢያቸውን እያሸተተ ያለውን የቆሻሻ ሬሳ ገንዘው ለመቅበርና ዘላቂ ጽዳትና ማስጠበቂያ ወጪ ለመሸፈን መንቀሳቀስ አለባቸው። ሌላ አይታለፌ አጻፊ ርእስ ቅድሚያውን ካልወሰደው በጀመርነው ጉዳይ ላይ ሳምንት እንመለስበታለሁ። ጸዳ ያለ ሳምንት ያድርግልንና!

 =======

አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: