Sunday, August 14, 2011

የምር አቀንቃኞች


(ጌታቸው አሰፋ) በወቅቱ እሠራበት የነበረው የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ገና መጀመሩ ነበር - እንደ ዩኒቨርስቲ። ከመደበኛ ሥራዬ ውጪ የአካባቢና የተፈጥሮ ሀብት ጉዳይ የሚገደን ሰዎች ተሰባስበን ክልላዊ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ በማስጨበጥ ሥራዎች ላይ የሚያተኩር መንግሥታዊ ያልሆነ ማኅበር አቋቁመን መንቀሳቀስ ጀመርን።እኔ የማኅበሩ ጸሐፊ፤ በግብርና ቢሮ የሚሠራ ሌላ ባለሙያ ደግሞ ሰብሳቢ ሆነን ነበር።  በወቅቱ የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ለበርካታ ዓመታት በፓሊቴክኒክነት የቆየውን ግቢ ወደ ቴክኖሎጂ ፋኩልቲ ደረጃ ለማሳደግ አስፈላጊ የነበሩ ግንባታዎችን በስፋት እያጧጧፈ ነበር። ግቢው ቀድመውኑም ቢሆን በጣም ሰፊ ነበርና የቦታ ጥበት አልነበረውም። ይሁንና እስካሁን ድረስ በማይገባኝ ምክንያት ነባር ዛፎች እየተቆረጡ  የነበሩበት ቦታ ላይ ህንጻዎች መተካት ጀመሩ። አንዳንዶቹ ዛፎች የማስፋፋቱ ሥራ ከመጀመሩ ከሠላሳ አራት ዓመታት በፊት ከተቋቋመው ፓሊቴክኒክ ግቢ በላይ እድሜ-ጠገብ ነበሩ።