(ጌታቸው አሰፋ) ጊዜው 1981 ዓ।ም। ነበር ። እኔም 11ኛ ክፍል ነበርኩ። መኝታ ቤታችን ውስጥ ከነበረው ቁም ሳጥን ላይ የእጅ መዳፍ የምታህል ላስቲካማ ወረቀት ተለጥፋለች። ውሃ ሰማያዊ መደብ፤ ቀይ ጠርዝ መሐል ላይ ቢጫ አበባ። ቁም ሳጥኑ ላይ ከተለጠፈች ሁለት ዓመት ሆኗታል። የአዲስ አበባን መቶኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀች ነበረች። በ1979 ዓ।ም। መሆኑ ነው። ዛሬ አዲስ አበባ የ124 ዓመት “ጎልማሳ” ነች። የአክሱም፤የጎንደር፤የላሊበላ፤የአንኮበር፤ የእድሜ የታናሽ ታናሽ - አዲስ አበባ። ከአዲስ አበባ መቆርቆር ጀርባ የነበረው መነሻ በጎ የሚባል አይነት አልነበረም። የማገዶ እና የቤት መሥርያ እንጨት እጥረት ጋር የተያያዘ መዘዝ ነው አዲስ አበባን ያስገኘልን።
ለብዙ የጥንት ስልጣኔዎች መንገራገጭ ምክንያት የሆነ መዘዝ። ለአንዳንድ ከተሞች መቆርቆዝ ለሌሎች ደግሞ መቆርቆር ምክንያት ሆኗል። በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት በቻይና በጃፓን የደን መጨፍጨፍና መመናመን ሰዎች የሚኖሩባቸውን ቦታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲቀያይሩ አድርጓል።