Wednesday, May 18, 2011

መከላከያና አካባቢ

(ጌታቸው አሰፋ) ጠበብ አድርገን ካየነው ኦሳማ ቢን ላደንን የመግደል ተልእኮ የፈጸሙት 4 ሄሊኮፕቶሮች፤ 24 ወታደሮች (እንደ ቆጣሪው ቢለያይም) እና አንድ “ካይሮ” የተሰኘ ስልጡን ውሻ ናቸው። አስፍተን ካየነው ግን ቢን ላደንን አንዴ የተፈጥሮ አካባቢን ደጋግሞ እየገደለ ያለው ከአቦታባድ ተልእኮ በስተጀርባ ያለው በዘመናዊ ውስብስብ ቴክኖሎጂና በመደበኛ የስለላ አውታሮች የሚታገዘው ግዙፉ የአሜሪካ መከላከያ ነው። የአሜሪካ መከላከያ በዓለማችን ከፍተኛና ስርጭተ-ሰፊ አካባቢ በካይና አጎስቋይ ተቋም የመሆኑ ነገር ነው የዛሬ “የአረንጓዴ ጉዳይ” መቆያችን። 

Thursday, May 5, 2011

የ”ጉ” ቤት ለግብጾች


(ጌታቸው አሰፋ)ወደ ጀልባው የገባሁት ዘግይቼ ነበር። ያልተያዘ ወንበር ያለበት ጠረጴዛ ስፈልግ አንድ ብቻውን የተቀመጠ ሰው አየሁና ሄጄ ተቀላቀልኩ። ተዋወቅኩት። ይህ የሆነው የዛሬ ሰባት ዓመት ካናዳ ቶሮንቶ ነው። ከየአገሩ የተሰባሰብን የኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ማብቂያ ላይ በኦንታሪዮ ሐይቅ እየተዟዟርን ለምንበላው እራት ነው ጀልባው ውስጥ የተገኘነው። “ከየት ነህ?” አልኩት። “ከዚሁ ከካናዳ ነኝ። ቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ ነው የማስተምረው” አለኝ። እኔም ተጠየቅኩ። “ከኢትዮጵያ ነኝ። አሁን ግን ስዊድን ነው ያለሁት” ብዬ የነበርኩበትን ዩኒቨርሲቲ ነገርኩት። ጠይምነቱ “መሠረትህ ግን ከየት ነው?” እንድለው ገፋፋኝ። ገና “ከግብጽ” ከማለቱ ሌላ ጥያቄ አስከተልኩ። “በጣም ጥሩ አጋጣሚ….. በመንግሥት ደረጃ ሳይሆን በተራ ግብጻዊ ደረጃ ስለአባይ የሚሰማችሁን ነገር እስቲ ንገረኝ።” የፊቱ  ቀለም ተቀያየረ።

ፉኩሺማዎች



(ጌታቸው አሰፋ)  በተወዳጅዋ ጃፓን በደረሰው አደጋ ወስዋሽነት ለዛሬ ስለኑክሌር ኃይል እጽፋለሁ። ሰኔ 27 1954 እ.አ.አ. የቀድሟ ሶቭየት ኅብረት መንግሥት  ንብረት የሆነው በዓለም የመጀመሪያው የኑክሌር ኃይል ማመንጫ  የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ ጀመረ። የኑክሌር ኃይል ማመንጫዎች ዋነኛ ግብአትና ጥሬ ዕቃ ዩራኒየም እንደሚሰኝ ይታወቅና እንቀጥል።  በዛው ዓመት ማለትም 1954 - አንድ ወር ቀደም ብሎ - ግንቦት 27  “ጄት” የተባለው የጥቁር አሜሪካዊያን መጽሔት እንደሚከተለው ዘገበ፡  “በዓለም ምርጥ ጥራት ካላቸው የዩራኒየም ማዕድናት ተርታ የሚሰለፍ በባለሥልጣናት ዘንድ ‘አብይ ግኝት’ የተባለለት  ዩራኒየም በኢትዮጵያ ተገኘ ሲሉ አጼ ኃይለ ሥላሴ በአዲስ አበባ ተናገሩ። አጼው የማዕድኑን መጠን ከመናገር  የተቆጠቡ ሲሆን ‘የባህር ኃይል መርከቦችን’ ጨምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ወታደራዊ ሰፈር ለማቋቋም የሚያስችል የ99 ዓመት ስምምነት ለማድረግ  ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር እየተነጋገርን ነው ብለዋል።” 
ዛሬ በዓለም ወደ 31 በሚሆኑ አገሮች ውስጥ ወደ 480 የኑክሌር ማብላሊያዎች (ሳሳጥረው ማብልያዎች) ይገኛሉ - የዛሬ ወር በርዕደ መሬትና በውኃ ነውጥ አደጋ የደረሰበት የጃፓኖቹን 6 የፉኩሺማ ዳይቺ የኑክሌር ማብልያዎችን ጨምሮ ።