Thursday, May 5, 2011

ፉኩሺማዎች(ጌታቸው አሰፋ)  በተወዳጅዋ ጃፓን በደረሰው አደጋ ወስዋሽነት ለዛሬ ስለኑክሌር ኃይል እጽፋለሁ። ሰኔ 27 1954 እ.አ.አ. የቀድሟ ሶቭየት ኅብረት መንግሥት  ንብረት የሆነው በዓለም የመጀመሪያው የኑክሌር ኃይል ማመንጫ  የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ ጀመረ። የኑክሌር ኃይል ማመንጫዎች ዋነኛ ግብአትና ጥሬ ዕቃ ዩራኒየም እንደሚሰኝ ይታወቅና እንቀጥል።  በዛው ዓመት ማለትም 1954 - አንድ ወር ቀደም ብሎ - ግንቦት 27  “ጄት” የተባለው የጥቁር አሜሪካዊያን መጽሔት እንደሚከተለው ዘገበ፡  “በዓለም ምርጥ ጥራት ካላቸው የዩራኒየም ማዕድናት ተርታ የሚሰለፍ በባለሥልጣናት ዘንድ ‘አብይ ግኝት’ የተባለለት  ዩራኒየም በኢትዮጵያ ተገኘ ሲሉ አጼ ኃይለ ሥላሴ በአዲስ አበባ ተናገሩ። አጼው የማዕድኑን መጠን ከመናገር  የተቆጠቡ ሲሆን ‘የባህር ኃይል መርከቦችን’ ጨምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ወታደራዊ ሰፈር ለማቋቋም የሚያስችል የ99 ዓመት ስምምነት ለማድረግ  ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር እየተነጋገርን ነው ብለዋል።” 
ዛሬ በዓለም ወደ 31 በሚሆኑ አገሮች ውስጥ ወደ 480 የኑክሌር ማብላሊያዎች (ሳሳጥረው ማብልያዎች) ይገኛሉ - የዛሬ ወር በርዕደ መሬትና በውኃ ነውጥ አደጋ የደረሰበት የጃፓኖቹን 6 የፉኩሺማ ዳይቺ የኑክሌር ማብልያዎችን ጨምሮ ። 


ጥቂት ስለ ቴክኖሎጂው 
የተለያየ አይነት ዩራኒየም አለ። ወደ 0.7 ፐርሰንት የሚሆነውና ለኃይል ማመንጫነት እየዋለ ያለው ዩራኒየም-235 የሚባለው ነው። ዩራኒየም-235ና መሰል ተፈርካሽ አቶሞች ኒኩለሳቸው(የአቶሞች ማዕከላዊ አካል) በኒውትሮን ሲነረት ሁለትና ከዛም በላይ ወደሆኑ ትንንሽ ኒኮለሶች ይፈረከሳሉ። በፍርከሳው ሂደት ኃይል፤ በይ-ጨረርና ሌሎች ኒውትሮኖች ይወጣሉ። እንደገና የተወሰኑት ኒውትሮኖች ሌላ ኒኩለስ ሲነርቱ ሌላ ኃይል፤ሌላ በይ-ጨረርና ሌሎች ኒውትሮኖች ይገኛሉ። ፍርከሳው ተቀጣጣይ ከመሆኑ የተነሳ የማያቋርጥ የኃይል ምንጭን ይፈጥራል።
የፍርከሳው ሂደት ገደብ እንዲኖረው ወደቀጣይ የፍርከሳ ሥራ የሚሰማሩት የኒውትሮኖች ብዛት እንዲመጠን  ይደረጋል። ለምሳሌ የኑክሌር ማብልያው አካባቢ የአደጋ አምጪ ምልክቶች ከታዩበት  የፍርከሳው እንዲቋረጥ የሚያደርጉ ኮምፒዩተር-መርና ሰው-መር ስርዓቶች አሉ። 
በፍርከሳው ሂደት የሚፈጠረውን ከፍተኛ የሙቀት ኃይል ከማብልያው ከርስ ወደ ኃይል ማመንጫው ክፍል ተሸክሞ የሚወስደው የማቅዝቀዣ ስርዓት የሚባለው ነው። አቀዝቃዡ የተሸከመውን የሙቀት ኃይል ወደ ውኃ  በማስተላለፍ ውኃዉን ከፍተኛ ግፊት ወዳለው እንፋሎት እንዲቀየር ሲያደርግ  መደበኛ ጂኔሬተራዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ስርዓት ይከተላል ማለት ነው።
የተለያዩ የኑክሌር ማብልያ ቴክኖሎጂዎች የተለያየ ግብአት፤ እና ማቀዝቀዣ ብሎም የመቆጣጠሪያ ስርአቶች አሏቸው። ለምሳሌ ለባህር ሰርጓጅ መርከቦች የሚሆነው ማብልያ አይነቱና ግብአቱ ከመደበኛው የኃይል ማመንጫ  ማብልያና ግብአት ጋር አንድ አይደለም። 
የኑክሌር ማገዶው በዱላ መልክ ይዘጋጃል። አንዴ ወደ ማብልያ የገባ ዱላ ኃይል እያመነጨ ለ6 ዓመታት በዛው ይቆያል።  በ6 ዓመት ቆይታው መጀመሪያ ይዞት ከገባው የዩራኒየም ይዘት ወደ 3.5 ፐርሰንት የሚሆነው ብቻ የፍርከሳና የኃይል ማመንጨት ሂደቱ ላይ ተሳትፎ ሲያበቃ የኑክሌር ከሰል ሆኖ ይወጣል።  የኑክሌር ከሰሉ ሙቀቱን ለመቀነስና የበይ-ጨረር ምንጨነቱን ለማስታገስ ለ5 ዓመታት ያህል በውኃ ገንዳ ይነከራል። ከዛም ወደ ቋሚ ደረቅ መጋዘን ከተቻለም እንደገና ጥቅም ላይ ሊውል ወደሚችልበት ቦታ ይወሰዳል። 
በተለያዩ አገሮች
በብዙ አገሮች በተለይ ባደጉት የኑክሌር ኃይል የብሔራዊ የኃይል ምንጭ ቀመራቸው ውስጥ አንድ ዋና አካል ነው።  ለምሳሌ በፈረንሳይ 58፤ በስዊድን 10፤በካናዳ 18፤ በአሜሪካ 104፤ በቻይና 13፤ በራሺያ 32 ማብልያዎች አሉ። በቻይና 27፤ በራሺያ 11 ማብልያዎች በግንባታ ላይ ሲሆኑ እንዲሁም በኮሪያ በሕንድ በኢራንና በሌሎች አገሮችም ግንባታዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ።  
ከአፍሪካችን ደቡብ አፍሪካ 2 ማብልያዎች ሲኖርዋት ሊቢያ ግብጽ ሞሮኮና አልጀሪያ የምርምር ጣቢያዎች አሏቸው። ግብጽ እስከ 2025 4 ማብልያዎችን ለመገንባት ከራሺያ፤ ፈረንሳይ፤ ቻይና፤ ኮሪያ፤ አሜሪካና አወስትራልያ እገዛ እየተደረገላት ነው።  እድሜያቸው ወደ አርባዎቹ የሆኑት እንደ ፉኩሺማ ዳይቺ አይነት በየአገሩ የሚገኙት ማብልያዎች ሲገነቡም ሆነ ሲጠገኑ ዝቅ ያለ ወጪ ነው የሚያስወጡት - በተነጻጻሪነት። ችግር ሲመጣ ደግሞ በቀላሉ ለአደጋ የሚጋለጡ አይነት ናቸው። ዛሬ በፉኩሺማ በደረሰው አደጋ ምክንያት የአደጋ መካች ቴክኖሎጂዎች ተፈላጊነት ይጨምራል- ምንም ውድ ቢሆኑ ። ፈረንሳይና ጃፓን በሰባዎቹ ዓ.ም. የኮረንቲ ኃይላቸውን ያገኙ የነበረው ከነዳጅ ዘይት ነበር። የ1973ቱ የነዳጅ ዘይት ቀውስ ግን ሁኔታውን ለወጠው።  ጃፓን 73% ከነዳጅ ዘይት ይገኝ ለነበረው የኤሌክትሪክ ኃይሏ መፍትሔ ስታፈላልግ የኑክሌር ኃይል ነው የደርሰላት። ሥራም ጀመረች። ዛሬ ወደ 54 ማብልያዎች አሏት። ጃፓን 30%፤ፈረንሳይ ደግሞ 80% የሚሆነው የኤሌክትሪክ ኃይላቸውን የሚያገኙት ከኑክሌር ኃይል ነው።አሜሪካ ፈረንሳይና ጃፓን 60% የሚሆነውን የዓለም ኑክሌር ኃይል በማመንጨት የአንበሳውን ድርሻ ይዘዋል።
ጠንቅና አደጋ  
የኑክሌር ኃይል ከካርቦን ልቀት ከሞላ ጎደል የፀዳ ነው ሊባል ይችላል። በሌላ በኩል የግንባታ ወጪው በጣም ከፍተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ዝቃጩ ወይም የኑክሌር ከሰሉ የአደገኛ በይ-ጨረር ምንጭ ስለሆነ ደኅንነቱ የተጠበቀ ቦታ ማስቀመጥን ይጠይቃል። ወደፊት ለጤናም ለአከባቢም ጠንቅ እንዳይሆን ማድረግ የሚችል ሂደት እስኪበለፅግ ድረስ ማለት ነው። ከማብልያው ሊያፈተልክ የሚችለው በይ-ጨረርም ስጋት ያሳድራል። በተጨማሪ ጥሬ እቃውም ሆነ የኑክሌር ከሰሉ በጥፋት ኃይሎች እጅ ገብተው ለኑክሌር ቦንብ መስሪያነት ሊውሉ ሰለሚችሉ ለአገራዊና አለምአቀፋዊ ደኅንነትም የስጋት ምንጭ ይሆናሉ። የኑክሌር ከሰሉ ክምችት ወይም ዝቃጭ የበይ-ጨረር መጠኑ በአርባ ዓመታት ውስጥ ወደ 0.1 ፐርሰንት ይወርዳል። አነስተኛ የሚመስለው ይህ መጠን አደገኛ ለመሆን ግን ከበቂ በላይ ነው። ለጤና አደገኛ ወደማይሆንበት ደረጃ ለማውረድ ወደ አስር ሺህ ዓመታት  መቆየት ይኖርበታል። ይህ ማለት ንግሥተ ሳባ ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ስትሄድ የተቀመጠ የኑክሌር ከሰል ክምችት ቢኖር ክምችቱ አሁን ድረስ የበይ-ጨረር ምንጭ እንደሆነ ይቀጥላል ብቻ ሳይሆን ከአሁን በኋላም ለሚቀጥሉት ሰባት ሺህ ዓመታት ለጤና ጠንቅ ሆኖ ይቆያል ማለት ነው። አሁን ባለው የሳይንስ እድገት እስኪበቃው ድረስ ጥቅም ላይ ዋለ የተባለለት የኑክሌር ከሰል ክምችትም ቢሆን ሕይወት ካለው ነገር ጋር ወደማይነካካበት ቦታ ወስዶ ከማጠራቀም ውጪ የተሻለ አማራጭ አልተገኘም።  
ከአሁን በፊት የተለያዩ አደጋዎች ደርሰዋል። በአሜሪካ ስሪ ማይል ደሴት በ1979 እንዲሁም በቀድሞ ሶቭየት ኅብረት ግዛት በቸርኖቢል (በአሁኗ ዪክሬይን ውስጥ የሚገኝ) ደግሞ በ1986  የተከሰቱት የኑክሌር አደጋዎች በብዙ አገሮች የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ግንባታዎች እንዲገቱ ምክንያት የሆኑ ነበሩ። የኑክሌር ኃይል ማመንጫ አደጋ መለኪያ ከ0-7 ሲሆን  7 የመጨረሻውን መጠነ ሰፊ ድንበርና ትውልድ ተሻጋሪ መዘዝ የሚያመጣ አደጋን ይወክላል።  የቸርኖቢል አደጋ ደረጃ 7 ሲሆን የእንፋሎት ፍንዳታና የማብልያው ማዕከል መቅለጥ ባስከተለው መዘዝ ወደ 4 057 ሰዎች ሲያልቁ ወደ 300 000 ሰዎች  ከተለያዩ ከየቀያቸው እንዲፈናቀሉ ያስገደደ ነበር። የስሪ ማይል ደሴት አደጋ ደረጃ 5 ሲሆን ፉኩሺማ መጀመሪያ ደረጃ 4 ከዛ ግን ደረጃ 6 አደጋ መሆኑ ታውቋል። 

ተቃውሞና መጪው ጊዜ
ከላይ በተጠቀሱት ጠንቆችና አደጋዎች ምክንያት የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ግንባታዎች ከድሮም ቢሆን በተቃውሞ የሚታጀቡ ነበሩ። ፈረንሳይ በሁለት አመት (1975-1977) ውስጥ ወደ አስር የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፎችን አስተናግዳ ነበር ። በፓላንድና አየርላንድ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ፕሮግራም በተቃውሞ እንዲቀር ተደርጓል።  በስዊድን በኦስትርያና በጣልያንም ተቃዋሚዎች ድል ያገኙባቸው ሕዝበ ውሳኔዎች ተደርገው ነበር።  ጣልያን የዛሬ ሁለት ዓመት ከ14 ዓመት በፊት ተደርጎ  የኑክሌር ፕሮግራሟ የተገታበት የሕዝበ ውሳኔ ውጤትን ሽራ ሕዝበ ውሳኔውን “አስቀያሚና 68 ቢልዮን ዶላር ያሳጣን ስህተት” ብላዋለች። 
ድኅረ ፉኩሺማ  ያለው ጊዜ ስለኑክሌር ኃይል ማመንጫዎች የሚባለውና የሚሰራው ነገር ላይ የሚለወጥ ነገር አይኖርም አይባልም። እንደዛም ሆኖ የነዳጅ ዋጋ መጨመር፤ የነዳጅ ዘይት ክምችት እየተመናመነ መምጣት፤ የአየር ንብረት ለዋጭ ጋዞች ልቀትና መዘዝ ስጋት፤ በየአገሮቹ ያለው በኃይል አቅርቦት ራስን የመቻልና የደኅንነት ጉዳዮች ተያያዥነት ተደማምረው የኑክሌር ኃይል ማመንጫዎች ግንባታ መስፋፋቱ የማይቀር ነው ያሰኛል። በ1980ቹ በአማካይ በየ17 ቀኑ አንድ አዲስ ማብልያ ይተከል የነበረ ሲሆን ከዛሬ አራት ዓመት በኋላ ግን በየ5 ቀኑ አንድ አዲስ ማብልያ ይተከላል የሚል ትንበያ የሚያስኬድ ነው።
በኢትዮጵያችን 
ወደ አገራችን ሁኔታ ስንመለስ አጼ ኃይለ ሥላሴ ከ57 ዓመት በፊት ተገኘ ያሉት ዩራኒየም ድምጹ ጠፍቶ ቆይቶ የዛሬ 5 ዓመት ሰኔ ወር ላይ እንደገና ተገኘ ተብሎ ነበር። በዛው ዓመት መስከረም ላይ ናሙና ወደ ካናዳ ከተላከ በኋላ ህዳር ላይ አሰሳው እንዲቋረጥ ተደረገ - በወቅቱ እንደተዘገበው። ባለፈው ወር ደግሞ ከራሺያ ጋር በመተባበር  የዩራኒየም ሀብታችን መጠን ለማጥናት ስራ እንደሚጀመር ተዘግቧል።  የኃይል አቅርቦት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሚዛን ደፊ አውታርነቱ የታወቀ ስለሆነ እንደኔ አገራችን ኑክሌርን ጨምሮ ከማልማት ወደኋላ የምትለው የኃይል አማራጭ ምንጭ መኖር የለበትም። በአቅም እጥረትም ይሁን በሌላ ዛሬ ህልም የሚመስሉና አሉታዊ ጎናቸው ብቻ ጎልቶ የሚታዩ ነገሮች ነገ በተቃራኒው መስመር ሊሰለፉ እንደሚችሉ የእስካሁኑ ትምህርት ሊሰጠን ይገባል። የኑክሌር ኃይል ጥሬ ዕቃው  አገር በቀል፤ የቴክኖሎጂው አዋቂ የአገሬው ሰው በሆነባቸው አገሮች የሰጠውን ጥቅም ግምት ውስጥ በማስገባት ዛሬ ባናደርገውም ቢያንስ ነገ ማድረግ እንድንችል ቅድመ ሁኔታ ሊሆኑ የሚችሉ የአእምሮ አቅምና የቴክኖሎጂ አቅም መገንባት መጀመር አለብን - ዛሬ - በአገራችን።
------------------------------- 
ሚያዝያ 8 ቀን 2003 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለውአዲስ ጉዳይመጽሔት ላይ መደበኛውየአረንጓዴ ጉዳይዓምዴ ላይ የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: