Wednesday, May 18, 2011

መከላከያና አካባቢ

(ጌታቸው አሰፋ) ጠበብ አድርገን ካየነው ኦሳማ ቢን ላደንን የመግደል ተልእኮ የፈጸሙት 4 ሄሊኮፕቶሮች፤ 24 ወታደሮች (እንደ ቆጣሪው ቢለያይም) እና አንድ “ካይሮ” የተሰኘ ስልጡን ውሻ ናቸው። አስፍተን ካየነው ግን ቢን ላደንን አንዴ የተፈጥሮ አካባቢን ደጋግሞ እየገደለ ያለው ከአቦታባድ ተልእኮ በስተጀርባ ያለው በዘመናዊ ውስብስብ ቴክኖሎጂና በመደበኛ የስለላ አውታሮች የሚታገዘው ግዙፉ የአሜሪካ መከላከያ ነው። የአሜሪካ መከላከያ በዓለማችን ከፍተኛና ስርጭተ-ሰፊ አካባቢ በካይና አጎስቋይ ተቋም የመሆኑ ነገር ነው የዛሬ “የአረንጓዴ ጉዳይ” መቆያችን። 

አሜሪካዊ ገደብ የለሽ ልቀትና ፍጆታ
የተቋሙ አደገኛ ብክለት በካይ ነዳጆችን ያለ ገደብ በመጠቀም፤ አየር ንብረት ለዋጭ ጋዞችን በስፋት በመልቀቅ፤ መጠነ-ብዙ በዪ-ጨረሮችን በመርጨት፤ ኬሚካሊያዊ በካዮችን ወደ አየር፤ውኃና የብስ በመልቀቅ የሚገለጽ ነው። የሚገርመው የዚህ ተቋም በካይነትና አጎስቋይነት ከአካባቢ ተቆርቋሪዎችና አቀንቃኞች በቂ ትችት ውጪ ሆኖ ቆይቷል።  እስቲ በሰላም ወደ ጦሩ እንጠጋ። 
ከጦርነቶች፤ከጣልቃ-ገብነቶችና፤ ከምሥጢራዊ  ዘመቻዎች ጋር የተያያዙ ከአንድ ሺህ በላይ ጦር ሰፈሮች በዓለም ዙሪያ አሉት።  በአገር ውስጥ ከ60 ሺህ በላይ የጦር ማዕከላት  ጋር በተያያዘ የሚለቀቁት የአየር ንብረት ለዋጭ ጋዞች ከአሜሪካ የልቀት ጣራ ስሌት ውጪ ነው። የአሜሪካ የመከላከያ ተቋም -ፔንታጎን- የዓለማችን ከፍተኛ የነዳጅ ዘይት ውጤቶች ተጠቃሚ ሆኖ እያለ ከሁሉም ዓለማአቀፋዊ የአየር ንብረት ስምምነቶች ውጪ ነው። በአሜሪካ ህግና በተመድ የአየር ንብረት ለውጥ የስምምነት ማዕቀፍ መሠረት ከአገር ውጪ የሚደረግ የጦር እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የሚለቀቅ በካይ ጋዝ እንደ ብሔራዊ ልቀት አይሰላም። አሜሪካ በታኅሣስ 1990 ዓ.ም. በኪዮቶ ጃፓን ይህንን መከላከያን ከተጠቀሰው ስሌት ነጻ የሚያደርግ ሃሳብ አቅርባ ተቀባይነት እንዲያገኝ አድርጋ ስታበቃ የቡሽ አስተዳደር የኪዮቶ የልቀት ቅነሳ ስምምነትን ለመጣል ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም። የአሜሪካ ኮንግረስም የአሜሪካ ጦር የኃይል ፍጆታ ቅነሳ እንዲያደርግ ቀርቶ እንዲለካም እንዳይገደድ ልዩ እይታ እንዲያገኝ ወስኗል። 
ለግል ኩባንያዎች ከሚሰጠው ኮንትራት ጋር በተያያዘና የጦር መሣሪያዎች ማማረቻን ሳይጨምር 320,000 በርሜል የነዳጅ ዘይት በቀን ይጠቀማል (የኢትዮጵያ አጠቃላይ ፍጆታን ሰባት እጥፍ ይሆናል)። ይህ በመንግሥት ደረጃ የሚታመንበት ነው። ፕሬዚደንት ኦባማ ለፌደራል መሥሪያቤቶች በአሥር ዓመታት ውስጥ የአየር ንብረት ለዋጭ ጋዞች ልቀት ቅነሳ ማዘዣን ሲጽፉ መከላከያን ነጻ አድርገውታል። ሰማንያ ፐርሰንት የፌደራል መሥሪያቤቶች የኃይል ፍጆታ የሚሆነው ግን ከመከላከያው  ጋር የተያያዘ ነው።  
ዓውደ ውጊያዎችን ጦር ሰፈሮች
ከመጋቢት 1995 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2000 ዓ.ም. በተደረገው የኢራቅ ጦርነት ጋር በተያያዘ በአሜሪካ በኩል ለ141 ቢልዮን ኪሎ ግራም የካርቦን-ዳይኦክሳይድ-አቻ ልቀት ምክንያት ሆኗል። የጦርነቱ ልቀት የሁሉም አገሮች ጠቅላላ ልቀት ጋር ሲነጻጸር 60 ፐርሰንቱን ያህላል። የኢራቅ ጦርነት የኢራቅን ዘጠና ፐርሰንት ጠቅላላ ስፋት ወደ በርሃነት መቀየሩ ብቻ ሳይሆን አገሪቱን ከምግብ ላኪነት የምግብዋን 80 ፐርሰንት  ከውጪ  የምታሰገባ አገር ወደ መሆን የቀየረ ነው።
የአሜሪካ መከላከያ አምስቱ የአሜሪካ ታላላቅ የኬሚካል ኩባንያዎች ተደምረው ከሚለቁት የአደገኛ ቆሻሻ መጠን ይበልጥ የሚለቅ ተቋም ነው። 
በሺዎች ኪሎዎች የሚገመት የዩራኒየም እላቂ በመካከለኛው ምስራቅ፤ በመካከለኛው ኤዥያ፤በደቡብ ምስራቅ አውሮፓ ተሰራጭቶ ይገኛል።
አሜሪካ-ሰራሽ ፈንጂዎች እና ክላስተር ቦምቦች በአፍሪካ፤ ኤዥያ፤ ላቲን አሜሪካ መካከለኛው ምሥራቅ በርካታ አከባቢዎችን አጎሳቁለዋል።
በአሜሪካ የጦርነት ታሪክ ጉልህ ስፍራ ያለው የቬትናም ጦርነት ከተካሄደ ከሰላሳ አምስት ዓመታት በኋላም ቢሆን “ዳዮክሲን” የተባሉ የጤና ጠንቅ በካዮች የብክለት መጠናቸው ከጤናማው መጠን ሶስት መቶ አምሳ ጊዜ በላይ ያለፈ ሆኖ ተገኝተዋል - በቦታው። እነዚህ የዳዮክሲን በካዮች ጉድለት-አዘል ልደትና እስከ ሶስት ትውልድ ድረስ ሊሄድ የሚችል የካንሰር በሽታን ያመጣሉ።
በአሜሪካ ውስጥም ለመጠጥ የሚሆን ውኃቸው፤ መደበኛ የከርሰ ምድር ውኃቸውና አፈራቸው በበካይ ኬሚካሎች (ለምሳሌ ፐርክሎሬትና ትራይክሎሮእታይሊን በመሳሰሉ) ከተበከሉባቸው ቦታዎች መካከል የጦር ሰፈሮች ያሉባቸው ስፍራዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ።
በደቡብ ምዕራብ አሜሪካና በደቡባዊ ሰላማዊ ውቅያኖስ ደሴቶች የሚደረጉ የኑክሌየር መሣሪያዎች ሙከራዎች ሰፋፊ የየብስና የውኃ አካላት በበዪ-ጨረሮች እንዲበከሉ አድርገዋል። የዩራንየም ተረፈ ማዕድን ደግሞ በደቡብ ምዕራብ አሜሪካ የሚገኘው የናቫጆ አካባቢን በክሏል።  ኬሚካሎችና የተለያዩ አሟሚዎችን የያዙ የዛጉ በርሜሎች በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች አካባቢ ያለ ምንም ጥንቃቄ ተጥለዋል።
አለ ገና?
የእስካሁኑ እንደተጠበቀ ሆኖ አሜሪካ በሰላማዊ ውቅያኖስ በምትገኘው የጉዋም ደሴት ላይ በ15 ቢልዮን ዶላር የጦር ግንባታ እያደረገች ነው።  በዚች ትንሽ አምሳ ኪሎ ሜትር ርዝመት ባላት ደሴት ወደ ሰማንያ ሺህ ሰዎች (ወታደሮችን ጨምሮ) ታሰፍራለች። የደሴቷ ነዋሪ በአጭር ጊዜ ውስት በአርባ ሰባት ፐርሰንት ሊተኮስ ነው ማለት ነው። ጉዋም በአሜሪካ ስር የሆነች ግን የአሜሪካ አካል ያልሆነች ደሴት ነች። ይህም ማለት የአሜሪካ ህገ መንግሥት የማይገዛት ብትሆንም የአሜሪካ ኮንግረስ ግን ከህገ መንግሥቱ አንቀጾች መርጦ የትኛው እንደሚመለከታት የመወሰን “ስልጣን” አለው።በተመድ ዓይን ይች ደሴት ራሳቸውን የማያስተዳድሩ ግዛቶች ወይም ቅኝ ተገዢ ከሚባሉት አንዷ ነች። ተመድ ቅኝ ተገዢነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማጥፋት ሁለት አሥርተ ዓመታትን በይፋ አውጆ በመጀመሪያው ሳይሳካለት ቀርቶ አምና ያለቀው ሁለተኛውም እንደዚሁ ውጤት አልባ በሆነበት ማግስት ነው አሜሪካ በጉዋም ከፍተኛ የአከባቢ ብክለትና መጎሳቆል የሚያስከትል ወታደራዊ መስፋፋት እያደረገች ያለችው። 
በጉዋም የታሰበው የጦር ሰፈር ግንባታ -  
1ኛ) ለአይነተ-ብዙ የባህር-ወለድ ውጊያዎች ስልጠና የሚሆን የቋሚ ሕንጻዎችና መሠረተ ልማቶች ግንባታ
2ኛ) በኒኩሊየር-ኃይል ለሚዘወሩ አውሮፕላን ተሻካሚዎች ማስተላለፊያ የሚሆን ጥልቅ ወደብ ግንባታ 
3ኛ) አኅጉር-ደረስ ተወንጫፊ ሚሳይሎችን ማምከን ላይ የተካነ የጸረ-ሚሳይል ኃይለ-ግብር መለማመጃ ጣቢያ ግንባታን ያጠቃልላል። 
እነዚህ ግንባታዎች ቢያንስ የሚከተሉትን የአካባቢ ተጽእኖዎች ያስከትላሉ። በደሴቲቱ ያለውን ጫካ መመንጠር፤ በአከባቢው ለመድኃኒትነት የሚሆኑ እጽዋቶችን ተደራሽነት መገደብ፤የአሳ ማጥመጃ ቦታዎችን ተደራሽ-አልባ ማድረግ፤ወደ ስድሳ ኳስ ሜዳዎች የሚያህል የኮራል ሪፍ (እየጠፉ ላሉ የብዝኃ ሕይወት ዝርያዎች መኖሪያ የሆነ እጅግ ጠቃሚ “የባህር ላይ ጫካ”) መውደም።     
ይህ መስፋፋት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በአሜሪካ ጦር የተወሰደውን የደሴቲቱ መሬት ከጠቅላላ የደሴቲቱ ስፋት ጋር ሲነጻጸር ወደ ሰላሳ አምስት ፐርሰንት ያደርሰዋል። 
እቅዱ ባለ አስራ አንድ ሺህ ገጽ  የአካባቢ ተጽእኖ ግምገማ ሪⶒርት የተሰራለት ቢሆንም ግምገማው ባለፈው ዓመት የካቲት በወጣው የዩኤስ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን (አጥባ)  ጥናት መሠረት “ብቁ ያልሆነ”  “አጥጋቢ ያልሆነ” ነው ተብሏል።  የደሴቲቱ የውኃ መሰረተ ልማት የህዝብ ጭማሪውን ለመደገፍ የማይችል የንጹህ ውሃ ሀብቷን ለብክለት የሚያጋልጥ ነው - እንደ ዩኤስ አጥባ ጥናት። እናም የፔንታጎን የግንባታ እቅድ እንዳለ መቀጠል አይገባውም ብሏል አጥባ።
በሌላ በኩል በሰሜን ዋልታ አካባቢ የሚገኘው አንዳች በሚያህል ጽኑ የግግር በረዶ ሽፋኑ የሚታወቀው የአርክቲክ ውቅያኖስ የዛሬ ሃያ ዓመት በረዶው በስፋት ከመቅለጡ የተነሳ መደበኛ የባህር መስመር ይሆናል በሚል የአሜሪካ ባህር ኃይል በከፍተኛ ደረጃ እየሰራ ይገኛል። ይህ ለውጥ ዓለም አቀፍ የባህር ጉዞ መስመርን ቅርጽ ሊቀይር የሚችል ለውጥ ነው የሚሆነው። አደገኛ የሥጋት ምንጮችን ከመለየት ጀምሮ ለቦታው ተስማሚ የሆነ የጦር መሣሪያና የባህር ውስጥ ውጊያዎችን አመካከት ወዘተ እያጠናች ነው - አሜሪካ። ይህ አይነት ልቅ ጥናት እስካሁን በድንግልና የቆየውን አካባቢ ከማርከስ ጀምሮ የአከባቢውን ተፈጥሮ በእጅጉ የሚያጎሳቁል አካሄድ እንዳይሆን ያሰጋል።
ጠቅላላ መከላከያና ኢትዮጵያ 
መከላከያዎች የአካባቢ ጉስቁልና ኃይሎች በመሆን ፋንታ የአካባቢ ጥበቃ ኃይሎች ወደ መሆን ሙሉ በሙሉ መሸጋገር አይችሉ ይሆናል። ሆኖም የስዊድን የጠቅላላ መከላከያ ምርምር ማዕከል የሚሰራቸው፤ የሚያሰራቸውና የሚደግፋቸው የምርምር አይነቶች ስንመለከት የአገሮች ደኅንነት በተናጠልና የዓለማችን የወል ደኅንነት ጉዳይ በተለምዶ ከምናውቀው የወታደራዊ ደኅንነት ጉዳይ በላይና ውጪ መሆኑን እንረዳለን። ለምሳሌ ስዊድን በነበርኩበት ወቅት ከአየር ንብረት መለወጥ ጋር በተያያዘ በአገር ውስጥ ያለው የማምረቻ ሥርዓት ካርበን-አነስ ሥርዓት በመሆኑ ከሌሎች አገሮች የሚገቡትን ምርቶችና አገልግሎቶች የካርበን-አቻ ልቀታቸው መጠን ለማስላት የገቢ ምርቶችንና አገልግሎቶችን ከካርቦን ልቀት አንጻር በማጠናበት ወቅት ከዚሁ የጠቅላላ መከላከያ ምርምር ማዕከል ተመራማሪዎች ጋር የሠራሁበት ጊዜ ነበር። 
ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነጻጸር አገራችን ለመከላከያ የምታወጣው ከጠቅላላ ምርታችን አንጻር ሲሰላ ዝቅተኛ እንደሆነ ይነገራል። ያለን የጦር መሳሪያ ብዛትና አይነትም ያን ያክል የተወሳሰበ ላይሆን ይችላል። ይሁንና ምድር ጦራችን ያለው የከፍተኛ፤ መካከለኛና አነስተኛ ታንኮችና መድፎች፤ የተለያዩ አነስተኛና መለስተኛ መሳሪያዎች፤ ጸረ-ታንክ ሚሳይሎችና አየር-በአየር ተምዘግዛጊ ሚሳይሎች በአንድ በኩል፤ እንዲሁም አየር ኃይላችን  ያሉት የተለያዩ ተዋጊ ሄሊኮፕተሮችና ጄቶች፤ የምድር-ተጠጌ ጥቃት አውሮፕላኖች፤ የእቃ ጫኝ አውሮፕላኖችና እና የስልጠና አውሮፕላኖች እንደ አቅማቸው አካባቢን ያጎሳቁላሉ ይበክላሉ። በሌላ በኩል መከላከያ ሰራዊታችን የአካባቢ ጉስቁልናን ከመከላከል አልፎ ለአካባቢ መልሶ መቋቋም ከፍተኛ አስተዋጽኦ የማድረግ እምቅ አቅሙን ማየት እንችላለን። 
በየግንባሩ የተለያየ ብዛት ያለው ወታደር አለን። እንደየግንባሩ አይነት ጦሩ ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ የጦር ሰራዊት አባላት ላለፉት አስራ ሁለት ዓመታት  በሰሜን ግንባር እንዳሉ ይታወቃል። የሚቆዩበት ጊዜ ረጅም መሆንና  ግዳጅን የመወጣት ወታደራዊ ባህላቸው በየሰፈሩበት አካባቢ አገር በቀልና ለአካባቢው ምቹ የሆኑ ብሎም ጥቅመ-ብዙ የሆኑ ዛፎችን በመትከል ብቻ ሳይሆን እስኪያድጉ ድረስ የመንከባከብ ሥራም ጭምር ለመሥራት ያስችላቸዋል።የአካባቢን እንክብካቤ በተመለከተ ምርምርና ስርጸት ለማድረግ እና ሰፊ የሠርቶ ማሳያ ግንዛቤ ለመፍጠር መከላከያ አቅሙም ሁኔታውም ይፈቅድለታል። ይህ አመቺ ሁኔታ ወደ ዘላቂና ሰፊ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መቀየር ሲቻል ስዊድኖች “ጠቅላላ መከላከያ”  ወደሚሉት ደረጃ ጠጋ አልን ማለት አይደል?
===========
ግንቦት 6 ቀን 2003 ዓ.ምአዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው “አዲስ ጉዳይ” መጽሔት ላይ መደበኛው “የአረንጓዴ ጉዳይዓምዴ ላይ የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

1 comment:

Manchilo said...

It is true that the Defense Dept. can play a paramount positive role in Env'tal protection. If desired, even we can take the best example of the previous derge regime in Ethiopia. Untill 1991, most of the mountains in Ethiopia were covered by forests, mostly with endemic tree species. Therefore, I would say your conclusion on the potential of the defense to bring positive influence in envi'tal protection will serve as an invaluable input for policy makers.

On top of that, your guts to write independent scholarly and scientific articles in native language will encourage others schoars to walk on the road you paved!

Humble Regards for your Contribution!