Wednesday, June 1, 2011

ታሪከ-ቁስ


(ጌታቸው አሰፋ) ታሪክ ሠሪም ባለ ታሪክም ነው ሰው - በሰፊው እንደሚታመንበት። እያንዳንዱ እሴት-አዘል ቁስም (ምርትና አገልግሎት) የራሱ የሆነ ታሪክ አለው -  “ታሪከ ቁስ” ብንለውስ።  አጭር ወይም ረጅም ሊሆን ይችላል። ጥሩም መጥፎም ሊሆን ይችላል። 
የአንድ ምርት ወይም አገልግሎት ታሪክ ሲመረትና ጥቅም ላይ ሲውል የሚያልፍበትን ሂደት የሚያጠቃልል  በጥንተ-ተፈጥሮ  ምንጩ ጀምሮ በጥንተ-ተፈጥሮ ማረፊያው የሚያበቃ ሰንሰለታዊ  ዑደትን የሚያጠቃልል ነው።  ባለሁበት ዩኒቨርስቲ በዚህ ሰንሰለታዊ ዑደት ወቅት በአካባቢ አየር፤ ውኃና የብስ ላይ የሚያደርሰውን ተጽእኖ የማስላትና የመገምገም ዘይቤ ነው “ወንበር ዘርግቼ” ጥናትና ምርምር የማደርገውና ትምህርትም የምሰጠው።

በዚህ ዘይቤ የፍቅር-ቀን የሚሰጥ የጽጌሬዳ አበባ፤የጫማ፤የሙዝ፤የኤሌክትሪክ ኃይል፤ የአውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ፤የኢትዮጵያ አንድ ብር ወረቀት፤ የቆሻሻ አስተዳደር ሥርዓት ወዘተን ማጥናት እንችላለን። በተለይ አንድ አገልግሎት ለማግኘት የተለያዩ መንገዶች ካሉ መንገዶቹን ከአካባቢ ተጽእኖ አንጻር ለማነጻጸር ይጠቅማል። ለምሳሌ እስካሁን ያለው የካናዳ ብር የሚሰራበት ጥሬ እቃ  ከቤኒን ከተገኘ ጥጥ (ለምሳሌ ነው) ሲሆን ከገበያ ውጪ የሆኑት ብሮች ተሰብስበው ከተሸረከቱ በኋላ በስርአት በተያዘ ቦታ ይቀበራሉ። የካናዳ ባንክ ባለፈው ዓመት ያወጣው ጨረታ ይህ አሁን ያለው ዑደትና ብሩ የሚሰራው ከላስቲካማ ጥሬ እቃ ቢሆን ሊፈጠር ከሚችለው ዑደት ጋር ከአካባቢ ተጽእኖ አንጻር እንዲጠናለት የሚጠይቅ ነበር። (እኔ እንደ ሦስተኛ አካል ገምጋሚ የገባሁበት ተጫራች ጨረታውን አላሸነፈም እንጂ ደስ የሚል ጥናት የሚወጣው ሥራ እንደነበር መገመት ይቻላል)።
የእንደዚህ አይነት ጥናት አስኳል የሆነው ሰንሰለታዊ  ዑደት  ለተለያዩ ግማደ ዑደቶች የሚሆኑ ግብአቶችን  ከተፈጥሮአዊ  ምንጮቻቸው ማውጣትን፤ወደየማንጠሪያዎች ማጓጓዝን፤ማንጠርን፤ ወደ ማምረቻ ቦታ ማጓጓዝን፤ ከተለየያዩ ግብአቶች ምርቱን ማምረትን፤ ወደ ገበያ ማጓጓዝን፤ ተስማሚ የገበያ ቆይታ መፍጠርን፤ ወደ ተጠቃሚ ማጓጓዝን፤ ጥቅም (ፍጆታ) ላይ ማዋልን፤ ከጥቅም በኋላ ያለውን ቆሻሻ ማጓጓዝን፤ የቆሻሻ አስተዳደርን፤ የመጨረሻ ማረፊያ ላይ ማኖርን ያጠቃልላል።
በዚህ ዘዴ በያንዳንዱ ግማደ ዑደት የሚወጣው  በካይ ጭስም ይሁን ፈሳሽና ዝቃጭ ይሰላል። ግማደ ዑደቶቹ እንክት የሚያደርጉት  የተፈጥሮ ሀብት መጠንም እንደዚሁ ይሰላል። 
የጠቅላላ በካዩ መጠንና ብሎም አካባቢና ጤና ላይ የሚያመጣውን ጠንቅ አስልቶ ለአምራቾች ለተጠቃሚዎችና ብሎም ለፓሊሲ አውጪዎች ድጋፍ መስጠት  ነው  የሙያው አላማ። 
እንደ ቁሱ አይነትና አመራረት (ቴክኖሎጂ፡ አገር ወዘተ) አንዱ ግማደ ዑደት ከሌላው ግማደ ዑደት ይልቅ የጎላ ወይም ያነሰ ጠንቅ ሊኖረው ይችላል። 
ይህን  ዘዴና ስሌት ለማስረዳት የሁለት ስኒዎች ቡና ምሳሌ እነሆ። ይህ ምሳሌ በአንድ ወቅት በአሜሪካ ድምጽ ቀርቤ ሙያዬን ያሰራዳሁበት ምሳሌ ነበር።
መቼም የምንጠጣውን ቡና ጣዕምና ዋጋ ማማረጥ የተለመደ ነው።  ከዚህ አልፎ  ግን የምንጠጣው ቡና ቅድመ-ስኒ ታሪኩ በመመልከት በአካባቢ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ተፅእኖ አነፃፅሮ ባለዝቅተኛ ተጽእኖ የሆነውን ቡና ለመጠጣት የሚፈልግ ተጠቃሚ በተለይ በምዕራቡ ዓለም እየጨመረ ይሄዳል። እስቲ አንድ ፒያሳ አካባቢ የሚሰራ ሰው በጠዋት የሻይ እረፍቱ ወደ አንድ ኬክ ቤት ሄዶ የጠጣውን አንድ ስኒ ቡና እና ከሰዓት በኃላ እረፍቱ ደግሞ ወደ ሌላ ኬክ ቤት ሄዶ የጠጣውን አንድ ስኒ ቡና እናነጻጽር። ሁለቱም በጣእም፤ በአፈላል፤ በመጠን፤ በተጠቀሙበት የቡና ዱቄት መጠን ጭምር አንድ አይነት ናቸው እንበል። ልዩነታቸው የጠዋቱ አገር ውስጥ የተመረተ የጅማ ቡና መሆኑ የከሰዓቱ ደግሞ በአንድ አስመጪ ከጣልያን የመጣ የብራዚል ቡና መሆኑ ላይ ብቻ ነው።
ስኒ አንድ - የጅማ  ቡና
ሲመረት ያለ ሰው-ሰራሽ ማዳበሪያ ያለ ሰው-ሰራሽ ጸረ ተባይ፤ ሲጓጓዝ በአህያ ወይም በሰው ጉልበት እና በጥቂቱ በመኪና፤ ከዛም ሲደርቅ በፀሐይ ብርሃን፤ ሲፈለፈል በሰው ጉልበት ፤ሲቆላ በእጽዋት-ነክ ነዳጅ ፤ሲፈጭ በካይ ጭሶችን በመልቀቅ በማይታወቀው ውኃዊ-ኃይል ሊሆን ይችላል።(ውኃዊ ኃይል በሌላ መልኩ በሚገለጽ ተፅእኖ ሊኖረው እንደሚችል ይታወቃል)።
እነዚህን ደረጃዎች ሲያልፍ የሚፈጠሩትን በካይ ጭሶች ፈሳሾችና ዝቃጮች ደምረን ቀንሰን በአንድ ስኒ ደረጃ አስልተን ስናበቃ እንደ ቦርሳ  ስኒውን ብናሸክም የቦርሳው መጠን እጅግ በጣም ትንሽ  ቦርሳ ይሆናል።
ስኒ ሁለት - የብራዚል ቡና 
የተመረተው ብራዚል የተቆላው ስፔይን የተፈጨው ጣልያን ነው ብለን እናስብ። ብራዚል ሲመረት ማዳበሪያው የመጣው ከቻይና ሲሆን ጸረ ተባይና ጸረ አርም ደግሞ ከጀርመን ተገዝቶ ገብቶለታል። ቡናውን  ለማድረቅና ለመፈልፈል  የተፈጥሮ ጋዝ ጥቅም ላይ ውሏል። ቡናው ከብራዚል ወደ ስፔን ከዛም ወደ ጣልያን ከዛም ወደ ኢትዮጵያ ለማጓጓዝ፤ ማዳበሪያውን ከቻይና ወደ ብራዚል፤ ጸረ ተባዩና ጸረ አረሙ ከጀርመን ወደ ብራዚል ለማጓጓዝ መርከብ ያስፈልጋል።
መርከቡን ለመስራት ደግሞ ብረት። የብረት ማዕድኑ የወጣው ከአውስትራልያ ሲሆን ማቅለጫ ያለው ደግሞ ደቡብ ኮሪያ ነው። የመሥሪያ ግብዓቶች ከተለያዩ አገሮች ከተሰበሰቡ በኃላ መርከቡ የተሠራው  ደግሞ ፊንላንድ አገር ነው። ለመርከቡና ለመንገድ ትራንስፖርት የነዳጅ ዘይት ያስፈልጋል። ለመቁያ  የተፈጥሮ ጋዝ የግድ ነው። ጣልያን አገር ያለው መፍጫ ደግሞ ከፈረንሳይ በሚመጣው የኑክሌር ኃይል ነው የሚሰራው። የነዳጅ ዘይቱ  የወጣው ከሳውዲ አረቢያ ሲሆን የተፈጥሮ ጋዙ ደግሞ ከራሺያ ነው። ከላይ ከተጠቀሱት ግማደ-ዑደቶች ይበልጥ የሚበዙ ያልተጠቀሱ ግማደ-ዑደቶች በርካታና ረጃጅም የማጓጓዝ ሥራዎች የሚጠይቁ አሉ። ለምሳሌ መቁያው መፍጫው የተሰራበት፤ ማዳበሪያው የተሰራበት ፋብሪካ ውስጥ ያሉት እቃዎች በተራቸው የተሰሩበት ብለን መቀጠል እንችላለን። 
በነዚህ ሁሉ ግማደ-ዑደቶች ወቅት በየአገሩና በየባህሩ  ወደ አካባቢ የሚለቀቁትን በካይ ጭሶች፤ ፈሳሾችና ዝቃጮች አስልተን እንደመጀመሪያው ስኒ በቦርሳ መልክ ብናሸክመው ከጅማው ቡና ጋር ሲነጻጸር  ተሸካሚው ስኒው በዓይን የማይታይ እስኪመስል ድረስ እጅግ በጣም የገዘፈ ቦርሳ ይሆናል። ልዩነቱን እጅግ በጥቂቱ ለማሳየት  መጓጓዣውን ብቻ እንኳ ብንመለከት ከጅማ አዲስ አበባ 350 ኪሎ ሜትር ሲሆን  የሁለተኛው ስኒ ቡና ርቀቶች በደምሳሳው የወፍ-በረር መስመርን ብቻ ግምት ውስጥ ስናስገባ ከጀርመን ብራዚል 9600 ከቻይና ብራዚል 17000 ሳውዲ አረቢያ ብራዚል 1100 ከብራዚል ስፔን 8000 ከራሺያ ስፔን 3000 ከአወስትራልያ ደቡብ ኮሪያ 9000 ከደቡብ ኮሪያ ፊንላንድ 7000 ከስፔን ጣልያን  1500 ከጣልያን ኢትዮጵያ 4500 ኪሎ ሜትር በድምሩ 70600 ኪሎ ሜትር ይሆናል። ይህ መጓጓዣ በመርከብ፤ በባቡር፤ በጭነት መኪና፤ በአውሮፕላን እንዲሁም በትቦዎች መረብ(ለምሳሌ ተፈጥሮ ጋዝ) ሊሆን ይችላል።
የሁለቱ የቡና አይነቶች ድኅረ ስኒ ታሪክ ተመሳሳይ ሰለሆነ ስሌቱ ውስጥ አይገባም። 
ይህ ንጽጽር የሚያሳየው ነገር ቢኖር በሁለት የፒያሳ ኬክ ቤቶች ውስጥ የሚጠጡ የጅማ ቡናና የብራዚል ቡና  ያላቸው ለዛሬ ብቻ ሳይሆን  ለሚመጣውም ትውልድ የሚተርፍ የብክለት ታሪክ እጅግ ትልቅ መሆኑን ነው።  የዚህ አይነት መረጃ በዓለም ዙሪያ እየጨመረ መምጣት ደግሞ የተለያዩ ባለ ድርሻ አካላትን ይጠቅማል። በተለይ አውሮፓና ጃፓን (በትንሹ ደግሞ ሰሜን አሜሪካ) ላለው አስተዋይ ቡና ጠጪ የሚጠጣውን ቡና በካይ ታሪክ አውቆና አገናዝቦ ለመወሰን ይረዳዋል።  ለቡና አቅራቢው  ደግሞ አስተዋይ ቡና ጠጪዎች ወደሚበረክቱባቸው አገሮች ቡና ሲያቀርብ ስለሚያቀርበው ቡና ሙሉ ተጽእኖው ምን ይህል እንደሆነ የሚያውቅ እንዲሆን ያደርገዋል።  ለመንግሥትም በአገር ደረጃ እንዲህ አይነት አቅም እንዲፈጠርና እንዲጎለብት ለማድረግ መሥራት የግድ ይለዋል። 
የኢትዮጵያ ቡና ለውጪ ገበያ ከማቅረብ አንፃር እየጨመረ ከሚመጣው የምዕራብ ዓለም ተጠቃሚዎች አካባቢያዊ ግንዛቤ አንፃር የዚህ አይነት ስሌት ጠቃሚነት እጅግ የጎላ ነው።
ፈረንሳይ  በብዛት ወደ አገርዋ የሚገቡት ዕቃዎች ላይ የተለያያ አይነት የአካባቢ ተጽእኖ መጠን የሚያሳይ የምርት አካባቢያዊ መዘርዝር እንዲኖራቸው የሚያስገድድ ህግ በዚህ ዓመት አውጥታለች። ይህ መዘርዝር በየምግብ ማሸጊያዎች የምናገኘው የንጥረ ነገሮች መዘርዝርን ያስታውሷል። በተለያዩ ምርቶች አካባቢን አይበክሉም የሚል መልእክት ለማስተላለፍ የተለያዩ በምርቶቹ ማሸጊያዎች የሚለጠፉ አርማዎች አሉ። በዓለም ዙሪያ ወደ ሰባት መቶ የሚጠጉ እንደዚህ አይነት አርማዎች አሉ። በጥናት እንደተረጋገጠው እነዚህ አርማዎች ሲሆን ሐሰተኛ መልእክት የሚያስተላልፉ፤ግልጽነት የሌለው መረጃ ላይ የተመሠረቱ ወይም ከፊል ሀቅ ብቻ የሚያንጸባርቁ ይገኙበታል።  የምርት አካባቢያዊ መዘርዘሩ ግን የምርቱን ቅንጭብ ታሪክ ሳይሆን ሙሉ ዑደቱን ያካተተ ስሌት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል። ፈረንሳይ ይህን ህግ የጣለችው በአገር ውስጥ በሚመረቱ ምርቶች ላይም ስለሆነ በዓለም የንግድ ድርጅት ማዕቀፍ አድልዎ ያለበት የንግድ እንቅፋት እንደፈጠረች ተደርጎ አይታይባትም። ይሁን እንጂ መዘርዝሩን ለመሥራት አገሮች መጠነ-ሰፊ አኃዛዊ መረጃዎች ስለሚያስፈልጋቸውና እንዲህ አይነት መረጃ ደግሞ ካናዳን በመሳሰሉ የሰሜን አገሮች (የሰሜንና የደቡብ አገሮች እንጂ ያደጉና ያላደጉ ወይም አንደኛና ሦስተኛ ዓለም አገሮች የሚለውን አከፋፈል ስለማልመርጠው)  ሳይቀር ስለማይገኝ ፈረንሳይ ያወጣችው ህግ ኢ-ታሪፋዊ የንግድ እንቅፋት ተደርጎ ቢታይ አይደንቅም። ይህ የፈረንሳይ ህግ ደግሞ ሳይውል ሳያድር የአውሮፓ ህብረት ሃያ አምስት አገሮች ውስጥ ህግ እንዳይሆን የሚያግደው ነገር የለም። በጃፓን ተመሳሳይ አሰራር ለመዘርጋት ጥረት እየተደረገ ነው። 
ከዚህ እያደገ ከሚመጣው ሂደት አንጻር በየአገሮቹ የሚያስፈልገው የአካባቢያዊ ተጽእኖ አኃዛዊ መረጃዎችን የሚያቁር ቋትና መሰረተ-መረጃ ማቋቋምና ማበልጸግ ይጠይቃል። አገራችንም የዚህ አይነት ተግባር የሚፈጽም አቅም ለመፍጠርና አስቻይ ስርዓትን ለመዘርጋት ዛሬውኑ ብትታትር ነገ የነሱ ከሆነላቸው አገሮች አንዷ ትሆናለች።

================
ግንቦት  20  ቀን 2003 ዓ.ምአዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው “አዲስ ጉዳይ” መጽሔት ላይ  መደበኛው  “የአረንጓዴ ጉዳይዓምዴ ላይ ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: