Wednesday, June 29, 2011

የችጋርን ቀለበት ሰበራ


(ጌታቸው አሰፋ)ቀለበት የቱ ጋ እንደሚጀምር ለማወቅ ያስቸግራል። እንደ ቀለበት እንዲቀጥል የምንፈልገው በጎ ቀለበት ከሆነ የትስ ቢጀምር ምን ገዶን። መሰበር ያለበት ክፉ ቀለበት ከሆነ ግን የቱ ጋ ነው የጀመረው የሚለውን ጥያቄ መመለስ ወሳኝ ነው። የአገራችን አካባቢ ጉስቁልና እንዲያገግም ለማድረግ በየጊዜው የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል።  እየተወሰዱም ነው። ተፈላጊው ውጤት በምንመኘው ልክና ጥራት ግን ለማየት አልቻልንም - እስካሁን። የዚህ እንቆቆልሽ  ቁልፍና የችግራችን መፍትሔ የሚያያዘው የችግሩን ክፉ ቀለበትነት ከመገንዘብ ጋር ነው።  

ኢንድራ ጋንዲ አካባቢን ከሚበክሉትና ከሚያጎሳቁሉት ነገሮች ክፉው ድህነት ነው እንዳለችው ከድህነታችን ጋር የተያያዘው ቀለበት የቱ ጋ ነው የሚጀምረው እንደ ቀለበት እንዳይቀጥል የምናደርገውስ ምኑን ብንሰብረው ነው የሚለውን ማወቅ የአካባቢ ጥበቃ ጥበብ መጀመሪያ ነው። ከትክክለኛው ቦታ ውጪ መቀጥቀጥ፤ ማሳሳት፤ መጨፍለቅ፤ መዳመጥና መደፍጠጥም ላያቅተን ይችላል። ያን ሁሉ አድርገን ግን የቀለበቱ ቅርጽ ይቀየር እንደሆነ እንጂ ቀለበትነቱ አይቀየርም። 
የችጋር ቀለበት
ለእርሻ የሚሆን መሬት ለማበጀት፤ ለቤት መሥሪያ የሚሆን እንጨት ፍለጋና በተለይ ደግሞ ለማገዶ ለሚሆን እንጨት ሲባል ደኖች ይመነጠራሉ። ዛፎች ይጨፈጨፋሉ።  
አፈር ይሸረሸራል - ሲገኝ በውኃ ሳይገኝ በነፋስ። አፈሩ ለምነቱን አጥቷል። ድሮ ድሮ የከብት እበት በየሜዳው ተጥሎ ይቀር ነበር። ደርቆ ኩበት ሲሆን ጊዜያቸውን ጠብቀው የተለያዩት የኩበቱ ክፍሎች በአፈር ውስጥ የሚመለከታቸውን መስመር ተከትለው ወደ ሥራ ይገባሉ።  በዳግም ሕይወት በሰብሎች አማካኝነት ወደ ሰውና እንስሳ ይመለሳሉ። እንደገና ሌላ ዑደት። እበት-ኩበት-አፈር።  ይሄው ዑደት እዛው ማሳ ላይ መቅረት ይገባው ለነበረውና ከአጨዳ ለተረፈውም ይሠራል። የሚነድ ነገር ሁሉ ስናነድ ኖረናል። መጀመሪያ በቅርብ ያሉ ቶሎ ሊተኩ የሚችሉ ዛፎችን፤ እነሱ ሲያልቁ በርቀት ያሉ ቶሎ ሊተኩ የሚችሉትን፤ እነሱ ርቀው ወይም ጠፍተው ሲያበቁ ደግሞ ወደ ቅርቡ በመመለስ በቀላሉ የማይተኩ እድሜ የጠገቡ ዛፎችን ማንደድ ቀጠልን። ጨረስናቸው። ሩቅ ወዳሉት ሄድን። ርቀቱ ከአቅም በላይ መሆኑ ሳያግደን ሌሎችም ከሌላ አቅጣጫ እያሳደዱ ስለሚያነዱ ድንበር ገድቦን አልያም አንድደን ጨረስን። ከዛም ሌላ የሚነድ ነገር ፍለጋ ተያያዝን። ኩበት ለቀማ ገባን - እስኪደርቅ ለመጠበቅ እንችል በነበረበት ጊዜ። ከዛ መጠበቅ አልቻልንም። እበት መጠፍጠፍ ጀመርን። እሱም አልበቃም። ተረፈ-አጨዳውን ከአፈሩ አፍ እየቀማን ከከብቶች ጋር መሻማት ጀመርን። ሁለቱ ለምግብ፤ እኛ እንደ ኃይል ምንጭ ለማንደድ። ወደ ከብቶቹ ሆድ የሚገባውን ነጠቅን ከሆዳቸውም የሚወጣውን ነጠቅን። ከብትና አፈር ጾሙን አደረ። ዛፍ መቁረጥ የተከለከለበት ክልል ቦታ ሄደን ለወትሮው የአፈር አልሚ ይሆን የነበረው ውድቅዳቂ ቅጠል መጀመሪያ ወድቆ የደረቀውን እየሰበሰብን መውሰድ ጀመርን። ከዛ የወደቀውን ብዙም ሳይቆይ ጋማ ማለት ቀጠልን። ያልወደቀውንና ለመውደቅ ያላሰበውን ቅጠል መውደቂያውን ማፋጠን አንዱ ሥራችን ሆነ። ዛፎቹ ያሉበት መሬት ዛፎቹ በአምሳለ-ቅጠል የተፉትን አልሚ ምግብ አፈሩ መልሶ በዛፎቹ ስር በኩል እንዳያጎርሳቸው ጉርሻውን ከአፈሩ እጅ ቀማን።
የአገራችን ብዙ አካባቢዎች በድርቅ መመታት የተለመደ ዜና ሆነ - የድርቅ ታሪካችን የቆየ ቢሆንም። ዝናብ ሲጠፋ ድርቅ አለ። የአገራችን ድርቅ-መራሽ ረሀብ ከእግዚአብሔር ይልቅ ከሰው ጋር የተያያዘ ነው። መፍትሔውም ወደ ሰው-ሰውኛው ያመዝናል። ለዝናብ መዝነብ የአየሩ እርጥበት አዘል መሆን ከወሳኝ ነገሮች አንዱ ነው። እሱ ሲቀንስ ዝናብ ይጠፋል። ድርቅ ይከተላል። ድርቅ የምርት እጥረትን ይወልዳል። የምርት እጥረት ረሀብን ትወልዳለች። በቂ እርዳታ በጊዜ ካልተገኘ ረሀብ ሞትን ታመጣለች።በአገራችን ዛሬም ራሳቸውን መመገብ የማይችሉ ወገኖች ቁጥር እንደ ምንጩ ቢለያይም ሚልዮኖች መሆናቸው ላይ ግን ሁሉም ይስማማል። ለእነዚህ ወገኖች የምግብ እርዳታ መፈለግና ማቅረብ ተገቢ ነው። ረሀብ እንደከዚህ ቀደሙ የወገኖቻችንን ሕይወት እንዳይቀጥፍብን መረባረብ የግድ አስፈላጊ ነው። እነዚህ ሁሉ ግን ጊዜያዊ መፍትሔዎች ናቸው። ምንም ቢደጋገሙ ምንም በሰፊው ቢቀርቡም ከጊዜያዊነት አያልፉም። ከዚህ አልፈንም ድርቅ በሚበዛበትና በሚበረታበት አካባቢ የአፈር ዕቀባ፤ዛፍ ተከላና የመሳሰሉትን ሥራዎች ብንሠራም እንኳ በራሳቸውና ብቻቸውን ዘላቂ መፍትሔ የሚሆኑ ሥራዎች አይደሉም። 
ለብዙ ወገኖች ሞት ምክንያት ድሮ ድሮ በየአስር ዓመቱ አሁን አሁን ደግሞ በጣም ባጠረ ምልልስ የሚከሰተውን ድርቅ ተከትሎ የሚመጣው ረሀብ ቢሆንም የችግር ቀለበቱ መስበሪያ ያለው ግን ሌላ ቦታ ነው - ኃይል አቅርቦት ጋ ። የችጋር ቀለበቱ  ከኃይል ፍለጋ ጋር ተቆራኝቶ ከተፈጠረ በኋላም ከፍተኛ ረሀብ በተከሰተበት ወቅትም ቢሆን ኃይል ፍለጋው ስለሚቀጥል ችግሩን እያቀጣጠለና እየቀጣጠለ ቀጥሏል። 
መስበሪያው መዶሻ
የችጋር ቀለበቱን በተሳካና በዘላቂነት መቁረጥ የምንችለው የኃይል አቅርቦት ችግርን በብቃትና በጥራት መፍታት ስንችል ነው። አሁን በአገራችን እየተስፋፋ ያለው የኃይል ማመንጫዎች ግንባታ ጠቃሚነት እንደተጠበቀ ሆኖ  ኃይልን በብቃትና በጥራት ለማቅረብ፤ ከኃይል መጠን አልፈን በኃይል አገልግሎቶች ደረጃ ማውራት አለብን። ኃይልን ለመብራት፤ ለመጓጓዣ፤ ለመዝናናት፤ለተግባቦት፤ ለማንበብ፤ ለማጠብ፤ ለማሞቅ፤ ለማብሰል ወዘተ እንጠቀምበታለን። እነዚህ የኃይል አገልገሎቶች ከተጠቃሚዎች ብዛትና አይነት አንጻር መተንተን ጠቃሚ ነው። በቤተሰባዊ ሸማቾች ደረጃ የምንሻው የኃይል አይነትና መጠን ለኢንዱስትሪዎች ከምንፈልገው ኃይል አይነትና መጠን ለያይቶ ማየትንም ይጨምራል። ለኢንዱስትሪዎቻችን መብራትና ማሽነሪዎች ማንቀሳቀሻ የሚሆነው የኤሌክትሪክ ኃይል ከማዕከላዊው የኃይል ማሰራጫ መገኘቱ ልክ ነው። ለተለያዩ የማምረቻ ሂደቶች ለሚያስፈልገው ሙቀታዊ ኃይል ፀሐያዊ የሙቀት መቀበያ ሰሌዳዎችን መጠቀም አዋጪ ይሆናል።እጽዋት-ነክ ነዳጆችንም የበለጠ ተገቢ የሚሆኑበት ቦታ ላይ መጠቀም ይኖርብናል።
ለመጓጓዣ አገልግሎት የነዳጅ-አረቄና የባዮዲዝል አቅርቦታችንን ከፍ ማድረግ ያስፈልገናል።
ኬሚካሊያዊ አየር-ወለድ የጤና ጠንቆችን ከማስወገድ አንጻር ምግብ ለማብሰል ለኤሌክትሪክ ኃይልን ቅድሚያ እንስጥ - ቢያንስ በከተማ - ዋጋው አይነኬ እስካልሆነ ድረስ። የከተማና የገጠር ተጠቃሚዎች ፍላጎት ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ይለያያል። በገጠር ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎች ሚናቸው ከፍተኛ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ትኩረቱ በምድጃዎች ላይ ብቻ ሳይወሰን ምድጃው ውስጥ የሚነደው ማገዶንም ማሻሻል አለብን። ለምሳሌ ከክብደቱ ወይም ከመጠኑ ጋር ሲነጻጸር ከፍ ያለ የኃይል መጠን ያለውና የአመድ መጠኑ ያነሰ ማገዶ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል - ስለሚቻል። ለገጠርም ለከተማም በነድጅ-አረቄ የሚሰራ ምድጃ ማስፋፋትም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው (ሌላ ቀን ይዘረዘራል)።
ተበታትነው ለሚኖሩ የገጠር ነዋሪዎች የመብራት አገልግሎት ከማሰራጫ መረብ ዝርጋታና ጥገና ወጪ አንጻር ከማዕከላዊ ማሰራጫ ይበልጥ በፀሀይ ኃይል የሚሰራ መለስተኛ ማመንጫ ተከላ ሊያዋጣ ይችላል። 
ኢኮኖሚው እያደገ ሲሄድ የኃይል ተጠቃሚዎች ብዛትና አይነት መለወጡ አይቀሬ ነው። ለምሳሌ መብራት፤ምግብ ማብሰልና መሞቅ ብቻ ላይ ተወስኖ የቆየ የኃይል አገልግሎት ፍላጎት፤ የቴሌቭዥንና የማቀዝቀዣ ባለንብረት ከመሆን ጋር ወደሚያያዝ ተጨማሪ ፍላጎት ያድጋል። ከዛም ወደ መጓጓዣ አገልግሎት ባለቤትነት ከፍ ይላል። የኃይል አይነቱና መጠኑም እንዲህ እያለ ይቀየራል። 
የኃይል አቅርቦት ጥያቄን መፍታት ማለት ነባርና አዳዲስ የኃይል አገልግሎት ፍላጎቶችን በአይነት በአይነት ማሟላት ማለት ነው። 
ኃይል ለሁሉም ሰውና ለሁሉም አገልግሎት ሁልጊዜ  ማቅረብ ሲቻል፤ ለማገዶ የሚመነጠር ዛፍ ይቀራል። ይህም  በነፋስና በውኃ ለመሸርሸር የሚጋለጠውን አፈር በእጅጉ ይቀንሳል። 
ኃይል እንደልብ ሲቀርብ ለማገዶ ተብሎ የሚጠፈጠፍ እበትና የሚለቀም ኩበት ይቀርና ከብቶች በግጦሽ ቦታ መጋጥ ብቻ ሳይሆን ከአፈር ካገኙት የተወሰነውን ወደ አፈሩ መመለስ ይጀምራሉ። አፈሩም በደስታ ሌላ ዙር የመስጠትና የመቀበል ገንቢ ቀለበት ውስጥ ይሳተፋል።
የኃይል አቅርቦት ችግር ከተወገደ ዛፍ አለመቆረጡ ብቻ ሳይሆን በራሱ ጊዜ የወደቀውንም ቅጠል ለቅመን ለማገዶ ማዋል እየተረሳ ይሄዳል። የንጥረ ነገሮች ፍትፍት ተመልሶ የዛፎቹን ልማት እንዲደግፍ ከፈቅድንና ለዘመናት ሲጎራረሱ የኖሩትን ፍጥረታት ስርዓት ካላወክን በልተን ማደራችን ትውልድ-ተሻጋሪ ይሆናል። 
ኃይል ካለ ዝናብ ቢጠፋም የገጸ-ምድር ውኃ ቢሰወርም ወደታች ወርደን በከርሰ ምድር ያለውን ውኃ አስተፍተን በመስኖ ማልማት እንችላለን።
የኃይል አቅርቦት ሲስፋፋ ምርቶች በተመረቱበት ቦታ ሳይወሰኑ የበለጠ ወደሚፈለጉበትና የተሻለ ዋጋ ወደሚያስገኙበት ቦታ በጊዜና በበቂ መጠን እንዲደርሱ ማድረግ ይቻላል - አረንጓዴ ረሀብን ማስቀረት ይቻላል።
የኃይል አቅርቦት እንደሚፈለገው አገልግሎት አይነትና መጠን መቼቱን (መቼና የት) ጠብቆ የሚቀርብበት ደረጃ ስንደርስ ቅድመ-ድርቅ፤ ጊዜ-ድርቅና ድኅረ-ድርቅ ያለው ወቅት ከቁጥጥራችን ውጪ ሳይወጣ አንድም ሕይወት ሳያልፍና ወገን ሳይጎሳቆል አገራዊ ሕይወትን አስቀጠልን ማለት ይሆናል። ይህም የድርቅን ዘርማንዘር- ከአያቶቹ እስከ ደቂቀ-ድርቅ (የልጅ ልጆቹ)  - በየደረጃቸው ቀንድ ቀንዳቸውን ለማለት ሰፊ እድል ይሰጠናል።  በአጭሩ ኃይል የችጋር ቀለበትን የምንሰብርበት መዶሻችን ነው። 
===============
ሰኔ  18  ቀን 2003 ዓ.ምአዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው “አዲስ ጉዳይ” መጽሔት ላይ መደበኛው  “የአረንጓዴ ጉዳይዓምዴ ላይ ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org


No comments: