Wednesday, July 13, 2011

“እቃሻሻ”

(ጌታቸው አሰፋ)(ደረቅ) ቆሻሻን የሆነ እቃ የቅርብ ዘመድ አድርገን ልንቆጥረው እንችላለን። ዝምድናው በተለያየ መልኩ ሊገለፅ የሚችል ነው። የእቃው አያቶች የሆኑትን ጥሬ ዕቃዎች ከማልማት ሂደት ጋር የሚገኝ ቆሻሻ አለ። እቃው ሲመረት የሚፈጠርም አለ። እቃው ጥቅም ላይ ሲውልም በማርጀት ወይም በመበላሸት ወይም ተጠቃሚው በሌላ ምክንያት እቃውን መጠቀም ሲያቆም የሚፈጠረውም ሌላው ነው።
የቆሻሻ መጥፎነት  - መጥፎ ከሆነ - ከመጠኑና ከይዘቱ ጋር የሚተሳሰር ነው። “ቆሻሻህን አሳየኝና ማንነትህን እነርግርሃለሁ” የሚል አባባል አለ ሲባል ከሰማን ኖረም አልኖረም አባባሉ ትክክል ስለሆነ የለም ብለን ባንከራከር ይሻላል።

ድሮ ድሮ በነፍስ ወከፍ የሰው ልጆች ይጥሉት የነበረው የቆሻሻ መጠን  በጣም ጥቂት ነበር። ይዘቱም ከተፈጥሮ የተገኘና በቀላሉ ወደ ተፈጥሮ በመበስበስ ሊመለስ የሚችል ነበር። እጅብ ብለን በከተማ መኖር ስንጀምር በአንዴና በአንድ ቦታ የሚፈጠረው ቆሻሻ መጠን ጨመረ። ከዘመን ጋር ኑሮው እየተቀየረ ሲመጣም የቆሻሻው ይዘት ውስብስብ እየሆነ መጣ። የእንስሳትና የእጽዋት ተዋጽኦ  የነበራቸው ምርቶች ይፈጥሩት የነበረው ቆሻሻም ያንን አይነት ነበር። የብረት ውጤቶች በምርት መሳሪያነት ጥቅም ላይ መዋል ሲጀምሩም በጥቅም  ላይ የሚቆዩበት ጊዜ እጅግ ረጅም ነበር። ከትውልድ ወደ ትውልድ የተሰሩበትን ጥቅም እየሰጡ የሚተላለፉ ነበሩ። አንድን ዕቃ ለብዙ ዘመን ማቆየት ራሱ ዋጋ ነበረው። አያቴ ቤት ያሉት ሶስት እቃዎች፤የምግብ መብያ ሳህን - የኔ ታላቅ፤ ራዲዮን - የኔ እኩያ፤ ትንሿ የሸክላ እቃ ደግሞ በቅርቡ ስድሳ አመት የሞላት የእናቴ እኩያ።

“የአያቴና የቅድመ አያቴ ነው” ማለት ራሱ ዋጋ ያሰጥ በነበረበት ህብረተሰብ ውስጥ የዕቃዎች እድሜ ዘለግ ያለ ቢሆን የሚጠበቅ ነው።
 
ድሮ ከትንንሽ እቃዎች እስከ ትልልቅ ህንጻዎች ተጠቃሚው በስም የሚያውቃቸው ግለሰብ ባለሞያዎች የጊዜና የክህሎት አሻራቸውን ያሳረፉባቸው ነበሩ። የሚመረቱትም በነጠላ በነጠላ ነበር። መርሆውም “ተጠብበሽና ጊዜ ወስደሽ አምርቺው ለትውልድም አስተላልፊው” የሚል አይነት ነበር። ቀጠለ። በድንጋይ ከሰል አቀጣጣይነት የኢንዱስትሪ አብዮት ፈነዳ። ማሽኖች ተሰርተው በምርት መሳሪያነት ለስራ ተሰማሩ። ኩባንያዎች መቋቋም ጀመሩ።ግለሰብ ባለሞያዎች ህጋዊ ሰውነት ላላቸው ኩባንያዎች የእውቅና ቦታ ለቀቁ። ምርቶችን በጅምላና በገፍ ማምረት ተጀመረ። መርሆው “እንደምንም፤ ከምንም ስሪው ኩባንያውን ከዘመነ ትርፍ ወደ ዘመነ ትርፍ አሸጋግሪው” ሆነ። በትውልድ የነዳጅ ዘይት ዘመድ የሆነው ላስቲክ ተሰርቶ ለእቃዎች ማምረቻነት ዋለ። የእቃዎች ክብደት ቀነሰ። ዋጋቸውም እንዲሁ።
ቀስ በቀስ የአገልግሎት እድሜያቸውም አጠረ። ኩባንያዎች ሰው የሚፈልገውንና ለሰው የሚያስፈልገውን ከማምረት ቀስ በቀስ አዳዲስና መቋጫ የሌለው ፍላጎት መፍጠርንም የስራቸው አንድ አካል አድርገው ያዙ።
እንዲያጥር የተደረገው የእቃዎች እድሜ የጎላ የተረዳ የምንለው መደበኛ እድሜያቸው ነው። የአንድ ዕቃ መደበኛ እድሜው ሲደርስ ተበላሽቶ ሲያበቃ የማይጠገን ሆኖ እርፍ። ወይም እንዲሰራ የሚያደርገው አዲስ መለዋወጫ ወይም ገባር እቃና አገልግሎት ከነባሩ እቃ ጋር የማይገጥም ሆኖ ቁጭ። በአጭሩ ይህ ሆን ተብሎ ከእቃው ጋር አብሮ የተሸመነው እድሜ ሲደርስ የእቃው እጣ መጣል ብቻ ሆነ።  ይህን እድሜ የሚወስነው በአምራች ኩባንያው ውስጥ ያለው እቃውን ዲዛይን የሚያደርገው ክፍል ነው። ዓላማው - ተጠቃሚው የገዛው እቃ እድሜ ያጥርና እንደገና አዲስ ይገዛል፤ የዚህም ያጥራል፤ አዲስ ይገዛል… እንዲህ እንዲህ እያለ ይቀጥላል። መች ይሄ ብቻ?! በዘመናችን እቃዎች እያጠረ ከመጣው ከመደበኛው እድሜያቸው የባሰ ያጠረ ሌላም እድሜ አላቸው። “ሃሳባዊ እድሜ” እንበለው። ከላይ እንደተገለጸው የጎላው የተረዳው እድሜ አምራቹ እቃው ላይ ካደረገው ነገር ጋር የተያያዘ ነው-ከእቃው ጋር የተሸመነና የተሰፋ። ሃሳባዊ እድሜው ደግሞ አምራቾችና አሻሻጮች በተጠቃሚዎች አእምሮ አንዲሳል ብቻ ሳይሆን እንዲሰፋና እንዲሸመን የሚያደርጉት ነው። ተጠቃሚዎች እርስ በርሳቸው እየተያዩ በ“የኔ ይበልጥ ፤ የእኔ አዲስ ነው” ፉክክር በደንብ የሚሰሩ እቃዎችን ወደ ማይሰሩት እቃዎች ዓለም ለማቀላቀል ከመጣደፋቸው ጋር የተያያዘ እድሜ ነው።
 የእጅ ስልክን እንደ ምሳሌ። ከሚመረትበት እቃና ሥርዓት አንጻር መደበኛ እድሜው እያጠረ መጥቷል። የኖኪያ ስልክን ብቻ  ብንወስድ Nokia 3310 የነበረው እድሜ ከእርሱ በኋላ የመጡት ሞዴሎች ካላቸው እድሜ ጋር ሲነጻጸር በጣም ረጅም ነው። አንዴ አይደለም ብዙ ጊዜ ወድቆ መነሳት ይችላል። ድንጋይን ባይገዳደር ብጋራህ የሚለው ጥንካሬ ግን አለው።
ምን ዋጋ አለው። ቅርጹ ይሁን፤ ማድረግ የሚችለው ነገር፤ ወይም “ውበቱ”  ብቻ - እየሰራ እያለም እንደማይሰራ  ተቆጥሮ የተጠቃሚዎችን እጆች እንዲለቅ ተደርጓል። በአገራችን ይህን ሞዴል የያዘ ሰው በሌሎች የ“ተሻለ” ሞዴል በያዙ ሰዎች ዘንድ የያዘው ስልክ ሳይሆን ሌላ ነገር እንዲመስለው በሚያስመስል መልኩ “እይታ” ውስጥ ይገባል። እናም በትክክል የሚሰራውን  ስልክ የ”እይታ”ውን  ሸክም የመሸከም የውዴታ ግዴታ ላለበት ሌላ ሰው ሲሆን በሽያጭ ካልሆነም በነጻ እንዲያሻግር “ይገደዳል”።  ተቀባይ ካጣም “ይጥለዋል”። የእጅ ስልክና የመሳሰሉት ኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ቢያንስ የተወሰንን ተጠቃሚዎች መቼም ቢሆን መጠቀም የማያስፈልጉንንና  መጠቀም የማንችልባቸውን አገልግሎቶች ይዘው ይመጣሉ። እነዚህ አገልግሎቶች እቃውን እንድንገዛ ብቻ ሳይሆን  በውድ ዋጋ እንድንገዛም ያደርጉናል። እቃውን ከገዛን በኋላ  ያሉትን አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ እንጠቀም ብንል፤ ቢያስፈልገንና ብንችልበትም እንኳ የሙሉ ጊዜ ስራችን እንዳይሆኑ ያሰጋሉ። አገልግሎቶቹን ጨርሰን ሳንጠቀምባቸው ብቻ ሳይሆን ምን ምን እንደሆኑ ሳናውቃቸው ሌላ አዲስ ሞዴል የማንፈልጋቸውና የማንጠቅምባቸው ግን የምንፈልጋቸውና የምንጠቀምባቸው የሚመስለን አዳዲስ አገልግሎቶችን ጨምሮ ሲመጣ ለመግዛትና ለማስገዛት እንሰማራለን።
በዚህም በዚያም ፤በአምራችም በተጠቃሚም የእቃዎች እድሜ ሲያጥር የ”ቆሻሻ” መጠን ይጨምራል። ቆሻሻ ከሚለው ቃል ይልቅ እቃሻሻ (እንዲሸሽ የተደረገ እቃ) በሚል አዲስ ቃል መግለጽን መርጫለሁ - ቆሻሻን ቆሻሻ ያሰኘው ሰው ነውና።
ሙሉ በሙሉ ቆሻሻ አልባ ኅብረተሰብ በትልቅ  ደረጃ መፍጠር ሊከብድ ይችላል። እቃን ደጋግሞና መላልሶ በመጠቀም ግን የቆሻሻ መጠን በእጅጉ መቀነስ የሚቻል ብቻ ሳይሆን የተቻለም ነው። ቆሻሻን መወገድ ያለበት እንከን ብቻ አድርጎ ከመቁጠር የዘለለ አመለካከትና ስልት ሊኖረን ይገባል። አምራቾችና አሻሻጮች እቃ ብለን የገዛነው ነገር ዞር ዞር ብለን ስንመጣ በሆነ ምትሐት ተለውጦ ቆሻሻ ሆኖ ቢታየን ደስታቸው ነው - ጥቅማቸው ስለሆነ። ተጠቃሚዎች ከግንዛቤ እጥረት አምራቾችና አሻሻጮች በከፈቱት ቦይ ኮለል ብለን ብንፈስ ቢያሳዝንም ላያስገርም ይችላል። መንግሥት የማይተካ ሚናውን መጫወት አለበት - የሚከተሉትን ሦስት ነገሮች በማድረግ።
“ቆሻሻ”ን ከምንጩ መቀነስ ዋናው ነው። ከውጪ የሚገቡም ሆኑ አገር ውስጥ የሚመረቱ እቃዎች መደበኛ እድሜ  በገበያ ላይ ካሉ አማራጭ እቃዎች የተሻለ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል።  የአገር ውስጥ አምራቾችንና ከውጪ የሚያስገቡ ነጋዴዎችን በማትጋት ሊፈጸም ይችላል። አማራጮች ባሉበት ደግሞ የተጠቃሚዎችን ግንዛቤ የሚጨምር መረጃ በማቅረብ  - ለምሳሌ በትምህርት መልክ። እንዲህ አይነት ጥራት ያለው መረጃ በተገቢው መንገድ ለተጠቃሚው ሲደርስ መደበኛ እድሜያቸው ከፍ ያሉ እቃዎች እንዲመረጡ ብቻ ሳይሆን የእቃዎችን ሃሳባዊ እድሜ የሚያሳጥሩ አመለካከቶችን ለመመከት ይረዳል።
መ(ላ)ልሶ መጠቀም ሌላው የመንግሥትን የአምራቾችንና የተጠቃሚዎችን ስራ የሚጠይቅ ነው። አንድ እቃ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ለጥቅም ተመ(ላ)ልሶ የሚውልበት ሥርአት ማበጀት ያስፈልጋል። መልሶ መጠቀምን በተግባር የሚያውለው - እንደ እቃው አይነትና ያለበት ደረጃ  - አምራች ወይም ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል።እንደ እቃ ወይም እንደ ጥሬ እቃ መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ስራ ላይ የተሰማሩትን ክፍሎች የሚያተጋ ስልት መቅረጽ ያስፈልጋል። በአገራችን እንዲህ አይነት መ(ላ)ልሶ የመጠቀም ስራ አዲስና ሀ ተብሎ የሚጀመር ሳይሆን የቆየውን የ”ቆርቆሮ-ያለው” (ቆራሊው) ስምሪትና በኅብረተሰባችን የሠረጸውን (በምርጫም ባይሆን)  “የሞቱ” እቃዎችን፤ሲሆን ሕይወት እየዘሩ ካልሆነም በዳግም ልደት ሌላ እቃ እንዲሆኑ ከዛም በሌላ አዲስ ህይወት ሌላ እቃ ሆነው እንዲቀጥሉ የማድረግ  ጥሩ ልማዶችን ያገናዘበ መሆን ይኖርበታል። የ”ቆርቆር-ያለው”ችንም ሆነ እቃ-ተኮር ህይወት ዘሪ ማኅበረሰባዊ ልማድን ተቋማዊ ቅርጽ እንዲኖራቸውና እንዲዘምኑ የመንግሥት ድጋፍ ወሳኝ ነው። የእቃዎች ህይወተ-ብዙ ሆኖ መቀጠልን የሚገዳደር የአዲሱ ትውልድና የሞጃዎች አስተሳስብ ላይ በጎ ተጽእኖ ማሳደር ጠቃሚ ይሆናል።

ከላይ የተጠቀሱት ሁለት ነገሮች ተደርገውም ለሚኖረው ቀሪ “ቆሻሻ” ኃይል ለማመንጨት፤ ማዳበሪያ ለማምረት ወዘተ የሚያስችሉን ተገቢ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም - በተለይ በአገር ቤት አቅም ሊበለጽጉ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን።
ከዛ የተረፈውን ቆሻሻ ደግሞ በታቀበ ማቃጠያ ማቃጠል መጠኑን አነስተኛ ፤ይዘቱን የማይጎዳ ያደርገዋል።  ለዳግም ሕይወት፤ ለኃይል ማመንጫ፤ ለማዳበሪያ ማምረቻ፤ ለመቃጠል ወይም ለአንዳች የማይሆነውን ደግሞ በጥብቅ መቅበሪያ መቅበር ይገባናል። ከአዳማ እስከ ድሬዳዋ በተለያዩ ከተሞች ለዚህ የሚሆኑ  የተለዩ ቦታዎች እየተዘጋጁ ነው። እስካሁን እንደ አዲስ አበባው “ቆሼ” ሁሉም አይነት ነገር የሚደፋበት ሳይሆን ቁጥጥር የሚደረግበት ማረፊያ መሆን አለበት። አለበለዚያ ዛሬ ቆሻሻ ብለን የምንቀብረውን ሁሉ የወደፊቱ ትውልድ ማዕድን ብሎ ሲያወጣው “ይህንንም ቀበሩት? አሁን ይሄ እንዴት ይቀበራል?” እያለ እንዳይገረምብን።
====================
ሐምሌ 2  ቀን 2003 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: