Wednesday, July 27, 2011

የነፍስ ቁርጥማት


(ጌታቸው አሰፋ)ድርቅ አጥቢያዊ መነሻና ምክንያት አለው። አሁን አሁን ደግሞ እንደ ሉላዊ አባባሽ ምክንያትና መነሻ የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ(በካባቢ አየር ሙቀት መጨመር የሚገለጸው) ይጠቀሳል። ኢትዮጵያ ውስጥ ድርቅ መከሰት የጀመረው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ሰውኛ መንስኤው ይበልጥ እየተረጋገጠ ከመምጣቱ ቢያንስ መቶ ዓመታት በፊት ነው። በመፍትሔ ደረጃ አጥቢያዊ መነሻው ላይ ስናተኩር የሚጨበጥ ነገር ማድረግ እንችላለን። ሉላዊ መነሻችን እንደ አገር ብቻችንን በተናጠል ከኃሌ-ኵሉ ሆነን የምንፈታው አይደለምና። በዛ ላይ አጥቢያዊ ምንጩን ስናደርቅ ሉላዊ ድርሻችንን ተወጣን ማለት ስለሚሆን አሪፍ ነው።
ለእውቀት ያህል ግን የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ በአንዳንድ ቦታዎች ድርቅን ሲያባብስ  በሌሎች ቦታዎች ደግሞ የጎርፍ መጥለቅለቅን ያመጣል (ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ)። 
ድርቅ፤ ረሃብ
ድርቅ ለኢትዮጵያ ወይም ለአፍሪካ ቀንድ ብቻ ተለይቶ በልካችን የተሰፋ ልብስ አይደለም። የትም ቦታ ይከሰታል። በድምጽ አልባ መሣሪያው ወገኖቻችንን በጅምላ የጨረሰው በቁሙ ድርቅ አይደለም። በዓለም አቀፍ ደረጃ ጯሂ ዜና እየተሰራበት ያለው ድርቅ አይደለም።ድርቅ ብርቅ አይደለምና። ድርቅ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ እንስሳ ወይም እጽዋት አይደለም። በየሄድንበት አንገት የሚያስደፋን፤ የሚያሸማቅቀንና ደስታን የሚነፍገን ጥሬ ወይም ደረቅ ድርቅ ሳይሆን እሱን ተከትሎ የሚከሰተው የምግብ እጥረት ነው። አዎ ረሀብ ነው ጅምላ ጨራሹ ። አዎ በረሀብና በጥም ብዛት የተጎሳቆለ የወገናችን ተክለ ሰውነት ማየት ነው አንጀት የሚያላውሰው። ወገን የሚቆረጠም ጥሬ እጦት ምግብ ፍለጋ ሲበተን ማየት የላመ የጣመ ለሚበላውም ክፍል ቃር ቃር ቢለው የሚገባ ነው። ይናገርበት ጉልበት ያጣ፤ ያይበት አቅም የተነሳ ወገን ዙሪያ የድሮም የዘንድሮም መረጃ ተቀናብሮ በምስል፤ በድምጽና በፊደል በየሄድንበት ስናየው፤ስንስማውና ስናነበው የነፍስ ቁርጥማት ቢሆንብን ወደን ነው?
በ1977 ዓ.ም. የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ።  የድሮን ነገር በማስታወስ ብዙ ጊዜ ባይሳካልኝም ሰባ ሰባትን ግን በአንድ ትንሽ ነገርና በአንድ ትልቅ ነገር አስታውሳታለሁ። 
ትንሹ - 7ኛው ቀን 7ኛው  ወር 77ኛው ዓመተ ምህረት (የጌትነት እንየው ግጥም አይመስልም?) ቅዳሜ ቀን እንደነበርና በዛን ቀን የጂኦግራፊ መጽሐፋችን ላይ የነበረው የተለያዩ አለቶችን የሚያሳይ የባለቀለም ምስሎች ሰንጠረዥ ከሆነች የክፍላችን ልጅ ጋር ሁኜ አጠና እንደነበር አሁን ድረስ ትዝ ይለኛል። ልጅቷ ግን ማን እንደነበረች ትዝ አይለኝም። አየ አእምሮአችን! መረጃዎችን ይጥቀሙም አይጥቀሙም ሲፈልግ ደብዛቸውን ያጠፋል፤ ሲፈልግ “አይረሴ” ፋይል ውስጥ ይደረድራቸዋል።
ትልቁ - የ77ቱ ረሃብ ወቅት በረሃብ አለንጋ ተገርፈው የተረፈረፉ ወገኖችን በአይኔ ያየሁበት። ወደሞት ያለው አጭር ርቀት ትንሽም ቢሆን ረዘም ለማድረግ ቅጠል የተባለውን ሁሉ(ከነበረ) ለመብላት ያደርጉት የነበረው ጥረት ዛሬ ድረስ ይታወሰኛል -እየነዘረኝ ። አሁን የምገኘው በዛን ጊዜ የስንዴ እርዳታ በመላክ ስሟ በየቤቱ ድረስ ታታወቅ የነበረችው ካናዳ ውስጥ ነው። የምገኝበት ክፍለ ግዛትም ለአገር ውስጥም ለውጪም (ቢያንስ ያኔ ኢትዮጵያን ጨምሮ) የሚሆን ስንዴ ከሚመረቱባቸው ሁለት ክፍለ ግዛቶች በአንዱ ነው።
እዚህ ከመጣሁ አይቀር “የረሃብ ዘመን በኢትዮጵያ ‘ታሪክ’ ሁⶈልና በችግራችን ጊዜ ድሮ ያኔ ድሮ ስለደረሳችሁልን እግዚአብሔር ይስጥልን። ለእኛ እንደሰጣችሁ እኛም ለተቸገሩት አገሮች እንሰጣለን።” የሚል መልክእክት ለማስተላለፍ ምኞቴ ነበር። ግን አልሆነም። በ77 በአካል (በልጅነት ጓጊና ፈሪ አይን) ያየሁትን እንዳስታውስ የሚያደርግ ዜናና ምስል በብዙኃን መገናኛዎች ዛሬ ልጅ ወልጄ (በተሸማቂቅና በቁጡ አይን) እያየሁት ነው። እርግጥ ነው ሁለቱም ወቅቶች እጅግ ይለያያሉ። ድህነታችንንና ረሃባችንን ሳይደብቁ ሳይቀባቡ የሚናገሩ መራሔ መንግሥት አሉን - ዛሬ። የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዐት ተዘርግቶ መረጃ በተሻለ ፍጥነት ይደርሳል - ዛሬ። የአሁኑ ረሃብ ወገኖቻችንን በጅምላ የሚጨርስበት ደረጃ አይደለም ያለው(አንዲት ነፍስስ ብትሆን ለምን በረሃብ ትቀጠፍ?)።  ያኔም ዛሬም ግን ምንም እንኳን መጠኑ ቢለያይም ረሃብ አለ። የምግብ እጥረት አለ። የውጪ የምግብ እርዳታ ዛሬም እንፈልጋለን። እርዳታን እርዳታ ያነሷል። እርዳታ ደስ የሚያሰኝና የሚያስመሰግን ነገር ቢኖረውም የሚያም ነገርም አለው - በተለይ የእርዳታ ኢንዱስትሪው ፓለቲካ ለሚገባው ሰው። የተቸገረ ከሌለ እርዳታ አያስፈልግም። እርዳታ ካላስፈለገ እርዳታን እንደ ሥራ የያዙ ሰዎች አይኖሩም - ለእርዳታ የሚውልና እርዳታን ለማስፈጸም የሚሆን ገንዘብ ስለማይገኝ። ይህ እንዳይሆን የሚፈልጉት የእርዳታ ድርጅቶች በብዙኃን መገናኛ በኩል ረሃባችንን አራግበው መጠቀሚያ እያደረጉት ነበር እያደረጉት ነው። በዚህ ሀቅ ዙሪያ በምዕራቡ ዓለም ታትመው የወጡ መጻሕፍቶችን በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል። እዚህ የእርዳታ ድርጅቶችን የሚተች ወሽመጥ ውስጥ ለአጭር ጊዜ የገባሁት ለግንዛቤ ያህል ብቻ ነው። አይዞን ልንወጣ ነው። የእርዳታ ድርጅቶችና የብዙኃን መገናኛዎች በማጦዝ፤ ለራሳቸው መጠቀሚያ በማድረግ አገራዊ ገጽታችንን አቧራ ያልብሱት እንጂ መነሻ ሀቅ ግን አላቸው - ኢትዮጵያ ውስጥ የምግብ እጥረት አለ- ድርብ ሰረዝ - የተራቡ ወገኖች አሉ - አራት ነጥብ።    
እርጥበትና ገንዘብ
በድርቅና በምግብ እጥረት(ረሃብ) መካከል ያለው ርቀት በአገራችን እንዲህ በጣም አጭር ሊሆን የቻለው ለምንድነው ነው? በሌሎች  አገሮች ድርቅ ይመጣል፤ ድርቅ ይሄዳል። የመጣው ድርቅ(በሉላዊም ይሁን በአጥቢያዊ መነሻ)  እግሩን ዘርግቶ ለፈለገው የጊዜ ርዝመት ቢቆይም እንኳ “ሲመረው”  ይለቃታል እንጂ የምግብ እጥረት አይከስትባቸውም። ታድለው! እኛ ጋ - ሁለት ክረምት ዘናብ ጠፋ …ደረቀ… ተራበ…. እነሱ  ጋ - ዝናብ ጠፋ ጠፋ ጠፋ ጠፋ ደረቀ ደረቀ ደረቀ … ረሀብ ግን የለም። 
በምግብ እጥረት ምክንያት ረሀብ እንዳይከሰት ለማድረግ (ውስብስቡን ነገር ከሀቁ የድንጋይ ውርወራ ያህል እንዳይርቅ አድርጌ ሳቀለው) ሁሌም በቂ እርጥበት እና/ወይም ገንዘብ ያሰፈልጋል(እነ ማዳበሪያ፤ ምርጥ ዘር፤ ጸረ ተባይ ወአረም ወዘተ ለጊዜው ማረፊያ ቤት ቆዩ ገንዘብ አይወክለንም ካላችሁ)።
እርጥበት -  ከቅርብ ወይም ከርቀት። ከሰማይ ወይም ከምድር። የቅርቡም የሩቁም፤ የሰማዩም የምድሩም እርጥበት የእግዚአብሔር ነውና  እርጥበት ካልንበት ባለንበት  ባልተገኘ ጊዜ የእግዚአብሔር ቁጣ ብቻ አድርግን መውሰድ አያዋጣም። እኛ ሰዎች እንጂ ተራሮች አይደለንም። እርጠበቱ ካለበት ሄደን ማምጣት አለብን። ከሰማይ ሲጠፋ ከምድር ገጽ ወይም ሆድ፤ ከቅርብ ሲጠፋ ከሩቅ ማምጣት የግድ ነው።ካመንበት፤ ካሰብንበት፤ ከተጨነቅንበት እንችላለን።  ቢጠፋ ቢጠፋ ጉሮሮአችንን ለማራስ የሚሆን ውኃ ያላጣን ወገኖች ተሰባስበን እርጥበት ያጡ ማሳዎቻችን ላይ ቢያንስ የተባበረ የምራቅ ክንዳችን እስከማሳረፍ ድረስ የሚያስብ የምር መጨነቅን ይጠይቃል። 
እርጥበትን ካለበት አምጥተን ወደሚፈለግበት ለመውሰድ ኃይል ያስፈልጋል (በአዲስ ጉዳይ የሰኔ 25 ዕት፣ የአረንጓዴ አምድ ላይ ይመልከቱ)። ከዚህ ጋር በተያያዘ መንግሥት በአፋጣኝ ማድረግ ያለበት ነገር አለ። ለጅቡቲ፤ ለኬንያና ለሱዳን በነሱ በኩል ደግሞ ለግብጽና ለሌሎች አገሮች ሊሸጠው ያሰበውና መሸጥ የጀመረውን የኤሌክትሪክ ኃይል በአነሰተኛ ምልክታዊ የሜጋዋት-ሰዓቶች መጠን መወሰን አለበት። ለአገራችን ከሚሰጠው ፓለቲካዊ ጥቅም አንጻርና ወደፊት ሊሰፋ በሚችለው የክፍላ-አህጉራዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ገበያ ላይ ወሳኝ ቦታ ከመያዝ አንጻር ሽያጩ ሙሉ በሙሉ መቆም አይኖርበትም።
የሜጋዋት-ሰዓቶቻችን ዋናው ክፍል ግን እንደ አዳኝ ውሻ እርጥበትን ከምድር ሆድም ይሁን ገጽ ከያለበት እያደነ አርሶ አደር የሆነው የኅብረተሰባችን አካል ተሰባስቦ ወደሚገኝበት ቦታ ሁሉ ለማድረስ መሰማራት አለበት። እያንዳንዱ ሜጋዋት-ሰዓት  ምን ያህል የአገሪቱን ክፍል፤ በምን ያህል የእርጥበት መጠን፤ ለምን ያህል ጊዜ አራሰ አለሰለሰ ብሎ መገምገም የሚችልበት አሰራርና ስርዓት መፍጠር አለበት - መንግሥት።
የምርምር ተቋሞች (የእርሻ፤የደን፤ የተፈጥሮና የማኅበራዊ ሳይንስ.. ወዘተ) እርጥበት-አዘል ቁምነገር ያለው ምርምር ቢያደርጉ ለዛሬና ለነገ ትርጉም ያለው ሥራ ለመስራታቸው ዋና ማሳያ ይሆናል። መንግሥት ይህን እውን ከማድረግ አንጻር ማትጊያ ፖሊሲዎችና ማስፈጸሚያና መከታተያ መመሪያዎችን ሊቀርጽ ይገባል።
የብረታብረትና ኢንጂንሪንግ ኮርፖሬሽን የህዳሴውን ግድብ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራን ለመስራት፤ አዳዲስ የአንበሳ አውቶብሶችን ለመገጣጠም/ለመስራትና፤ፋብሪካዎችን በራስ አቅም ለመትከል ብቃት እንዳለው ተወሰቷል። ደስ ያሰኛል። ይሁንና መጀመሪያ ከትንሽ እስከ ብዙ ወገኖች ነፍስ፤ከዛም አገራዊ ገጽታችንን ከሚያጠፋውና በየጊዜው በመደበኛነት ከሚከሰተው ረሃብ ለመገላገል ኮርፖሬሽኑ እርጥበት-ተኮር ዋና ክፍል ሊኖረው ይገባል። ይህ ክፍል ከውኃዊ ኃይል ግድቦቻችን የሚገኘውን ሜጋዋት-ሰዓት እየዋጡ ወይም በአገር ውስጥ የተመረቱ እጽዋት-ሰር ነዳጆችን እያቃጠሉ እርጠበትን ከየተገኘበት ጎትተው በሚፈለግበት ቦታ የሚተፉ ሞተሮችን በአገር ውስጥ አቅም በስፋት ማምረት መቻል አለበት።    
ኃይልን በመጠቀም እርጥበትን ቀርቶ ምንም ነገር ቢሆን ስንጠራው አቤት፤ ስንልከው ወዴት ማለቱ አይቀርም። 
ሁለተኛው ገንዘብ ነው። ገንዘብ ደስታ አይገዛም ወዘተ ወዘተ። ልክ ነው። ምግብን ግን ይገዛል። ድርቅ እየመታቸው ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ ቤተኛ የሆነባቸው አገሮች ሳይቀሩ ወደ ረሃብ የሚያደርስ የምግብ እጥረት አይከሰትባቸውም። ለምን? እርጥበት ጠፍቶ ምግብ ማምረት ባይችሉም፤በፊት ያመረቱትንም በልተው ቢጨርሱም ካለበት ይገዙታል። ገንዘብ አላቸዋ! በአገራችን በግብርና-መር ምጣኔ ሀብት ላይ ብዙ ጊዜ ከቆየንና ወደ ኢንዱስትሪ-መር ምጣኔ ሀብት የሚደረገውን ጉዞ ቶሎ ካላፋጠንነው የገንዘብ ምንጭ ያደረግነውም ገንዘባችን የሚያስፈልገውም ዘርፍ አንድና ያው  - ግብርና (የአገልግሎት ዘርፍን ስናስወጣ)-  ይሆንና ጥረታችን የተዘጋ መንገድ ላይ የመንዳት ያህል የማይቻል ይሆናል። ገንዘብን ከሌሎች ኢንዱስትሪዎች አግኝተን ምግብ ሲያሰፈልግ ካለበት ለመግዛት የምንችልበት ሽግግር ይዋል ይደር የሚባል መሆን የለበትም።
====================
ሐምሌ  16  ቀን 2003 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: