Wednesday, June 15, 2011

የሚደላን ማመቻመች

(ጌታቸው አሰፋ) ለዛሬ ስለመሬት እጽፋለሁ። ኢትዮጵያችን እንደ አገር ምን ምን እንደሚያስፈልጋት የታወቀ ነው። በራሷ አቅም ህዝቧን መመገብ፤ የውጪ ምንዛሪ ምንጮችን ማስፋት፤ ለዜጎችዋ ቁጥረ-ብዙ የሥራ እድልን መፍጠር፤ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ለማበልጸግ የሚያስችሉ እድሎችን መፍጠርና መጠቀም አለባት። እነዚህን በአጥጋቢ መጠንና ጥራት ማድረግ ያለመቻልዋን የሚያሳብቁ ነባራዊ ተግዳሮቶችን ለመግጠም አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ክስተቶች ግንዛቤ ውስጥ መግባት አለባቸው። በተለይ በዓለም ገበያ ላይ ጥገኛ ከመሆን አልፈን የዓለም ገበያን እኛ ላይ ይሄ ነው በሚባል ደረጃ ጥገኛ ለማድረግ ያልቻልን እኛና መሰል አገሮች ዓለም አቀፋዊ የለውጥ ዜማዎችን ተከትለን እስክስ ማለታችን የግድ ሆኗል።

በዓለም ደረጃ በተለይ ካለፉት አምስት አመታት ወዲህ የተከስተውና ‘የመሬት ያለህ’ እያሰኘ ያለው ዜማ ደግሞ ለነዳጅና ለምግብ የሚሆኑ ሰብሎች ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ መጨመር ነው። ፍላጎት ሲጨምር አቅርቦት በተመጣጣኝ ደረጃ ካላደገ ዋጋ ይጨምራል - መሰረታዊ የስነ-ምጣኔ-ሀብት እሳቤ እንደሚያስረዳን። ለሁለቱም አይነት ሰብሎች የሚሆን መሬት በስፋት የሚገኘው ደግሞ በአፍሪካና በላቲን አሜሪካ ነው። በነዚህ አህጉሮች ያለው የመሬት አቅርቦት መጠን ምን ያህል እንደሆነ ባይታወቅም አቅርቦቱ ከፍተኛ አቅራቢዎቹም ብዙ ከሆኑ ከውጪ ለሚመጡት ባለሀብቶች መሬቱ የሚሰጥበት ውል ይዘት ወደ ባለሀብቱ እንዲያደላ የሚያስገድድ አስቻይ ሁኔታን ይፈጥራል።
ይሁንና የመንግሥት የማይተካ ሚና የሚሆነው ለጽድቅ የማይመጡት የውጪ ኩባንያዎች ወደ አገራችን ሲመጡ የሚዋዋሉት ውል የኢትዮጵያን የአሁኑና ዘላቂውን ጥቅም የሚያስጠብቅ መሆኑን ከማረጋገጥ አኳያ የሚያደርገው ማመቻመች የሚደላን ማመቻመች ማድረግ ነው። የዚህ ሥራ ሀ እና ፐ ደግሞ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ነው።
የመረጃ ድንግዝግዝ
ከሁለት ወራት በፊት አካባቢ ሁሌ እንደማደርገው የኢትዮጵያን ቴሌቭዥን በኮምፒዩተሬ እየተመለከትኩ ነበር። ሼክ መሐመድ አላሙዲን ኩባንያቸው በጋምቤላ የሚያካሄደውን የሩዝ እርሻ እየጎበኙ ነበር። ዘጋቢው የግብርና ሚኒስቴር መረጃን መሠረት አድርጎ ኢትዮጵያ ለእርሻ ሊውል የሚችል ከ111 ሚልዮን ሄክታር በላይ መሬት አላት አለ። ከየትኛው ክፍል ወይም ማን የሚባል የሥራ ኃላፊ መረጃውን እንደሰጠው አልተናገረም - ጋዜጠኛው። ይሁንና የተጠቀሰው ሊለማ የሚችለው የመሬት ስፋት የአገሪቱን ጠቅላላ ስፋት እንጂ ለእርሻ የሚሆነው መሬት አይደለም። በቁጥር የሚቀመጡ ነገሮች በተመለከተ ወጥ የሆነ ቁጥር መጥራት አልሆነልንም - በአገር ደረጃ። እናም እንደዚህ አይነት ስህተቶች መፈጠራቸው የሚጠበቅ አድረገን እንወስደው ይሆናል። የጋዜጠኛው ስህተትም የሚካበድ አይደለም ብለን ልንተወውም እንችላለን። ይሁንና በመሬት ጉዳይ ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ጉዳዮችም ጭምር ቁም ነገር ለመነጋገር ቁጥሮች ወሳኞች ስለሆኑ ነው የአገሪቱን ጠቅላላ የመሬት ስፋት በተመለከተ ሳይቀር ያለውን የመረጃ ድንግዝግዝ ማንሳቴ። የግብርና ሚኒስቴርና የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣንን መረጃ መሠረት በማድረግ በተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት እንደሚለው በአገሪቱ ያሉ የእርሻ-ወ-ስነ ምህዳር ቀጠናዎች ከሚሸፍኗቸው ስፋቶች ጋር በስድስት አበይት ክፍሎች ተጠቃለው የቀረቡበት ዘገባ አለ። በዚህ መረጃ መሠረት የአገሪቱ ጠቅላላ የመሬት ስፋት ወደ 130.6 ሚልዮን ሄክታር ይሆናል። ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት የወጣውና በግብርና ሚኒስቴር ገጸ ድር ላይ በወጣው የኢንቨስትመንት ሰነድ ደግሞ የአገሪቱ ጠቅላላ ስፋት 111.5 ሚልዮን ሄክታር እንደሆነ ያሳያል። እነዚህ ከሞላ ጎደል አንድ ምንጭ ያላቸውን መረጃዎችን ብቻ ብንወሰድ ያላቸው ክፍተት ቀላል አይደለም። ለምሳሌ በ130.6 ሚልዮን ሄክታርና በ111.5 ሚልዮን ሄክታር ያለው ልዩነት አንድ ድፍን ዩጋንዳን ወይም ሁለት ኤርትራን ሊሆን ምንም ያህል አይቀረውም። በግዘፍ ያለውን የአገሪቱን ጠቅላላ የመሬት ስፋት ላይ እና ከዚሁም ውስጥ ሊለማ የሚችለው፤ እስካሁን የለማው ስፋት ላይ ያለን የመረጃ ጥራትና ወጥነት ላይ መሥራት እጅግ ወሳኝ ነው።
ውል ያለው ውል
ከውጪ ባለሀብቶች አገራችን የምትዋዋለው የመሬት ሊዝ ውል ባለ ሃያ አንድ አንቀጽ ሲሆን የሊዝ ሰጪና የሊዝ ተቀባይ መብትና ግዴታ፤ የመሬቱ መጠንና ክፍያ እንዲሁም የሊዙን ዘመን የሚገልጽ ነው። ውሉ ላይ መጠቀስ ሲገባው ያልተጠቀሰው ከሚመረተው ምርት ምን ያህሉ ለአገር ውስጥ ገበያ ይቀርባል ወይም መቅረብ አለበት የሚለው ነው። በመንግሥት በኩል እዚህ ሽጥ እዛ ግዛ የሚል አሠራር ከምንከተለው የነጻ ገበያ መርህ ጋር የሚጣረስ ነው የሚል መልስ ይሰጣል። ከነጻ ገበያ መርሆች ለአገሪቱ የበለጠ ይጠቅማሉ ያላቸውን ብቻ መርጦ በገቢር እንደሚያውል ለሚታወቅ መንግሥት ይህ መልስ አጥጋቢ መልስ አይሆንም።
ይልቁንም ውሎቹ በዓመት ከሄክታር መሬት አገሪቱ ማግኘት ያለባትን ጥቅሞች በዝርዝርና በቁጥር የሚያሳዩ ጥናቶችና ማብራሪያዎች መደገፍ አለባቸው። በየክልሉ ባለው እያንዳንዱ ሄክታር ማግኘት የምንችለው የውጭ ምንዛሪ፤ የምናስቀረው ወጪ፤ የምንፈጥረው የተለያየ ደረጃ ያለው የሥራ እድል ብዛት፤በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ ለምናደርጋቸው ቤተሰቦች ብዛት ያለው ድርሻ፤ ለአገር ውስጥ ኢንዱስትሪና ሸማች ፍጆታ የሚውለው የምርት መጠን ስሌት መሥራት ይጠበቅብናል። አንዴ ለውጪ ባለሃብቶች ሲሰጥ የሚገኘው ውጤት ለአገር ውስጦች ሲሰጥ ከሚገኘው ጋር ማነጻጸር። ሁለቱ ክፍሎች ያሏቸው አቅም ዝንባሌና የሚያስፈልጋቸው የማትጊያ አይነትና መጠን የሚለያይ መሆኑም ግንዛቤ ውስጥ የሚገባ ይሆናል። በራችንን ጥርቅም አድርገን፤ ወይም በሄክታር የምናስከፍለው የገንዘብ መጠን በጣም ጨምረን አልያም ከሌሎች አቻ አገሮች አንጻር ውሉን ባለሀብቶችን ሊያርቅ በሚችል መልኩ ብናጠብቀው የምናገኘው ጥቅም አይኖርም። ይሁንና በረጅም ጊዜና በጣም ዝቅተኛ በሆነ ክፍያ እንዲሁም በአካባቢው ሊደርስ የሚችለውን የተፈጥሮና ማኅበራዊ መጎሳቆልን እንዲያስቀር ወይም በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ የማያስገድድ ውልም ሊኖረን አይገባም።
ከዚህ አንጻር እንደ መንግሥት ተደራሽና መረጃ-ጠገብ አሠራር መዘርጋት ይጠበቅበታል። እንደዚህ አይነት አሠራር የሚመልሳቸው ጥያቄዎች አሉ - የሚከተሉት ጥቂቶቹ ናቸው። ባለሀብቱ ከውጪ ይዞት የሚመጣው ሀብት ምን ያህል ነው? ከአገር ውስጥ ባንኮች የሚበደረውስ ምን ያህል ነው? በተለያየ ምክንያት ሥራውን ቢያቋርጥ በሰውና በተፈጥሮ ሀብት ላይ ለደረሰው ጉዳት ተጠያቂው ማን ነው የሚሆነው? ለም እና ለሰብል ልማት አመች የሆኑ መሬቶች የት ነው ያሉት? ምን ያህልና ምን አይነት መመንጠር የሌለባቸው የደን ሽፋን አላቸው? በአነስተኛ ግብዓት ከፍተኛ የሰብል ምርት ለረጅም ጊዜ የምናገኘው የት ቦታ ነው? የአፈሩ ለምነት በአጭር ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ እንዳይመጣና ከሚገባው በላይ ጨውማና አሲዳማ እንዳይሆን ምን መደረግ አለበት?
ጅማሮው እንዲቀጥል
በዕቅድ በተመሠረተና በክትትል ጥላ ሥር ባለ የመሬት አጠቃቀም አሠራር የታገዙ ውሎች ጠቃሚነት ምን ያህል ግልጽና ክፍት ናቸው ከሚለው ጋርም ይያያዛል። ውሎቹ ለህዝብ ክፍት መሆን አለባቸው ከሚል አንጻር ለሃያ አራት ባለሀብቶች የተሰጠው የመሬት መጠን የሚገልጸውና በግብርና ሚኒስቴር ገጸ ድር የወጣው መረጃ መልካም ጅምር ነው። መረጃው ከገጸ ድሩ ውጪ በምን አይነት ሌሎች አውታሮች እንደተዘረጋ አላውቅም። ይሁና እስካሁን ያልተደረገ ከሆነ አገር ውስጥ ላለው ሕዝብ በቀላሉ መድረስ በሚችልበት ቅርጽና መንገድ መቅረብ እንዳለበት ግን መጠቆም የግድ ይላል። ከሃያ አራቱ ባለሀብቶች ውስጥ ስምንት የሕንድ፤ አንድ የቻይና፤ አንድ የሳውዲ(ሼክ አላሙዲ) ሲሆኑ፤ ስምንት ኢትዮጵያዊያን፤ ስድስቱ ደግሞ በዝርወት ያሉት ትውልደ ኢትጵያዊያን ናቸው። መሬቶቹ በደቡብ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልል፤ በጋምቤላና በቤንሻንጉል ጉምዝ የሚገኙ መሆናቸውን መረጃው ያሳያል - አንድ የህንድ ኩባንያ ከወሰደው የአማራ ክልል መሬት ውጪ ማለት ነው። በመረጃው የተካተተው ጠቅላላ የመሬት ስፋት 350 099 ሄክታር ሲሆን ይኸውም ለአንድ ዳያስጶራ ከተሰጠው ትንሹ የ431 ሄክታር መሬት አንስቶ ካሩቱሪ ለተባለው የህንድ ኩባንያ እስከ ተሰጠው የ100 ሺህ ሄክታር መሬትን ያካትታል። እያንዳንዱ ኩባንያ ለእያንዳንዱ ሄክታር በዓመት የሚከፍለው የመሬት ኪራይ በቀረበው መረጃ መሠረት ሳሰላው ከፍተኛው ኪራይ 713ብር ስሆን ሁለተኛው ደግሞ 658 ብር ነው። የመጀመርያው በቤንሻንጉል ጉሙዝ ለአትክልትና ለስብሎች ልማት የሚሆን 431 ሄክታር የወሰደው ከላይ የተጠቀሰው ዳያስጶራ ነው። ሁለተኛው ደግሞ በዚሁ ክልል ለሰሊጥና ለባቄላ ማምረቻ አምስት ሺህ ሄክታር የወሰደው አገር-በቀሉ አክሰስ ካፒታል የተባለ ኩባንያ ነው። ዝቅተኛውን የሚከፍሉት ደግሞ ከላይ የተጠቀሰው ካሩቱሪ ብር ሀያ እንዲሁም የሳውዲው ስታር ኩብንያ ብር ሰላሳ ናቸው። ካሩቱሪ ለፓልም ዘይት፤ ለጥራጥሬ፤ ለሩዝና ለሸንኮር አገዳ ልማት ነው መሬቱን የተረከበው። ስታር ኩባንያ ደግሞ ለሩዝ ምርት። ሁለቱም ኩባንያዎች አዲስ አሠራር ከመዘርጋቱ በፊት ነው መሬቱን የተረከቡት ይላል ገጸ ድሩ። ከዛ አልፎ ግን ይሄን በጣም ዝቅተኛ ዋጋ መከለስ ያልተቻለበት ምክንያት አያብራራም። ከነዚህ አራት ውጪ ያሉ አስራ አንድ ኩባንያዎች 158 ብር ሲከፍሉ ሌሎች አራት ደግሞ ብር 111 ይከፍላሉ። ሁሉም መሬት ዋጋው አንድ ነው ባይባልም ልዩነቱን አሳማኝ የሚያደርጉ ወጥ መስፈሪያዎች ግን በግልጽ መቀመጥ አለባቸው። ለምሳሌ እንደመሬቱ ስፋት የሚለያይ ከሆነ - በስፋት የወሰደ በሄክታር የሚከፍለው የሚያንስ ከሆነ ፤ እንደ ቦታው የትነት ከፍና ዝቅ የሚል እንደሆነ፤ ከሚያመርተው ምርት አይነት ጋር ያለው መስተጋብር ወዘተ መተንተን ይኖርበታል። በሌላ በኩል እኛ ማቅረብ የምንችለው የመሬት አይነትና መጠን ወይም የበለጠ ማቅረብ የሚችሉ ወይም ለውጪ ባለሀብቶች እያቀረቡ ያሉ ተፎካካሪ አገሮች በሄክታር የሚያስከፍሉትን የገንዘብ መጠንን ያገናዘበ አሠራር የምንከተል ከሆነም አንድ ጥሩ መነሻ ሊሆን ይችላል። ለማንኛውም የሁሉም ነገር መሠረት የሆነው መሬት ላይ ያለን መረጃ ጥራቱና ወቅታዊነቱ የተጠበቀ መሆን አለበት። መውጣት የጀመረው መረጃም ከተጨማሪ ዝርዝር ጋር መቀጠል አለበት። እንዲሁም የመሬት ማልሚያ ስልታችን የአሁኑንና መጪውን ትውልድ በሚጠቅም መልኩ መቀረጽ ይኖርበታል።

===============
ሰኔ 4 ቀን 2003 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው “አዲስ ጉዳይ” መጽሔት ላይ መደበኛው “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ ታትሞ የወጣ ጽሁፍ። www.akababi.org

1 comment:

Zereality said...

መለስ ኢትዮጲያን ሸጣት .....ለወጣት.....ምናምን ምናምን....ሰልችቶኝ ነ በር....የመረጃና የትንታኔ ጥማቴን እና ረሀቤን ስላስታገስክልኝ ....ላመሰግንህ ግድ ይለኛል....