Saturday, April 9, 2011

የነዳጅ አረቄ(ethanol) ድብልቅ


(ጌታቸው አሰፋ)በቅርቡ ለወራት ሳይከለስ የቆየው የተለያዩ የነዳጅ ዘይት ውጤቶች የችርቻሮ ዋጋ ተከልሷል። የቤንዚንና የነዳጅ አረቄ (ethanol) ድብልቅ በሊትር 16 ብር ከ55 ሳንቲም  ወደ 18 ከ33 ሳንቲም ከፍ እንዲል ከተደረገ በኋላ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ወደ 17.88 ዝቅ እንዲል ተደርጓል። በመቀነስ የሂሳብ ስሌት ሲታይ— የ1ብር ከ33 ሳንቲም ጭማሪ አሳይቷል ማለት ነው። ምክንያት— የዓለም የድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ዋጋ መጨመር። የዓለም የድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ዋጋ መጨመሩ ምክንያት ደግሞ— የሰሜን አፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ውስጥ ላለፉት ሁለት ወራት የታየው አለመረጋጋት።
በመንግሥት መግለጫ መሠረት የነዳጅ ውጤቶች የችርቻሮ ዋጋ የተጨመረው ለሰባት ወራት ወደ ተጠቃሚው በማውረድ ፋንታ ከአንድ ነጥብ አምስት ቢልዮን ብር የሚጠጋው ሸክም መንግሥት ተሸክሞት ከቆየ በኋላ ነው። የዓለም የድፍድፍ ዘይት ዋጋ ጭማሪ ጩኸት በየነዳጅ ማደያዎቻችን ደርሶ እስኪሰማ ድረስ ጊዜ ይወስዳል ማለት ነው። መውሰድም አለበት— የዓለም የድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ዋጋ የሚቀያየርበት ፍጥነት በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ለመከታተል ከሚቻልበት ደረጃ በላይ ስለሆነ። ለምሳሌ ይህን ጽሑፍ በምጽፍበት ቀን ቃጢፍ በተባለችና በነዳጅ ዘይት በበለጸገው ምሥራቃዊው የሳውዲ አረቢያ ክፍል ውስጥ በምትገኝ  ከተማ 300 የሚደርሱ ሰላማዊ ሰልፈኞችን ፖሊስ በተነ የሚል ሪፓርት ወጣ። ይህ ዘገባ በወጣ ደቂቃዎች ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ዋጋ የሁለት ዶላር ጭማሪ አሳይቷል። የነዳጅ ዋጋ እንዲጨምር የሚያደርጉት ከአቅርቦትና ከፍላጎት ጋር የተያያዙ ምክንያቶች ናቸው። ነዳጅ አቅራቢ አገሮች የሚገኙበት ፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የጸጥታ ሁኔታ ለዓለም ገበያ የሚቀርበውን የነዳጅ ዘይት መጠን ይወስናል። ምን ይሄ ብቻ….የጸጥታ ሁኔታው የነዳጅ ዘይት ገበያ ላይ የሚያሳድረው ያለመረጋጋት መንፈስም የነዳጅ ዘይት ዋጋ መጨመር ላይ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። በአጠቃላይ የዓለም የነዳጅ ዘይት ዋጋ እንደ እብድ ያደርገዋል - የቃጢፍ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ በደቂቃዎች ወደ ሁለት ዶላር ጭማሪነት መመንዘሩ አይነት። (ይህ ጽሑፍ ለሕትመት ሲበቃ ሁኔታዎች የተለዩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ልብ ይሏል)። እስቲ አሁን ደግሞ በፋብሪካዎቻችን ከታኘከ ሸንኮር አገዳ ተገኝቶ በመኪኖቻችን እየተጠጣ ስላለው የነዳጅ አረቄ(ethanol) ድብልቅ እናንሳ።

የድብልቁ መጠን ቤንዚን 95 ፐርሰንት ነዳጅ አረቄ ደግሞ 5 ፐርሰንት ስለሆነ ድብልቁ ኢ-አምስት (E-5) ተብሎ ይጠራል። በቤንዚን የሚነዱት መኪኖች የሞተር ዲዛይን ለውጥ ሳያስፈልጋቸው እንዲነዱ የሚያስችላቸው ይህ የኢ-አምስት ድብልቅ በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ ከዋለ እነሆ ሁለት ዓመታት አለፉት።
ካለንበት ከመጋቢት ወር ጀምሮ ደግሞ የነዳጅ አረቄ ድርሻ ወደ 10 ፐርሰንት አድጎ የኢ-አሥር (E-10) ድብልቅ በአዲስ አበባና አካባቢዋ በሚገኙ ነዳጅ ማደያዎች ለገበያ እየቀረበ ይገኛል። ላለፉት 13 ዓመታት በፊንጫ ስኳር ፋብሪካ በዓመት ሲመረት የነበረው 8 ሚሊዮን ሊትር የነዳጅ አረቄ አደበላቆ የሚሸጥ ማደያ ባለመገኘቱና ቀደም ብለው ተስፋ የተደረገባቸው ጅምር ውሎችም ወደ ስምምነት ባለማምራታቸው መጀመሪያ እንዲሁ በከንቱ እየተቃጠለ የነበረ ሲሆን ቀጥለው ለነበሩት አራት ዓመታት ደግሞ ወደ ውጪ ሲላክ ቆይቶ ነበር። ባለፉት 2 ዓመታት ደግሞ 5 ፐርሰንት በማደባለቅ ጥቅም ላይ ይውል የነበረው የሱዳን ኩባንያ በሆነው ናይል ፔትሮልየም ሱልልታ በሚገኘው ማደባለቂያው እያደባለቀ በማከፋፈሉ ነበር።  የነዳጅ አረቄውን  ድርሻ እ.ኤ.አ. 2012 ወደ 10 ፐርሰንት፤ በ2013 ወደ 15 ፐርሰንት፤ በ2014 ወደ 20 ፐርሰንት  እና በ2015 ደግሞ ወደ 25 ፐርሰንት ለማሳደግ እቅድ ተይዞ  ነበር። አሁን የተጀመረው የ10 ፐርሰንት ድብልቅ ከታቀደለት በወራት ቀድሞ መተግበሩ ነውና ደስ ይላል። በመተሐራ የተደረገው የማስፋፋት ሥራን ተከትሎ እስከ 10.5 ሚልዮን ሊትር ነዳጅ አረቄ  ወደ ገበያው መጨመር የሚችል አዲስ አቅም ነው ወደ ኢ-አሥር የተደረገውን ሽግግር እውን ያደረገው።
ነዳጅ አረቄ በኢትዮጵያ የሚመረተው ከስኳር ፋብሪካ ከሚገኘው “ሞላሰስ” ከተባለ ተረፈ ምርት ሲሆን ለረጅም አመታት አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩት የመተሐራና የወንጂ ስኳር ፋብሪካዎች ፊንጫ እንዳለው አይነት ሞላሰስን ወደ ነዳጅ አረቄ የሚቀይር ክፍል አልነበራቸውም። 
ኢትዮጵያ አገር ውስጥ የምታመርተውን ነዳጅ አረቄ ከውጪ ከምታስመጣው ቤንዚን ጋር አደባልቃ መጠቀሟ ምጣኔ ሀብታዊና የአካባቢ ጥበቃ ጠቀሜታዎች አሉት።

ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታው
እንደሚታወቀው ሀገራችን የነዳጅ ዘይት የምታስገባው ከውጪ አገር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በሚጠይቅ ግዢ ነው። ከአጠቃላይ የውጭ ንግድ ገቢያችን ወደ 90 ፐርሰንት የሚጠጋው የሚውለው ለትራንስፖት ለፋብሪካዎችና ለቤት ፍጆታ የሚሆን የነዳጅ ዘይትና ሌሎች የፔትሮሊየም ውጤቶችን ከውጪ ለማስገባት ነው። ስለዚህ ለትራንስፖርት የሚውለውን ቤንዚን ድርሻ ወስደን ስናየው መኪኖቻችን ይወስዱት ከነበረው 10 ፐርሰንቱ በራሳችን አገር በተመረተ ነዳጅ አረቄ መተካቱ ለቤንዚን የምናወጣውን የውጪ ምንዛሪ ይቀንስልናል። በተጨማሪም ትክክለኛ ዋጋ ከተተመነ ባለመኪኖች የሚገዙት የድብቅሉ ዋጋ በሊትር ላይም ቅናሽ ማምጣት ይችላል። እርግጥ የዚህ የዋጋ ቅናሽ መጠንና ጥቅም-አዘል ትርጉም የሚወሰነው ቀሪው 90 ፐርሰንት ቤንዚን በዓለም ገበያ ያለው ዋጋ፤ አገራችን አንድ ሊትር ነዳጅ አረቄ ለማምረት የሚያስፈልገው ወጪ እንዲሁም በነዳጅ አረቄና በቤንዚን ተሸካሚነት  የምናገኘው መኪና ለመንዳት የሚውለው የኃይል መጠን ልዩነት ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነው። 
ሌላው የምጣኔ ሀብት ጠቀሜታ በሸንኮር አገዳው ልማትም ሆነ በፋብሪካው እንዲሁም በማደባለቂያው ዙሪያ አነሰም በዛም የሚከፈተው አዲስ የሥራ እድል ነው።
  
 የአካባቢ ጥበቃ ጠቀሜታው
የአካባቢ ብክለትን ከመቀነስ አንጻር የከባቢ አየርን ሙቀት በመጨመርና የአየር ንብረትን በመለወጥ ዋነኛ በካይ የሆኑት ጋዞች ልቀት መጠንና አይነት እንደምንጠቀመው የነዳጅ አይነት ይለያያል።  ከሁሉም የባሰው የድንጋይ ከሰል ሲሆን ከዛ የተሻለው የነዳጅ ዘይት ከዛ ደግሞ የተፈጥሮ ጋዝ ነው።  ነዳጅ አረቄ ደግሞ ከነዚህ ሁሉ የበለጠና የተሻለ ነው። እርግጥ የበለጠና የተሻለ ነው ሲባል እንደተመረተበት ሁኔታ ይለያያል። ለምሳሌ እንደ አሜሪካ ባሉ አገሮች ከበቆሎ የሚመረተው ነዳጅ አረቄ ከ”ልደት” እስከ “ሞት” ሙሉ ታሪኩን ከተመለከትነው ከነዳጅ ዘይት ባልተናነሰ ከባቢ አየርን የሚበክል መሆኑ ሲታወቅ እንደ ብራዚል ባሉት አገሮች ከሸንኮራ አገዳ የሚመረተው ነዳጅ አረቄ ደግሞ የብክለት መጠኑ በጣም አነስተኛ ነው። ኢትዮጵያም የነዳጅ አረቄዋን የምታመርተው ከሸንኮር አገዳ ስለሆነ ከቤንዚን ጋር መደባለቅዋ ለአካባቢ ጥበቃ የሚኖረው ጠቀሜታ የሚናቅ አይደለም።
የነዳጅ አረቄን ሙሉ በሙሉ ለመኪኖች ማሽከርከሪያነት ጥቅም ላይ በማዋል ሲሆን 100 ቢያንስ ግን 50 ዓመታት የሚደርስ ልምድ ያላት አገር ብራዚል ነች። የስኳር ፋብሪካዎችዋ የስኳር ዋጋ ሲወደድና የነዳጅ ዘይት ዋጋ ሲቀንስ ስኳር እንዲያመርቱ፤ ስኳር ሲረክስና የነዳጅ ዘይት ሲወደድ ደግሞ ነዳጅ አረቄ እንዲያመርቱ ከማድረጓም በላይ አስፈላጊ ሲሆን ሙሉ በሙሉ በነዳጅ አረቄ  መነዳት የሚችሉ መኪኖችን በራሷ አገር እንዲመረቱ ያደረገች አገር ነች— ብራዚል።
በአጠቃላይ በአገራችን እየተደረገ ያለውን ነዳጅ አረቄን ከቤንዚን ጋር አደበላልቆ የመጠቀም ሥራው የሚደገፍ ሲሆን ሥራው በአገር ደረጃ የሚያስገኘው ጠቀሜታ የጎላ እንዲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በአጭርና በረጅም ጊዜ የሚያደርሰው ጉዳት ደግሞ የቀነሰ እንዲሆን ከአሁኑ መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎች እንዳሉ ማስገንዘብ ያስፈልጋል። አስፈጻሚው የመንግሥት አካል ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ከምላቸው ጥንቃቄዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል- 
1ኛ) ለሸንኮራ አገዳው ልማት ከሚያስፈልገው መጠነ ብዙ ውሃ ጋር በተያያዘ ልማቱ በየሚካሄድባቸው አጥቢያዎች የወደፊት የመጠጥና የሌላ ውሃ አቅርቦት ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ከጥናት ከማድረግ ጀምሮ ውኃ ቆጣቢ የመስኖ አጠቃቀምና ሌሎች መፍትሄ የሚያመጡ አሠራሮችን መዘርጋት ያስፈልጋል።  
2ኛ) አሁንም ከመስኖው ጋር በተያያዘ በረጅም ጊዜ ሊመጣ የሚችለው የአካባቢው አፈር የጨው መጠን መጨመር እንዳይከተልና ቦታው “እንዳይመክን” አስፈላጊው ሁሉ መደረግ አለበት። 
3ኛ) ለሸንኮራ አገዳው ልማት ተብሎ የሚጨፈጨፍ ደን እንዳይኖር ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።
4ኛ) በተቻለ መጠን ለምግብ ሰብል ሊውል የሚችል መሬትን የማይነካ እንዲሆን መደረግ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። 
5ኛ) እንዲሁም ከልማቱ ጋር በተያያዘ የሚደርስ መፈናቀል የሚያስከትላቸው ማኅበራዊ ቀውሶች እንዳይኖሩ ቢያንስ ግን በእጅጉ ያነሱና አማራጭ መፍትሔ የተበጀላቸው እንዲሆኑ መደረግ አለበት።
6ኛ) ከፋብሪካዎችም የሚወጡት ዝቃጮች የአካባቢውን ውሃም ይሁን ሌላ የተፈጥሮ ሀብት የሚበክሉ እንዳይሆኑ ተመጣጣኝ የጥንቃቄ እርምጃ መወሰድ አለበት። ፋብሪካዎቹም የአገዳውን እኛኪ መልሶ በመጠቀም ኡደት ውስጥ በማሳለፍ የኤሌክትሪክ፣ የሙቅ ውሃና እንፋሎት ፍላጎታቸውን አሟልተው የተረፈውን የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ መብራት ኃይል ማሰራጫ የሚሸጡበት አደረጃጃት መበጀት አለበት— ስለሚቻል።
---------------
መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ।ም. አዲስ አበባ ላይ ታትሞ የወጣው “አዲስ ጉዳይ” መጽሔት ላይ መደበኛው “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምድ ላይ ለወጣው ጽሁፍ መነሻ የሆነ:: www.akababi.org

No comments: