Tuesday, March 15, 2011

እስካሁን ከመሬት በታች ያላገኘነውን ከመሬት በላይ ለማግኘት - በእንተ ባዮ ዲዝል

(ጌታቸው አሰፋ )ባዮ ዲዝል እንደ መደበኛው ዲዝል ከድፍድፍ ነዳጅ ዘይት የሚገኝ ሳይሆን ከእጽዋትና ከእንስሳት ተዋጽኦ (ዘይትና ሞራ) የሚመረት የዲዝል አይነት ነው። ለባለ ዲዝል ሞተር መኪኖችና ለዲዝል ጀነሬተሮች እንዲሁም ለመሳሰሉት የመገልገያ እቃዎች ይውላል።
አገራችን በ2003 ዓ.ም. የበጀት ዓመት በአጠቃላይ የነዳጅ ዘይት ውጤቶችን ከውጪ ወደ አገር ቤት ለማስገባት 23.60 ቢልዮን ብር ያስፈልጋታል። ይህም ዲዝልን ጨምሮ ከ2.2 ሚልዮን ቶን በላይ ነዳጅን ለማስገባት የሚውል ነው።ይህም ወጪ ከአጠቃላይ የአገሪቱ የዘንድሮ 72.2 ቢልዮን በጀት ወደ 32 ፐርሰንት የሚሆነውን ይሸፍናል።
ከውጪ የሚገባው ማንኛውም ምርት በአገር ውስጥ ምርት መተካት በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉና የባሕር በር በሌላቸው አገሮች ጠቀሜታው እጅግ የጎላ ነው። ይልቁንም በየቀኑ ከሚጨምረው የዓለም ነዳጅ ዋጋ አንጻር የነዳጅ ዘይትን በአገር ቤት ምርት መተካት መቻል ለአገራችን የሚኖረው አዎንታዊ አንድምታ በርካታ ነው።

ይሁንና እንደማንኛውም ነገር ሁሉ ከውጪ የሚገባውን አገር ቤት በሚመረተው የመተካቱ ሥራ አዎንታዊ ጎኑን ለማጉላት ከፓሊሲ ጀምሮ እስከ ትግበራ የምርና ሁሉ አቀፍ ጥቅምና ጉዳትን ያሰላና ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ አካሄድ ያስፈልጋል።
ለዛሬ ከውጪ የሚገባውን ዲዝል ከመተካት ጋር በተያያዘ ያለውን እንቅስቃሴና አካሄድ እንመለከታለን።
ባዮ-ዲዝል በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ከጃትሮፋ (በአንዳንድ ቦታ አይደርቄ ወይም በሌላ ቦታ ደግሞ የድንበር ሽማግሌ ተብሎ ይታወቃል)፤ ከጉሎ ወይም ከፓልም ዛፍ ሊመረት ይችላል። ከሦስቱም ብዙ የሚነገርለት ግን ጃትሮፋ ሲሆን ከዛም ጉሎ ነው። የፓልም ዘይትም በኢትዮጵያ የተወሰኑ አካባቢዎች ሊለማ የሚችል ነገር ነው። በሌሎች አገሮች በተለይ በበለጸጉት አገሮች ሌሎችም የቅባት እህሎች ለዚህ ጥቅም እየዋሉ ይገኛሉ። እነዚህ የቅባት እህሎች ግን ለምግብም የሚውሉ ከመሆናቸው አንጻር የሰውን ሆድ ሙሉ በሙሉ ሞሙላት ባልቻሉት እንደኛ ባሉ አገሮች ከሰው አፍ ወስዶ ወደ ሞተሮች አፍ መዶል ተገቢም ስላልሆነ እዚህ ላይ አናነሳውም። እንዲያውም በበለጸጉት አገሮችም ቢሆን ለምግብ የሚውልን ነገር ለመኪኖች ማድረግ እየሰፋ ከሄደ የዓለም ምግብ ዋጋን እያናረ ከፍተኛ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ቀውሶችን እያስከተለ እንደሚሄድ ከጥንድ ዓመታት በፊት ያያነው ነገር ነው።
ጃትሮፋ ዲዝል ከማምረት አንጻር ያለው ጥቅም ሳይታወቅ ከረጅም ጊዜ በፊት በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች እንደ ለምለም አጥር ሲያገለግል ቆይቷል። ጉሎ በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ ለምጣድ ማሰሻነት ጥቅም ሲውል የነበረ እና እየዋለ ያለ ነው። በእንግዝሊኛ Castor Seed ተብሎ የሚጠራው ነው - ጉሎ።
ወደ ሰባ የሚጠጉ ባለሃብቶች ጃትሮፋን በማልማት ሥራ ላይ ለመሰማራት ፈቃድ ወስደዋል ተብሏል። ከነዚሁ ወደ አሥራ አምስት የሚሆኑት ደግሞ ባለሀብቶች በደቡብ ኢትዮጵያ፤ በአማራ፤ በኦሮሚያ፤ በትግራይ፤ በቤንሻንጉል ጉሙዝና በሶማሌ ክልሎች ውስጥ በመሥራት ላይ እንደሚገኙ ይነገራል። ከነዚህ መካከል ከእንግሊዝ፤ ከአሜሪካ፤ ከጀርመን ከእስራኤልና ከጣልያን የመጡት እነ Sun BioFuel ፤Becco Biofuels ፤ Hovev Agriculture Ltd ፤Flora Ecopower ፤ Global Energy እና Fri El Green Power ኩባንያዎች ይገኙበታል።
በንድፈ ሃሳብ ደረጃ እንደ ብዙኃን መገናኛዎች ትንተና፤ እንደ ኩባንያዎች ማብራሪያና እንደ መንግሥታት መግለጫዎች ጃትሮፋ ብዙ ጥቅሞችን የሚሰጥ ተክል ነው - እንደ አፋቸው ያድርግልንና።
እንደነዚህ ምንጮች አባባል ከሆነ ጃትሮፋ ድርቅን የሚቋቋምና በፍጥነት የሚያድግ አንዴ ማፍራት ከጀመረ እስከ ሀምሳ አመት ድረስ በየዓመቱ ምርት ሊሰጥ የሚችል ነው። የዝናብ መጠናቸው ከ300-1000 ሚሊ ሜትር እና የሙቀት ልካቸው ከ20-28 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በሆኑ ደረቃማ ቦታዎች ላይ ይበቅላል። የአፈሩ የንጥረ ነገር መጠን ዝቅ ባለበት ለም ባልሆነ ቦታም ቢሆን ተተክሎ ለፍሬ የሚበቃ ተክል ነው። ጃትሮፋ የማይበላ የዘይት ምንጭ ሲሆን የዘይት መጠኑ ወደ 37 ፐርሰንት ይሆናል።
በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ፍሬ መስጠት የሚጀምር ከመሆኑም በላይ በአንዳንድ ቦታዎችም ላይ በዓመት ሁለቴ ሲያፈራ በሄክታር በዓመት ወደ 8 000 ኪሎ ግራም የሚጠጋ ምርት ይሰጣል። ከአንድ 10 ኪሎ ፍሬ ወደ 6 ሊትር ባዮ ዲዝል ይገኛል። ጃትሮፋ ከባዮዲዝል ሌላ ከምርቱም፤ ከተረፈ ምርቱም ማዳበሪያን ጨምሮ የተለያዩ ነገሮችን ማምረት ይቻላል።
ማኅበራዊ
የባዮ ዲዝል ልማት አዳዲስን ሥራ በስፋት የሚፈጠር አቅም አለው። የሚፈጠረው ሥራ ጥራትና ቋሚነት ወሳኝ ነው። የሠራተኞችን መብት ማክበር አንዱ ወሳኝ ነገር ነው። ለሠራተኞቹ ደመወዝ ለወራት ሳይከፋላቸው የቆየው Flora EcoPower የተባለው የጀርመን ኩባንያ አንዱ ምሳሌ ነው። ገበሬዎች ኩባንያ ሥራ ይሰጣችኋል ተብለው መደበና ሥራቸውን የሚተውበት መንገድ አለ። መጨረሻ ላይ ተስፋ የተደረገበት ነገር ተግባራዊ ሳይሆን ሲቀር ማኅበራዊ ቀውስ ያሳድራል። በቤተሰብ ደረጃ የበለጠ ገቢ ያስገኛል በሚል ሃሳብ መሬታቸውን ለጃትሮፋ ያደረጉ ገበሬዎች የተጠበቀው ምርትና ገቢም አለማስገኘቱ ብቻ ሳይሆን የሚያጠፉት ግዜ፡ ያልለመዱት ግብአት ለመግዛት የሚያወጡት ወጪና ከመሳሰሉት ጋር በተያያዘ የሚመጣው ችግር ገበሬዎቹ ለአዲስ ችግር እያጋለጣቸው ይገኛል። ገበሬው እያለማ ኩባንያው ምርቱን ይገዛል በሚል አሠራር የተጀመረው አካሄድ ባልተጠኑ ፍሬዎች ላይ ገበሬው የሚያወጣውን ወጪ ካወጣ በኋላ ካልተሳካለት ሸክሙ ገበሬው ላይ የሚጥል ስለሆነ ከባድ ነው።
ምጣኔ ሀብታዊ
ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ ሊመጣ የምችለው ኩባንያዎቹ ከሚያመጡት ገንዘብ ጀምሮ አሠራራቸውና ሽያጫቸው በትክክል የሚሄድ ከሆነ ነው።
ለምሳሌ የጀርመኑ Flora Eco Power ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ውጪ ሦስት ጊዜ ያህል የጃትሮፋ ዘይት ጫማቂ ልኮ ነበር። ኩባንያው ከባንክ የተበደረውን 15 ሚልዮን ብር መክፈል አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን አምና ሚያዝያ መጨረሻ ላይ በወጡት ዘገባዎች መሠረት የኩባንያው አመራሮች ለወራት ድምጻቸውን ማጥፋታቸው እና የጉሎ ዘይት ልማቱ መቋረጥ ቀላል የማይባል አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል።
የባድዮ ዲዝል ልማት በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅም የሚሰጠው ምርቱ እስከ ባዮ-ዲዝል ድረስ ያለው ሂደት አገር ውስጥ ጨርሶ ለአገር ውስጥ ጥቅም ሲውል ብቻ ነው። አሁን ያለው አሠራር ግን ኩባንያዎቹ ወይ ጥሬ ፍሬውን ወይም የተጨመቀውን ዘይት ወደ ውጪ የሚልኩበት አሠራር ነው። እስካሁን ራሱ የላኩ ወይም ለመላክ እቅድ ያላቸው ኩባንያዎች ናቸው ያሉት። በአፍሪካም በኢትዮጵያም ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ሲደረግ እንደነበረው ጥሬ እቃን ተጨማሪ እሴት ሳይሰጠው ወደውጪ መላክ ከባድና ያልተመጣጠነ የገቢ ክፍፍል የሚያስከትል መሆኑ ታይቷል። እነሆ ዛሬም ከ100 ዓመት በፊትም አፍሪካችን የጥሬዎች ጥሬ እቃን (ከተፈጥሮ እንደወረደ - በሰሞነኛው የአዲስ አበቤዎች አባባል ሙባረክ እንደሆነ -) ትልካለች።
ባዮዲዝል አምርተን በከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ የምናስገባውን ዲዝል የማይተካልን ከሆነ በረጅም ጊዜ የጎላ ችግር ይፈጥራል። ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ መንግሥት ማድረግ ሲገባው እስካሁን ያላደረገው ብቻ ሳይሆን ለማድረግም እቅድ ያልያዘበት ጠቃሚ ነገር አለ። ይኸውም ፍሬውን ወይም ጭማቂውን ወደ ባዮዲዝል የሚቀይር ቴክኖሎጂ ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፈሰስ ነው። መንግሥት በኩባንያዎች በገበሬዎችና በማኅበራት የሚመረተውን ፍሬ እየተቀበለ ጨምቆ ወደ ባዮ ዲዝል ቀይሮ ለአገር ውስጥ ፍጆታ ማዋል ካልቻለና በአንጻሩ የውጪ ኩባንያዎች በርካሽ የሰው ኃይል ያመረቱትን ጥሬ ፍሬ ወይም እንደዘበት የጨመቁትን ዘይት ብቻ ወደ ውጪ የሚልኩ ከሆነ ቴክኖሎጂ ዝውውርም የማያመጣ ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታው ያነሰ አካሄድ ስለሆነ እንደገና በእጅጉ ሊመረመር ይገባል። ሲሆን ሲሆን አሁን ያሉት የብረታ ብረት ማምረቻዎችን በዚህ ሥራ ላይ ቢሰማሩና የተወሰነውን እቃ በአገር ውስጥ ቢያመረቱት። ካልሆነም ቴክኖሎጂውን ከውጪም ቢሆን አስገብቶ ከላይ እንዳልኩት አገር ውስጥ አምርቶ አገር ውስጥ መጠቀም መጀመር አለበት። ሩዋንዳ በዚህ ላይ ለአገራችን ትምህርት ሊሆን የሚችል ሥራ እየሠራች ትገኛለች። እነሆም በትንሹ ማምረት የቻለችው ባዱ ዲዝል ተጥቅማ ከኪጋሊ ሩዋንዳ ወደ ቡጅምብራ ቡሩንዲ የሚደረግ የአውቶብስ ጉዞን በባዮዲዝል ሞክራ አሳይታለች። በገዛ አገራችን ያያነው ነዳጅ አረቄ(ethanol) የማደባለቅ የሁለት ዓመት ልምድም የሚነገረን ነገር ቢኖር ይኸው ነው። መንግሥት የዘገየውና ባዮ-ዲዝልን ከመደበኛ ዲዝል ጋር እየደባቁ ለመጠቀም ካቀደውና እስካሁን ከዘገየው እቅድ በላይ መሄድ አለበት።
አካባቢያዊ
Flora Eco Power ወደ 8,000 ሄክታር መሬት በፈዲሴ ከአራት ዓመት በፊት የጀመረ ሲሆን 80 ፐርሰንት የሚሆነው መሬቱ ከ40 ዓመት በፊት ከተቋቋመው የባቢሌ የዝኆኖች መነሐሪያ የሚጋራ መሆኑ አስደንጋጭ ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት ቢያንስ 23.3 ሚልዮን ሄክታር መሬት እንዳዘጋጀ ተናግሯል።
በተፈጥሮ ባለብዙ ዝርያ የነበረ ቦታን በአንድ ወጥ ዝርያ መተካት የአካባቢውን ተፈጥሮአዊ የመሸከም አቅምን የሚቀይር ይሆናል። በአንድ አካባቢ ያለው የብዝኃ ሕይወት መጠንና ጥንቅር በሽታን ከመከላከል ጀምሮ የንጥረ ነገር ሚዛንን መጠበቅና በአካባቢው የሚገኙ የተፈጥሮ የሕይወት መሠረቶች በረጅም ጊዜ መቀጠልና መፋፋት ላይ ተጽእኖ የሚያሳድር ነው። ስለዚህ በባዮዲዝል ልማት ብዝሀ ሕይወት እንዳይቀንስ እንዳይጠፋና እንዳይበረዝ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።
ከላይ እንደተገለጸው ጃትሮፋን በተመለከተ የሚፈልገው ውኃ መጠን አነስተኛ ነው ቢባልም Nature የተባለው በዓለማችን የታወቀው ሳይንሳዊ መጽሔት በ2007 እትሙ የምርቱ መጠንም በትክክል ያልተጠና፤ ጥሩ ምርት ለማግኘት የሚያስፈልጉት ግብአቶች ምን ምን እንደሆኑ ያልታወቀ፤ የትልልቅ የጃትሮፋ እርሻዎች በአካባቢ የሚያደርሱት ተጽእኖ በቅጡ ያልተጠና፤ የሚያስፈልገው የውኃ መጠን ምን ያህል እንደሆነ አሁንም ያልታወቀ መሆኑን ዘርዝሯል።
ይሄም በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ያለው በጎ ነገሩ ወደ ትግበራ ሲሻገር መሬት ላይ የሚኖረው ሁኔታ ከንደፈ ሃሳቡ ጋር ምን ያህል እንደሚቀራረብና እንደሚራራቅ በተለይ ምን ያህል ውሃ ያስፈልጓል? ምን ያህል ማዳበሪያ ይጠይቃል? ምን ያህል ምርታማ ይሆናል? የሚሉት ገና በቂ ሁኔታ ለምቶና ተመርቶ ስናየው የምንመለስበት ይሆናል። ለጊዜው ማየት የምንችላቸው ማስያዎች አልጠፉም። በወላይታ አካባቢ ለወትሮው ለሌላ ስብል ይውል ከነበረው የገበሬ መሬት ጭምር የተወሰነው ገበሬው ወደ ጉሎ ልማት እንዲቀይረው ይጠየቃል። በመደበኛ ሰብሎች ከሚያገኘው የበለጠ ገቢ እንደሚያገኝ ቃል ስለተገባለት አደረገው። በዚህ ቃል ውስጥ ከእስራኤላዊው ኩባንያ - Global Energy Ethiopia-እ ለአልሚ ገበሬዎች የተነገረው በሄክታር በዓመት ከ5000 እስከ 10000 ኪሎ ግራም ፍሬ ይገኝበታል ተብሎ ነው። ይህ ብቻ አይደለም በዓመት ሦስት ጊዜ ምርት እንደሚታፈስም ጭምር ተነግሮታል። እነሆ ገበሬው ከሚገኘው ምርት እንዴት ተጠቃሚ እንደሚሆን ተስፋ እያደረገ ቆየ። የተባለው ምርት ግን ሊገኝ አልቻለም። በአካባቢው በአማካይ ከ1000 ኪሎ ግራም በላይ ያመረተ ሰው አልተገኘም። ጥናቱን ያካሄደው የአፍሪካ የብዝሀ ሕይወት ኔት ወርክ (African Biodiversity Network) እንደሚለው በዓመት ሦስት ሊመረት ቀርቶ ሁለት ጊዜ እንኳን ያመረተ ገበሬ የለም - በቦታው። ችግሩ የመጣው ይህ ኩባንያም ሆነ ሌሎች እንዲሁም የመንግሥት አካላት የጎሎ ምርታማነት ሆነ የነጃትሮፋ ምርታማነት በተመለከተ የሚሰጡት መረጃም ሆነ የሚጠቅሱት አኃዝ በእስራኤል በቻይናና በህንድ የሙከራ ማሳዎች ላይ በተመሰከረለት አሠራርና በአመቺ ቦታ የተገኘውን ምርት መሠረት ያደረገው መሆኑ ነው። እንግዲህ ጎሎውም ሆነ ጃትሮፋው እያለ ያለው እዛ ሌላ እዚህ ሌላ መሆኑ ነው።
እንግልዛዊው Sun Biofuels የተባለው ኩባንያም በወላይታ የነበረው የ5 000 ሔክታር የጃትሮፋ ልማት በቦታው ለም አለመሆንና በውኃ እጥረት ምክንያት በቂ ምርት አለማግኘቱን ዋቢ በማድረግ ከሁለት ዓመት በፊት በማጫ ወላይታ የነበረውን ልማቱን ዘግቷል።
መንግሥት የዛሬ አራት ዓመት እጽዋት መሠረት ያደረገን ነዳጅ ለማልማት የሚሆን 23.3 ሚልዮን ሄክታር (ወደ 46.4 ሚልዮን ኳስ ሜዳዎች የሚያሰራ) አለኝ ብሎ ለዓለም አውጇል። ደግ ነገር ነው - አገራችንን ለመጥቀም ቀላል የማይባል ሚና ለሚጫወት ዘርፍ ማስፋፊያ የሚውል ነገር ነውና። ይሁንና ይህን ያህል ስፋት ስላለው መሬት ዘርዘር ያለ መረጃ በመንግሥት ደራጃ እንኳን የለም። ለምሳሌ ምን ዓይነት መሬት ነው አኃዙ ውስጥ የተካተተው? ምን ያህሉ ደን አለው? ካለውስ ምን አይነት ደን? ምን ያህሉ ለም ነው? ምን ያህሉ የብሔራዊ ፓርክ ክልል መሬትን ይጋራል? ምንም የተተነተነ መረጃ የለም - እስካሁን።
የባዮዲዝል ልማቱ በመረጃና በጥናት ሲመሠረት ብቻ ነው በጎ ጎኑ አመዝኖ አገራችን ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ የሚያደርገው። ለዚህ ደግሞ ገበሬዎቻችንን ችግር ውስጥ በማይከት መልኩ በራሳችን ሰዎች በየትኛው ቦታ ምን ቢመረት ምን ያህል ምርታማ ይሆናል ከሚለው ጀምሮ እያጠናንና እየተገበርን መሄድ አለብን። ያን ጊዜ ምናልባትም እስካሁን ከመሬት በታች ያላገኘነውን ነዳጅ ከመሬት በላይ ማግኘት እንችል ይሆናል።
_____________________
“አዲስ ጉዳይ” መጽሔት ላይ የካቲት 26 ቀን 2003 ዓ.ም. እትም “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምድ ላይ የወጣ
____________________
ጸሐፊው በካናዳ የዩኒቨርስቲ ኦፍ ካልጋሪ የኢንቫይሮንመንታል ዲዛይን ተባባሪ ፕሮፌሰር፤ የአቴና ላይፍ ሳይክል አሰስመንት ቼር፤የኢንስቲትዩት ፎር ሳስተይነብል ኢነርጂ ኢንቫይሮንመንት ኤንድ ኤኮኖሚ ፌለው፤የባዮ ኤነርጂ ኢንተርናሽናል ማጋዚን ኤዲተር፤የኢንደስትሪስ ፎር አፍሪካ ፋውንዴሽን አባል፤ በኢትዮጵያ የአካባቢ ጉዳዮችና እና የኃይል አቅርቦትና ፍጆታ ጉዳዮች ላይ የረጅም ጊዜ ጸሐፊ ናቸው www.akababi.org

1 comment:

Anonymous said...

A few things. 1. This was a very informative article and has brought my attention to an issue that I didn't even know existed until now. 2. If I could write this eloquently in Amharic, I would be significantly happier.

Thanks a lot Getachew!