Friday, September 2, 2011

የብክለት ወጥ


(ጌታቸው አሰፋ) አዲስ አበባ የመጀመሪያዋን መኪና ከዛሬ 104 ዓመት በፊት አስተናገደች - ታህሳስ 22 1889 ዓ.ም.። የታርጋ ቁጥሯ D3130 ነበር ተብሏል። አስር ሚልዮን ሕዝብ ያስተዳድሩ የነበሩት አጼ ምኒልክ ቴሌፎንን ወደ አገራችን ባስገቡ ከአራት ዓመት በኋላ ያስገቧት ነች። መጀመሪያ አለማማጃቸው፤ ከዛም እሳቸው፤ ከዛም ሾፌራቸው የነበረው ህንዳዊው ኤዳልጂ የነዷት መኪና ታወጣው የነበረ በካይ - ለምሳሌ ካርቦን-ዳይ-ኦክሳይድ - የአዲስ አበባን ንጹህ አየር በመቀላቀል አሃዱ ያለ አውቶሞቢላዊ በካይ ሆነ - የአገራችን የአካባቢ ብክለት ታሪክ ቅምሻ
[ፎቶ 1 - አጼ ምኒልክና መኪና አለማማጃቸው ] [ፎቶ 2 - አጼ ምኒልክ ሲስቁ]። ደግነቱ ከመኪናቸው ይወጣ የነበረው ካርቦን-ዳይ-ኦክሳይድ(እሱን ብቻ ካየን) በስፋት ካስተከሏቸው ባህር ዛፎች መካከል በጥቂቶቹ ብቻ ወደ ውስጥ ተተንፍሶ ወደ ቅጠልነትና ግንድነት ሊቀየር የሚችል መጠን ነበረው። 



መኪናዋ በገባች ሀያ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ከአራት መቶ ሺህ  የማይበልጥ ህዝብ በነበራት አዲስ አበባ መንገዶች ከአህዮችና በቅሎዎች ጋር የሚጋፉ መኪኖች ይታዩ ነበር። ከለገሃር ባቡር ጣቢያ ወደ ሆቴሉ በፎርድ መኪና እንደሄደ አንድ ስዊዲናዊ በ1926 እ.አ.አ በጻፈው መጽሐፉ ላይ አስፍሯል። 
የአንድ መኪና ሙሉ ዑደታዊ ተጽእኖውን እንመልከት ካልን እያንዳንዱ የመኪናው አካል - አሁን ወደ አስራ አምስት ሺህ ይሆናል-  ሲመረት፤ሲጓጓዝና ሲገጣጠም የፈጀውን የተፈጥሮ ሀብትና ወደ አየር፤ውሃና አፈር የለቀቀውን በካይ እንዲሁም ሲነዳ የሚጠቀምበት ነዳጅ ሲመረትና ሲጓጓዝ የፈጠረው ብክለት ሁሉ ማየት ግድ ሊል ነው(ለዝርዝሩ፡ ‘ታሪከ-ቁስ’  - የግንቦት ሀያ አዲስ ጉዳይ እትም)። የዛሬ ትኩረቴ በአዲስ አበባ አሁን ያሉት ወደ ሁለት መቶ ሺህ የሚጠጉ መኪኖች በሚፈጠሩት ልቀታዊ ብክለት ላይ ነው። ሁለት መቶ ሺህ የኔ ግምት ነው። ያገኘሁት የመንግሥት መረጃ የዛሬ ስድስት ዓመት በአገሪቱ በጠቅላላ ያለው ቁጥር ከኔ ቁጥር በሃምሳ ሺህ ያንሳል።
ከመኪኖች ጭስ ማውጫ የሚለቀቁ በካዮች በፀሐይ ብርሃንና በሌሎች ክስተቶች አማሳይነት ለሰው ልጆች ጤናና ለሌሎች ህያዋን ደህንነት ጠንቅ የሆነ የብክለት ወጥ ይወጠውጣሉ። 
በካይ ልቀቶች
ከተለያየ ምንጭ - መኪናን ጨምሮ - በቀጥታ የሚለቀቁት በካዮች ቀዳምያን በካዮች ተብለው ይታወቃሉ። ቀዳምያን በካዮች አየር ላይ ከተለቀቁ በኋላ እርስ በርሳቸውና ከአካባቢያቸው ጋር በሚፈጥሩት መስተጋብር የሚከሰቱት በካዮች ደግሞ ካልዓን በካዮች እንላቸዋለን። ዋናዎቹ መኪናዊ ልቀቶች  ካርቦን-ዳይ-ኦክሳይድ፤ ካርቦን-ሞኖ-ኦክሳይድ፤ ጠጣር ብናኞች፤ ሰልፈር-ኦክሳይዶች፤ናይትሮጅን-ኦክሳይዶች፤እና ተናኝ ኦርጋኒክ ውህዶች ሲሆኑ በካልዕ በካይነት ደግሞ እነ ኦዞን የመሳሰሉ ፀሐይ-ብርሃን-ወለድ ኬሚካልያዊ ለብላቢዎች ይገኛሉ። 
ካርቦን-አዘል የሆነ ነዳጅ ሙሉ በሙሉ ቢቀጣጠል - አይቀጣጠልም እንጂ - የሚፈጠረው ካርቦን-ዳይ-ኦክሳይድና ውሃ ነው።  ካርቦን-ዳይ-ኦክሳይድ የአየር ንብረት ለውጥን በማስከተልና በማባባስ ይታወቃል(ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ)።
ነዳጁ ሙሉ በሙሉ አለመቀጣጠሉን ተከትሎ ካርቦን-ሞኖ-ኦክሳይድና ጠጣር ብናኞች ይፈጠራሉ። 
ካርቦን-ሞኖ-ኦክሳይድ በተፈጥሮው ቀለም-የለሽ፤ ሽታ-አልባ፤ ጣዕም-የለሽ  መርዛማ ጋዝ ነው። በመሆኑም “አየሁት፤ሸሸተኝ፤ምላሴ ላይ እንትን እንትን አለኝ” ብለን በአንድ ቦታ መኖር አለመኖሩን የምናውቀው አይነት አይደለም (ለዚህም ነው ማታ በዝግ ቤት በቆሎ በከሰል ጠብሰው የበሉ ሰዎች በተኙበት ሞተው የሚገኙት)። ወደ ሳንባችን ከገባ በኋላ በሕይወት ለመኖር አስፈላጊ የሆነውን ኦክስጅንን ወደ ጎን በመግፋት ለወትሮው ኦክስጅንን በመሸከም ወደየሚፈለግበት ቦታ ሁሉ በሚያደርሰው ሆሞግሎቢን በተባለው የደም ክፍላችን ላይ በመፈናጠጥ ኦክስጅን በበቂ ሁኔታ እንዳይዳረስ አድርጎ ይገድላል። ምክንያት፡ ኦክስጅንና ካርቦን-ሞኖ-ኦክሳይድ አብረው ካሉም ሆሞግሎቢን ከኦክስጅን ይበልጥ ለካርቦን-ሞኖ-ኦክሳይድ ያለው ስበት ሁለት መቶ አስር ጊዜ ስለሚበልጥ።
ጠጣር ብናኞች ከጥላሸትና ከጥቁር ጭስ በተጨማሪ በዓይናችን የማናያቸው የተለያየ መጠን ያላቸው አስም፤ የሳንባ ካንሰር፤የልብና የደም ቧንቧ በሽታዎችን የሚያስከትሉ እስከ ሞትም የሚያደርሱ ብናኞች ናቸው።  አገራችን የዛሬ ስምንት ዓመት እርሳስ(ሌድ)-አዘል ጋዞሊን መጠቀም ከማቆሟ በፊት የእርሳስ (ሌድ) በካይ ልቀትም አሳሳቢ ነበር - በህጻናትና አዋቂዎች ላይ ከሚያደርሰው አይነተ-ብዙ ጠንቅ አኳያ።
ከነዳጁ ይዘት ጋር ተያይዞ ከሚፈጠሩት በካዮች መካከል ሰልፈር(ዲኝ)-ኦክሳይዶች ተጠቃሽ ናቸው። የነዳጁ የዲኝ መጠን ዝቅተኛና ከፍተኛ መሆን የልቀቱን መጠን ይወስናል። ሰልፈር-ኦክሳይዶች ከጠጣር ብናኞች ጋር በመሆን መርዛማ ጭጋግን ይፈጥራሉ። በለንደን በ1952 እ.አ.አ. በሦስት ቀን ውስጥ የዚህ አይነት መርዛማ ጭጋግ ለአራት ሺህ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኖ ነበር። አሲዳማ ዝናብንም ይፈጥራል። የእጽዋት የምግብ ማምረቻ የሆነውን ክሎሮፊንን ያወድማል፤ እጽዋቱ የተገነቡበትንም ቲሹ ያፈራርሳል (እስቲ ትራፊክ መብራት አካባቢ ያሉ ደሴቶች ላይ ያሉትን እጽዋት ተመልከቱ)። በሕንጻዎችና መሠረተ-ልማቶችም ላይ እንዲሁ ጉዳት ያደርሳል። እጽዋትና ደኖች መጎዳት የሚጀምሩት የብክለቱ መጠን ሰዎችን መጉዳት ከሚችልበት መጠን እጅግ ባነሰ ደረጃ ላይም እያለ ነው።
ካርቦን-ዳይ-ኦክሳይድ፤ ካርቦን-ሞኖ-ኦክሳይድ፤ ጠጣር ብናኞችና ሰልፈር-ኦክሳይዶች የሚፈጠሩት በነዳጅ ይዘት ጋር በተያያዘ ነው። ናይትሮጅን-ኦክሳይዶች የሚፈጠሩት ግን በአየር ውስጥ ባለው ናይትሮጅን ምክንያት ነው። የከባቢ አየር ሰባ ስምንት ፐርሰንት ያህሉ ናይትሮጅን፤ ሀያ አንድ ፐርሰንቱ ደግሞ ኦክስጅን እንደሆነ ይታወቃል። ናይትሮጅንና ኦክስጅን አየር ውስጥ አትድረስብኝ አልደርስብህም ተባብለው (መብረቅ ሲያጋጫቸው ካልሆነ በስተቀር) የኖሩትን ያህል የመኪናው ማቀጣጠያ ውስጥ ሲገናኙ ነዳጁ ሲቀጣጠል በሚፈጠረው ከፍተኛ ሙቀት አቃጣሪነት ተደራርሰው ሲያበቁ ናይትሮጅን-ኦክሳይዶችን ይፈጥራሉ። 
አዳዲስ ስሉጥ የመኪና ሞተሮች ሳይቀሩ የነዳጁን መቀጣጠል ሙሉ ወደሚባል ደረጃ ቢያደርሱት እንኳን የካርቦን-ሞኖ-ኦክሳይድንን መጠን ይቀንሱታል እንጂ የናይትሮጅን-ኦክሳይዶችን መጠን አይቀንሱም። ናይትሮጅን-ኦክሳይዶች በራሳቸው ለሰው ልጅ ጤና ብሎም ለእንስሳትና ለእጽዋት ደህንነት ጎጂዎች ናቸው። የአሲዳማ ዝናብ ከሳቾችም ናቸው። ከተናኝ-ኦርጋኒክ-ውህዶች ጋር በመሆንም የሚያስከትሉት ሌላ መዘዝም አለ። ተናኝ-ኦርጋኒክ-ውህዶች ካንሰር ሊያመጡ የሚችሉ ካልተቃጠለ ነዳጅ የሚገኙ የተናኝ ኬሚካሎች ስብስቦች ናቸው። ተናኝ-ኦርጋኒክ-ውህዶች ከናይትሮጅን-ኦክሳይዶች ጋር በመዋሃድም በፀሐይ ብርሃን አማሳይነት የሚወጠውጡት ክፉ የጋዝ ወጥ አለ። የዚህ የብክለት ወጥ ዋና አካል የሆነው ኦዞን የተባለው ጋዝ ነው። አንድ ራስ ፤ሁለት ራስ ሽንኩርት እንዲሉ ኦዞን አንድ ከግማሽ ራስ ኦክስጅን ነው። የኦዞን ክፋቱና ደግነቱ የሚያያዘው ከተገኘበት የከባቢ አየር ክፍል ጋር ነው። ከላይኛው ክፍል ባለው የከባቢ አየር ክፍል ማለትም ከአስር ኪሎ ሜትር በላይ ባለው ከሆነ አደገኛ የፀሐይ ጨረርን ስለሚከላከልልን “ደጉ ኦዞን” እንለዋለን። በታችኛው ክፍል ከኛ ጋር አብሮ ሲውል፤ ሲያድር ግን “ክፉው ኦዞን” ይሆናል። የሰው ልጅን (ለምሳሌ የመተንፈሻ አካላት ሕመምን በማስከተል)፤ እጽዋትንና ሰብሎችን፤ ቁሶችን(ለምሳሌ ከጎማ  የተሠሩትን)፡ቀለማትንና፤ ጨርቃ ጨርቅንም ሳይቀር ያጠቃል - ክፉው ለብላቢው ኦዞን። 
ምን ይደረግ? 
በአጠቃላይ መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ፤ የከባቢ አየር ሁኔታ ወዘተ የብክለት ወጡን መጠንና ጉዳት የማባባስ ሚና ይጫወታሉ። ለአዲስ አበባ የአየር ብክለት ደግሞ በዋና ተጠያቂነት እየጨመረ የመጣው የመኪና ብዛትና አሮጌነት (አማካይ እድሜያቸው እስከ ሀያ ዓመት ነው) ይጠቀሳሉ - የመንገዶች አነስተኛና መሆንና አመቺ ያለመሆን እንዳለ ሆኖ።
የፀሐይ ብርሃንና የትራፊክ ፍሰት በሚበረታባቸው ከተሞች (ለምሳሌ ታላቋ የሎስ አንጀለስ ከተማ) እና  ጊዜያት (ለምሳሌ በሥራ መግቢያ ሰዓት) የብክለት ወጡ መጠን ከፍ ይላል። ፍሰቱና ብርሃኑ ሲቀንስም እንዲሁ ብክለቱ ይቀንሳል። አዲስ አበባ በፀሐይ ብርሃን በኩል ለሌሎችም ትተርፋለች። በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓትም በከተማዋ የሚታየው የትራፊክ ፍሰት በካይ ወጡን ለማንተክተክ ከበቂ በላይ ነው። 
ለአዲስ አበባ አየር መበከል ምክንያት የሆነው የኅበረተሰብ ክፍል አነሰም በዛም በአንጻራዊነት የተሻለ ኑሮ የሚኖረው ነው ቢባል ያስኬዳል። በብክለቱ የበለጠ የሚጠቃው ደግም የሕክምና ወጪውን መሸፈን ቀርቶ ለዕለት ጉርሱ የሚሆን ገቢ የሌለው ወይም የሚያጥረው ወገን ነው - ኢፍትሃዊ ብክለት (ፍትሃዊ ብክለት የሚባል ነገር ባይኖርም)። 
መደረግ ያለበት፡ 
  • ወደ ሌድ-አልባ ነዳጅ የተደረገው ሽግግር ቀላል ያደረገው የሁለቱም አይነት ነዳጆች የዓለም ዋጋ አንድ ስለነበር፤ ከሌድ-አዘል ነዳጅ ጋር የተቆራኘ የራሳችን የነዳጅ ማጣሪያ ስላልነበረን፤ በክምችት የምንይዘው ነዳጅ መጠን ዝቅተኛ የነበረ መሆኑ ወዘተ ቢሆንም መንግሥትም ይህንን ጠቃሚ ውሳኔ ትኩረት ሰጥቶ መወሰኑ ጉልህ ሚና ነበረው።  አሁንም የሰልፈር መጠኑ ዝቅተኛ የሆነ ነዳጅ በማስገባት ወይም እንዲገባ በማድረግ አይተኬ ሚናውን መጫወት አለበት።
  • የልቀት መጠናቸው ከፍተኛ የሆኑ መኪኖች ላይ ተገቢውን ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት፤ በአንጻሩ የልቀት መጠናቸው ዝቅተኛ ለሆኑ መኪኖች ባለቤትነት የማትጊያ መርሐ-ግብሮችን መቅረጽ ያስፈልጋል።
  • ተከታታይና ቋሚ የአየር ጥራት ጥናትና ምርምር መርሐ-ግብሮችን መንደፍና መፈጸም። የበካይ ልቀቶችን መጠን በየወቅቱ ሲያስፈልግ በየሰዓቱ (ለምሳሌ ለኦዞን) መለካት እንዲሁም በአየር ላይ ያለው የብክለት መጠን በተመለከተ በየዓመቱ መረጃን መሰብሰብ የስጋት ደወሎችን ለማሰማት፤ ተመጣጣኝ የማሻሻያ እርምጃዎችን ለመቅረጽና ውጤታማነታቸውን ለመከታተል አስቻይ ሁኔታን ይፈጥራል። ሌድ-አዘል ነዳጅ መጠቀም ካቆምን በኋላም እንኳ የረጅም-ጊዜ ጠንቅን ከማጥናት አንጻር በአዲስ አበባና በሌሎች ቦታዎች በአስፋልት ዳርና ዳር ባለው አፈር ውስጥና እንዲሁም በሕጻናት የወተት ጥርስ ውስጥ ያለው የሌድ መጠን ለማወቅ የተደረጉት ጥናቶች ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው።   
  • መኪና-ቀነስ የከተማ ልማት ንድፍና ትግበራ እንዲሁም ብዙ ሰዎች በመኪና ከመጓዝ በጅምላ መጓዝን እንዲመርጡ በሚያደርግ መልኩ የጅምላ መጓጓዣ መሠረተ ልማትን መዘርጋትና ማስፋፋት እንዲሁም ምቾት ያላቸው የሕዝብ መመላለሻ አውቶብሶችንና የከተማ ቀላል ባቡሮችን በብዛትና በጥራትና ማሰማራት ወሳኝ ነው። 
  • የማስተማርና የንቃተ-ህሊና ማዳበሪያ መርሐ-ግብሮችን መቅረጽ አላስፈላጊ የመኪና አጠቃቀምን ለመቀነስ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
ለጤናና ለአካባቢ ጥበቃ ወደፊት ለማውጣት የምንገደደውን ከፍተኛ ወጪ ከመቀነስ አንጻር ዛሬውኑ ከላይ የተጠቀሱትን ጉዳዮች በዝቅተኛ ወጪ (በንጽጽር) በትኩረትና ትጋት ማስፈጸም ብልህነት ነው። 
====================
ነሐሴ 14  ቀን 2003 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

2 comments:

Anonymous said...

how i can get you and write some valuable messages. I am MSc student "climate chnage and Development" please i need you to share ideas i mean Dr Getachew Assefa

Akababi said...

Hi.... please e-mail me getachew at akababi dot org. written this way to avoid spamming...