Thursday, October 13, 2011

በዓል - ከጓዳ እስከ አካባቢ

(ጌታቸው አሰፋ) እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ። ከአንድ ሁለት ሳምንት በፊት የሸገር ራዲዮ “ዳጉ አዲስ”ን እያዳመጥኩ ነበር- በኢንተርኔት የቀጥታ ስርጭት። ወንዶች ሴቶችን በቤት ሥራ ማገዝ አለባቸው ወይስ የለባቸውም በሚል ርዕስ ስር ከተለያዩ ወጣቶች ጋር ቃል ምልልስ ያደርጋሉ - ዳጉዎች። ሁለት ወንድ ወጣቶች ቤታቸው ውስጥ ሽሮ ወጥ ሲሠሩ ከፕሮግራሙ አዘጋጆች አንዱ ተገኝቶ አሠራራቸውን በድምጽ ለራዲዮ አድማጮች ያስተላልፋል። ልጆቹና ጋዜጠኛው እያወሩ ከጀርባቸው አንድ አውራ ዶሮ ድምጹን ከፍ አድርጎ አሰምቶ ይጮሃል። የአሥር ወር ልጄን አየሁት። እየጮኸ ያለው አውራ ዶሮ መሆኑን ሊያውቅ እንደማይችል አሰብኩ። የእሱ አስተዳደግ በአካል ከሚታይ አውራ ዶሮ ጋር ያለው ርቀት የኔ አስተዳደግ ከአውራ ዶሮ ጋር ከነበረው ቁርኝት ጋር ያለው ልዩነት እያስደመመኝ ዓመት በዓል በመጣ ቁጥር ስለማስበው ነገር ማብሰልሰል ጀመርኩ - ስለ ዶሮ ወጥ።

ዶሮ ወጥ
ዶሮ ወጥ በብዙ ሰው ዘንድ የተወደደ ነው። አሁንማ ዶሮ ሁለት ጊዜ ነው የተወደደው - በጣዕም ከድሮም የሚወደደውን ያህል በዋጋም በጣም ተወደደ ። የዋጋ ጭማሪው ተወደደ ሳይሆን “ተጠላ” በሚያሰኝ ደረጃ ከፍ ያለ ቢሆንም - መቼም አማርኛው ነውና አሁንም ተወደደ እንበለው። ስለ ጣዕሙም ይሁን ስለ ዋጋው ድፍን ሰብአ-አቢሲንያ የሚያውቀው ነገር ስለሆነ እዚህ ላይ ላቁመው። ዛሬ የተነሳሁት የዶሮ ወጥን ከሌላ ማእዘን ለማየት ነው። ይህን እይታ ዶሮ ርካሽ በነበረበት ወቅት መጻፍ ብችል ጥሩ ነበር። ምክንያቱም ሰው ወዶ ፈቅዶ እንዲለወጥ በሚያስችል ወቅት መጻፍና እንደ ቀበሮ ‘እንዲያውም ስለማይጣፍጥ ትቼዋለሁ’ በሚያሰኝ ወቅት መጻፍ ስለሚለያይ።
በአገራችን በዶሮና በዶሮ ወጥ መካከል ያለው ርቀት ላጋንነው ካልኩ በ”አልቦ” እና በ”ቦ” ያለው ርቀት ሊሆንብኝ ይዳዳል- (መጽሐፍ ‘እም ሀበ አልቦ ሀበ ቦ” - ካለመኖር ወደ መኖር- እንዲል)።
ርቀቱን የምገልጸው በሚፈጀው ጊዜ፡ በሚፈጀው የሰው ጉልበት፤ በሚፈጀው ኃይል፤ በሚፈጀው ሽንኩርት፤ በሚፈጀው በርበሬ፤ በሚፈጀው ቅቤ ነው- አሁን ደግሞ በሚፈጀው ብር ተብሎ ይጨመርበት።
ብዙ ጊዜ ዛፎች የሚጨፈጨፉት በሦስት ምክንያት ነው። ለማገዶ፤ ለቤት መሥሪያ የሚሆን እንጨት ፍለጋና፤ የእርሻ ቦታን ለማስፋት። ለማገዶ ከሚለው ክፍል ውስጥ ለዶሮ ወጥ መሥሪያ የሚውለው ክፍል ቀላል እንዳልሆነ ለማወቅ ትንሽ ማሰብ ብቻ ነው የሚጠይቀው።
በእንጨትም ይሁን በኬሮሲን፤ ወይም በኤሌክትሪክ ያ ሁሉ ሽንኩርት ሞክሙኮ እስኪለጠልጥ፤በዘይት ወይም በቅቤ ሽንኩርቱ ‘እስኪጠይም’፡ በርበሬው ተጨምሮ እስኪቁላላ፡ የዶሮው ብልቶች ተጨምረው እስኪበስሉ፡ከዋናው ቅቤ በኋላም እንቁላሉ ተቀቅሎ እንደገና ከዶሮው ጋር ለዳግም ብስለት እስኪበቃ ወዘተ የሚፈጀው የኃይል መጠን ስንትና ስንት ነው። በከተማም ይሁን በገጠር አሁን ድረስ በአብዛኛው የምንጠቀመው ነዳጅ የድሮውን ነው - ማገዶ - ጥሬ ደረቅ እንጨት፤ ኩበት፤ ቅጠላ ቅጠል የመሳሰለውን። በክፍት ጉልቻ መሳይ ምድጃ። ይህ ምድጃ ደግሞ ነዳጁ ከያዘው እምቅ ኃይል ውስጥ እጅግ በጣም ትንሹን ነው ለዶሮው ማብሰያነት የሚያውለው። የሚበዛውን እጅ እንዲሁ በከንቱ አየሩ ላይ ነው የሚበትነው። የዚህ አይነት ስሉጥ ያልሆነ የኃይል አጠቃቀም አንድምታው አሉታዊ ነው። ከምድጃው የሚወጣው ልቀት እስከ ሞት የሚያደርስ የቤት ውስጥ የአየር ብክለትን ያስከትላል። ‘ሙት’ የማስነሳት ስልጣን ቢኖረን አይ-ፈጠሬና አይ-ሞቴ የሆነውንና የባከነውን ኃይል ከአየር፤ አመዱን ከአፈር አንስተን ዳግም እንጨት አድርገን ማየት ብንችል ከዘመናት በፊት ከነበረው የአገራችን የደን ሽፋን ውስጥ ምን ያህሉ ከአባካኝ የኃይል አጠቃቀም ጋር ተያይዞ እንደወደመ ይገለጽልን ነበር ።
ዶሮ ወጥና ቢ.ፒ.አር.
ዶሮ ወጥ ባይሠራ ሕይወት አትቀጥልም ማለት አይደለም - ይቺን ሲያነብ “ኧረ በስመአብ በል” የሚል አንባቢ ካለ የሚቀጥለውን ዐረፍተ ነገር ያንብብ። እሺ ለዘመናት ሲደረግ የነበረን ነገር በአንዴ ማቆም አይቻልም ወይም አያስፈልግም እንበል። የአሠራር ሂደቱ ግን አጠር እንዲል ተደርጎ ቢከለስ - ቢ.ፒ.አር ቢጎበኘው- ምንድነው ጉዳቱ? ሥጋው ተዘጋጅቶ በሚቀርብበት በውጪ አገር እንኳን ዶሮ ወጥ መሥራት ግማሽ ቀን ይፈጃል - በተለመደው አሠራር ሲሠራ። ደግነቱ የተለያየ አገር የባህል ምግብ አሠራር ወስደው ለሌላ ማኅበረሰብ የሚያስተዋውቁ ምግብ ሠሪዎች የዶሮ ወጥ አሠራር ሂደትንም እያሳጠሩት ነው። እስቲ እናስበው በአገራችን የተለመደው የዶሮ ወጥ አሠራር ሂደት ሙሉ በሙሉ በቀጥታ በቴሌቭዥን ይተላለፍ ቢባል ርዝመቱ ያሰለቻል፤ የሚፈጃቸው ነገሮች ሲታሰብ ደግሞ ያስፈራል።
ያለ ምንም ችግር ማጠር ከሚችሉት ሂደቶች መካከል ቅድመ መብሰልና ጊዜ-መብሰል ውስጥ የሚካተቱትን ማየት ይቻላል። ከመታረዱ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ በቤታችን ውስጥ እያየነው ካልተሠራ ሞተን እንገኛለን እስካላልን ድረስ ከቤታችን ወጥተው በማዕከላዊነትና በጅምላ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች አሉ። በያንዳንዱ ቤት ለዶሮ ማጠብ የምንጠቀምበት ውኃም ሆነ ለመሥራት የምንጥቀምበት ኃይል በአንድ ማዕከላዊ ቦታ በጅምላ ቢሠራ እንደ ኅብረተሰብ አጠቃላይ የውኃና የኃይል ፍጆታችንን መቀነስ ይቻላል ብዬ አምናለሁ። ምን ያህል ይቀንሳል የሚለውን በቁጥር ለማስቀመጥ ጥናት ቢጠይቅም።
ማዕከላዊ የጅምላ አሠራር ኃይልና ውኃ የመሳሰሉት ግብአቶች ብቻ መቀነሱ ብቻ ሳይሆን ከበዓላት ጋር ተያያዞ የሚከሰተው የደረቅና የፈሳሽ ቆሻሻ አያያዝንም ስርዓት ለማስያዝ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። በየቤቱ ተበታትኖ የሚወጣውንና ከሌላ አይነት ቆሻሻ ጋር የምናደብልቀውን ካርቦናዊ ቆሻሻ በአንድ ቦታና ጊዜ ከሌሎች የቆሻሻ አይነቶች ጋር ሳይቀላቀል ስለሚገኝ ከቆሻሻው ልናመርተው ለምንችለው ባዮ ጋዝ የመሳሰለ ጠቃሚ ምርትም በቂ መጠን ይሰጠናል- ጥቅል የዓመት በዓል ካርቦናዊ ቆሻሻችን ብዙ ስለሆነ።
ይሄ ብቻ አይደለም። በየቤቱ ዶሮ ወጥ እየሠሩ ያሉትን ወገኖች ጊዜና ጉልበትም በእጅጉ ያሳጥራል።
ዶሮው በማእከላዊነት ከታረደ፤ ከተበለተና ከታጠበ በኋላ ለገበያ መቅረብ ይችላል - አሁን በአዲስ አበባ ትልልቅ መደብሮች ውስጥ እንደምናገኘው። ከዚህ አሠራር ጋር ተያይዘው የሚመጡት ነገሮች አሉ - ማሸግያ፡ማጓጓዣ፡ ማቀዝቀዣ(እንዳይበላሽ) የመሳሰሉት። እነዚህን ምርቶችና አገልግሎቶች የሚሰጡ አካላት ስለሚያስፈልጉ አዳዲስ ሥራ ይፈጠራል ማለት ነው። በዛው ልክ አዳዲስ ችግሮችን እንዳንፈጥር አሠራሩ ረጃጅም በካይ ጉዞዎችን እንዳይከተል፤ ማሸግያዎቹም አካባቢን ከማይበክሉ ጥሬ ዕቃዎች እንዲመረቱና ዳግም ጥቅም ላይ እንዲውሉ፤ ኃይል ቆጣቢ ማቀዝቀዣዎች እንዲኖሩ መደረግ አለበት።
አሁን ያሉት ጅምሮች እንዳሉ ሆነው የዶሮ ወጥን የእያንዳንዱ ቤት ወይም ሴት የባለሙያነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት አድርጎ በሚያስብ ኅብረተሰብ መካከል የማዕከላዊ አሠራር ሰፊ ተቀባይነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ መሆኑን እረዳለሁ። በከተሞቻችን እንጀራን ገዝቶ መብላት ከሀያ ዓመታት በፊት የነበረውን ተቀባይነትና አሁን ያለበትን ደረጃ ለሚያውቅ ሰው ራሳችንን ከጊዜና ከሁኔታዎች ጋር የማስተካከል ችሎታችን የምንገምተው ያህል ዝቅተኛ ላይሆን እንደሚችል ሊያሳይ ይችላል - ቀሰ በቀስም ቢሆን ።
እርግጥ ነው እንደየ እምነቱ ባርኮና አስባርኮ ማረድና ማሳረድ ለለመደና ለሚፈልግ ሰውም እምነቱንና ፍላጎቱን የሚረዳና እንደፍላጎቱም የሚያደርግለት ተቋም መሆን አለበት - ዶሮውን የሚያዘጋጀው ተቋም። እዚህ ላይ ክበበው ገዳ ወዳለሁበት ከተማ ሰሞኑን ብቅ ብሎ የተጫወተልን ቀልድ ላጫውታችሁ። በየቤቱ ማረድ በማይቻልበት ሰሜን አሜሪካ አበሻው ከከተማ ወጣ ብሎ ማሳረድ እንደመፍትሔ ወስዶታል። አራጆቹ ደግሞ ሜክሲኮያዊያን ናቸው። ታድያ በብዛት ወደ አንዱ ሜክሲኮያዊ እየሄዱ የሚያሳርዱት በጉ ከመታረዱ በፊት እንደየእምነታችው ወይ “በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አኃዱ አምላክ አሜን” ወይም “ቢስሚላሂ አል ራህማን አል ራሂም” ሲሉ በተደጋጋሚ ይሰማል። የሚሉት ምን እንደሆነ ባያውቀውምና ጸሎት መሆኑም ባይገባውም ነገሩን ከመልመዱ የተነሳ ከማረዱ በፊት አሳራጆቹ የሆነ ነገር እንዲሉ ይጠብቃል። ታዲያ አንዱ አበሻ መጥቶ ምንም ሳይል ሲቀር “ወንድም በጉ ከመታረዱ በፊት የምታናግረው ነገር የለህም?’ አለው - አለን ክበበው። ዶሮውን ያዘጋጁ የምላቸው ተቋሞች ስለኅብረተሰቡ እሴት ያላቸው ግንዛቤ ከዚህ ሜክሶኮያዊ እንዲሻል ይጠበቃል።
ጊዜ፤ ኃይልና የሰው ጉልበት ጨራሽ የሆነው ሌላው ሂደት ማቁላላት ነው። ይህም ከቤት ወጥቶ መሄድ ያለበት ሥራ ነው። ቢያንስ መሠረታዊ ልንለው የምንችለው ቁሌት በማዕከላዊነት ከተሠራ ወደቤት ሲሄድ የየቤቱን ወይም የየሴቱን(ለጊዜው ቢያንስ በብዛት ሴቶች ስለሚሠሩትና ‘ቤቱ’ ከሚለው ቃል ጋር ‘ሴቱ’ የሚለው አብሮ ስለሚሄድ) አሻራ የሚያንጸባርቅ አከላለስ በመጠቀም “የቤት የቤት” እንዲል ማድረግ ይቻላል።
ያላገባና ቀን በሥራ፤ማታ በትምህርት የተጠመደ ሰው እየበዛ በሚመጣባቸው አዲስ አበባና መሰል ከተሞች ውስጥ ሙሉ በሙሉ በማዕከላዊነት ተሠርቶ ያለቀለት የዶሮ ወጥም ቢሆን ተፈላጊነቱ እየጨመረ ይመጣል።

ይህ ሁሉ ሲሆን ትልቁ ተግዳሮት ጥራትና ማዕከላዊነትን ማስማማት መቻል ነው። ሠሪውና በዪው አንድ አለመሆናቸው፤ እንዲሁም ሠሪው እገሌ ተብሎ ሊጠየቅ የሚችል ሰው (ኅብረተስባችን የለመደው አይነት) መሆኑ ቀርቶ ተቋም መሆኑ ተቋሞችን በኃላፊነት የመጠየቅ ልምዱ ዝቅተኛ በሆነው ተጠቃሚ ዘንድ ከጥራት አንጻር ችግር ይፈጥራል። እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ጥብቅና የምር የጥራት ቁጥጥር የማስፈጸም አቅም እንዲኖረው ተደርጎ ከተደራጀ የመንግሥት አካል የሚጠበቀው።
ሁሉም ሰው አንድ አይነት አሠራር መከተል አለበት ብሎ ማሰብ ቀርቶ መመኘት አመክንዮያዊ ስለማይሆን በአንድ በኩል በየቤታችን እየሠራን እንድንቀጥል የሚያደርገን በሌላ በኩል ደግሞ በአካባቢ ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ለመቀነስ እንድንችል በትንሽ የኃይል መጠን የሚያስፈልገውን ሥራ መሥራት የሚያስችሉን ስሉጥ ማብሰያዎችን አምርተን ተደራሽ ማድረግ አለብን። ነዳጁም (ማገዶ እንጨት) ከክብደቱና ከይዘቱ ጋር ሲነጻጸር የተሸከመው እምቅ ኃይል ከፍተኛ እንዲሆን መደረግ አለበት። ለምሳሌ የእርጥበት መጠኑን አውርዶ እፍግታውን በመጨመር መጠኑ ከፍ እንዳለ ክኒን አይነት ተደርጎ ቢሠራ በቀላሉ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለማጓጓዝና ለማከማቸት ይመቻልም ይረክሳልም። ለማንደድም እንዲሁ ይቀላል። የዶሮ ወጥን ነገር መነሻ በማድረግ እስቲ ዓመት በዓልን አካባቢንና የሰው ጉልበትን እያቁላላ እንዳይቀጥል እናስብበት። መልካም በዓል!
==========
ጳጉሜ 5 ቀን 2003 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው “አዲስ ጉዳይ” መጽሔት ላይ መደበኛው “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ ታትሞ የወጣ ጽሁፍ። www.akababi.org

No comments: