Thursday, October 13, 2011

ቀመሩ እንዲሰምር

(ጌታቸው አሰፋ)ስለ ግብርና እጽፋለሁ - ለዛሬ። መንግሥት ሁለት የማዳበሪያ ፋብሪካዎችን እገነባለሁ ማለቱ ነው መነሻዬ። መልካም ዜና ነው። እስቲ ወደ ኋላ ከመቶ ሃምሳ ዓመታት በላይ እንንደርደር።
ከአጼ ቴዎድሮስ ጋር ለአሥር ዓመታት በአገራችን የኖረ ስዊዘርላንዳዊው ሚሶንያዊ ቴዎፍሎስ ቫልድማየር በዚህ ወር ግን ከ153 ዓመታት በፊት ወደ አቢስኒያ ተጓዘ። ከአምስት ወር በኃላም ገባ። ይህ ከሆነ ከሀያ ስምንት ዓመታት በኋላም ስለአሥር ዓመት ቆይታው መጽሐፍ ጻፈ (የተሳሳቱ መረጃዎች ያሉበት)። በመጽሐፉ የዛሬው ጉዳዬ ስለሆነው እርሻችንና ተያያዥ ነገሮችን በተመለከተ የተጻፈውንና የተሳሳተ ነው የሚያስብል ነገር ያላገኘሁለትን ወደ አማርኛ እንዲህ መልሼዋለሁ። 


ስለእኛ
“ገበሬዎቹ እጅግ ደካማና ጥንታዊ በሆነ መሣሪያ ነው መሬቱን የሚያለሙት። እንደዛም ሆኖ የሚያፍሱት ምርት ከፍተኛ ነው። ገብስ፤ ስንዴ፤ በቆሎ፤ምስር፤ ጥጥ፤የዘይት እህሎችና የተለያዩ አትክልቶችን ያመርታሉ። ገበሬዎች በቀላሉ ሀብታም መሆን ይችላሉ፡ የአፈሩን ለምነት ብቻ ካየን።” ጤፍን አልጠቀሰም።
የገበሬዎቹ የገሀዱ ዓለም ኑሮ ግን ምን እንደሚመስል ሲገልጽ “በጣም ድሆች ናቸው” ይላል። ምክንያቱም የግብርና ሥራቸውን የሚሠሩት በተከፋ መንፈስ ሆነው ነው ይልና ሲያብራራ “መዝራቱን ይዘራሉ ግን መጨረሻ ላይ ምርት ማግኘታቸውን እርግጠኛ አይደሉም። የአቢስኒያ ወታደሮች  ፈረሶቻቸውን፤ በቅሎዎቻቸውንና አህዮቻቸውን በሰብል የተሸፈነው ማሳ ላይ ለቀው ሲያበቁ ማሳውን እስኪያወድሙ ድረስ ይተዋቸዋል። እኔ ራሴ ገበሬዎች ከእንባ ጋር እንሳስቱን ከማሳው እንዲያወጡላቸው ሰብሮ ገቦችን ሲለማመጡ ብዙ ጊዜ አይቻለሁ። እንደዛም ለምነዋቸው አይሰሟቸውምም አይራሩላቸውም።” ይላል። አየሁ የሚለውን ነገር መሠረት አድርጎ አገሪቱ እንድታድግ የሚያስፈልጋት ነገር ምን እንደሆነ የሚመስለውን ይገልጻል። “አቢሲንያ ጥሩ መንግሥትና የጥንት ወደቧ የሆነው ምጽዋን የምታገኝ ከሆነ ወዲያው በዓለም እጅግ ከበለጸጉት አገሮች አንዷ ትሆን ነበር።”
ከጊዜ፤ ከወሬና ከሙግት ጋር ተያይዞ እንዲህ ሲል ይወርድብናል ። “ጊዜ በአበሾች ዘንድ ዋጋ ቢስ ነው። ሰዎቹም ጠንክረው አይሠሩም። መሬቱ ለምና ሀብታም ስለሆነ በቀላሉ ለፍላጎታቸው የሚሆነውን ያህል ይሰጣቸዋል። የሚሠሩት ትንሽ ትንሽ ስለሆነ ሰብሰብ ብለው ቁጭ ማለትንና አንዳቸው ለአንዳቸው እያከታተሉ መተራረክ ይወዳሉ። በዚህ ምክንያት በጥቅም የለሽና እርባና ቢስ ንግግሮች ብዙ ጊዜ ያጠፋሉ። እሰጥ አገባንም እጅግ ይወዳሉ። በረጃጅም የሙግት ሂደቶች ራሳቸውን ይጠምዳሉ።”
የግብርና ምርት በበቂ ተመርቶ፤ ገበሬው ራሱን ችሎ ከተሜውንም መግቦ የአገሪቱም ታሪክ እንዲቀየር ለማድረግ የታሰበበትና ዘላቂና ብዙ ነገሮችን የሚያቅፍ ስሙር ቀመር እንደሚያስፈልግ የቴዎፍሎስ ቫልድማየር ጽሑፍ አያሳይም ይሆን?  ቀመሩ ያልሰመረላት ኢትዮጵያ ብሎም አፍሪካ ውስጥ የግብርና ምርታማነት ከሞላ ጎደል ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።ለዚህ የሚጠቀሱ በርካታ ምክንያቶች ይኖራሉ። ቴክኒካዊም ፓለቲካዊም ሊሆኑ ይችላሉ። ቴክኒካዊዎቹ የሚወጡት ከፓለቲካው ነው። በቴክኒካዊ ማዕዘን ስንመለከተው የግብዓቶች ሚና እጅጉን የጎላ ሆኖ ነው የምናገኘው። ምርጥ ዘር፡ ውኃ፤ ማዳበሪያ፡ጸረ ተባይ፤ጸረ በሽታ እና ጸረ አረም ዋናዎቹ ግብአቶች ናቸው። የምርት መሣሪያም ወሳኝ ነው። ዋናው መሣሪያ ደግሞ መሬት ነው። ስለ መሬት በሰኔ የመጀመሪያው እትም ላይ ተጽፏል ወደፊትም ይጻፋል።  ማረሻ፤ውኃ ማጠጫ፤ ማጨጃ፤መውቂያ መሣሪያው ሁሉ መዘመን አለበት።  እነዚህ ሁሉ መጀመሪያ መገኘት አለባቸው። ከተገኙ በኋላ ደግሞ አስተባብሮ የሚጠቀም ባለእውቀት አምራች ያስፈልጋል።
ማዳበሪያ 
ሰብሎች እንደየአይነታቸው አበይት አልሚዎችና ንዑሳን አልሚዎች ያስፈልጓቸዋል። አበይት አልሚዎች ናይትሮጅን፤ፎስፎረስ፤ ፓታሺየምና ሰልፈር ሲሆኑ ገበያ ላይ የሚቀርቡት ማዳበሪያዎች ምንነት የሚያያዘውም እነዚህን አልሚዎች በመቶኛ ምን ያህል እንደያዙ ከሚያሳየው መግለጫቸው ጋር ነው። የአገራችን አፈር በዋናነት የሚፈልገው ናይትሮጂን እና ፎስፎረስ በመሆኑ አገራችን ከውጪ የምታሰገባቸው ማዳበሪያዎችም እነዚህን የያዙ ዩሪያ(ናይትሮጅን ብቻ) እና ዳፕ(ናይትሮጅን እና ፎስፎረስ) የተባሉትን ማዳበሪያዎች ናቸው። በማዳበሪያዎቹ ውስጥ ከአበይት አልሚዎች ጋር ንዑሳኑም የሚኖሩ ሲሆን የአፈሩን ሌሎች ከምርታማነት ጋር የተያያዙ ጉድለቶችም ላይ የጥገና ሥራ ይሠራል።
በዋናነት በዚህ ዓመት ለመጪው የበልግና የመኸር የምርት ወቅት የሚያስፈልገው ማዳበሪያ 75 ሚልዮን ኩንታል ዳፕ እና 55 ሚልዮን ኩንታል ዩሪያ ነው - በመንግሥት መረጃ መሠረት። ይህንኑ መጠን ለማስገባት  በተጫራቾች የቀረበው ዝቅተኛ ዋጋ ከፍ በማለቱ ጨረታውን እንዲሰርዝ አስገድዶታል ተብሏል። በኩንታል ለዩሪያ አምስት ዶላር ከአምሳ አንድ ሳንቲም የቀረበ ሲሆን ለዳፕ ደግሞ ስድስት ዶላር ከዘጠና ሳንቲም ነው ዝቅተኛው። እንደ አዲስ ፎርችን ዘገባ ከአምና ተመሳሳይ ወቅት የዓለም ገበያ ዋጋ በዩሪያ የሰባ ፐርሰንት፤ በዳፕ ደግሞ የሃምሳ አምስት ፐርሰንት ጭማሪ ነው ያሳየው። የማዳበሪያ ፍላጎት እየጨመረ ይሄዳል። ይህ ፍላጎት እየጨመረ ሲሄድ አቅርቦትም በዛው መጠን እየጨመረ ካልመጣ በደኅና ዓመት- ቀመሩ የሰመረበት ወቅት - ላይ ያገኘነውን ምርት እንኳን ለማግኘት ራሱ እንቸገራለን። 
ሙሉ ቀመር 
ኢትዮጵያ ራሷን ለመቻል የሚያስፈልጋት የምርት መጠን በ2002 ዓ.ም.  አንድ ነጥብ ስምት ቢልዮን ኩንታል ነበር። ታመርተዋለች ተብሎ ይጠበቅ የነበረው ግን ወደ አንድ ነጥብ ሰባት ቢልዮን ይሆናል። ይህም ወደ መቶ አርባ አምስት ሚልዮን ኩንታል ልዩነት ያመጣል። ወይ በግዢ ወይም በእርዳታ መሞላት ያለበት። ከላይ እንዳየነው ማዳበሪያ አንድ የቀመሩ አካል እንጂ ሙሉ ቀመሩ አይደለም።
ለዚያውም ማዳበሪያን መጠቀም ከተደራሽነትና ከዋጋ ጋር የሚያያዝ ነው። በተለይ የማናመርተውን ማዳበሪያ ዋጋውን የመቆጣጠር አቅማችን ውሱን በሆነበት ሁኔታ ነው። መቼና ምን ያህል መጠን ነው የሚያስፈልገን ወዘተ የእቅዱ አካል ነው መሆን ያለበት። በአገራችን ዋናው ምርት የመኸር ምርት ነው። የበልግ ምርት አስተዋጽኦ የመኸሩ ያህል አይሆንም። በሁለቱም ወቅቶች ጥቅም ላይ የዋለው መሬት ስንት ነው? አሁንም የምናገኘው ቁጥር የተምታታ ነው። አንድ አመት ባስቆጠረው የእድገትና የለውጥ እቅድ መጨረሻ ከዛሬ አራት ዓመት ሰብል ይመረትበታል የተባለው መሬት ስፋት አሁን እየተመረተበት ነው ከሚባለው ያነሰ ሆኖ ነው ያገኘሁት። ይህ መዘባረቅ የሚያሳየን በትክክል በሰብል የሚሸፈነው መሬት ያነሰ እንዲሆን እቅድ እንደተያዘ ሳይሆን አሁን የት እንዳለንና ወዴት መሄድ እንደምንፈልግ ለማሳየት የምንጠቀምባቸው ቁጥሮች ጥራት የሌላቸው መሆኑን ነው። በአገራችን “ቁጥር እንደጠሪው” (ሕልም እንደፈቺው እንዲሉ) እስከመቼ እንደሚለያይ ግራ ያጋባል።  
ሌላው ትልቁ የቀመሩ አካል የማምረቻ መሣሪያ ነው። የዛሬ አራት ዓመት በዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ ውስጥ ሦስት ሺህ ትራክተሮች ነበሩ። ይህ ማለት አሁንም ልክ እንደጥንቱ ሟች በሬን ነው የምንጠቀመው። ለዛውም ከአጠቃላይ አሥር ነጥብ ሦስት ሚልዮን ከሚሆኑት የግብርና ባለይዞታዎች(አራሾችና አሳራሾች) መካከል ወደ አርባ ሁለት ፐርሰንቱ አንድም በሬ የሌላቸው ናቸው። ያላቸውም ቢሆኑ በድርቅ እስኪጠቁ ድረስ ነው። በድርቅ ወቅት መጀመሪያ የሚያልቁት ሟች ትራክተሮቻችን የሆኑት በሬዎችን ጨምሮ እንስሳት ናቸው። ቀጥሎ ከወተት ይገኝ የነበረውን ሕይወት ሰጪ አልሚ እንኳን የሚያጡት ህጻናት ይረግፋሉ። በድርቅ ወቅት ያለቁትን እንስሳት ለመተካት ለገበሬዎች ከአቅማቸው በላይ ነው። እንገደና ገዝቶ የሚሰጣቸው አካል እንኳን ቢገኝ የሚቀጥለው የድርቅ ዙር ላይ እንደማይሞቱባቸው ዋስትና መስጠት በማይቻልበት ሁኔታ ነው የሚሆነው። አገራችን ሕያዋን ጠማጆች እንጂ ሕያዋን ተጠማጆች ይዛ ብዙ መጓዝ አትችልም - የእስካሁኑ ትምህርት ከሆነን።  
ቢያንስ ማዳበሪያን በአገራችን ማምረት ከጀመርን ምጣኔ ሀብታዊው ጠቀሜታው የጎላ ነው።ምግብ ነገር ሙሉ በሙሉ አገር ውስጥ በሚገኙ ግብኣቶች በበቂ ሁኔታ የሚመረቱበት መንገድ ለማመቻቸት ስለሚረዳ። የማዳበሪያ ፋብሪካዎች ጥናት በየጊዜው ሲከለስ ቆይቶ የዓለም የማዳበሪያ ዋጋን ትራንስፖርቱንም ጨምሮ የሚያስወጣን ወጪና በአገር ቤት ቢመረት የሚኖረው የተከላና የማምረቻ ጠቅላላ ወጪ ሲነጻጸር አገር ውስጥ ማምረቱ አዋጪ አይሆንም በሚል ነበር እስካሁን ውድቅ ሲደረግ የቆየው። የማዳበሪያ የዓለም ገበያ ዋጋ ከፍተኛ ደረጃ በደረሰበት ወቅትም ጭምር። ዋናዎቹ ጥሬ እቃዎች በአገራችን የሚገኙ ከመሆናቸው ጋር አሁን የተከላ ሥራውን በብረታ ብረት ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ለማሠራት ይቻላል ከሚል ይመስላል ፕሮጄክቱ አረንጓዴ መብራት ተሰጥቶታል። 
የግብርናችን ምርታማነት መጨመር አለበት። ለዚህም በአገር ውስጥ የሚመረት ማዳበሪያ ያስፈልጋል። ይሁንና ለማዳበሪያው ማምረቻ የሚሆነው የከሰል ድንጋይ የሚወጣበት የአገራችን አካባቢ የሚገኘው የተፈጥሮ ሀብት እንዳይጎሳቆል ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ከአጠቃቀም አንጻርም አሲድማነትን የሚጨምሩ ማዳበሪያዎችን ማስወገድ ያስፈልጋል። አገራችን በሄክታር የምትጠቀመው የማዳበሪያ መጠን አሁንም ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ አይደለም። ይሁንና መጠኑ እየጨመረ ሲመጣ እንደገና ለየትኛው ቦታ ምን አይነት ማዳበሪያ ያስፈልጋል ከሚለው ጀምሮ ማሳው ላይ ወጪ ከተደረገው ማዳበሪያ ውስጥ ካሉት የአልሚዎች መጠን ምን ያህሉ ወደ ሰብሉ ይደርሳል? በቀላሉ ወደ ከርሰ ምድር ወይም ወደ ገጸ ምድር ውኃ የሚቀላቀልና የሚበክል እንዳይሆን ምን መደረግ አለበት? ምን ያህሉስ ወደ አየር ይተናል? ከብቶችን የሚመርዝ እንዳይሆንስ? ወዘተ ብለው በማዳበሪያው ውስጥ የሚገኙትን አልሚ ንጥረ ነገሮች ዙሪያ ከወጪ ቀሪ ሂሳብ መሥራት ይጠበቅባቸዋል - የምርምር ተቋሞቻችን። በካይ የሆኑ የከባድ ብረቶች መጠንና የጨው መጠኑ ምን ያህል ነው? መመለስ አለበት
የማዳበሪያው መገኘትና የሚሸጥበት ዋጋ ከፍና ዝቅ ማለት በገበሬው ማኅበራዊ ኑሮ ላይ የራሱ የሆነ ተጽእኖ አለው። በተለይ የማዳበሪያው ዋጋ ሲወደድና ለማዳበሪያው የሚከፍለው ገንዘብ የሚያገኘው በቅድመ ሁኔታ በታጠረ ብድር በሚሆንበት ወቅት ተጽእኖው ይጎላል።
ግዙፍ የኢንቨስትመንት ገንዘብ የሚጠይቁ ትክሎች ቀርቶ ሌሎች አገራዊ መፍትሔዎችም ላይ ቢሆን አገሪቱ እንቁላሎችዋን  ሁሉ አንድ ዘምቢል ውስጥ ማስቀመጥ የለባትም። የተፈጥሮ ማዳበሪያና ብስባሽ የመሳሰሉት አማራጮች በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉበት መንገድ መፈለግ አለበት። ቀመሩ እንዲሰምርም መዘመን ያለባቸው መሣሪያዎችና አሠራሮችም እንዲሁ። 
==========
መስከረም  13  ቀን 2004 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: