Thursday, October 13, 2011

ባለአረንጓዴ ቀበቶ ጀግና


(ጌታቸው አሰፋ) ዛሬ ይህ አምድ ኬንያዊቷን ዋንጋሪ ማታይን ያስባል። ዋንጋሪ ሙታ ሜሪ ጆ ማታይ ከሰባ አንድ ዓመታት በፊት በሞኞች ቀን(April 1) የተወለዱ ልባም ሴት ነበሩ።  የመጀመሪያ ዲግሪያቸውንና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በስነ-ህይወት ከአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ በእንስሳት ጤና ሳይንስ ስነ-ብልት ጥናት ከናይሮቢ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል። እሁድ መስከረም አስራ አራት 2004 ዓ.ም. በሞት ተለዩን። ሥራቸው ግን ከመንደራቸው፤ ከአገራቸውና ከአህጉራቸው አልፎ ከፍተኛ ዓለም አቀፋዊ እውቅናን ያገኘ ህያው ሥራ ሆኖ ይቀጥላል።  

በ1970 ዓ.ም. የአረንጓዴ ቀበቶ ንቅናቄ የተባለውን መንግሥታዊ ያለሆነ ድርጅት አቋቋሙ።
በዚህም በኬንያና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ለአርባ አምስት ሚልዮን ዛፎች መተከል ዋና ምክንያት ሆኑ። የአካባቢ እንክብካቤ ብቻውን የቆመ ደሴት ሳይሆን ከሴቶች እኩልነትና ከሌሎች የሰብዓዊ መብቶች ጋር ተንሰላስሎ መሠራት ያለበት ነው ብለው ያምኑና ይሠሩ የነበሩት ዋንጋሪ ማታይ ዘጠኝ መቶ ሺህ ሴቶች የችግኝ ማፊያ ጣቢያዎች ባለቤቶችና ሠራተኞች እንዲሆኑ አድርገዋል።
ከ 2002 እስክ 2007 እ.አ.አ የኬንያ ፓርላማ አባል እንዲሁም ከ2003 እስከ 2007 እ.አ.አ የኬንያ የአካባቢና ተፈጥሮ ሀብት ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።
ኖቤልና ሰላም 
በመንደር፤ በአገርና በአህጉር ደረጃ ለዓመታት ይተጉለት የነበረው ጉዳይ የዛሬ ሰባት ዓመት ዓለም አቀፍ እውቅናን ሊያገኝ በቃ። አካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ማለት የሰላም አካል ነው፤ ሰላምም ነው የሚል መልእክት በሚያስተላልፍ መልኩ ታዋቂውና የዓለማችን የሽልማቶችና የእውቅናዎች እንቁ የሆነው የኖቤል የሰላም ሽልማት ለእኝህ ታላቅ ጀግና ተሰጠ። የኖቤል የሰላም ሽልማቱ ከተለመደው ወጣ ባለ መልኩ ለአካባቢ ጉዳይ አቀንቃኝ፤ ተሟጋችና፤ ትጉህ ሠራተኛ ሲሰጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር። የኖቤል ሽልማት ስዊዲናዊው ኬሚካል መሐንዲስ አልፍሬድ ኖቤል በአምስት የተለያዩ ዘርፎች በዓለም የላቀ እምርታ ያሳዩ ባለሞያዎችን- ግለሰቦችንና ድርጅቶችን - በየዓመቱ ለመሸለም የሚያስችል ገንዘብና ሃሳብ በተናዘዘው መሠረት የሚፈጸም ሽልማት ነው። በኬምስትሪ፤ በፊዚክስ፤ በህክም ጥናት እና በምጣኔ ሀብት ጥናት ዘርፍ ስቶክሆልም ስዊድን ከሚገኘው የከተማው ማዘጋጃ ቤት በሚደረግ ስነስርዓት የሚሰጡ ሽልማቶች ሲሆኑ የሰላም ሽልማቱ ደግሞ ኦስሎ ኖርዌይ በሚደረግ ስነስርዓት ይሰጣል። የኖቤል የሰላም ሽልማት መሰጠት የተጀመረው የዛሬ መቶ አሥር ዓመት በፊት ነው። አልፍሬድ ኖቤል ዲናማይትን የፈጠረ መሐንዲስ ነው። ኖቤል የዳይናማይትን የፈጠራ ባለቤትነት ማረጋገጫ ባገኘ በዓመቱ ነበር ጎንደር ጋፋት ላይ አጼ ቴዎድሮስ ሴባስቶፓል የተሰኘውን መድፍ ሲያሠሩ የነበሩት። ዳይናማይት ለማዕድን ቁፋሮ፤ ለካባ ሥራና ለመንገድ ብሎም ለሌሎች መሠረተ ልማት ሥራዎች የመሠረት ቁፋሮ የሚጠቅም ሲሆን በወቅቱ ግን በአማጺያን ለጥቃት ጥቅም ላይ ይውል ነበር። ምናልባት ይህ የፈጠራ ስራው በአሉታዊ መልኩ መጠቀሚያ መሆኑ ስለሰላም እንዲያስብ አድርጎት ይሆናል በተፈጥሮ ሳይንስና በማኅበራዊ ሳይንስ ላይ ካተኮሩት አራቱ የሽልማት ዘርፎች ጋር አምስተኛ አድርጎ የሰላም ሽልማት ዘርፍ እንዲኖር ያደረገው የሚሉ አሉ። ኖቤል ያረፈው የአድዋ ጦርነት ከተደረገ በዘጠኝ ወር ውስጥ ነው። የመጀመሪያው የሰላም ሽልማት መስጠት የተጀመረው ደግሞ ከጦርነቱ ከአምስት ዓመታት በኋላ መሆኑ ነው። የኖቤል ሙያና የፈጠራ ስራ ከአፍራሽ አጠቃቀም ጋር ተያያዞ የመቅረቡ ጉዳይ እኔ ኬሚካል ምሕንድስናን እንደትምህርት ዘርፍ በመረጥኩበት ጊዜ የነበረውን አጋጣሚ ያስታውሰኛል። ወቅቱ የኬሚካል ምሕንድስና እንደዛሬ በኢንዱስትሪዎቻችንም በሌላውም ዘንድ የማይታወቅበት ጊዜ ነበር። ደርግ በወደቀ በዓመቱ። በደርግ ጊዜ ይመረቁ ከነበሩት መካከል ጥይት ፋብሪካ የተቀጥሩ ነበሩ መሰለኝ ኬሚካል ምሕንድስናም ከዛ ጋር ተያይዞ ይነሳ ነበር። ሁለተኛ ዓመት ተማሪ ነበርኩ - አምስት ኪሎ። አስራ ሁለት ስጨርስ መማር እፈልግ የነበረው ህክምና ነበር - በቂ መረጃ ሳይኖረኝ ማለት ነው። ወጤቴ ጥሩ ስለነበር ያው ባላውቀውም በሁሉም ሲፈለግ የሰማሁትንና እኔም የፈለግሁትን ሕክምናን አንደኛ ምርጫዬ አድርጌ መጠባበቅ ያዝኩ። መስከረም አስር ቡራዩ ጸዴኒያ ማርያምን አንግሼ ስመለስ ፒያሳ ስኒማ ኢትዮጵያ ከሚገኘው/ከነበረው የዘጠኝ ቁጥር አውቶብስ ማቆሚያ ተደግፌ ያየሁት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ግን ሕክምና ወዲያ እኔ ወዲህ እንደሆንን የወሰነ ነበር- ስሜ አራት ኪሎ የተፈጥሮ ሳይንስ ከሚለው ስር ተከሰተ። መረጃ-አልባ ፍላጎቴ ያለመሳካቱ የወለደው ብስጭቴን ዋጥ አድርጌ በመረጃ መንቀሳቀስ ጀመርኩ። ከአራት ኪሎ አምስት ኪሎ፤ ከአምስት ኪሎም ኬሚካል ምሕንድስና ለመወሰን ጊዜ አልወሰድብኝም። ነፍሱን ይማረውና ሜካኒካል መሐንዲስ የነበረው አጎቴ የሰጠኝ መረጃ ተንተርሼ ማለት ነው። ኬሚካል መሐንዲስ የትም ምንም መሥራትና መሆን ይችላል ተብሎ ሊጠቃለል በሚችል መልኩ ተንትኖ ነግሮኝ ነበርና የየትምህርት ክፍሉ ኃላፊዎች ስለ መስካቸው የሚያብራሩበት/የሚያግባቡበት መድረክም መሳተፍ ሳያስፈልገኝ አንደኛ ምርጫዬን አድርጌ ሞላሁ። እኔ ብቻ ሳልሆን በወቅቱ ኬሚካል ምሕንድስናን ከተቀላቀሉት ዓመተኞቼ አብዛኛዎቹ አንደኛ ምርጫቸው አድርገው የሞሉ ነበሩ። ሥራ አያስገኝም የሚለውን ስጋት ጨምሮ ብዙ ጥርጣሬዎች ነበሩ። አንዱ ጓደኛችን ታዲያ “ቤተ ክርስቲያን እየሄድን እና እንሂድ እያልን እንዴት ጥይት ፋብሪካ የሚያስገባ መስክ ውስጥ እንገባለን?” ብሎ የትምህርት መስክ ምርጫችን ላይ ጥያቄ አነሳ። ደግነቱ የአጎቴ አሳማኝ መረጃ መሠረት አድርጌ ጓደኛዬን አሳምኜ አብረን ኬሚካል ምሕንድስናን አጠናን። ልጁም ተመርቆ ጥይት ፋብሪካ ሳይሆን ስኳር ፋብሪካ ሲሰራ ነበር።
ወደ ቀደመ ነገራችን ስንመለስ  የኖቤል የሰላም ሽልማት ድርጅት የሰላምን ትርጉም ሰፋ ባለ መልኩ እንዲያየው ያደረገው መሸለም የሚገባት የዋንጋሪ ማታይ የሚታይና የሚጨበጥ ሥራ ነው። ኖቤል በሕይወት ዛሬ ቢኖር ኖሮ የአካባቢ እንክብካቤና ጥበቃ አራቱን የሽልማት ዘርፎችን ከሰላሙ ዘርፍ ጋር እንዴት እንዳገናኛቸው ሲያይ ይደሰት ነበር ብዬ አምናለሁ። 
አካባቢ፤ሰላም፤ ሴቶች
የአካባቢ ጉዳይ የሰላም ጉዳይ ማለት መሆኑን ለማወቅ ሩቅ ሳንሄድ ማየት እንችላለን። በአገራችን ተጎራባች ክልሎችና ዞኖች እንዲሁም መንደሮች በሚያዋስናቸው ቦታ የሚገኝና እየተመናመነ የሚሄድ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ሕይወት እስከመጠፋፋት የሚያደርስ ግጭት ውስጥ በየጊዜው እንደሚገቡ ይታወቃል። በቂ እንክብካቤና ጥበቃ በሌለበት ሁኔታና ከሚጎሳቆል አካባቢ የሚገኝ ሀብት ለዛሬና ለነገ ተጠቃሚዎች ሰላም በማያደፈርስ መጠንና ጥራት ማቅረብ እንችላለን ብሎ ማሰብ ላም ካልዋለችበት ቦታ ኩበት ከመልቀም ይብሳል (ይህ ተረት ላም እንጂ በሬ ያልነበረው ሰው የተረተው ይሆን? ወይስ በእናት ነው የሚጠራው? ወይስ ኩበታምነታቸው በመጠን ይለያይል? ወይስ? )። ከተፈጥሮ ጋር ያለን ሰላም ከደፈረሰ እርስ በርሳችን ያለን ሰላም ይደፈርሳል። አካባቢ ወይም ተፈጥሮ ስንል ስለሀብት ነው የምናወራው። ገበያ የሚያውቀውም የማያውቀውም የተፈጥሮ ሀብታት ለበርካታ ግጭቶች መነሻ ነበሩ፤ ናቸው፤ እንደሆኑም ይቀጥላሉ። 
ዋንጋሪ ማታይ  የተፈጥሮ ሀብትን በማልማትና በመንከባከብ ሰላም ከተፈጥሮ ጋርና ሰላም በሰዎች መካከል እንዲሰፍን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። 
ምን ይሄ ብቻ የኅብረተሰባችን ግማሽ ግን ወሳኝ አካል የሆኑትን የሴቶችን መብት ለማስጠበቅ ታግለዋል። በብዙ ዘርፍ የመጀመሪያ የሚባሉ እንደነበሩ የሕይወት ታሪካቸው ያሳያል።
በምስራቅ አፍሪካና በመካከለኛ አፍሪካ የዶክትሬት ዲግሪ በመያዝ የመጀመሪያዋ ሴት ነበሩ። በአጠቃላይ ከ1969 ዓ.ም. ጀምሮ ለአስራ አንድ ዓመታት የብሔራዊ የሴቶች ምክር ቤት ውስጥ በንቃት ያገለገሉ ሲሆን ለሰባት ዓመታት ደግሞ በሰብሳቢነት መርተውታል። ሰፊ መሠረት ያለውና ድህነት ማጥፋትን ከዛፍ ተከላ ጋር ያቀናጀ የአረንጓዴ ቀበቶ ንቅናቄን ከዛሬ ሠላስ አራት ዓመት በፊት በመመሥረትና በመምራት ሴቶችን ማዕከል አድርገው ከማሳ፤ ከትምህርት ቤቶችና ከአብያተ ጸሎት ጀምሮ በዛፎች እንዲሸፈኑ አድርገዋል። የመሬት ሽሚያን የሚቃወሙ ዘመቻዎችንም መርተዋል። ጥቂቶች ያለገደብ የሚያግበሰብሱት መሬት በሴቶችና በሌሎች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ አምርረው ታግለዋል። የተሳተፉባቸውና የመሯቸው ዓለምአቀፍ ድርጅቶች፤ የተሸለሟቸው ሽልማቶች ያገኙዋቸው የክብር ዶክትሬቶች በርካታ ናቸው። አሜሪካ፤ ጃፓን፤ ፈረንሳይ፤ ህንድ፤ ስፔይን፤ ሆላንድ፤ እንግሊዝ፤ ስኮትላንድ፤ ስዊድን፤ ኖርዌይ የተለያያ እውቅና ሰጥተውቸዋል፤ ሽልማት አበርክተውላቸዋል። በተባበሩት መንግስታት የተለያዩ ድርጅቶች፤ የአፍሪካ ህብረትና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ፤ አህጉራዊና ክፍለ አህጉራዊ ድርጅቶች ሾሟቸዋል፤ ሸልመዋቸዋል። 
በአገራችንም ሆነ በአህጉራችን የዋንጋሪ ማታይ ፈለግ ተከትሎ የሳቸው አይነት ትግል የሚታገል ሰው ልማትን አደናቃፊ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም። ከአንድ ፋብሪካ ወይም የማዕድን ቁፋሮ ወይም የመንገድ ሥራ ጋር ተያይዞ የሚፈጠር አካባቢያዊ ተጽእኖን በብርቱ ሊቃወምና ሊያስቆምም ይችላል፤ ይገባልም - መረጃን መሠረት አድርጎና ወደ መፍትሔ በሚያመራ መልኩ። ዛሬ እሳቸው ለክብር የበቁና በተለያየ መልኩ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጀግናም የተደረጉ ይሁን እንጂ ቀደም ሲል በአገራቸው አጥፊና ወንጀለኛ ተደርገው የተወሰዱበት ጊዜም ነበር። ይህ በአህጉራችን ብቻ ሳይሆን ዛሬ ካናዳ ለደረሰችበት በሁለንተናዊ መስፈርት የበለጸገ የደን ልማት አንድ ብሎ እንዲጀመር የገፉት ከዛሬ ሰላሳ ዓመት በፊት የካናዳን ልማት የማይፈልጉና ሰው ሰርቶ እንዳይበላ የሚያደናቅፉ እየተባሉ በየፍርድ ቤት ሳይቀር ሲከሰሱ የነበሩ አቀንቃኞች ናቸው። ዋንጋሪ ማታይ “አትንኩ! አትቁረጡ!” ባይ ብቻ አልነበሩም የሚተክሉ፤የሚያስተክሉና አስቻይ ፓለቲካዊ ንጣፍ ለመፍጠርም የሠሩና የተጉ ነበሩ - በመሳተፍ። ዛሬም ከአገራችን አቀንቃኞች የዚህ አይነት ዘርፈ ብዙ ተሳትፎ ይጠበቃል።  
በካንሰር ሕመም ምክንያት መሞታቸው ሲሰማ ከቀድሞው የአሜሪካ ምክትል ፕረዚደንትና የአካባቢ ጉዳይ እንደገባቸው ከምንመስከርላቸው አል ጎር እስከ ፕረዚደንት ባራክ ኦባማ፤ ከባንኪ ሙን እስከ ዴዝሞን ቱቱ የሚገኙበት በርካታ የዓለማችን ታዋቂ ሰዎች ያስተላለፉት የሐዘን መግለጫ መልእክት የዋንጋሪ ማታይን ባለ ብዙ ዘርፍና አቅጣጫ የሰላም ታጋይነትን አጉልቶ የሚያሳይ ነበር። ሰላም ለነፍሳቸው!
ድኅረ ነገር - ከዋንጋሪ ማታይ ጋር ተያይዞ ስለሴቶች ስጽፍ በአገራችን በሴትነታችው ለሞትና ለአካል ጉዳት የሚያበቃ ጥቃት የደረሰባቸው እነ ካሚላት፤ ትዕግስትንና አበራሽን የመሳሰሉትን በመሪር ሀዘን እያሰብኩ ነው። ሴቶቻችን የአሳፋሪ አሰተሳሰቦችና ድርጊቶች ሰለባዎች ሆነው መቀጠል የለባቸውም (መፈክር ያይደለ ቁጭት-ወለድ እንትን - ምን ልበለው ታዲያ -  ነው)።
==========
መስከረም  27  ቀን 2004 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org


No comments: