Saturday, November 5, 2011

የአየር ንብረት ለውጥና ፍኖተ ደርባን


(ጌታቸው አሰፋ)የዛሬውና የቀጣዩ ጽሑፌ ትኩረት በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ይሆናል። ምክንያት - አለም አቀፉ አስራ ሰባተኛው የአየር ንብረት ለውጥ ባለጉዳይ አካላት ጉባኤ ከፊታችን ህዳር 18 እስከ  ህዳር 29 በደቡብ አፍሪካ ደርባን ከተማ ስለሚካሄድ። 
ላለፉት አስራ አራት ዓመታት የተካሄዱት አለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ድርድሮች የሚያጠነጥኑት የኪዮቶ ፕሮቶኮል ተብሎ በሚጠራው ስምምነት ዙሪያ ነው። የኪዮቶ ፕሮቶኮል ባለ ሀያ ስምንት አንቀጽና ሁለት አባሪዎች ስምምነት ሲሆን ጃፓን በሚገኘው የኪዮቶ ከተማ ታህሳስ ሁለት 1990 .. የጸደቀ ነው።
ስምምነቱ ላደጉት አገሮች  አሳሪ የልቀት ቅነሳ/ገደብ ይዟል። በፕሮቶኮሉ የተካተቱት አየር ንብረት ለዋጭ ጋዞች ስድስት ሲሆኑ እነሱም ካርቦን ዳይኦክሳይድ(CO2) ሚቴን(CH4)፤ናይትረስ ኦክሳይድ(N2O) ሃይድሮፍሎሮካርበንስ(HFCs) ፤ ፐርፍሎሮካርበንስ(PFCs)  እና ሰልፈር ሄክሳ ፍሎራይድ(SF6) ናቸው። እነዚህ ጋዞች ከኃይል ማመንጫዎች፤ ከመጓጓዣ አገልግሎት፤ከከባድ ኢንዱስትሪዎችና ከግብርና ዘርፍ ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ ናቸው። እነዚህ ዘርፎች ደግሞ በአንድ አገር የምጣኔ ሀብት እድገት ላይ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ።  በዚህ ምክንያት የልቀት መጠን ቅነሳ ቢያንስ በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ ምጣኔ ሀብት እድገት ላይ ትርጉም ያለው ተጽእኖ አለው። በተለይ ዘርፈ ብዙ አቅም በሌላቸው አገሮች ላይ። ይህ አንድምታ ከስራ እድልና አጥነት ጋር ቀጥተኛ ዝምድና ስላለው በስልጣን ላይ ላሉ ፖለቲከኞች በመራጭ ዘንድ እንዲኖራቸው ለሚፈልጉትና ለሚጠብቁት ተቀባይነት አሉታዊ ትርጉም ይሰጣል። 
ልቀት ቅነሳና ገደብ
የኪዮቶ ፕሮቶኮል ቅጥያ አንድ አገሮች ተብለው የሚጠሩት ላይ ነው የልቀት ቅነሳ ወይም ገደብ የሚጥለው። የቅጥያ አንድ አገሮች ዝርዝር ወደ አርባ የሚደርስ ሲሆን የአውሮፓ አገሮች፤ አሜሪካ፤ካናዳ፤አውስትራልያንና ራሺያን ይጨምራል። ቅጥያ ሁለት ተብለው የተዘረዘሩት አገሮች ደግሞ በማደግ ላይ ላሉ አገሮች የፋይናንስ ድጋፍና የቴክኖሎጂ ሽግግር የማድረግ ኃላፊነት የተሸከሙ ሲሆን ወደ ሃያ ሦስት አገሮችን ያቅፋል። ከቅጥያ አንድ ውጪ ያሉ አገሮች አገራችንን ጨምሮ እነቻይና ፤ብራዚል፤ ሕንድና ደቡብ አፍሪካ የሚገኙበት ሲሆን የኪዮቶ ፕሮቶኮል ያጸደቁ፤ የተቀበሉና የፈረሙም ቢሆን እንኳን አሁን ባለው ሁኔታ የልቀት ቅነሳም ይሁን ገደብ አልተጣለባቸውም። በኪዮቶ ፕሮቶኮል አንቀጽ ሀያ ሦስት መሰረት 1990 ... ከነበረው የቅጥያ አንድ አገሮች የልቀት መጠን ቢያንስ ሀምሳ አምስት ፕርሰንቱን የሚሸፍኑ የቅጥያ አንድ አገሮችን ጨምሮ ቢያንስ በሀምሳ አምስት አገሮች ከጸደቀ በኋላ በዘጠናኛው ቀን በሥራ ላይ መዋል ነበረበት።  በመሆኑም ፕሮቶኮሉ ለአስራ አራት ዓመት በፊት ሥራ ላይ የሚውልበትን ቀን ቢጠብቅም ራሺያ በየካቲት 9 ቀን 1997 .. ስታጸድቀው ወደ ሥራ ገብቷል። አሜሪካ ፕሮቶኮሉ ለፊርማ ክፍት በሆነ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ብትፈርምበትም ወደ አገሪቱ ሕግ አውጪ አካል ወስዳ ማጸደቅ በሚጠበቅባት ጊዜ የቢል ክሊንተን የሥልጣን ዘመን አብቅቶ የአየር ንብረት ለዋጭ ጋዞች ዋና ምንጭ በሆነው የነዳጅ ዘይት ዘርፍ ባለሀብቶች የሚደገፉትና የዘርፉን ጥቅም አስጠባቂ የሆኑት ጆርጅ ቡሽ ስልጣን የወጡበት ወቅት በመምጣቱ የኪዮቶ ፕሮቶኮል በአሜሪካ ሳይጸድቅ እነሆ እስከዛሬ ድረስ አለ (ባራክ ኦባማም በሌሎች ራስ ምታቶች ተጠመደው ቁጭ አሉ) 
በፕሮቶኮሉ ለልቀት ቅነሳ ወይም ገደብ ኢላማ መነሻ ዓመት ያደረገው 1990 ... ሲሆን የኢላማው ስኬት የሚለካው ደግሞ 2008-2012 ... ባለው ጊዜ ነው። ስለዚህ 2012 .. በኋላ የኪዮቶ ፕሮቶኮል የሥራ ጊዜ ስለሚያበቃ በሌላ ስምምነት መተካት ይኖርበታል። 1990 ... ልቀታቸው ጋር ሲነጻጸር 2008-2012 ... ያለው ዓመታዊው ልቀታቸውን መቀነስ የሚገባቸው 8 ፐርሰንት የአውሮፓ ህብረት፤ 7 ፐርሰንት አሜሪካ፤ 6 ፐርሰንት  ካናዳ፤ ፖላንድ፤ ሀንጋሪና ጃፓን ሲሆኑ 5 ፐርሰንት ደግሞ ክሮሺያ ናቸው።  ከመነሻው ዓመት ጋር ሲነጻጸር እስከ ሚቀጥለው የአውሮፓውያን ዓመት የልቀታቸው ልዩነት ዜሮ እንዲሆን የሚጠበቅባቸው  ኒውዝላንድ፤ ራሺያና፤ ዩክሬን ናቸው። በገደብ መጨመር የሚችሉት ደግሞ 8 ፐርሰንት አውስትራልያ፤በአንድ ፐርሰንት ኖርዌይና 10 ፐርሰንት አይስላንድ ናቸው። ይህ ስሌት ታሪካዊ ልቀታቸውን መነሻ ያደረገ ነው። የአውሮፓ ህብረት በጋራ የተሰጠውን 8 ፐርሰንት የመቀነስ ኢላማ ለአባል አገሮቹ ያከፋፈለ ሲሆን የተወሰኑት አገሮች እንዲጨምሩ የተወሰኑት እንዲቀንሱ ሆኖ ተሰጥቶዋቸዋል። ለምሳሌ በስሌቱ መሰረት ስዊድን በአራት ፐርሰንት እንድትጨምር ሲፈቀድላት ጀርመን ደግሞ በሀያ አንድ ፐርሰንት እንድትቀንስ ትገደዳለች። አገሮች የልቀት ቅነሳ ወይም ገደብ ኢላማቸውን ለማሳካት በዋናነት ብሔራዊ መፍትሔዎችን ያዘሉ መርሐግብሮችን መቅረጽ ቢጠበቅባቸውም የኪዮቶ ፕሮቶኮል ሦስት ተጨማሪ ስልቶችን ይፈቅዳል። እነዚህም የልቀት ንግድ፤የማይበክል የእድገት ክንውንውታ እና የጋራ ትግበራ የሚባሉት ናቸው። የልቀት ንግድ ማለት ልቀት ተፈቅዶላቸው ግን የተፈቀድላቸውን መጠን መጠቀም የማያስፈልጋቸው አገሮች፤ ከተፈቀደላቸው ጣራ በላይ ልቀት ላለባቸው አገሮች መሸጥ የሚችሉበት መንገድ ነው። የማይበክል የእድገት ክንውንውታ ደግሞ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ተቀርጸው የሚተገበሩ ልቀት ቀናሽ ፕሮጆክቶችን ያካትታል (ለምሳሌ በወላይታ የሚገኘው የሁምቦ ደን ልማት ፕሮጄክት) የጋራ ትግበራ ማለት ደግሞ አንድ ቅነሳ ወይም ገደብ ያለበት አገር ሌላ ቅነሳ ወይም ገደብ ያለበት አገር ሄዶ  የቅነሳ ፕሮጄክት እንዲፈጽም የሚያስችለው መንገድ ነው። ተቀባይ አገር የውጪ ኢንቨስትመንትና ቴክኖሎጂ በማግኘቱ ሲጠቀም ፈጻሚ አገር ደግሞ ፕሮጄክቱ የሚያስመዘግበው የልቀት ቅነሳ መጠን ለራሱ ያደርጋል ማለት ነው። በሦስቱም መንገዶች ማለትም በልቀት ንግድ፤በማይበክል የእድገት ክንውንውታ እና በጋራ ትግበራ የልቀት ቅነሳ መጠን እንደመደበኛ ሸቀጥ ለገበያ የሚውል ሲሆን እያንዳንዱ የልቀት ቅነሳ መጠን አንድ ቶን ካርቦን ዳይኦክሳይድ ያህል ነው። 
በሌላ በኩል በዝቅተኛ የእድገት ደረጃ ያሉ አገሮች (የእኛን ጨምሮ) የአየር ንብረት ለውጥ በአገራቸው ሊያስከትለው የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችሉ ስራዎችን የሚያካትት ብሔራዊ የማጣጣሚያ መርሐግብር መቅረጽ ይጠበቅባቸዋል። እነዚህ አገሮች ለዚህ መርሐግብር ቀረጻ ይረዳቸው ዘንድ በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ከሚያደርገው የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ከቅጥያ ሁለት አገሮች የገንዘብ ድጋፍ ያገኛሉ። የቀረጹትን መርሐ ግብር ለተጠቀሰው የተመድ አካል ማስረከብ አለባቸው። የተለያዩ አገሮች ከማጣጣሚያ ስልት በተጨማሪ የልቀት ስርየት ስልትም በመቅረጽና በመተገበር ላይ ናቸው።
ኮፐንሀገን ሲታወስ
ደርባን የሚደረገው ጉባኤ ከሁለት ዓመት በፊት ኮፐንሀገን ዴንማርክ ተደርጎ የነበረው አስራ አምስተኛውና ከዛም አምና በካንኩን ሜክሲኮ ተደርጎ የነበረው አስራ ስድስተኛው ጉባኤ ተከታይ ነው። የእነዚህ ጉባኤያት ትኩረት ድህረ ኪዮቶ ሊኖር የሚገባው የልቀት ቅነሳ ስምምነት እንዴት ይቀረጽ እና ምን ይዘት ይኑረው የሚሉት ጥያቄዎች ዙሪያ ላይ ነው። ስምምነቱ ከኪዮቶ ፕሮቶኮል የቅነሳና ገደብ ስሌት ውጪ የነበሩ ባለፉት አስርተ ዓመታት የምጣኔ ሀብት እድገታቸውም የልቀት መጠናቸውም ከምንጊዜውም በላይ እየጨመረ የመጣው እነ ቻይና፤ ህንድና ብራዚል የመሳሰሉትን አገሮች ማካተት እንዳለበት ቢታመንም እንዴት የሚለው ግን ገና ያልተፈታ ጉዳይ ነው።  ፈራሚ ብትሆንም በፕሮቶኮሉ ሳትታሰር የቆየችውን አሜሪካንም በማቀፍ የአየር ንብረት ለውጥን በተጨባጭ የሚገታ እንዲሆን ይፈለጋል - አዲሱ ስምምነት።  
ኮፐንሀገን ተደርጎ የነበረው ኮንፈረንስ ከተለያየ አቅጣጫ በጉጉት ሲጠበቅ እንደነበር ይታወሳል። የተጠበቀው ግን ሳይሆን ቀረ። የሆነውና የተደረገው  ነገር ላይም እንኳን ከሁለት ዓመት በኋላም የተለያየ ግንዛቤ ነው ያለው። ምክንያቱም በከፍተኛ ደረጃ የሚደረግ ፓለቲካንና ምጣኔ ሀብትን የሚነካ ውስብስብ ድርድሮች ስለተካተተበት። እነዚህ ድርድሮች በኮንፈረንሱ የአስራ ሁለት ቀናት ቆይታ የተገደቡ ሳይሆኑ ከዛ በፊት በይፋና ከመጋረጃ በስተጀርባ ይካሄዱ የነበሩ የሁለትዮሽና የቡድን ድርድሮችን ያካትታሉ።   በኮንፈረሱ ወቅትም ቢሆን ይፋዊውና ለሁሉም ተደራዳሪዎች ክፍት ከሆነው ይልቅ በተናጠል ይካሄዱ የነበሩ የሰጥቶ-መቀበል ጥረቶች ጥቂት አልነበሩም።
በቅርቡ በስቶክሆልም ኢንቫይሮንመንት ኢንስቲትዩት የተደረገው ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ የአውሮፓ ህብረት በኮፐንሀገኑ ጉባኤ ወቅት ሲገፋው የነበረው ምክረ ሃሳብ የሦስተኛ ዓለም አገሮችን ጥቅም የሚጎዳ ነበር - የወደፊት የምጣኔ ሀብት እድገታቸውን ጥያቄ ውስጥ በማስገባት። ምክረ ሃሳቡ እስከ 2050 ... የዓለማችን የልቀት መጠን በአምሳ ፐርሰንት እንዲቀንስ ለማድረግና የበለጸጉ አገሮች ደግሞ በሰማንያ ፐርሰንት እንዲቀንሱ የሚያስገድድ ነበር። ብራዚል፤ደቡብ አፍሪካ፤ ህንድና ቻይና ምክረ ሃሳቡ በራሳቸውና በተቀሩት ሦስተኛ ዓለም አገሮች ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖ በማገናዘብ አሜሪካን ከአውሮፓ ህብረት ተባባሪነት ለይቶ በመነጠል የአምስትዮሽ ድርድር አድርገው ለኮፐንሀገኑ ስምምነት መረቀቅና በኋላም መፈረም ምክንያት ሆነዋል። የአውሮፓ ህብረት ያራምደው የነበረው የዴንማርኩ ረቂቅ ተብሎ በሚጠራውና በኋላ ውድቅ በሆነው ረቂቅ ላይ የተካተተው ምክረ ሀሳብ ላይ ላዩን ሲታይ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች የልቀት መጠናቸውን በከፍተኛ ደረጃ እየጨመሩ ሄደው 2030 ... ጀምሮ ግን እንዳይጨምሩ ሲሆን በዝርዝር ሲታይ ገን ኦሮማይ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያለው የነዚህ አገሮች የነፍስ ወከፍ ልቀት መጠን አስር ዓመት ቀድሞ 2020 ... ጀምሮ እንዲቀንስ የሚያደርግ ነው (ምጣኔ ሀብታዊ ትርጉሙየእድገት ፍሬን ያዙቢያንስወደ ዝቅተኛ ማርሽ ቀይሩነው) 
ከካርቦን ሱስ የተላቀቀችኢትዮጵያ 
አገራችን የኪዮቶ ፕሮቶኮልን ሚያዝያ 6 1997 .. አጽድቃ በዛው ዓመት ሐምሌ 6 በሥራ እንዲውል አድርጋለች። ይሁን እንጂ ከላይ እንደተጠቀሰው ከቅጥያ አንድ ውጪ በመሆኗ አስገዳጅ የልቀት ቅነሳ ወይም ገደብ የለባትም። ከአራት ዓመት በፊት የአየር ንብረት ለውጥ ብሔራዊ የማጣጣሚያ መርሐግብር ቀርጻ ለተመድ አስረክባለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በቅርቡ በዴንማርክ ኮፐንሀገን በተደረገው የሉላዊ አረንጓዴ እድገት መድረክ ላይ ኢትዮጵያ 2025 ... (13 ዓመታት ውስጥ የልቀት መጠኗን ዜሮ ለማድረግ እንደምትሰራ ተናግረዋል። በወቅቱ ከተናገሩት ተቀንጭቦ (ሙሉ ንግግራቸውን ከመድረኩ አዘጋጆች ለማግኘት ያደረጉት ጥረት አልተሳካም) የሰማሁት ጥቅል አባባል በመሆኑ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ያጭራል።
ዜሮ የሚገባው የልቀት መጠን ውስጥ የተካተቱት በካይ ጋዞች እነማን ናቸው? ካርቦንዳዮክሳይድ ብቻ ነው ወይስ ሌሎች ጋዞችን ለምሳሌ ሚቴንን ይጨምራል? ከምንጭ አንጻርስ የኢንዱስትሪው ልቀት ብቻ ማለታቸው ነው? ወይስ የትራንስፖርትና የግብርናንም ይጨምራል? ስሌቱስ ጥሬ ልቀት (እንደወረደ) ላይ የተመሰረተ ነው ወይስ የተጣራ ልቀት (በደን ልማት የሚታቀበው ካርቦን ከጥሬ የካርቦን ልቀት ተቀንሶ) ነው? ለነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መልስ የያዘ መንግሥታዊ ዶሴ እስካሁን አላየሁም። ይህ የጠቅላይ ሚንስትሩ አባባል በአምስቱ ዓመት የእድገትና የልውጠት ዕቅድ ውስጥ ለዘብ ባለ መልክና በሁለት ዓመት ተራዝሞ (2020 ..) ቀርቧል። በእሳቸው የተነገረው የአገሪቱ የልቀት መጠን ዜሮ የማድረግ ግብ አንድምታና በእድገትና ልውጠት ዕቅዱ ላይለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገርና በካርቦን ሱስ ያልተጠመደ ኢኮኖሚእውን ማድረግ ተብሎ የቀረበው ግብ አንድምታ ይለያያሉ።  ግቡን ለማሳካት ልንከተለው የሚገባን ስልትም የሚወሰነው በግቡ ዙሪያ ያለን የጠራ መረጃ ነው። ኢትዮጵያ አርአያነት ያለው ሩቅ ተመልካች ግብ ማስቀመጧን እደግፋለሁ(በጣት የሚቆጠሩ አገሮች ናቸው ያንን ያደረጉት) ይሁንና የተቀመጠው ግብ በተሻለ ወጪ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት እድገትና የሥራ እድል የሚፈጥሩ የልማት ሥራዎችን (ከዓመታት በፊት ከአለም ባንክ ተቃውሞ የቀረበበትን ከድንጋይ ከሰል ኃይል ማመንጨትን ጨምሮ) የሚገድብ መሆን የለበትም - ሌላ ቀን እመለስበታለሁ።  
በሚቀጥለው እትም ደግሞ የደርባኑ ጉባኤ ላይ የተለያ አገሮችና ስብስቦች ሚና፤ የሚጠበቀው ውጤትና ሌሎች ጉዳዮችን እተነትናለሁ።
==========
ጥቅምት  11  ቀን 2004 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org


No comments: