Saturday, November 12, 2011

350 የካርበን ዳይኦክሳይድ ፊኛዎች?


(ጌታቸው አሰፋ)ይህ ካለፈው የቀጠለ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የሚያጠነጥነው ጽሑፍ ነው። ለዛሬ ስለ ሳይንስ በተቻለ መጠን ቀለል አድርገን እናወራለን። የአየር ንብረት ለውጥ ማለት በዓለም ደረጃና በረጅም ጊዜ የሚታዩ የለውጥ መገለጫ የሆኑት የከባቢ አየር ሙቀት፤ የዝናብ መጠንና የመሳሰሉት መገለጫዎች መለወጥ ማለት ነው። በአንድ ቦታና በአጭር ጊዜ ያለው የአየር ሁኔታ ለውጥ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ሊገናኝም ላይገናኝም ይችላል። 
የመስተዋታዊ ቤተ-ተክል ጠንቅ
የአየር ንብረት ለውጥ ሉላዊ ሞቅታ ተብሎም ይጠራል። ለውጡም የሚገለጸው በዓለም የከባቢ አየር አማካይ ሙቀት መጨመር ነው። በሌላ በኩል የመስተዋታዊ ቤተ-ተክል ጠንቅ ተብሎም ይታወቃል። ይህን ስም ያገኘው ግድግዳቸውና ጣራቸው ከመስተዋት ወይም ከፕላስቲክ ከሚሰሩት ለአትክልቶች ለአበቦችና ለመሳሰሉት ማልሚያ ከሚሆኑት ቤቶች ጋር በተያያዘ ነው።  በነዚህ ቤቶች የፀሐይ
የሚታይ ጨረር ከገባ በኋላ ቀቱ የሚጨምረው ውስጥ ያለው አየር ወደ ውጪ በሚፈለገው መጠን ስለማይወጣ ቤቶቹ ውስጥ ያለው ሙቀት ከአካባቢው የአየር ሙቀት የበለጠ ከፍ ያለ ነው። በተወሰነ ደረጃም ቤቶቹ ውስጥ ያሉት ነገሮች ከተቀበሉት ሙቀት የተወሰነውን በተመላሽ ጨረር መልክ ሲተፉት መስተዋቱ ደግሞ ተመላሽ ጨረርን ከሚታይ ጨረር ባነሰ መጠን ስለሚያሳልፍ  የተወሰነው ተመላሽ ጨረር ቤቶቹ ውስጥ ይቀራል። ይህ ሂደትም ድርሻው ትንሽ ቢሆንም የቤቶቹ ውስጥ ሙቀት እንዲጨምር የተወሰነ አስተዋጽኦ ያደርጋል። በተመሳሳይ መልኩ የአየር ንብረት ለዋጭ ጋዞች የምድራችን ከባቢ አየር ሙቀት ከወትሮው የበለጠ ከፍ እንዲል ያደርጉታል። ምሳሌ ዘይሐጽጽ እንዲል መጽሐፍ ውስብስብ የሆነው የአየር ንብረት ለውጥ ሂደት በመስተዋታዊ ቤተ-ተክል ጠንቅ ሂደት ሙሉ በሙሉ የሚገለጽ አይደለም።
ባለፈው ጽሑፍ እንደገለጽኩት የአየር ንብረት ለዋጭ ጋዞች በርካታ ቢሆኑም በኪዮቶ ስምምነት ውስጥ የተካተቱት ዋናዎቹ ግን ስድስት ናቸው። ከነሱም በብዛት ስሙ የሚነሳው ካርበን ዳይኦክሳይድ ነው። ይህ ጋዝ በከባቢ አየር ውስጥ በተፈጥሮ ከሚገኙት ናይትሮጅንና ኦክስጅን ቀጥሎ ድርሻ ያለው ጋዝ ነው። ድሮ ድሮ የከባቢ አየር ዜሮ ነጥብ ዜሮ ሦስት ፐርሰንቱ ካርበን ዳይኦክሳይድ ነበር (አሁን ጨምሯል ወደታች እመለስበታለሁ) ይህ መጠን ምን ማለት ነው? ከባቢ አየር እንዳለ አንድ ሚልዮን እኩል መጠን ያለቸው ፊኛዎች አድርገን ብንወስደው ከሚልዮኖቹ ፊኛዎች ውስጥ ሦስት መቶው ብቻ ናቸውንጹህ ካርበን ዳይኦክሳይድ የሚይዙት ማለት ነው።
ካርበን ዘሕይወት፤ ካርበን ዘቅሪት
ካርበን ዳይኦክሳይድ ጣዕም አልባ፤ ቀለም የለሽና አይሸቴ ጋዝ ነው። የስራ ድርሻው ግን ከሕያዋን ሕይወትና ሞት ጋር በእጅጉ ይያያዛል። ማንኛውም የሞቀ አካል (አነሰም በዛም) ሙቀት ይተፋልና ምድራችንም በፀሐይ የሚታይ ጨረር ስትሞቅ ከምታገኘው ሙቀት የተወሰነው አይነቱ ተቀይሮ ተመላሽ ጨረር ሆኖ ወደ ሕዋ የመልስ ጉዞ ያደርጋል። ተመላሽ የሙቀት ጨረሮች በከባቢ አየር ከሚገኘው ካርበን ዳይኦክሳይድ ጋር ሲገናኙ ጨረሮቹ ካርበን ዳይኦክሳይድ ውህዶች ይመጠጣሉ። በመጠጣው ወቅት የጋዞቹ የኃይል መጠን ስለሚጨምር የከባቢ አየር ሙቀትም በዛው ይጨምራል። ይህ ተፈጥሮአዊ ሂደት ነው።
ይህ የካርበን ዳይኦክሳይድ ተፈጥሮአዊ አቅም ለምድራችን ማኅደረ ሕይወት መሆንና ሆኖ መቀጠል እጅግ ጠቃሚ ነው። ይህ ጋዝ በከባቢ አየር ውስጥ ባይኖር ኖሮ የዓለማችን የከባቢ አየር ሙቀት በአማካይ 14 እና 15 ዲግሪ ሴንት ግሬድ መሆኑ ቀርቶ -18 እና -19 ዲግሪ ይሆን ነበር። ይህም ማለት አሁን ካለበት ወደ 33 ዲግሪ ይቀንስ ነበር ማለት ነው - ከአቅመ-ሕያዋን በላይ ይሆን ነበር ማለት ነው።
ስለዚህ ካርበን ዳይኦክሳይድ ተመላሽ ጨረሮችን መጥጦ የማስቀረት አቅሙ ለሕይወት አስፈላጊ ነው።  የከባቢ አየር ሙቀት በጣም ወርዶም ሆነ በጣም ጨምሮ ለሕይወት አስጊ ሁኔታን እንዳይፈጥር በከባቢ አየር ውስጥ ያለው የዚህ ጋዝ መጠን ልክ ወሳኝ ነው።
የካርበን ዳይኦክሳይድና መሰል ጋዞች መጠን በከባቢ አየር ላይ በጨመረ መጠን የምድራችን ከባቢ አየር ሙቀት ደግሞ እንዲሁ ይጨምራል። ካርበን ዳይኦክሳይድ ሲጨምር የከባቢ አየር ሙቀት እንደሚጨምር በቁጥር በማስቀመጥ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ያጠናው ስዊድናዊው ሳይንቲስት ስቫንት አርሄነስ ሲሆን ጊዜውም 1896 ... ነበር (የጣልያን ወራሪ በጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ወላፈን በተለበለበበት ዓመት)
እሳተ ገሞራና የመሳሰሉት የተፈጥሮ ክስተቶች ሲከሰቱ ካርበን ዳይኦክሳይድም ሆነ አንዳንድ አየር ንብረት ለዋጭ ጋዞች ወደ ከባቢ አየር በገፍ ይለቀቃሉ። ከነዚህ አይነት ተፈጥሮአዊ ልቀቶች ይበልጥ አሳሳቢ የሆነው ግን ከዛሬ ሁለት መቶ ስድሳ ዓመታት ወዲህ (ድኅረ ኢንዱስትሪ አብዮት)የድንጋይ ከሰል፤ የነዳጅ ዘይትና የተፈጥሮ ጋዝ በስፋት ከሚማግደው የምጣኔ ሀብት አደረጃጀት ጋር ተያይዞ የሚለቀቀው የካርበን ዳይኦክሳይድ መጠን በከፍተኛ ደረጃ መጨመር ነው። ይህ ልቀት በከባቢ አየር ያለውን የካርበን ዳይኦክሳይድ መጠን እንዲጨምር አድርጎታል።
በቅድሙ የሚልዮን ፊኛዎች ምሳሌ ብንቀጥል ከኢንዱስትሪ አብዮት በፊት 260 እስከ 270 ፊኛዎች ደረጃ ተወስኖ የነበረው የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን የዛሬ ሀምሳ ዓመት ወደ 310 ጨምሮ አሁን በዚህ ዓመት ደግሞ ወደ 392 ፊኛዎች ደርሷል። የዓለም ምጣኔ ሀብት ከካርበን ጋር ያለው ቁርኝት እስካሁን እንዳለው የሚቀጥል ከሆነ እንደቆየነው በዓመት ሁለት ፊኛ ካርበን ዳይኦክሳይድ ጭማሪ እናያለን።  
በከባቢ አየር ከሚገኘው ካርበን ዳይኦክሳይድ አረንጓዴ ተክሎች የተወሰነውን ይምጋሉ (ከእርስዎ እስትንፋስ የወጣችውን ካርበን ዳይኦክሳይድንም ይጨምራል) ካርበኑም ለሕያው ቁስ ማምረቻ ይውላል- በአረንጓዴው ፋብሪካ። ሕያው ቁሱ በዘመናዊም ሆነ በጥንታዊ መንገድ ለማገዶነት ሲውል ከከባቢ አየር የተማገው ካርበን ዳይኦክሳይድ እንደገና ወደ ከባቢ አየር ይለቀቃል። ጥሩ የደን ልማት ባለበት ሁኔታ ካርበን ዳይኦክሳይዱ እንደገና በአጭር ጊዜ ውስጥ በሌላ አረንጓዴ ተክል ስለሚማግ በከባቢ አየር ላይ ጭማሪ የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን አያስከትልም። ይህ አይነቱን ካርበንካርበን ዘሕይወትእንለዋለን። በሌላ መልኩ በድንጋይ ከሰልነት፤ በነዳጅ ዘይትነትና በተፈጥሮ ጋዝነት ለዘመናት የቆየውን ካርበን ከተከማቸበት ሥፍራ (በአብዛኛው ጥልቅ ከርሰ ምድር) አውጥተን በኢንዱስትሪ ነዳጅነት፤ በኃይል ማመንጫነት፤ ለትራንስፓርት አገልግሎትና ለመሳሰሉት ስናቃጥለው የሚለቀቀው ካርበን የአየር ንብረት ለውጥን ያፋጥናል። ይህኛውንካርበን ዘቅሪትእንለዋለን።
ሳይንሳዊ ጥናት
የአየር ንብረት ለውጥን በሚመለከት የሚወጡ ጠንካራ ሳይንሳዊ ጥናቶች ለተግባራዊ እርምጃዎች መነሻ መሠረት ይሆኑ ዘንድ በማመቻቸት ዓለም አቀፍ የሳይንቲስቶች ጉባኤ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ይህ የሳይንቲስቶች ጉባኤ የአየር ንብረ ለውጥ በይነ መንግሥታት ጉባኤ ተብሎ የሚታወቅ ይታወቃል። የተቋቋመው የተ.. አካላት በሆኑት የዓለም ሜትሮሎጂ ድርጅትና የአካባቢ ፕሮግራም ድርጅት ሲሆን ከተቋቋመ እነሆ ከአንድ ወር በኋላ ሀያ ሦስት ዓመታት ይሆነዋል። ቡድኑ የራሱ ምርምሮችን አያደርግም። ጥራታቸው ከፍተኛ የሆኑና በአቻ ግምገማ አልፈው ለህትመት የበቁ ጥናቶችን መሰረት በማድረግ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የግምገማ ሪፖርቶችን ያወጣል።
ይህ ቡድን እስካሁን አራት ሪፖርቶችን ያወጣ ሲሆን የመጀመሪያውን ከሀያ አንድ ዓመታት በፊት፤ ሁለተኛውን ከአስራ ስድስት ዓመታት በፊት፤ ሦስተኛውን ከአስር ዓመታት በፊትና አራተኛውን ደግሞ ከአራት ዓመታት በፊት አውጥቷል። ቀጣዩ ሪፓርት ከሦስት ዓመታት በኋላ ያወጣል ተብሎ ይጠበቃል።
 እያንዳንዱ ጋዝ ተመላሽ የሙቀት ጨረርን የማስቀረት አቅሙ ይለያያል። ልዩነቱን የሚያሳዩ  በዚህ ቡድን የተገመገሙ አባዢዎች ጠቅላላ ካርበን ዳይኦክሳይዳዊ-አቻን ለማስላት ይጠቅማሉ። ካርበን ዳይኦክሳይድን እንደ መነሻ በማድረግ በንጽጽር የሚቴን ሀያ አንድ እጥፍ ሲሆን የናይትሮስ ኦክሳይድ ደግሞ 310 ነው። የሃይድሮ ፍሎሮ ካርበንስ (የተለያዩ ጋዞች የወል ስም ነው140 እስከ 11 700 ይደርሳል። የፐርፍሎሮካርበንስ 6500 እስከ 9200 (የተለያዩ ጋዞች የወል ስም ነው) ሲሆን፤ የሰልፈር ሄክሳ ፍሎራይድ  23900 ነው። ይህ ማለት አንድ አይነት የልቀት መጠን ቢኖራቸውም የከባቢ አየር ሙቀትን የመጨመር አቅማቸው ከላይ በተጠቀሱት አኃዞች መሠረት ይለያያል።
በአራተኛው ሪፓርት ላይ እንደተመለከተው በያዝነው ክፍለ ዘመን መጨረሻ (ከዛሬ ሰማንያ ዘጠኝ ዓመታት በኋላ) አማካይ የምድራችን ሙቀት ከዛሬ ሠላሳና ሀያ ዓመታት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር 1.1-እስከ 6.4 ዲግሪ ሴንትግሬድ ይጨምራል። የተሻለ ግምት ተብሎ በሪፓርቱ የተቀመጠውን ደግሞ ስንመለከት  1.8 እስከ 4.0 ዲግሪ ሴንትግሬድ የሚደርስ ጭማሪ ይሆናል። ይህ ጭማሪ አማካይ እንደመሆኑ መጠን ሁሉም የዓለማችን ክፍሎች ላይ አንድና ወጥ ሆኖ አይከሰትም። ለምሳሌ በአብዛኛው የሰሜን አሜሪካ ክፍል፤ አፍሪካ በሞላ፤ አውሮፓ፤ ሰሜንና መካከለኛው ኤዥያ እንዲሁም አብዛኛው የመካከለኛውና የደቡብ አሜሪካ አገሮች የከባቢ አየር ሙቀታቸው ከአማካይ ጭማሪው በላይ ይሆናል ተብሎ ነው የሚጠበቀው።   
በአሁኑ ወቅት ስነምህዳራዊ ሀብቶችና ውቅያኖሶች ማቀብ ከሚችሉት መጠን በላይ እየተለቀቀ ያለው የካርበን ዳይኦክሳይድ ልቀት ያለገደብ የሚቀጥል ከሆነ የያዝነው ክፍለ ዘመን ከማለቁ በፊት የካባቢ አየር ሙቀት ጭማሪው፤ የታላላቅ ዋልታዊና አህጉራዊ የበረዶ ግግሮች መቅለጥ፤ የባህር ወለል ከፍ ማለት፤ የድርቅና ጎርፍ መስፋፋትና መደጋገም፤ የቆላ በሽታ ወደ ደጋው መውጣት ወዘተ እየባሰ እንዳይሄድ ያሰጋል (ላለማስፈራራት)
ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ሊመጡ የሚችሉ መጠነ ሰፊና አይነት ብዙ ጥፋቶች እንዳይከሰቱ ለማድረግ ቀይ መስመር ተደርጎ እየተወሰደ ያለው በዓለም አማካይ የከባቢ አየር ሙቀት ጭማሪው ከሁለት ዲግሪ ሴንትግሪድ በላይ እንዳይሆን ማድረግ የሚል ነው። ይህ ጭማሪ ቅድመ የኢንዱስትሪ አብዮት ከነበረው የከባቢ አየር ሙቀት ጋር ሲነጻጸር ማለት ነው። ይህ የሁለት ዲግሪ ጭማሪን ለማምጣት የካርበን ዳይኦክሳይድ ፊኛዎች ቁጥር በአንድ በኩል 450 መሆን አለበት የሚል እምነት ቀደም ብሎ ነበር። አሁን ደግሞ 350 ነው እንደ ኢላማ መያዝ ያለብን የሚል ክፍልም አለ። በሌላ በኩል የፈንጂ ወረዳው ከሁለት ዲግሪ በላይ ሳይሆን ከአንድ ነጥብ አምስት ዲግሪ በላይ ተደርጎ መወሰድ አለበት ብለው የሚታገሉም አሉ። በቀጣዩ ጽሑፌ እመለስበታለሁ። አስራ ሰባተኛው የአየር ንብረት ለውጥ ባለጉዳይ አካላት ጉባኤ የፊታችን ህዳር 18 እስከ  ህዳር 29 በደቡብ አፍሪካ ደርባን ከተማ ተካሂዶ እስከሚጠናቀቅ ድረስ በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች ላይ መጻፌን እቀጥላለሁ። ሰላም ለሁላችን! ሰላም ለአየራችን!
==========
ጥቅምት  25  ቀን 2004 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: