Friday, February 3, 2012

2 ዲግሪ ሴንትግሬድ፤100 ቢልዮን ዶላር

(ጌታቸው አሰፋ, ኅዳር  9  ቀን 2004 ዓ.ም) ባለፈው ጽሑፍ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዘውን ሳይንስ ተመልክተናል። ዛሬም በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ዙሪያ ነው የሚጻፈው።  ከዘጠኝ ቀን በኋላ ማለትም የፊታችን ህዳር 18 17ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ባለጉዳይ አካላት ጉባኤ በደቡብ አፍሪካ ደርባን ከተማ ይጀመራል። በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ የሚጠናቀቅ ከሆነ ጉባኤው እስከ ህዳር 29 ይቆያል። በአውሮፓ ህብረት ለረጅም ጊዜ ሲገፋበት የነበረው የሁለት ዲግሪ ሴንትግሬድ(ቅድመ ኢንዱስትሪ አብዮት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር) ቀይ መስመር
የዛሬ ሁለት ዓመት በኮፐንሀገን ስምምነት ውስጥ እንዲሰፍር ተደርጓል። የበለጸጉት አገሮች ፓለቲከኞች ከሞላ ጎደል በዚህ ቀይ መስመር ይስማማሉ። የማይስማሙት ያላደጉት አገሮችና በተለይ ደግሞ ትንንሾቹ ደሴታዊ አገሮች ናቸው። እነሱ የሚሉት የሁለት ዲግሪ ሴንትግሬድ የጭማሪ ጣራ ከፍ አለ። እንደ ዓለም ኅብረተሰብ ግባችን የአንድ ነጥብ አምስት ዲግሪ ሲንትግሬድ ጣራ ነው መሆን ያለበት ባዮች ናቸው። ይህ የትንንሽ ደሴታዊ አገሮች ህብረትና የበርካታ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ስብስብ አቋም በኮፐንሀገኑ ጉባኤ ጊዜ ሁለንተናዊ ተቀባይነት ባያገኝም በበለጸጉት አገሮች ውስጥ ባሉ የአካባቢ አቀንቃኞችና ሌሎች ተቆርቋሪዎች ድጋፍ ግን አለው። አሁን ባለንበት ደረጃ ራሱ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰባቸው ያሉ አገሮች አሉ። የነጥብ አምስት ዲግሪ ጭማሪ ልዩነት ማለት ለነሱ ብዙ ጉዳት ያመጣል። የበለጸጉት አገሮች ግን ግቡን በነጥብ አምስት ዲግሪ ዝቅ ማድረግ የሚያስከፍላቸውን ምጣኔ ሀብታዊና ሌላ ፓለቲካዊ ዋጋ ስለሚያሰጋቸው የአንድ ነጥብ አምስት ዲግሪ ሴንትግሬድ ጣራ አራማጅ አገሮችን ጩኸት ጆሮ ዳባ ልበስ ብለውታል። በኮፐንሀገንና በካንኩን ስምምነቶች የሁለት ዲግሪው እንደ ጣሪያ የገባ ሲሆን አንድ ነጥብ አምስቱ በረጅም ጊዜ ተጨማሪ ሳይንሳዊ ጥቆማዎችን መሠረት አድርጎ የሚገመገም ብቻ ተብሎ ተጠቅሷል። ከዚህ ባለፈ አንድ ነጥብ አምስትን እንደ ግብ ማራመድ ድርድሮች ስኬታማ እንዳይሆኑ አስዋጽኦ እንደማድረግ እየተቆጠረ ነው።
ሊጀመር ከሁለት ወር ያነሰ ጊዜ በሚቀረው የምዕራቡ ዓለም አዲስ ዓመት  ማብቂያ ላይ የሥራ ዘመኑ የሚያከትመው የኪዮቶውን ስምምነት  መፃኢ እድል(መራዘም፤ መተካት ወይም ማብቃት) የደርባኑ ጉባኤ ዋነኛ አጀንዳ ነው። በደቡብ አፍሪካ በቀላሉ ስምምነት ይደረስባቸዋል ተብለው ከሚጠበቁት ጉዳዮች ውስጥ የማጣጣም ጉዳዮች፤ የግብርና፤የቴክኖሎጂ፤ ከደን ምንጣሮና ከደን ጉስቁልና ጋር የተያያዘ የልቀት ቅነሳ እና ብሔራዊ ተሰማማሚ የስርየት መርሐ ግብር የተመለከተቱት ናቸው። ይወሰናል። የልቀት ቅነሳ መጠና የገንዘብ ድጋፍም ዋናዎቹ ይሆናሉ።
የልቀት ቅነሳ  መጠን 
ኪዮቶን ሊተካው የሚችለው ስምምነት ቅርጽና ይዘት ምን ይምሰል? ለሚለው ጥያቄ ቢያንስ የመነሻ መልስ ይገኛል ተብሎ ተስፋ ይደረጋል።  በዓለም አቀፍ ደረጃ ምን ያህል የልቀት ቅነሳ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ይደረግ? የትኞቹ አገሮች በምን ያህል መጠን በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ይቀንሱ? 
በቅርቡ የወጣ ጥናት እንደሚያሳየው እየቀጠለ ያለውን የከባቢ አየር ሙቀት ጭማሪ ጣራ ከሁለት ዲግሪ እንዳይበልጥ ለማድረግ የዓለም አገሮች የጋራ ልቀት መጠን (የካርቦን ዳይኦክሳይድ አቻ) በ 2020 እ.አ.አ. ከ44 ቢልዮን ቶን በታች መሆን ይኖርበታልይሁንና ዓለማችን እንደ እስከዛሬው የምትቀጥል ከሆነ በጊዜው (ከዘጠኝ ዓመት በኋላ) የሚኖረው የልቀት መጠን መሆን ካለበት በ12-16 ቢልዮን ቶን የበለጠ ይሆናል (ከ56 እስከ 60 ቢልዮን ቶን)። አሁን ወደ 48 ቢልዮን ቶን የሚሆነው ጠቅላላ ልቀት ወስደን በኮፐንሀገኑ ስምምነት መሠረት ቃል የተገባው ጠቅላላ ቅነሳ በተግባር ይውላል ብለን እንኳን ብናስብ ልቀቱ ወደ 49 ቢልዮን ቶን ነው የሚሆነው - በ2020 ። የአምስት ቶን ክፍተት ያስከትላል ማለት ነው። ይህ መጠን የዛሬ ስድስት ዓመት በዓለም የነበሩት መኪኖች ጭነቶችና አውቶብሶች የልቀት መጠን የሚያህል ነው። የተገባው ቃል አነስተኛ መሆን ብቻ ሳይሆን ላይፈጸም መቻሉም ነው።
በስፋት የሚጠቀሱት የልቀት ቅነሳ የጊዜ ገደቦች እ.አ.አ. 2020 እና 2050 ናቸው። እየተነሱ ያሉት ቅነሳዎች ደግሞ በፐርሰንት 20፤ 30ና 80 ሲሆኑ በአውሮፓ ህብረት እስከ 2020 እ.አ.አ. 20 ፐርሰንት እንቀንስ በሚሉና በ30 ፐርሰንት እንቀንስ በሚሉት አገሮች ልዩነት አለ። ሁለቱም ግን እስከ 2050 እ.አ.አ. 80 ፕርሰንት መቀነስ ላይ ይስማማሉ። እነ ፖላንድ የመሳሰሉት አገሮች የ2020ው የቅነሳ ግብ ወደ 30 ፐርሰንት ከፍ ከተደረገ ምጣኔ ሀብታዊ ተጽእኖ ያሳድርብናል ከሚል ስጋት የተነሳ ከዚህ ጋር የተያያዘ አሳሪ ስምምነት ውስጥ መግባት አይፈልጉም። ከፍ ላለ ቅነሳም ቢሆን ዝግጁ የሆኑ እንደ ስዊድን የመሳሰሉት አገሮች ደግሞ በአንጻሩ  በ2020 40 ፐርሰንት ድረስ ለመቀነስ እያለሙ ነው። የሆነ ሆኖ የአውሮፓ ህብረት ኪዮቶ ታድሶ ቢቀጥል አብሮ እንደሚቀጥል የገለጸ ሲሆን እንደ ቅድመ ሁኔታ ግን ሌሎች የበለጸጉ አገሮች  መቼና እንዴት በሕግ አሳሪ ወደሆነ ዓለም አቀፋዊ የቅነሳ ስምምነት እንደሚቀላቀሉ በግልጽ የሚያሳይ ስምምነት መኖር አለበት ባይ ነው። እስካሁን የኪዮቶ አካል የነበሩት አሁን ግን እያንገራገሩ የሚገኙት ካናዳ፤ጃፓንና ራሺያ አሁኑኑ አብረውን የታደሰ ኪዮቶ ውስጥ ካልቀጠሉ ሞተን እንገኛለን አንልም ባይ ነው - ህብረቱ። በኪዮቶ ለታቀፉት አገሮች የማራዘሚያ ስምምነት በአንድ በኩል ለሌሎች (አሜሪካ ፤ ቻይና፤ ህንድ፤ ብራዚል) ደግሞ አሳሪ የቅነሳ ግብ የሚያካትት  ስምምነት ቢበጅ  ክፍተት ሳይፈጠር መቀጠል ይቻላል የሚል እምነት አለው።
እነ አሜሪካ ካናዳ፤ ጃፓንና ራሺያ ኪዮቶ ከእነአካቴው መተካት ወይም ማብቃት ነው ያለበት ይላሉ። በተጨማሪም የሚተካው ስምምነት ደግሞ ከገንዘብ ድጋፍም ሆነ ከሌላ ቅድመ ሁኔታ ጋር ባልተያያዘ መልኩ እነ ቻይና፤ ህንድና ብራዚልን ወደ ሕጋዊ አሳሪ ስምምነት እንዲገቡ የሚያደርግ መሆን አለበት ባዮችን ናቸው።
የአፍሪካ ቡድን፤ ቡድን ሰባ ሰባትና ቻይና ተብለው የሚጠሩት መቶ ሰላሳ ሁለት አገሮች የኪዮቶ ስምምነትን ከጨዋታ ውጪ መሆንን ይቃወማሉ። በደርባንም ሲሄዱም የኪዮቶን መራዘም እንደ ግብ ይዘው ነው የሚሄዱት። እነዚህ ታዳጊ አገሮችና እነ ቻይና፤ ህንድና ብራዚል የሚያደርጉት የሥርየት ሥራዎች ከኪዮቶ ስምምነት ውጪ መሆናቸው ይታወቃል። 
ፓናማ ላይ በተደረገው ቅድመ ደርባን ውይይት የኪዮቶ ስምምነትን በሦስት ዓመት የሚያራዝምና ሕጋዊ መሠረትንና የተጀመሩ እንዳይጠፉ ሆነው ከዛም ሁለንተናዊ ስምምነት ከደርባን በኋላ የሚደረስበትን መንገድ መፈለግ የሚለው ድጋፍ አግኝቷል።
ከላይ የተገለጸው ሁሉም አገሮችን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ አሳሪ የቅነሳ ስምምነት  ውስጥ ይካተቱ የሚለው የነአሜሪካ ሀሳብ ላይ ላዩን ፍትሐዊ ቢመስልም ለኪዮቶ ስምምነት መነሻ የሆነው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ማዕቀፍ አካል የሆነው “የጋራ ግን ተመጣጣኝ ኃላፊነት” ተበሎ የሚታወቀው የየአገራቱን ታሪካዊ የብክለት መጠን ታሳቢ መሆን እንዳለበት እውቅና ከሚሰጠው ሀረግ  ጋር የሚጻረር ነው።
በበለጸጉት አገሮች በኩል በደርባንና ድኅረ ደርባን በሚኖሩት ድርድሮች ወቅት ተቀባይነት እንዲያገኝ እየተገፋ ያለው የስምምነት መነሻ ልል የስርየት ወሰንና ዓለም አቀፍ ያይደለ ብሔራዊ የቅነሳ ቃል መግባትና የግምገማ ስልት ያካተተ  የ“ደስ ያለህን ያህል አድርግ” አካሄድ ያለበት ነው። ይህ አካሄድ የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን የመፍታት ሸክም ለመፈጠሩ እጅግ አነስተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ የመዘዙ ግን ዋነኛ ተጠቂ ወደሆኑት ታዳጊ አገሮች የሚገፋ ነው። እንዲህ አይነት የመፍትሔውን ድርሻ ኢፍትሃዊ በሆነ መልኩ የማሸክም አካሄድ በታዳጊ አገሮች ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ላይ የሚያመጣው ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል።
ኪዮቶን ጥሩ ያደረገው አሳሪና ዓለም አቀፍ መሆኑ እየታወቀ ኃላፊነቱን ወስደው የመሪነት ሚና መጫወት ይገባቸው በነበሩት አገሮች ዘንድ ከዓለም አቀፍ ስምምነት የመሸሽ አዝማሚያ መታየቱ ስጋትን ይፈጥራል።
ሀሳቡ ወደ ስምምነት የመቀየር እድል ከተሰጠው አማካይ የዓለማችን የከባቢ አየር ሙቀትን ወደ አምስት ዲግሪ (ሁለት ዲግሪም አንድ ነጥብ አምስት ዲግሪም ሳይሆን) የሚያደርስ ሲሆን በአፍሪካ ደግሞ ከሰባት እስከ ስምንት ጭማሪን ሊያመጣ ይችላል - ትኩሳት።
የገንዘብ ድጋፍ 
ባላደጉት አገሮች ውስጥ ለሚደረጉ የማጣጣሚያና የማስተሰሪያ መርሐ ግብሮች ድጋፍ የሚውል ገንዘብ ከየት ይምጣ? ማን ያስተዳድረው? እንዴትና መቼ ይከፈልና ተያያዥ ጥያቄዎችን ይመልሳል ተብሎ ይጠበቃል - ደርባን።
ካቻምና ህዳር በኮፐንሀገን ዴንማርክ ከዛ ደግሞ አምና በተመሳሳይ ወር ካንኩን ሜክሲኮ ላይ የበለጸጉት አገሮች ከ2020 እ.አ.አ ጀምሮ በዓመት 100 ቢልዮን ዶላር በመለገስ አረንጓዴ የአየር ንብረት ፈንድ ለማቋቋም ቃል ሲገቡ እንዲሁም መነሻ የሚሆን ፈጣን ድጋፍ ደግሞ እስከ ሚቀጥለው ዓመት (2012 እ.አ.አ.)  ደግሞ 30 ቢልዮን ዶላር እንሰጣለን ብለው ነበር። ከኮፐንሀገኑ ስምምነት ሦስት ወር በኋላ የካቲት ውስጥ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ሰያሚነት የገንዘብ ድጋፉን ከየት ሊገኝ እንደሚችል አጥንቶ እንዲያቀርብ የተቋቋመ ቡድን ነበር። በዚህ ቡድን ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና የኖርዌዩ አቻቸው የንስ ስቶልተንቤሪ  (የእንግሊዙን ጎርደን ብራውንን በመተካት) በሰብሳቢነት ያሉ ሲሆን በአባልነት ደግሞ የአንድ አገር መራሄ መንግሥት፤ የተለያዩ አገር ሚኒስትሮች፤ ምሁራኖች፤ ባለሀብቶችና የባንክ ተወካዮች ተካተዋል። ቡድኑ በተቋቋመ በአስራ አንድ ወሩ ውስጥ ለተመድ ዋና ጸሐፊ ያቀረበው ሪፓርት ላይ በ2020 እ.አ.አ በዓመት 100 ቢልዮን ማሰባሰብ ቀላል ባይሆንም የሚቻል መሆኑን ነው ያመላከተው። 
እንደ ማጠቃለያ ምናልባት ኪዮቶ ስምምነት ያለ አሜሪካ፤ ካናዳ፤ ጃፓንና ራሺያ ተሳታፊነት ሊራዘም ይችላል። የአውሮፓ ህብረት ልቀቱን በቀላሉ መቀነስ ስለሚችልና ስለቀነሰም ለቅነሳው የሚረዱ ቴክኖሎጂዎችን በማበልጸግና በመሸጥ ወደፊት ተጠቃሚ ይሆናል። የአፍሪካ ቡድን አሳሪ ወደሆነና በረጅም ጊዜ የአህጉሪቱን እድገት ለሚገድብ ስምምነት ድጋፍ እንዳይሰጥ ብትሰጉ አይፈረድባችሁም። ዝርዝሩ ባይታወቀም የአውሮፓ ሰዎችና የአፍሪካ ቡድን በቅርቡ ድርድር ነክ ውይይት እያደረጉ እንደነበር ይታወቃልና። ደርባን ጥቂት አገሮች ሌሎችን ትተው ስምምነት ለመድረስ የብቻ ድርድር ያደረጉበት የኮፐንሀገን ጉባኤ አይነት እንዳይሆን እየተመኘን እንጠብቃለን። በሚቀጥለው የምንገናኘው ጉባኤው ከተጀመረ በኋላ ነው - ስለሱ እናወራለን። 
==========
ኅዳር  9  ቀን 2004 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org


No comments: