Friday, February 3, 2012

ደርባን፡ለኪዮቶ ዳግም ሕይወት ወይስ ሞት


(ጌታቸው አሰፋ, ኅዳር  23  ቀን 2004 ዓ.ምከ12 000 በላይ ልዑካን፤የአካባባቢ ጉዳይ አቀንቃኞችና ተቆርቋሪዎች፤ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ጋዜጠኞች በዚህ ሳምንት ሰኞ ኅዳር 18  የተጀመረውን 17ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ባለጉዳይ አካላት ጉባኤን ምክንያት በማድረግ ደርባን ከተማ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ተገኝተዋል። በዛው ቀን
ከደርባን 13 567 ኪሎሜትር ርቀት በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ ካለችውና የካናዳ መንበረ መንግሥት ከሆነችው ኦታዋ ከተማ የአገሪቱ የአካባቢ ጉዳይ ሚንስተር ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ እየሰጡ ነበር። ሚንስትሩ ወግ አጥባቂው መንግሥታቸው የንጹሕ አየር አጀንዳየን በተጨማሪ የስድስት መቶ ሚልዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ አጠናክሬ እቀጥላለሁ ለማለት ነበር ጋዜጣዊ መግለጫውን የጠሩት።የተጠየቁት ጥያቄ ግን “ካናዳ ከኪዮቶ ስምምነት ራሷን ለማግለል እቅድ አላት የሚባለው እውነት ነው ወይ?” የሚል ነበር። ጥያቄው በተደጋጋሚ ቀርቦላቸውም እንኳን ሚንስተር ኬንት ግን አዎም አይደለምም ማለት አልፈለጉም። ከሰዓት በኋላም በፓርላማ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ያንኑ ጥያቄ ያስተናገዱት እርግጡን ባለመናገር ነበር። ከምዕራቡ ዓለም የገና በዓል በፊት ግን ካናዳ ራሷን ከኪዮቶ ስምምነት ውጪ እንደምታደርግ ይፋ ለማድረግ እንደተዘጋጁ እየተነገረ ነው። ቅድመ ደርባን የነበሩት ውይይቶችና ድርድሮች ወቅት ካናዳ ይህን አቋም መውሰዷ ብቻ ሳይሆን ሌሎች አገሮችም አብረዋት  ከኪዮቶ እንዲወጡ ለማድረግ ስታባብልና ስታስተባብር  እንደነበር ሲታሰብ የደርባኑ ጉባኤ ከኪዮቶ ቀጣይ ጉዞ አንጻር ከወዲሁ ውጤት አልባ መሆኑ አይቀርም ያስብላል።   
ተሳታፊዎች 
ደርባን እስከ ህዳር 29 ወደ 20 000 ለሚደርሱ ተሳታፊዎችና (ወደ መጨረሻ አካባቢ ጉባኤውን የሚቀላቀሉት የየአገራቱ መራሂያነ መንግሥት ጨምሮ) ለማስተናገድ ሽር ጉድ ስትል ሰንብታለች። 
አርብ ኅዳር 15 ድረስ የተመዘገቡ ተሳታፊዎች ቁጥር በተመድ መረጃ መሠረት 14 570  ናቸው። ዝርዝራቸው እነሆ፡


የአገራት/ድርጅቶች ብዛት
የተመዘገቡ ተሳታፊዎች ብዛት
ባለጉዳይ አገሮች
192
6164
ታዛቢ መንግሥታት
2
8
ድምር (ባለጉዳይና ታዛቢ)
194
6 172
የተመድ ድርጅቶች
23
327
ትኩረት ያደረጉ ድርጅቶች
20
278
በየነ መንግሥታት ድርጅቶች
52
486
መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች
707
5 884
ድምር (ድርጅቶች)
802
6 975
ብዙኃን መገናኛ
545
1 423
ጠቅላላ የተሳታፊዎች ብዛት 
14 570

ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጨምሮ ከአምሳ ባላነሱ የመንግሥትና የመያድ ሰዎች ትወከላለች።

ድኅረ ኪዮቶ 
ከዋናዎቹ የደርባን አጀንዳዎች መካከል የኪዮቶ እጣ ፈንታ አንዱ ነው። በሌላ እትም እንዳየነው የጃፓን ከተማ በሆነችው የኪዮቶ ከተማ ታኅሳስ 2 1990 ዓ.ም. የጸደቀው የኪዮቶ ፕሮቶኮል ተብሎ የሚጠራው ስምምነት ዓለም አቀፍ የልቅት ቅነሳና ገደብ መጠንን የደነገገ ስምምነት ነው።

በኪዮቶ ፕሮቶኮል መሠረት የቅጥያ አንድ ተብለው የሚጠሩት ሰላሳ ሰባት የበለጸጉ አገሮችና የአውሮፓ ህብረት የሚገኝበት ስብስብ የልቀት መጠን በአማካይ በአምስት ፕርሰንት እንዲቀንሱ ያዛል።  
በፕሮቶኮሉ የአምስት ፐርሰንት የልቀት ቅነሳው መሳካቱን አለመሳካቱን የሚታወቀው ከ2008 እስከ 2012 እ.አ.አ. ባሉት አምስት ዓመታት ውስጥ የሚኖረው ልቀት በ1990 እ.አ.አ. ከነበረው ጋር በማነጻጸር እንደሚሆን ሰፍሯል።  ከዚህ የተነሳ የስምምነቱ አንደኛ ዙር የሚያበቃው በታኅሳስ 2005 ዓ.ም. (2012 እ.አ.አ. መጨረሻ ላይ) ነው።  የስምምነቱ ቀጣይ  ዙር በተመለከተ የሚደረግ ውይይት የመጀመሪያው ዙር ከማብቃቱ ከሰባት ዓመት በፊት እንዲጀመር  ነው ስምምነቱ የሚጠቁመው።  
በመጀመሪያው ዙር የቅነሳ ድርሻ 8 ፐርሰንት የአውሮፓ ህብረት፤ 7 ፐርሰንት የአሜሪካ እንዲሁም 6 6 ፐርሰንት  ደግሞ የካናዳና የጃፓን ነበር። ራሺያ መጨመር ባይፈቀድላትም የመቀነስ ግዴታ ግን አልተጣለባትም።   በሌላ በኩል ጨምረው (በገደብ) መልቀቅ የሚችሉ አገሮችም ተዘርዝረዋል በፕሮቶኮሉ።   በ8 ፐርሰንት አውስትራልያ፤በአንድ ፐርሰንት ኖርዌይና በ10 ፐርሰንት አይስላንድ መጨመር ይችላሉ። 
የኪዮቶ አሳሪነት ለቅጥያ አንድ አገሮች ብቻ እንዲሆን የተደረገውና በነሱ መካከልም በተለያየ መጠን እንዲከፋፈሉት የተደረገው ያለፉት 150 ዓመታት ታሪካዊ ልቀት-ጠገብ የኢንዱስትራሊያዊ እድገታቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ነበር። ከቅጥያ አንድ ውጪ ያሉት ቻይና ፤ብራዚል፤ ሕንድና ደቡብ አፍሪካ የሚገኙበት ስብስብ የኪዮቶ ፕሮቶኮል አካል ቢሆኑም በፕርቶኮሉ የመጀመሪያ ዙር የልቀት ቅነሳም ይሁን ገደብ አልተጣለባቸውም ነበር።  የኪዮቶ  ቀጣይ ዙር  ያለክፍተት እውን መሆን ካለበት እነሆ የመጨረሻው እድል በደርባን እጅ ነው።
ይሁንና እስካሁን ያሉት የፖለቲካ አካሄዶች የሚያመለክቱት ደርባን የኪዮቶ መቃብር እንጂ የኪዮቶ ቀጣይ የሕይወት እስትንፋስ የምትሆን አትመስልም።
ለምን ቢባል በኪዮቶ የቅነሳና የገደብ ጣራ ስር የነበሩት የበለጸጉት አገሮች በኪዮቶ የሥራ ዘመን ወቅት ቅነሳም ገደብም ያልተጣለባቸው አገሮች በምጣኔ ሀብት ሲተኮሱና በዛው ልክም ጠቅላላ የልቀት መጠናቸው ቅድመ ኪዮቶ ከነበረው በእጅጉ በልጦ መገኘቱን ሊቀበሉት አለመቻላቸው ነው። ከኢንዱስትሪ  አብዮት ወዲህ የየአገራቱ የምጣኔ ሀብት እድገት የተመሠረተው  በተነጻጻሪነት ርካሽ በሆኑ ቅሪታዊ ነዳጆች ማለትም የድንጋይ ከሰል፤ የተፈጥሮ ጋዝና የነዳጅ ዘይት ላይ መሆኑ ይታወቃል። ያለገደብ መልቀቅ ማለት ከነዳጆቹ በተጨማሪ በነዚህ ቅሪታዊ ነዳጆች የሚዘወር ረከስ ያለ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ማምጣት ይቻላል - በአጭርና በመካከለኛ ዘመን ሲታይ። 
ከዚህ የተነሳ እንደ መጀመሪያዉ ዙር ሁሉ የልቀት ቅነሳና ገደቡ ለተወሰኑት አገሮች ብቻ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያደርግ ቀጣይ ዙርን አይቀበሉም- የበለጸጉት አገሮች።
ካናዳ ከላይ እንዳየነው በኪዮቶ ቀጣይ ዙር ቀርቶ ምናልባትም ማብቂያው ከተቃረበው የመጀመሪያው ዙርም ልትወጣ ትችላለች። አሜሪካ ከመጀመሪያው ዙርም ውስጥ እንዳልነበረች ሁሉ ቀጣይ ዙር ውስጥ ለመግባትም ጉጉት የላትም። የኪዮቶ መወለጃ ጃፓን ሳትቀር በአንደኛው ዙር ያለምንም የልቀት ገደብ በምጣኔ ሀብት ሲያድጉ የነበሩትን እነ ቻይናንና ሕንድን መነሻ በማድረግ እነሱንም የማይገድብ ቀጣይ ዙር ብሎ ነገር የለም ባይ ነች። 
እነ ሕንድ ደግሞ ታሪካዊው የበለጸጉት አገሮች ልቀት በአንድ ዙር ብቻ የሚወራረድ አይደለም የሚል አቋም ይዘዋል። የኪዮቶ ቀጣይ ዙር መኖር አለበት። ቀጣዩ ዙር እንዲያውም የበለጸጉት አገሮች የበለጠ ልቀታቸውን እንዲቀንሱና እንዲገድቡ ሆኖ መቀረጽ አለበት። ይህ የቻይና ድጋፍ ያለው የነህንድ ድምጽ ነው። ራሺያ ዓለም አቀፍ የቅነሳ ስምምነት ውስጥ ለመግባት በቅርቡ ዝግጁ አይደለችም።
የአውሮፓ ህብረት ኪዮቶ አረጀ አፈጀ ተብሎ መጣል የለበትም ይልቁንም ቀጣዩ ዙር ደርባን ውስጥ ሕይወት እንዲዘራበት ለማድረግ ፈቃደኛ ከሆኑ አገሮች ጋር ለመሥራት ዝግጁ ነኝ ብሎ ነው ወደ ደርባን ልዑካኑን የላከው - ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ። አሁን ተጣድፈን ስምምነት ውስጥ አንገባም የሚሉ አገሮችም ቢሆኑ መቼና እንዴት ወደ ዓለም አቀፍ የቅነሳና ገደብ ስምምነት እንደሚገቡ በግልጽየሚያሳዩበት ሌላ ስምምነት ውስጥ ለመግባት ፈቃደኛ መሆን አለባቸው የሚል ነው ቅድመ ሁኔታው።  

ነገረ ገንዘብ
የደርባኑ ጉባኤ በተከፈተ በሁለተኛው ቀን መታየት የጀመረውና ሌላው አቢይ ነገር የአረንጓዴ የአየር ንብረት ለውጥ ፈንድ ጉዳይ ነው። ከደርባኑ ጉባኤ አንድ ዓመት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና በኖርዌዩ አቻቸው  በሚመራው ቡድን በኩል እንደመነሻ  የቀረበው ሪፓርት አርባ አገሮች በሚሳተፉበት ቡድን ላለፈው አንድ ዓመት በተደረጉ ውይይቶችና ክርክሮች ሲዳብር ቆይቶ ነበር።  ይህ ሰነድ በቅርቡ ለደርባን በውሳኔ ሀሳብነት ይቀርባል ተብሎ ሲጠበቅ  በአሜሪካና ሳውዲ አረቢያ ተቃውሞ ስለቀረበበት በደርባንም የልዩነት ነጥብ ሆኗል። በሚቀጥሉት ስምንት ዓመታት እያደገ መጥቶ ከ2020 አ.አ..አ ጀምሮ ወደ መቶ ቢልዮን ዶላር በዓመት የሚደርሰው ፈንድ ለታዳጊ አገሮች የማጣጣሚያና የስርየት ሥራዎች ትግበራ የሚውል ነው። አሜሪካ በፈንዱ የግሉ ዘርፍ ሰፊ ተሳትፎ ይኑረው በሚል፤ ሳውዲ ደግሞ ከቅሪታዊ ነዳጆች ወደ ታዳሽ ኃይል በሚደረገው ለውጥ ምክንያት ለሚደርስብኝ ምጣኔ ሀብታዊ ኪሳራ ካሳ ሊታሰብልኝ ይገባል በሚል ነው በፈንዱ ላይ ለመስማማት ያልቻሉት።
በታዳጊ አገሮች በኩል ፈንዱ እስካሁን በሌላ ስም ለተረጂ አገሮች ሲሰጥ የቆየውን ገንዘብ አሁን አዲስ የስም መጠቅለያ ብቻ በመቀየር የሚሰጥ እንዳይሆን ስጋት አለ። ይህን ስጋት ከሚያስወግዱት መካከል ገንዘቡ በከፊል ከዓለም አቀፍ የባህር ትራንዚት፤ከአየር ጉዞ ቲኬትና ፤ ከገንዝብ ልውውጥ አገልግሎት በፐርሰንት መሰበስብ ከሚያስችል አዲስ ምንጭ ይገኛል መባሉ ነው። የዚህን ፈንድ እውን መሆንና ተግባራዊነት በተመለከተ ጠቃሚ ውሳኔ መተላለፍ ከደርባን ተስፋ ይደረጋል።

ሦስቱ ሪፖርቶች
አይ.ፒ.ሲ.ሲ (የአየር ንብረ ለውጥ በይነ መንግሥታት ጉባኤ ተብሎ የሚታወቀው የተመድ የሳይንቲስቶች ጉባኤ) የካቲት ላይ ሊያወጣው ካሰበው አዲስ ሪፖርት ውስጥ ዋና ዋና ሃሳቦችን ጨምቆ ባለፈው ሳምንት ይፋ አድርጓል። የሪፖርቱ ዋና ማጠንጠኛ ጫፍ የያዙ የአየር ሁኔታ ክስተቶች ናቸው።  የነዚህ ክስተቶች ቁጥርና የጥፋት መጠን በዓለም ዙሪያ ባለፉት ዓመታት መጨመርና  በቀጣይ ዓመታትም መባባስ ከሰው ሰራሽ የአየር ንብረት ለውጥ ጋር ያለውን ግንኙነት በተለያዩ የይሁንታ ደረጃዎች አስቀምጧል። 
የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅትም በዚህ ሳምንት ሰኞ አንድ ሪፖርት ያወጣ ሲሆን እንደ እስካሁኑ ከቀጠለ በ2050 አ.አ.አ. የዓለም ሕዝብን (ዘጠን ቢልዮን ሲሆን) ለመመገብ የዓለም ገበሬዎች የሰባ ፐርሰንት ተጨማሪ ምርት ማምረት ይጠብቅባቸዋል። በዓለም ደረጃ ያለው የእርሻ መሬት ባብዛኛው ኦሮማይ በጥቅም ላይ እየዋለ ያለ ነው።  በዛ ላይ በጥቅም ላይ እየዋለ ካለው የእርሻ መሬት አንድ አራተኛው ያህል የተጎሳቆለ ነው ብሏል ሪፓርቱ። የአየር ንብረት ለውጥ ሃይ ካልተባለ የምግብ እጥረት ይባባሳል ነው የሪፓርቱ መልእክት። 
የተመዱ የዓለም ሜትሮሎጂ ድርጅት የአየር ሁኔታ መረጃ መያዝ ከተጀመረበት ከ1850 እ.አ.አ.  ጀምሮ የዘንድሮው ዓመት (2011) አስረኛው ወበቃም ዓመት ሆኖ መመዝገቡን ማክሰኞ(ኅዳር 19) ይፋ አድርጓል - አስራ ሦስቱም ወበቃማ ዓመታት ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት ነበሩ። የድርጅቱ ሪፖርት የምሥራቅ አፍሪካን ድርቅ፤ የኤዥያን በጎርፍ መጥለቅለቅ፤ እያንዳንዳቸው ከአንድ ቢልዮን ዶላር በላይ ጉዳት በአሜሪካ ላይ ያደረሱ አስራ አራት የአየር ሁኔታ አደጋዎችን እንደ ምሳሌ አካቷል። የአርክቲክ ግግር በርዶም እንደ ዘንድሮ ሳስቶ አያውቅም- እንደ ሪፓርቱ። አጥጋቢ መፍትሔ ወዲያው ካልተበጀ አማካይ የዓለም የከባቢ አየር ሙቀት የቀይ መስመር ተደርጎ የተወሰደውን የሁለት ዲግሪ ሴንትግሬድ ጭማሪን በቀላሉ ያልፋል - መዘዙም ቀላል አይሆንም ይላል የሜትሮሎጂ ድርጅቱ ሪፓርት። ሦስቱ ሪፓርቶች በተለያየ መልኩ የደርባኑ ጉባኤ እንዲሁ እንደዋዛ ያለውጤት እንዳይበተን የማስጠንቀቂያ ደወል ሚደውሉ ናቸው።  

ተስፋና እውነታ
በገንዘብ ድጋፉም ሆነ በድኅረ ኪዮቶ ጉዞም ተሰፋ መቁረጥ አይገባን ይሆናል። መሬት ላይ ያለው ሐቅ ግን ከወዲህ ነው። የደወል ሪፓርት ሌላ ፓለቲካ ሌላ - ነው ነገሩ።
ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ቀዳሚ ሚና የምትጫወተውና በዛው ሚና ለመግፋት የምትፈልገው አውሮፓ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ቀውስ ላይ ነች። በአሜሪካ ቀጣዩ ዓመት የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዓመት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዙ ህጎችና ደንቦች የአሜሪካን ምጣኔ ሀብት ይጎዳሉ የሚሉ የባራክ ኦባማ ተቀናቃኞች እየበዙ ነው - እዛው አሜሪካ ውስጥ። 
ከዚህ የተነሳ የአየር ንብረት ለውጥ መዘዝና መፍትሔ የመፈለጉ አጣዳፊነት ዙሪያ እየደሰኮሩ አፋቸውን እንጂ ልባቸውን የማይሰጡት ጉዳይ ወደመሆን ደረጃ እየወረደ ነው - በአንዳንድ አገሮች። የፖለቲካ ፈቃድ፤ ስትራተጂና ፖሊሲ የሚጠይቀውን ተጨባጭ እርምጃን ግን  በተቻለ መጠን ወደፊት ማስተላለፍን ሆን ብለው የያዙት አቋም ይመስላል። የነዳጅ ኩባንያዎች የሚያባብሏቸው፤ የምርጫ ዘመቻ ወጪያቸውን የሚሸፉኑላቸውና፤ በተለያየ መልክ የሚደግፏቸው ገዢ ፓርቲዎች ያሉባቸው አገሮች በሙሉ ልብ በሳይንሳዊ ጥናቶች ላይ ለተመሰረቱ ሪⶒርቶች ከልብ ትኩረት የሚሰጡ ስትራተጂዎችን ይዘው ይሄዳሉ ብለው መጠበቅ ቀላል አይሆንም።
ፓለቲከኞች ለአጭር ጊዜ ነው የሚመረጡት። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ግን የሚታዩ አዳዲስ የሥራ እድሎችን መፍጠር አለባቸው - በአገራቸው። የአገራቸውን ምጣኔ ሀብት ከሌሎች አገሮች በተነጻጻሪነት በበለጠ ማሳደግ አለባቸው።  
ወደ ደርባን ስንመለስ…..በየቀኑ የተለያዩ የአገራትና የድርጅት ስብስቦች የየራሳቸው ስብሰባ እያደረጉ ይገኛሉ። የነዚህ ስብስብ ውጤትና ሂደት ነው በተወሰነ መልኩም ቢሆን ለባለጉዳይ አካላት ድርድር ግብአት የሚሆነው። ጉባኤው ገና መጀመሩ ነው። ይህ ጽሑፍ ከጄ የሚወጣው የጉባኤው ሦስተኛ ቀን አጋማሽ ላይ መሆኑ ነው - ጉባኤው ወዴት እያመራ እንደሆነ ለመገመት ጊዜው ገና ነው። በሚቀጥለው ሳምንት አርብ ለቅዳሜ ማታ የሚጠናቀቀው ውይይትና ድርድር ውጤት በሚቀጥለው ጽሑፌ የሚዳሰስ ይሆናል። ደርባን ሆይ ከኮፐንሃገን የተሻልሽ ያድርግሽ!
=======
አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: