Wednesday, February 29, 2012

ከተማን እንደ ዘአካል


(ጌታቸው አሰፋ፤ የካቲት 17 ቀን  2004 ዓ.ም.) ዘአካል ማለት በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የሚገለጽ ሰብሰብ ያለና የራሱ የሆነ አካል (የሚታይም የማይታይም) ያለው ህያው  ማለት ነው - ኦርጋኒዝም የሚባለው ማለት ነው። ዘአካል ያድጋል፡ይራባል። ሲተነኮስ ግብረ መልስ የመስጠት ባህርይም አለው። ዘአካሎች ህያው ሆነው እንዲቀጥሉ የሚያደርጋቸው  ግብአት (ምግብና ኃይል0 ያስፈልጋቸዋል። እነዚህን ግብአቶች በአካባቢያቸው ከሚያገኝዋቸው ምንጮች ገቢ አድርገው ሲያበቁ በግንባንደት ሂደት (ሜታቦሊዝም) አካላቸውን እየገነኑ ወደ አካባቢያቸው ደግሞ ውጣት ይለቃሉ። ይህ ውጣት ጠጣር፡ፈሳሽ ወይም ጋዛማ ሊሆን ይችላል። ኃይልም ሊሆን ይችላል።
ማንኛውም ከተማም ህይወት
አለው። ካልሞተ። እርግጥ ከተሞች ሙሉ በሙሉ ላይሞቱ ይችላሉ - በመደበኛ ሂደት። የሚንፈራፈር ከተማ፤ የአልጋ ቁራኛ የሆነ ከተማ፤ካሉት በታች - ከሌሉት በላይየሆነ ከተማ ግን አለ። ይኖራልም።  ከተሞችን እንደ ዘአካል የማየት እሳቤ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው።  ዘአካሎች እንደሚበሉ እንደሚጠጡ ሁሉ፤ ዘአካሎች ወደውስጥም ወደውጭም እንደሚተነፍሱ ሁሉ፤ ዘአካሎች ጠጣር ፈሳሽና ጋዛማ ውጣት እንዳላቸው ሁሉ ከተሞችም እንዲሁ ይሄ ሁሉ ነገር አላቸው። ለዝርዝሩ . . . አብረን እንቀጥል።
ግብአቶች
ውኃ ለአንድ ከተማ ወሳኝ ነው ማለት ወሳኝነቱን በደንብ መግለጽ ላይሆን ቢችልም እንበለው። ውኃው ንጹህ መሆን አለበት። በቂ መሆን አለበት። የጥራትና የመጠን ብቃቱም በዘላቂነት የሚቀጥል መሆን አለበት። 
ማንኛውም ከተማ ለነዋሪዎቹ የሚሆን ምግብ (የእንስሳት መኖ ወዘተን ጨምሮ) ጭራሽ ወይም በበቂ መጠን ስለማያመርት ከውጪ የሚያስገባው ጥሬና የተሰናዳ ምግብ እጅግ በርካታ ነውየነዋሪ ምግብ ብለን እንጥራው?   በቁመትም በስፋትም እያደገ ሲመጣ ከተማው ከመስፋቱና ወደላይ ከማደጉ ጋር የሚቆራኘው በከፍተኛ መጠን ጥቅም ላይ የሚውለው ሌላው አይነትምግብነው። -ነዋሪ ምግብ ብንለውስ?   አይነቱ ብዙ ነው። እነዚህ የተለያዩ ምግቦች ከሞላ ጎደል ከከተማው ውጪ የሚገቡ ናቸው። 
ውኃውና የነዋሪና -ነዋሪ ምግቦች ወደከተማው ገብተው በግንባንደት ሂደት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ ኃይል ያስፈልጋል። ለማሞቂያነት፤ ለማሽከርከሪያነትና፤ ለሰው-ሰራሽ ብርሃንነት ወዘተ የሚሆን ኃይል። ይህ ኃይል ወደከተማው የሚገባው እና/ወይም ጥቅም ላይ የሚውለው በሙቅ ውኃ ወይም እንፋሎት፤ በኤሌክትሪክ ወይም በነዳጅ መልክ ሊሆን ይችላል። ነዳጅ ስንልም የማገዶ እንጨት፤ የድንጋይ ከሰል፤ የተፈጥሮ ጋዝ፤ ነዳጅ ዘይት፤ ነዳጅ አረቄ፤ ባዮዲዝል፤ ባዮጋዝን ሁሉ ይጨምራል።
ለከተማ ሕይወት የሚያስፈልጉት ከላይ የተጠቀሱት ብቻ አይደሉም። አንድ ከተማ መረጃም  ያስፈልጋዋል። ድምጻዊ አኃዛዊና ፊደላዊ እንዲሁም ምስላዊ መረጃ በበቂ ጥራት መጠንና ፍጥነት በከተማው መዳረስ አለበት። 
ማንኛውም ከተማ በበቂ ሁኔታም መተንፈስ አለበት። አዎ በቂ አየር በቂ ንፋስ ማግኘት አለበት። ጥራቱ የተጠበቀና ሙቀቱ የተመጠነ አየር፤ ፍጥነቱ ያልበዛም ያላነሰም ንፋስ ለከተማ ከተማነት አይተኬ ሚና አለው።
ሰው ሰራሽ ያደለ ብርሃንና ጥላው በተለያዩ የከተማው ክፍሎች ሲገኙ ህይወትን ይዘራሉ። ህይወትን ይቀጥላሉ፤ያስቀጥላሉ። ብርሃንና እና ጥላ የተለያየ የብርሃን መጠኖች ናቸውና የሚፈለጉበት ቦታና ጊዜ እስከታወቀ ድረስ ሁለቱንም በአግባቡ የሚጠቀም ከተማ የኔ በሆነ ቢያስብል አይገርምም።
እንግዲህ ከተማ  ሲባል የሚበላና የሚጠጣ ከሆነ ፤የሚተነፍስ ከሆነ፤የሚያይ የሚሰማና የሚያነብ ከሆነ እነዚህን ሥራዎች ያለምንም እንከን እንዲያከናውን የሚያደርገው ተገቢ የከተማ ክፍል (ክፍለ-አካል ወይም ብልት) ያስፈልገዋል ማለት አይደል?  
የከተማ ክፍለ-አካሎች  
አዎ ማንኛውም ከተማ ክፍለ-አካሎች ወይም ብልቶች አሉት። የሚበላው ነዋሪና -ነዋሪ ምግብ ወደከተማው በአግባቡ እንዲደርሰውና በከተማው ውስጥ ከአንድ ክፍል ወደሌላ ክፍል እንዲጓጓዝ ወሳኝ የምግብ ማስተላለፊያ ሆነው የሚያገለሉት መንገዳዊ ክፍለ-አካሎች ናቸው።
መንገዶች ሰፊም ጠባብም፤ አስፋልት-ለበስ፤ ጠጠር-ለበስ ወይም ሳር ለበስ ሊሆን ይችላል - እንደቦታው -እንደሁኔታው።  ዋናው ቁም ነገር ያለው በትክክለኛው ቦታ፤ ትክክለኛው የመንገድ አይነት፤ በትክክለኛው ስፋትና ርዝመት መገኘቱ ላይ ነው። ይህ በማይሆንበት ጊዜ አንድ ዘአካል ከደም ማስተላለፊያው ጋር በተያያዘ የሚያጋጥመው የጤና እክል እንዳለው ሁሉ ከተማም ከተማዊ ጤንነቱ ላይ እክል ይገጥመዋል - ለምሳሌ መንገዶች በበቂ ጥራትና ስርጭት በማይገኙበት ሁኔታ።  በመንገዳዊ ክፍለ-አካሎች ስር ከየብሳማ መንገዶች ሌላ የባቡር መስመሮች፤ የአየር መስመሮች፤ አውሮፕላን ማረፊያዎች ወዘተን አካቶ ማየት ያስፈልጋል።  ውኃንም ወደከተማዋ ጉሮሮና ወደተለያዩ የከተማው አቅጣጫዎች በበቂ ሁኔታ ለማዳረስ ያልዛጉና የማያፈሱ እንዲሁም በበቂ ግፊት ማስተላለፍ የሚችሉ የውኃ ትቦዎች የግድ ያስፈልጋሉ።  
የኤሌክትሪክ መስመሮች የተለያየ የኤሌክትሪክ ምንጮችን ከከተማው የተለያዩ ክፍሎችና ተጠቃሚዎች ጋር ማገናኘት የሚችሉ መሆን አለባቸው- መቼም ሁሌም።  መረጃ ከያለበት መንዶቅዶቅ አለበት። መረጃ ከየቦታው በየቦታው ፏፏ ማለት አለበት። አዎ መረጃ ደኅንነቱ ተጠብቆና የተጠቃሚንም ደኅንነት አደጋ ላይ ሳይጥል መፍሰስ አለበት። ለዚህ ሁሉ የመረጃ ጎዳናዎችን ሌላ ወሳኝ የከተማ የደም ስር  የሚባሉ አይነቶች ናቸው።
ፋብሪካዎች፤ህንጻ ግንባታ የሚከናወኑባቸው ቦታዎችና ማሽነሪዎች ወዘተ ሁሉ የከተማ አስፈላጊና -ነዋሪ ምግቦችን ማብላሊያ ክፍለ-አካሎች ናቸው። እንደ ጨጓራና እንደ አንጀት ግብአቶችን የሚፈጩባቸውና የሚሰለቀጥባቸው። እነዚህ ብልቶች እንከን አልባ የሆኑላት ከተማ የታደለች ወይም የታገለች ነች መኖሪያዎች፤ ቢሮዎች ሆስፒታሎች ወዘተ የየራሳቸው ሚና የሚጫወቱ ሌሎች ክፍለ-አካሎች ናቸው።
የውኃ ማጣሪያ ትክሎችና የቆሻሻ ቤተ-ውገዳዎች እንደነ ኩላሊት ለጤናማው የከተማ ህይወታዊ ኑሮ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው። ግን በደንብ መስራት አለባቸው። 
ልዩ እስትንፋስ ጭቃን ሰው አድርጓል። መደበኛ እስትንፋም የመኖር ምልክት ነው። አዎ መተንፈስ ሕይወት ነው። የትንፋሽ ሀገሯ ደግሞ ሳንባ ነው። የከተሞች ሳንባ ደግሞ ለከተማው ሰፋትና አቀማመጥ የሚመጥኑ በአግባቡ የተሰሩና የተያዙ ፓርኮች - አረንጓዴ ክልሎች- ናቸው። ከውኃ አካል ጋር የተዋሀደ፤ የአይነትና የብዛት ምጣኔ ካላቸው ዛፎችና አበቦች ጋር የተዋደደ ስርጭትና አያያዝ ያስፈልጋቸዋል - ፓርኮች - እስትንፋሰ ከተማ።
ውጣቶች
አንድ ከተማ ቁሳዊና ኃይላዊ ግብአቶችን አስገብቶ ሲያብላላ በግንባንደት ሂደት ጊዜ የሚፈጥራቸው ውጣቶች በርካታ ናቸው። እያንዳንዱ ክፍለ-አካል ሲገነባም ሆነ በስራ ላይ በሚውልበት ወቅት ስለሚያወጣው ውጣት ነው እያወራሁ ያለሁት። ከየፋብሪካው፤ ከየሆቴሉ፤ከየሆስፒታሉ፤ ከየቤቱ  የሚወጣው እጣቢ፤ የሽንት ቤት ቆሻሻ፤ ደረቅ ቆሻሻ ሁሉ የከተማውን ምንነት የመግለጽ ባህርይ አለው። በመጥፎ ሽታው ሲገለጽ ያላየው ማን አለ? ለእይታ አስቀያሚ መሆኑስ ላይ ማን ይጠራጠራል? ከሁሉ በላይ ደግሞ ከውኃ ብክለት ጋር በተያያዘ የሰውን ህይወት ለሚቀጥፉ ተላላፊ በሽታዎች መንደርደሪያ ነው - እንደነዚህ አይነት ውጣት - በስርዓት ካልተያዘ  
ጭሳጭስም አለከቤትም ከፋብሪካም ከሌሎችም የሚለቀቅ ጋዛዊ ልቀት። በአይን ቢታይም ባይታይም በካይነቱ ግን የማያጠራጥር የጭስ አይነት ሁሉ ይወጣል። ቅሪታዊ የካርቦንዳይኦክሳይድ ልቅት በአይን ከማይታዩት ውስጥ ይመደባል። 
ፓርክ በፓርክ የሆነች ከተማ ውስጥ እንጨት ሲማገድ የሚለቀቀው ካርቦንዳይኦክሳይድ በፓርኩና ከፓርኩ ውጪ ባሉ ዛፎች ወደውስጥ ስለሚማግ ከሞላ ጎደል ችግር-አልቦ ነው።  ዛፎቹና ባልደረቦቻቸው ወደውስጥ የሚመጥጡት የከተማ ነዋሪዎች ወደ ውጪ ያስፈነጥሩትን ካርቦንዳይኦክሳይድ ጨምሮ ሲሆን በምትኩ ምን የመሰለ ኦክስጅን ለነዋሪዎቿ ጀባ ይላሉ። 
ከተማን እንደዘአካል ብናየውም የከተማው ሞትም ሆነ ትንሳኤ የሚገለጸው ግን በክፍለ-አካሎቹ ደረጃ ነው - በሙሉ ከተማነቱ ደረጃ ሳይሆን። ማንኛውም የከተማ ክፍለ-አካል አስፈላጊ የእድሳት ሥራ እየተደረገለት ከቆየ በኋላ የአገልግሎት ጊዜው ሲያበቃ ወይም አዲስ ክፍለ-አካል በቦታው መተካት ሲፈለግ ይፈርሳል። ፈርሶ በተመሳሳይ ክፍለ-አካል ወይም በሌላ አይነት ክፍለ-አካል ሊተካ ይችላል። እያንዳንዱ ክፍለ-አካል ሲታደስም ሆነ ሲፈርስ የሚፈጠረው ቆሻሻም የማንኛውም ከተማ ዘአካላዊ ሕይወት መገለጫ ነው። 
እና ምን ይጠበስ?
ከተሞቻችንን ከላይ በተገለጸው የዘአካላዊ ሞዴል አይን ስናያቸው አብረው የሚነሱ ጥያቄዎችና ጉዳዮች ይመጣሉ። 
ለመሆኑ ጤነኛ ከተማ በአገራችን አለ? የነዋሪና -ነዋሪ ምግብ ማስተላለፊያ መንገዶች፤ የውሃ ማሰራጫ መስመሮች፤ የመረጃ ጎዳናዎች ያሉት፤ ቢኖሩትም በደንብ የሚሰሩለት ከተማ የትኛው ነው? የፈሳሽና የደረቅ ቆሻሻ አይጎዴ የሚደረጉበት ደረጃቸውን የጠበቁ ቤተ ውገዳዎች ያሏቸው ስንት ከተሞች ናቸው? አካላቸው ሽንት በሽንት ያልሆነባቸው በእንትን ያልተለቀለቁ ከተሞች የትኞቹ ይሆኑ? አንድ ከተማ የተበላሸ መንገድ፤የሚያፈስ ወይም የሚቋረጥ የውኃ መስመር  እያለው ሁሉም አማን ነው ብሎ ቁጭ ማለት አንድ የኛ ቢጤ ዘአካል ችግር ያለበት የደም ቧንቧና ወደውስጥ ደም የሚፈስበት ክፍለ-አካል  እያለው ሁሉም ጤና ነው ብሎ ቁጭ የማለት ያህል ከባድነቱ ሊሰማን ይገባል።
አንድ ከተማ ከጅማሮው አንስቶ በምን መልኩና ፍጥነት ወዘተ ማደግ እንዳለበት የተቀመጠለት ነገር ከሌለ ሲጀመር የታመመ ከተማ ነው። መወገድ ይችል የነበረ፤ ግን ያልተወገደበተለያዩ ክፍለ-አካሎቹ ላይ የሚገለጥ ህመም። ለማከምም ይቀል የነበረ፤ ግን ከማከሚያ ወጪው ከእጅግ ከፍተኛ መሆን አንጻር ከባድ የሆነ ሕመም።
በዚህ እይታ ከከተሞቻችን ስንቶቹ ናቸው እየተንፈራፈሩ ያሉት? ስንቶቹስ እያጣጣሩ ናቸው? ስንቶቹ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ፤ አነሰም በዛም የታመሙ ናቸው? ቢያንስ የመጨረሻው ጥያቄ መልስ) ሁሉምየሚል መሆኑ አያጠራጥርም። እንደዛም ሆኖ ግን ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም (ዛፍም ቆርጠን ተስፋም ቆርጠን ስለማይሆንም ጭምር) አዎ ከተሞቻችንን አንድ በአንድ ጤነኛ ዘአካሎች ማድረግ እንችላለን። የሚያስፈልገው እያንዳንዱ ከተማ የተለያዩ አብረው የሚሰሩ፤ የሚመጋገቡና የተሳሰሩ ክፍለ-አካሎች ያሉት ትልቅ ዘአካል አድርጎ የሚያይ የተቀናጀና የተጠና እውቅና የሚሰጥ አይናማ  አሰራር ነው።  የዚህ አሰራር አይናማነት አይን ያለው ደግሞ ብሌኑ ላይ ነው - እንደማንኛውም አይን። ብሌኑ ደግሞ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ነው። ጨረስኩ። ድኅረ ነገር - በዚህ ሳምንት የገባው ታላቅ ጾም ለበረከት ያድርግልንና ወራቱ ከፈቀደልን ዘንድ ስለጾምና አካባቢ ጾሙ ከማለቁ በፊት እጽፍበት ይሆናል።  
=======
አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: