Friday, February 3, 2012

የሕንጻዎቻችን ጉዳይ

(ጌታቸው አሰፋ፤ ጥር 19 ቀን  2004 ዓ.ም.) ሕንጻዎች ለሃምሳ ወይም ለስድሳ ዓመት ተብለው ይሰራሉ። ይሁን እንጂ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ ሕንጻዎች ከመቶ ዓመት በላይ ይቆያሉ። አንድ ትውልድ ማለት ሃያ አምስት ዓመት ማለት ስለሆነ አንድ ሕንጻ ቢያንስ ከተገነባበት ጊዜ ጀምሮ እድሜ ጠግቦ እስኪፈርስ ድረስ
ከሁለት እስከ አራት ትውልድ ድረስ ይቆያል ማለት ነው። 
ለዚህም ነው ከሌሎች ጥሪቶችና ‘ግንባታዎች’ ይልቅ ሕንጻዎች ሲገነቡ ስህተት ካለባቸው ትውልድ ተሻጋሪ የሚሆነው። ሕንጻዎችን ለመገንባት የሚወጣው ወጪም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ የሚሰራው ስህተት ውድ ዋጋ የሚያስከፍል ስህተት ነው የሚሆነው።
እዚህ ካናዳ የምሰራበት ዩኒቨርስቲ ውስጥ የሕንጻ ግንባታ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርት ላይ ባለፈው ሳምንት ተጋባዥ አስተማሪ ሆኜ ክፍል ውስጥ ቆሜያለሁ። በክፍሉ ውስጥ ካሉት ከሃምሳ በላይ በአርክቴክቸርና በሲቪል ምህንድስና ለሁለተኛ ዲግሪያቸው የሚሰሩ ተማሪዎች የሚበዙት ሲሆኑ በጣት የሚቆጠሩ ደግሞ ለፒ.ኤች.ዲያቸው የሚሰሩ ናቸው። እንዳስተምርበት የተሰጠኝ ርዕስ ሕንጻዎችንና ለሕንጻ ግንባታ የሚውሉ ዕቃዎችን ከአዛላቂነት አስተምህሮ አንጻር መዳሰስ ነበር። የአዛላቂነት አስተምህሮ የምርቶችና አገልግሎቶች ዑደታዊ ተጽእኖ ግምገማ ለማየት የሚያስፈልገው ምርቶቹ(ምሳሌ ሕንጻ፤ መኪና፤ ጅንስ ሱሪ…) እና አገልግሎቶቹ(ምሳሌ የኃይል አቅርቦት) ተነጻጻሪ የሚያደርጋቸው በአኃዝ የሚነገር የግልጋሎት ልኬትና በስታንዳርድ የሚገለጽ የጥራት አቻነት ሲኖራቸው ነው። ለምሳሌ በቤንዚን የሚነዳ መኪናና በነዳጅ-አረቄ ከሚነዳ መኪና ጋራ በዑደታዊ ተጽእኖ አይን ለማነጻጸር የምንጥቀምበት የግልጋሎት ልኬት የሚጭኑት የሰው ብዛትንና የሚሄዱትን ርቀት ግምት ውስጥ ያስገባ ግልጋሎት ነው። በየቀኑ በየጊዜ  ሆን ብለን እናስበውም አናስበውም እንጂ የሁሉም ምርትም ሆነ አገልግሎት መኖር ወሳኙ ነገር ለተጠቃሚው የሚሰጠው የግልጋሎት ልኬቱና ጥራቱ ነው። አንድ ምርት ወይም አገልግሎት የግልጋሎት ልኬት ጥራቱን ጠብቆ ሲሰጥ አጅበውት የሚመጡት አካባቢያዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድሎችና ተግዳሮቶች የጥናትና የግምገማው ዋና አካል ናቸው። 
በዚህ መነሻ ነበር በክፍሉ ውስጥ የምስጠውን ትምህርት ከመጀመሬ በፊት የጠየቅኩት ጥያቄ “ውስብስብ ከሆነው ‘ሕንጻ’ ከምንለው ‘ምርት’ የምናገኘው የግልጋሎት ልኬት ምንድነው?” የሚል የሆነው።
የጥያቄዬ መልስ ተራና ቀላል ቢሆንም (ቢያንስ ቢመስልም) ለዛን ቀን ትምህርቴና ለዛሬው ጽሁፌ ግን ትርጉም ያለው መልስ ነበር።  አዎ ሕንጻዎች የሚሰሩት በ’ስፋት’ ልኬት የሚመጠን ምቹ (ለምሳሌ የመኖሪያ ወይም የመስሪያ) ስፍራን ለመፍጠር ነው። ከአንድ ሕንጻ የምናገኘው ግልጋሎት በቂ ስፋት ያለው ምቹ ስፍራ ነው። ሕንጻዎች ይህን በቂ ምቹ ስፍራ ለሕንጻው ተጠቃሚዎች ወይም ተገልጋዮች ለማቅረብ እንዲችሉ የሚያደርጋቸው አንድና ወጥ መንገድ አይደለም ያለው። ከዲዛይን እስከ ግንባታ እንዲሁም ሕንጻውን ከመጠቀምና ከማስተዳደር ጀምሮ በርካታ አማራጭ ዘዴዎች አሉ። አንዱን ሕንጻ ከሌላው ሕንጻ የሚለየውም እነዚህ አማራጮች ጥቅም ላይ የሚውሉበት መንገድ ከሕንጻ ሕንጻ ስለሚለያይ ነው። የሕንጻዎች የማንነት ልዩነት ላይ የሕንጻዎቹ ቅርጽ፤ አቀማመጥ፤ ለግንባታ የሚውሉት እቃዎች፤ የኃይል አቅርቦታቸውና የመሳሰሉት መገለጫዎች የየራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ።
የዑደታዊ ተጽእኖ ግምገማ (ዑተግ) ስልት መነሻ የሚያደርገው ለምሳሌ ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ አንድን ሕንጻ ለመስራት የሚያስችሉ አማራጮች ማነጻጸርን ሊሆን ይችላል። ከሕንጻው አንድ ካሬ ሜትር ምቹ ስፍራን ለማግኘት ጥቅም ላይ የዋሉት አማራጮቹ የሚያሳዩት ኢኮኖሚያዊ፤ ማኅበራዊና አካባቢያዊ ብልጫ የንጽጽሩ ውጤት ይሆናል ማለት ነው። 
በ52 ሺህ 200 ሄክታር መሬት (ለ104 ሺህ 400 ኳስ ሜዳዎች የሚሆን) ላይ ያረፈችው አዲስ አበባ ውስጥ እየታየ ላለው ከፍተኛ የሕንጻ ግንባታ እንቅስቃሴ ከላይ የተቀመጠው እይታ የሚሰጠው ትምህርት ካለ በግርድፉ መዳሰስ ነው የዛሬው ጽሁፍ ዋና ተልዕኮ። ከዛ በፊት እስቲ ከአክሰስ ካፒታል የጥናት ክፍል የተገኙ ቁጥሮችን ሌሎች መረጃዎች መሠረት አድረግን የግንባታ እንቅስቃሴውን እንየው ። 
የሕንጻ ግንባታ
አዲስ አበባ የሕንጻ ግንባታዎቿ የሚካሄዱት በተለያየ መልኩና በተለያዩ አካላት ነው። በመንግሥት በኩል ወደ 81 000 የሚሆኑ የጋራ ሕንጻ ቤቶች (ኮንዶሚንዮሞች) ተገንብተው ነዋሪዎች ተረክበዋል። በሪል ስቴት ኩባንያዎች የተገነቡት ሕንጻዎች ቁጥር ማግኘት እንኳን ባልችልም አዲስ አበባ መስተዳደር 1996/1997 እስከ 1999/2000 ለሪል ስቴት ኩባንያዎች በአጠቃላይ 270 ሄክታር መሬት መስጠቱ እንደ መነሻ መውሰድ ይቻላል። በራሳቸው በባለቤቶቹ የሚሰሩ ቤቶች የድሮ ያህል ባይሆኑም አሁንም ድራሻቸው ጉልህ ነው። ሌላው ክፍል ደግሞ በቤት ስራ ማኅበራት የሚሰሩትን የሚያጠቃልል ነው። 
መጻኢው ፍላጎት
በየዓመቱ ወደ 240 000 አዳዲስ ከተሜዎች ይጨመራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ተጨማሪዎቹ ከተሜዎች የሚኖሩባቸውና የሚሰሩባቸው ሕንጻዎች ያስፈልጋሉ። መጋቢት/ሚያዝያ 2002 ዓ.ም. ለዕጣ ቀርበው ለነበሩ 10 700 ቤቶች ተመዝግቦ የነበረው 485 000 የሚያህል ቤት ፈላጊ የሚያሳየው ምናልባት የቤት ፍላጎቱ ለረጅም ጊዜ ከነበረው ወደ 456 000 በላይ ሊሆን እንደሚችል ነው። መንግሥት በእድገትና ውልጠት ዕቅዱ ውስጥ  ከ2003 ዓ.ም. እስከ 2007 ዓ.ም.  በየዓመቱ 30 000 ቤቶችን በአጠቃላይ በአምስት ዓመት ውስጥ 150 000 ቤቶችን እሰራለሁ ያላቸውም ቢሆኑ ችግሩን ሙሉ በሙሉ አይፈቱትም።
መሐል ከተማ ውስጥ ያሉ የድሮ ሰፈሮችን በማፍረስ የሚሰሩ ሰማይ ጠቀስ የቢሮና የንግድ ሕንጻዎችም ቢሆኑ እየጨመሩ መሄዳቸው አይቀርም - ፍላጎቱ አለና።
እነዚህ ቤቶች በተለይ ደግሞ ሰማይ ጠቀሶቹ ሕንጻዎች እንዴት ይሰሩ የሚለው ነው ወሳኙ ጥያቄ።
ለሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች አሰሪዎች ከሞላ ጎደል ሊባል በሚችል መልኩ በብቸኝነት ገዢ ሆኖ እየታየ ያለው መስፈርት ለአይን በሚያብረቀርቅ መልኩ፤ አነስ ባለ የግንባታ ዋጋና በአጭር ጊዜ ውስጥ ማድረስ ነው። ለአርክቴክቶቻችን እየተሰጣቸው ያለው ተልእኮም ይህንን ከሌሎች አርክቴክቶች በበለጠ ‘እሺ ባይነት’ ማከናወን ይመስላል። ይህን ተልእኮ ለመፈጸም እየተመረጠ ያለው የግንባታ መንገድ በኮንክሪት (አልፎ አልፎ በስቲል) ስትራክቸር ካቆሙ በኋላ ሕንጻውን ከላይ እስከታች በመስተዋት ማልበስ ነው።
እስካሁን በተለያዩ መንገዶች የሚሰማውና በአዲስ ጉዳይም ከአንድም ሁለት ጊዜ የጽሁፍ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ የነበረው የመስተዋት ለበስ ሕንጻዎች የተጠቃሚዎችና የቅርብ ሩቅ ተመልካቾች የምሬት መነሻና መወያያ ለመሆን መብቃታቸው ነው። የምሬቱ ይዘት ከሕንጻዎች የምቹ ስፍራ ልኬት አንጻር ስንመለከተው ግን የነዚህ ሕንጻዎች እንከን መዘዝ ለተጠቃሚዎቹና ለቅርብ ሩቅ ተመልካቾች ብቻ ሳይሆን ለባለቤቶቹ፤በመንግሥት በኩል ለአገሪቱ በመላ የሚተርፍ ነው። እንዴት? 
ባለ ረጅም እጁ እንከን
የሚሰራው እያንዳንዱ ሕንጻ በተቻለ መጠን ከሦስት የአካባቢ ክፍሎች አንጻር እንከን የለሽ ሆኖ መሠራት አለበት።
የመጀመሪያውና ዋነኛው ከምቹ ስፍራ ልኬት ጋር የሚገናኘው የሕንጻው የውስጠኛው አካባቢ ነው። በዚህ የውስጥ ምቾት የሚካተቱት በቂ ብርሃን፤ ንጹህ አየር፤ ምቹ ሙቀት የተሟላለትና እንዲሁም ከሽታ፤ ከድምጽና ከኬሚካል ልቀት የጸዳ ስፍራ መሆኑን ማረጋገጥ ነው። በነዚህ ሕንጻዎች ውስጥ ያሉት ቢሮዎች የሚሰሩ ሰዎች በሙቀትና በቅዝቃዜ እየተማረሩ እንደሆነ ተዘግቧል። ከውጭ በሚገባ ድምጽም መረበሽ አለ። ከበቂ መጠን በላይ ለሆነ ብርሃን መጋለጥም አዋኪ ነው። ይህ ሁሉ ተደምሮ ሲበዛ የጤና መታወክ ቢያንስ ግን የሰራተኞች ስሜት በማበላሸት ምርታማነት ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀርም።ይህ ደግሞ ሕንጻውን የተከራየውን መስሪያ ቤት ኪሳራ ውስጥ የሚከት ነው። የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ሳይቀሩ በእነዚህ ሕንጻዎች ተከራይተው እየተጠቀሙ እንደሆነ ይታወቃል። በቀጥታም በተዘዋዋሪም ኪሳራው የአገሪቱ ይሆናል። ለጊዜው አነስ ባለ ዋጋና በአጭር ጊዜ ውስጥ አብረቅራቂ ሕንጻ እንዲሠራለት ያደረገው ባለሀብት በደንብ የተሠሩ ሕንጻዎች በመጡ ቁጥር ተከራይ እያጣ ሲሄድ መጀመሪያ ከቆጠበው ይበልጥ ይከስራል። ሕንጻዋን አስተካክሎ ተወዳዳሪ ለማድረግ እንኳን ቢያስብ መስራት የሚገባው የእርምት ሥራዎች (ለምሳሌ የአየር ማቀዝቀዣዎችን መግጠም) የሚያስከትሉት ተጨማሪ ወጪ ለባለቤቱ፤ ለአዲስ ተከራይ (ከኃይል አጠቃቀም አኳያ) እንዲሁም ለአገሪቱ የሚተርፍ አስቀድሞ ሊወገድ ይችል የነበረ ጉዳት ነው። 
ሁለተኛው ለአጥቢያው አካባቢ የሚተርፈው መዘዝ ነው። አንድ ጓደኛዬ ጋ ደውዬ ስለዚህ ጉዳይ አንስተን ስናወራ “በመስትዋት ለበስ ሕንጻዎች ምክንያት ሁላችንም መነጽር ታዞልናል” ብሎ የቀለደው መስተዋት ለበስ ቤቶች የቅርብ ሩቅ ተመልካችን የሚያስቸግሩ የአይን ወጊ ንጽብራቄዎች ምንጭ መሆናቸውን የሚያሳብቅ ነው።  
DH Geda

Edna Mall 

Dembel

Getu Commerical Bldng

Nani

Alem Bldng

AU Bldng Design, Inaugurated January 2012 

Axum Bldng

Commercial Bank Bldng Design

Friendship Bldng


ያለምንም አሳማኝ የዲዛይን አመክንዮ ለመስተዋት ልባስ ቅድሚያ እየተሰጠ መምጣቱ ነው የችግሩ ምንጭ። የመስተዋት ልባስ የግድ ነው ከተባለም ተጠቃሚዎች በሕንጻዎቹ ውስጥ ለስራም ይሁን ለሌላ እንቅስቃሴ በሚያሳልፉበት ጊዜ ሁሉ የሚመች የውስጥ አካባቢን ከመፍጠር አኳያና ለአጥቢያው አካባቢም ያለው ተጸእኖ አንጻር ተጠንቶ  ልባሱ ዲዛይን መደረግ አለበት።የዚህ አምድ ስፍራ ለዛሬ እዚህ ላይ አልቋል። እስቲ በሚቀጥለው እትም እንመለስ። 
=======
አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: