Friday, February 3, 2012

ይዘት አልባው የደርባን ስምምነት


(ታኅሣሥ 7 2004 ዓ.ም. ጌታቸው አሰፋ)የድርድሩ ሂደት ሰኞ ኅዳር 18 ከተጀመረ በኋላ ለአንድ ሳምንት ያህል የተካሄደው ከየአገራቱ በተሰባሰቡት ኤክስፐርቶች አማካይነት ነበር። ሚኒስትሮች በሁለተኛው ሳምንት ማክሰኞ ኅዳር 26 ወደ ደርባን ሲገቡ በከፍተኛ ባለስልጣናት ደረጃ ድርድሩ ቀጠለ። መጀመሪያ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት አርብ ኅዳር 29 እንዲያበቃ ስለነበር አርብ ይደረግ የነበረው ድርድር በጣም እየከረረ መጥቶ የመጀመሪያው የስምምነት ረቂቅ ቀረበ። ረቂቁ ከቻይና፤ ከህንድና
ከአውሮፓ ኅብረት ተቃውሞ ገጠመውና ድርድሩ ሌሊትም ቀንም ቀጠለ።
የተለያዩ አገሮች ሚና
የአውሮፓ ኅብረት ወደ ድርድሩ ሲሄድ ይዞት የሚሄደውን የጠራ የድርድር ሃሳብ ወደፊቱ ወደ ስምምነት የሚወስድ ፍኖተ-ካርታ በተመለከተ በይፋ ሲገልጽ የቆየና በድርድሩ ወቅትም ገንቢ ሚና ሲጫወት የነበረ ነው። 
የኦባማ አስተዳደር የአሜሪካን ምጣኔ ሀብት የሚነካ  ምንም አይነት ዓለም አቀፍ ስምምነት  ውስጥ ቢገባ ከዴሞክራቶች ውጪ የሆነው በሥራ ላይ ያለው ኮንግረስ እንደማያጸድቅለት ይታወቅ ነበር። በመሆኑም አስተዳደሩን በአሉታዊ መልኩ የሚያስነሳ ስምምነት ውስጥ መግባት ፓለቲካዊ ዋጋ እንደሚያስከፍለው ስለሚያውቁ በተቻለ መጠን ኦባማ በሕግ አሳሪ ወደ ሆነ ስምምነት መግባት እንደማይፈልጉ እሙን ነበር። በዛ ላይ የአውሮፓ ኅብረት የመሪነት ሚና በሚጫወትበት ሂደት “መምራት እንጂ መከተል አይሆንላትም” የተባለችው አሜሪካ ብዙም ደስተኛ አልነበረችም።  
የአፍሪካው ቡድን ሁለቱ አንኳር ጉዳዮቼ ብሎ የያዛቸው የኪዮቶ ፕሮቶኮልን  በሁለተኛው ዙር ማስቀጠልና የፋይናንስ ጉዳይን ነበር። በዚህ በኩል ለአውሮፓ ኅብረት ያለውን ድጋፍ ከመግለጽ ውጪ ድምጹን ከፍ አድርጎ ሲያሰማ አልታየም። ወደ ደርባን ለሁለት ቀን አቅንተው የነበሩት የአፍሪካው ቡድን መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስም በዋናዎቹ የድርድር ቀናት አርብና ቅዳሜ በቦታው አልተገኙም። ብራዚልና ደቡብ አፍሪካ አስቀድመው ለአውሮፓ ኅብረት የድርድር መስመር ድጋፋቸው ሲሰጡ ቻይናና ህንድ በዛው ቅደም ተከተል የድርድሩን መቀጠልና አለመቀጠል የመወሰን ሚና ነበራቸው።
ስድብ ቀረሹ ምልልስ
የህንድ የአካባቢና የደን ሚኒስትር የአውሮፓ ኅብረት ተደራዳሪዎች ላይ ያነጣጠረው የ“አታግቱን” ንግግር እንዲያደርጉ ያስገደዳቸው በተመዱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ማእቀፍ ውስጥ የተካተተውን “የጋራ ግን የተመጣጠነ ኃላፊነት” የሚለውን መርህ በሚጥስ መልኩ ይገፋ የነበረው የወደፊቱ ስምምነት የሚመለከተው ስምምነት ነው። የአገራቸው እንደ እንቅፋት መቆጠር ያበሳጫቸው ሚኒስትሯ  በአገራቸው ላይ የሚደረገው ግፊት “የ1.2 ቢልዮን ዜጎችን ዘላቂ ሕይወት አሳልፎ በሚሰጥ መልኩ” ገና ይዘቱን በማያውቁት የአውሮፓ ኅብረት ፍኖተ-ካርታ ምክንያት “ደረቅ ቼክ”  ላይ ለመፈርም የመገደድ ያህል ነው። የቻይናው ዋና ተደራዳሪም ከህንዳዊቷ ሚኒስትር ጎን በመቆም የበለጸጉት አገሮችን ግብዝነት በመንቀፍ “እኛ [ታዳጊ አገሮች] ማድረግ ያለብንን ነገር ለመናገር ብቃቱን ማን ሰጣችሁ? እኛ ሥራችን እየሠራን ነው። እናንተም ሥራችሁን ስትሠሩ ማየት እንፈልጋለን።” ብለው አጠንክረው ተናገሩ።
በሠላሳ ስድስት ሰዓታት የተራዘመው ድርድር ተደራዳሪዎች አርብ ሌሊት ለሦስት ሰዓታት ብቻ እንዲተኙ፤ ቅዳሜ ሌሊት ደግሞ ምንም እንዳይተኙ አድርጓል። አንዳንዶች በተንጣለለው አዳራሽ ውስጥ በነበሩት ታጣፊ አልጋዎች ላይ ጋደም ብለው ታይተዋል። አንዳንዶችም የሚናገሩት ንግግር ሳይቀር ሲደነቃቀፍባቸው እንደነበር ተዘግቧል - በድካም ብዛት።


በስተመጨረሻ ላይ መስመር በመስመር እየተናበቡ የተደራደሩበት ባለ 200 ገጽ ዋና ዋና የውሳኔ ሀሳቦችን የያዘው የስምምነት ሰነድ ነው። ይህን ጽሑፍ በምጽፍበት ወቅት ይፋ የሆነው ግን ስምንት አንቀጾች የያዘው ባለ ሁለት ገጹ የደርባን አጀንዳ ለተጨማሪ ሥራ ተብሎ የወጣው የውሳኔ ሀሳብ ብቻ ነው። ደርባን ከአስተናጋጇ አገር መሪ ውጪ የአገራችንና የኖርዌይን መሪዎች እንዲሁም ሌሎች አስር የአፍሪካና የሌሎች ደሴታማ አገሮች መሪዎች ብቅ ያሉበት ነበር።  ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ኮፐንሀገኑ ጉባኤ ያቀኑት ግን የመቶ አገሮች መሪዎች ነበሩ። 
በደርባን ስምምነት ከተካተቱት ዋና ዋና ውሳኔዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል።
የወደፊቱ ስምምነት
በመጨረሻዎቹ ወሳኝ ቀናት የድርድር ማጠንጠኛ የነበረውና የመጨረሻው ስምምነት ዋናው አካል የሆነው የወደፊት ዓለም አቀፍ የልቀት ቅነሳ ስምምነትን የሚመለከተው ስምምነት ነበር። ይህ የወደፊት ስምምነት ይዘቱ አሁን አይታወቅም። ይዘቱን የሚወስነው ድርድር የሚጀመረው በሚቀጥለው ዓመት(2012 እ.እ.አ.) ሲሆን የሚጠናቀቀው ደግሞ በ2015 እ.አ.አ. ነው። የወደፊቱ ስምምነት ከ2020 እ.አ.አ. ጀምሮ ነው ተግባራዊ የሚሆነው። ከኪዮቶ ፕሮቶኮል በተለየ መልኩ የወደፊቱ ስምምነት እነ ቻይና፤ ህንድ፤ ብራዚልና ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ ሁሉንም አገሮች እንዲያካትት ነው ደርባን ላይ ስምምነት የተደረሰው።  የህንድ እስከመጨረሻው ድረስ መከራከርና መቃወምም የሚያያዘውም ህንድ “የታሪካዊው የልቀት መጠን ሚዛን የሚያመዝነው ወደ በለጸጉት አገሮች ሆኖ እያለ ምን በወጣን ነው የልቀት ቅነሳ ስምምነት ውስጥ የምንካተተው?” ከሚል ከቆየና ተገቢ ከሆነ አቋሟ ጋር ነው። እስካሁን ባለው ራሱ ጥሩ የቅነሳ ሥራ መሥራት የሚጠበቅባቸው የበለጸጉት አገሮች ሲሆኑ በተግባር እየሠሩ ያሉት ግን ታዳጊዎቹ ናቸው። 
የወደፊቱ ስምምነት ይዘት ሳይሆን ህጋዊ ምንነት በደርባኑ ሰነድ የሚቀመጥበት አገላለጽ በሁለት ወገን ካሉት አገሮች ማለትም ከነአሜሪካ  በአንድ በኩል፤ ከነህንድ በሌላ ወገን ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። በአውሮፓ ኅብረት በኩል የቀረበው የመጀመሪያው አገላለጽ  ‘ህጋዊ አሳሪ’ የሚለው ነበር። አሜሪካ ‘የወደፊቱን ስምምነት የሚያመጣ የድርድር ሂደትን ለመደገፍ እንጂ የድርድሩን ውጤት ከአሁኑ ግልጽና ጠንከር ተደርጎ መቀመጡን አልደግፍም’ በማለት ተቃወመች። እነ ህንድም ቀድሞውኑም ቢሆን ‘ማንኛውም ስምምነት ታሪካዊ በካዮች ላይ እንጂ እኛ ላይ ማተኮር የለበትም’ ባይ ስለነበሩ ‘ይህ ጠንካራ አገላለጽ እኛንም የሚጨምር ከሆነ ፈጽሞ አንቀበለውም’ የሚል አቋም ይዘው ነበር። ሁሉንም የሚያግባባ ሐረግ ፍለጋ ቃላት እየተሰረዙ፤ቃላት እየገቡ መጨረሻ ላይ ተቀባይነት ያለው ሐረግ የሚያካትት ስምምነት እንዲያመጡ እድል የተሰጣቸው ለህንድና ለአውሮፓ ኅብረት ተደራዳሪዎች ነበሩ። 



አሁን በመጨረሻው ሰነድ ላይ በ2015 እ.አ.አ. እልባት የሚያገኘው ስምምነት ህጋዊ ምንነት የተገለጸበት ሐረግ  “ፕሮቶኮል ወይም ሌላ የሕግ መሣሪያ ወይም ስምምነት የሚደረሰበት ሕጋዊ ሀይል ያለው ውጤት” የሚል ላላ ያለ አገላለጽ ነው። በመሆኑም የደርባኑ ስምምነት ሁሉም አገሮች ይዘቱ በማይታወቀው በወደፊቱ ስምምነት ለመስማማት መስማማታቸውን የሚያሳይ ብቻ ነው። ይህ በተግባር ሲገለጽ ለየአገራቱ የሚኖረው ተጨባጭ አንድምታ ከጊዜ በኋላ የምናየው ይሆናል።  
ዳግማዊ ኪዮቶ
“እስከ 2020 እ.አ.አ. ባሉት ዓመታትስ ምን ይደረግ?” ለሚለው ጥያቄ ደርባን የሰጠችው መልስ የአውሮፓ ኅብረት የፍኖተ-ካርታ ሀሳብ  መሠረት የኪዮቶ ፕሮቶኮል በሁለተኛው ዙር እንዲቀጥል የሚል ነው - በተወሰኑ አገሮች ብቻም ቢሆን።  የዛሬ አስር ዓመት ‘የለሁበትም’ ብላ ከስምምነቱ የወጣችው አሜሪካን ጨምሮ ራሺያና ጃፓን በኪዮቶ አንቀጥልም ብለዋል። የአንደኛው ዙር ማብቂያ አንድ ዓመት በቀረበት ሁኔታ የቅነሳ ግዴታዋን መወጣት የማትችለዋ ካናዳ የሚደርስባትን እስከ 14 ቢልዮን ዶላር (በቅሪታዊ ነዳጅ ኩባንያዎች የሚነዳው የገዢው ወግ አጥባቂ ፓርቲ የአካባቢ ጉዳይ ሚኒስትር አጋንነው ያቀረቡት ቁጥር ነው።) የሚደርስ ቅጣት ላለመክፈል አሁኑኑ ከፕሮቶኮሉ ወጥቻለሁ ብላለች። ሚኒስትሩ ይህንን አስገራሚና አሳፋሪ መግለጫ የሰጡበት ያለፈው ሰኞ የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለካናዳ ‘ጥቁር ቀን’ ብለውታል። ዝርዝሩና የጊዜ ሰሌዳው የሚወሰነው በቀጣይ ድርድር ቢሆንም አሁን ባለው ግን በኪዮቶው ሁለተኛ ዙር የሚቀጥሉት የአውሮፓ ኅብረት፤ ኖርዌይና ስዊዘርላንድ ሲሆኑ የቅነሳና የገደብ መጠን የሌለባቸው ሌሎች ታዳጊ አገሮችም ስምምነታቸውን ገልጸዋል። የአውሮፓ ኅብረት በራሱ ጊዜ እስከ 2020 እ.አ.አ. የልቀት መጠኑን በ20 ፐርሰንት ለመቀነስ አስቀድሞ ስለወሰነ ይህንን ውሳኔውን ወደ ሁለተኛው ዙር መውሰድ ይችላል። የኪዮቶ ፕሮቶኮል ሁለተኛው ዙር መራዘም በዓለም ደረጃ አዲስ የሚጨምረው  የቅነሳ መጠን እንኳ ባይኖር በ2020 እ.አ.አ. ሥራ ላይ መዋል ይጀምራል የተባለው አዲስ ዓለም አቀፍ ስምምነት ተግባራዊ እስኪሆን ድረስ ክፍተት እንዳይፈጠር ከማድረጉም በላይ ከፕሮቶኮሉ ጋር ተያይዘው የተፈጠሩት የማስፈጸሚያ ስልቶችና መሣሪያዎች ህያው ሆነው እንዲቀጥሉና ለአዲሱ ስምምነት የሚሆን የይዘትም የማስፈጸሚያ ግብአትም ይሰጣል የሚል ተስፋ አለ። 
የልቀት ቅነሳን በተመለከተ ከሁለተኛው የኪዮቶ ዙር ውጪ ላሉት አገሮች ለጊዜው ያለው ከሁለት ዓመት በፊት በኮፐንሀገኑ ድርድር መሠረት ቃል የገቧቸውና ይፋ ያደርጓቸው በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረቱት ብሔራዊ የልቀት ቅነሳ  እቅዶች ናቸው። ለምሳሌ አሜሪካ እስከ 2020 እ.አ.አ. በ17% እቀንሳለሁ እንዳለችው አይነት። 
ገንዘብና ሌሎች
ባለፈው የአዲስ ጉዳይ እትም ጽሑፌ ላይ እንደጠቆምኩት ሌላው አቢይ ጉዳይ የአረንጓዴ አየር ንብረት ፈንድን የተመለከተው ነበር። ይሁንና ፈንዱ ሥራ እንዲጀምር ከመወሰን ባለፈ ገንዘቡ ከየት፤ እንዴት፤ በምን መጠን እንደሚመጣ ደርባን ይሄ ነው የሚባል ውሳኔ አላሳለፈም። ፈንዱ ገንዘብ አልባ ሆኖ ነው የሚጀምረው ማለት ነው። ቀደም ብሎ የነበረው ስምምነት ከ2010 እስከ 2012 እ.አ.አ. ድረስ ለመነሻ የሚሆን 30 ቢልዮን ዶላር እንዲኖር ከ2020 እ.አ.አ. ጀምሮ ደግሞ በዓመት 100 ቢዮልን ዶላር የሚደርስ መጠን እንዲሆን ነበር። እስካሁን የተጀመረ ነገር ለመኖሩ ምንም ምልክት የለም። ታዳጊ አገሮች ወደ ደርባን የሄዱት ፈንዱ በአፋጣኝ ገንዘብ ያለው እንዲሆን፤ ከገንዘቡም ግማሽ በግማሽ ለስርየትና ለማጣጣሚያ ሥራዎች የሚውል ሆኖ እንዲዋቀር ለማስደረግ ነበር። ይልቁንም በደርባን ስምምነት ፈንዱ ለግል ኩባንያዎች ብሔራዊ፤ ክልላዊና ዓለም አቀፋዊ የስርየትና የማጣጣሚያ ፕሮጄክቶችን እንዲፈጽሙ የሚያስችል ተደርጎ መዋቀሩ የፈንዱን ገንዘብ የምዕራባዊያኑ ትልልቅ ኩባንያዎች ሲሳይ እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል የሚል ስጋት አለ። 
የቴክኖሎጂ ክንውንታም ሌላው የደርባኑ ስምምነት አካል ነው። የአየር ንብረት ቴክኖሎጂ ማዕከልና መረቦች ማቋቋም አንዱና ዋናው ሥራ ሲሆን የማዕከሉ አላማም ለታዳጊ አገሮች የሚሆኑ የስርየትና የማጣጣሚያ ቴክኖሎጂዎችን ማልማት፤ ማስፋፋትና ጥቅም ላይ ማዋል ነው። የተመዱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ማዕቀፍ ጽ/ቤት የማዕከሉን መቀመጫ ለመወሰን የሚረዳውን ሁኔታ ለማመቻቸት በሁለት ወር ውስጥ የመቀመጫ ሀሳቦችን መቀበል እንዲጀምር በደርባን ተወስኗል። የማጣጣሚያ ኮሚቴም ተቋቁሟል። የደን ምንጣሮን ለመቀነስ የሚያስችሉ ፕሮጄክቶችንም ለመደገፍና  በተቻለ መጠን ለመምራት ከስምምነት ላይ ተደርሷል። የካርበን ማስወገጃና ዕቀባ ፕሮጀክቶችም የኪዮቶ ፕሮቶኮል አንዱ አካል በሆነውና ‘የማይበክል የእድገት ክንውንውታ’ ተብሎ በሚጠራው ስልት ውስጥ እንዲጨመር ተደርጓል- በደርባን ። የማይበክል የእድገት ክንውንውታ  በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ተቀርጸው የሚተገበሩ ልቀት ቀናሽ ፕሮጄክቶችን የሚመለከተው ስልት ነው። ለምሳሌ በኢትዮጵያ  በወላይታ የሚገኘው የሁምቦ ደን ልማት ፕሮጄክት የዚህ ስልት አካል ነው። ታዳጊ አገሮች በቴክኖሎጂ ክንውንውታ ላይ ያነሱትና ስምምነቱ ላይ እንዲካተት የጠየቁት ከቴክኖሎጂዎች ጋር የተያያዘ የአእምሮአዊ ንብረት መብት ጉዳይ ሳይካተት ቀርቷል። አለመካተቱ አሁንም ቴክኖሎጂን የሚያለሙት የበለጸጉት አገሮች ኩባንያዎች የታዳጊ አገሮችን የቴክኖሎጂ ገበያ እንዲቆጣጠሩ የሚያስችል ለማድረግ ይሆናል የሚል ሥጋት አለ።
ተደምሮ ተቀንሶ በደርባን የተደረሰበት ስምምነት በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የሚደረገውን የተመድ የድርድር ሂደትን ከመበታተን አድኖታል። የዓለም የከባቢ አየር ሙቀት እየጨመረ እንዳይሄድ የሚታደግ ስምምነት ግን አይደለም። ሳይንሱ እንደሚያሳየው ከሁለት ዲግሪ ሴንት ግሪድ የጭማሪ ጣራ በታች ለመሆን ውኃ የሚቋጥር የቅነሳ ሥራ መሠራት ያለበት ቅድመ 2020 እ.አ.አ. ነው። ደርባን ግን ሁሉን አቀፍ አስገዳጅ የቅነሳ ሥራን ወደ 2020 እንዲገፋ ነው ያደረገው። በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረቱት የቅነሳ ቃል ኪዳኖች ላይ መሠረት ያደረጉት ስሌቶች የሚያሳዩት ደግሞ የከባቢ አየር ሙቀት ጭማሪ ከሁለት ዲግሪ በታች መሆኑ ቀርቶ ከሦስት እስከ አራት ሴንቲ ግሬድ ሊደርስ እንደሚችል ነው።  ‘ሁለት ዲግሪ ራሱ በዛ፤ አንድ ነጥብ አምስት ዲግሪ ነው መሆን ያለበት’ እያሉ ሲጮሁ ለነበሩት የትናንሽ ደሴታዊ አገሮች ስብስብና አፍሪካን ለመሳሰሉት የአየር ንብረት ለውጥ ተጠቂ ክፍለ ዓለሞች የደርባኑ ስምምነት ይዘት አልባ ነው።
ከሁለት ዓመታት በኋላ የተመዱ የበይነ-መንግሥታት የአየር ንብረት ሳይንቲስቶች ቡድን ማለትም አይ.ፒ.ሲ.ሲ. አምስተኛው ሪፓርቱን ሲያቀርብ የቀጣይ ድርድሮች አካሄድና የወደፊቱ ስምምነት ይዘት ላይ የሚያደርሰው በጎ ተጽእኖ ይኖራል ተብሎ ተስፋ ይደረጋል።
የሚቀጥለው የባለጉዳይ አካላት ጉባኤ የሚደረገው በኳታር ነው። ጊዜው ከኅዳር 17 እስከ 28 ቀን 2005 ዓ.ም. ሲሆን ኳታር ለዝግጅቱ የደቡብ ኮሪያን እገዛ ታገኛለች። በዚህ ዓምድ ለአምስት ተከታታይ እትሞች በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የቀረቡት ጽሑፎችም እነሆ ፍጻሜ አገኙ። 

=======
አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: