Friday, February 3, 2012

ሰነድ ወደ መሬት ሲወርድ

(ጌታቸው አሰፋ፤ ጥር 5 ቀን  2004 ዓ.ም.) የዛሬ ሁለት ሳምንት በወጣው ጽሑፌ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት በደርባን ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ይፋ ባደረገው በእንግሊዝኛ  የቀረበው “የኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስልት” ሰነድ ላይ በመመሥረት የሰነዱን ይዘት በወፍ በረር ተመልክተን ነበር።
ለዛሬ በዚህ ሰነድና በአምስት ዓመቱ የዕድገትና ውልጠት ዕቅድ ሰነድ ላይ ስለ ደን ጥበቃና ልማት የተባለውንና መሬት ላይ እየተደረገ ካለው ጋር እንመለከታለን።

የደን ሀብታችን
ነገሮችን በአሀዝ በትክክልና በወጥነት የማስቀመጥ ችግር ያለበት አገር ይዘን በአሀዝ ለመነጋገር መድፈራችን ከባድ ቢሆንም መንግሥትም ከላይ በተጠቀሱት ሁለት ሰነዶችም አሀዞችን ስላስቀመጠ ቁጥሮችን መጠቃቀስ የግድ ይለናል። ሁለቱም ሰነዶች ስለ ደን የጠቀሱበት ክፍል ውስጥ ሳይቀር የአገሪቱ የደን ሀብት ምን ያህል እንደሆነ ምንም ያሉት ነገር የለም።
እስከ 2007 ዓ.ም. ድረስ 2000 ኪሎ ሜትር ካሬ የተራቆተና የተጎዳ ተዳፋት መሬት በደን መሸፈን 25000  ሜትር ካሬ ምርታማ ደን  ማልማት በዕድገትና ውልጠት ዕቅድ ሰነድ ላይ የሰፈረ ነው። በተጨማሪም በዛው ሰነድ  2876 ኪሎ ሜትር ካሬ  የተፈጥሮ ደን፤ 4390.6  ኪሎ ሜትር ካሬ ቅጠለ ረገፍ ደን፤261840 ኪሎ ሜትር ካሬ የጥምር ደን ሥራ ማካሄድ እስከ 2007 ዓ.ም. ድረስ ከሚተገበሩ ሥራዎች መካከል ተብለው ተይዟል። በዋናው ሰነድ እነዚህ ሥራዎች ምን ማለት ናቸው የሚለውን አናገኘውም። ለምሳሌ 2876 ኪሎ ሜትር ካሬ  የተፈጥሮ ደን ምን ለማድረግ ነው? ለመጠበቅ ከሆነ ለምን ይሄ ብቻ? ወይስ ያለን የተፈጥሮ ደን ይሄ ብቻ ነው? መልሱን የምናገኘው በሰነዱ የፓሊሲ ሰንጠረዦች ሰነድ ላይ ነው። ከዛ በፊት ግን ለመሆኑ የደን ሀብታችን ምን ያህል ስፋት አለው? ከታች እንደምንመለከተው አንዳንድ የመንግሥት ሹሞች ወደማያሳምንና ‘ደን ምን ማለት ነው?’ ወደሚያሰኝ አይነት የግብር ይውጣ ክርክር ሳንገባ ከመንግሥትና ከሌሎች ምንጮች የተገኘው የተፈጥሮ የደን ሀብታችን በተመለከተ መረጃ የሚከተለውን ይመስላል።
ከ18 ዓመታት በፊት የወጣ መረጃ 2.3 ሚልዮን ሄክታር እንደሆን ሲነግረን፤ 4 ዓመት ቆይቶ ደግሞ ሌላ መረጃ  5.755 ሚልዮን ሄክታር ነው አለን።  ከ11 ዓመታት በፊት 4.506 ሚልዮን ሄክታር እንደሆነም የሚናገር አለ። በሦስተኛው ዓመት የአገሪቱ የተፈጥሮ ደን 4.072 ሚልዮን ሄክታር እንደሚሸፍን ደርሸበታለሁ ያለው የመንግሥት የጥናት ፕሮጄክት ነው። በዓመቱ ከዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት የተገኘ መረጃ ደግሞ ይሄን ቁጥር በሦስት እጥፍ አሳድጎ ወደ 12.509 ሚልዮን ሄክታር  ነው ይላል። 
የረጅም ጊዜው ስልት ሰነድ በሚጠቅሰው የመንግሥት ፕሮጄክት መሠረት የአገራችን የተፈጥሮ የደን ሽፋን 4.072 ሚልዮን ሄክታር (40 720 ኪሎ ሜትር ካሬ) መሆኑ ነው። በዕድገትና ውልጠት ዕቅድ ሰነድ ላይ የሰፈረውና ከላይ የተጠቀሰው 2 876 ኪሎ ሜትር ካሬ የተፈጥሮ ደን እንግዲህ ከአጠቃላዩ ሰባት ፐርሰንት የሚሆነውን በደን ጥበቃ ላይ ለተመሠረተ የካርቦን ስርየት ፕሮጄክቶች ለመቅረጽና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድጋፍ ለማስገኘት ይውላል ማለት ነው።
መንግሥት ከካርቦን ዕቀባ ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፍ “ገበያ” ያስገኙልኛል ብሎ በዕድገትና ውልጠት ዕቅዱም ሆነ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስልቱ ውስጥ የጠቀሳቸው የፕሮጄክት ሀሳቦች የተፈጥሮ ደን አዛላቂ በሆነ መልኩ ማስተዳደርን ብቻ አይደለም። በስልቱ ላይ ከአሁን በፊት ደን ያልነበረበት ወደ ሁለት ሚልዮን ሄክታር የሚሆን የግጦሽ መሬትን በደን መሸፍን አንዱ ሥራ ተደርጎ ተወስዷል። ሌላውም ከአሁን በፊት ደን የነበረበትና የተራቆተ ወደ አንድ ሚልዮን ሄክታር የሚሆን መሬት በደን ማለበስም በስልቱ ውስጥ የተካተተ ነው። እነዚህ ሦስት ከደን ጋር የተያያዙ ጥሩ ሥራዎች ምን ያህል ካርቦን ማሰረይ እንደሚችሉና ለመተግበር የሚያስፈልጋቸው ወጪ በሙሉ በዶላር ተሰልቶ ተቀምጧል- በስልቱ።
ለዛሬ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ እንቆቁልሽ የሚመጣው ግን በአንድ በኩል አዳዲስ የደን ልማቶች አካሂዳለሁ የሚለው መንግሥት ለባለሀብቶች ለሰፋፊ እርሻዎች እንዲሆናቸው ከሚሰጣቸው መሬት ጋር በተያያዘ እየተመነጠረ ያለው የተፈጥሮ ደን ሀብት በተመለከተ በሹሞቹ በኩል የሚሰጠው ሲቃለል ግራ አጋቢ፤ የምር ሲታይ አሳሳቢ የሆነው መልስ ነው። 
የጉማሬ ቀበሌ እንደ ምሳሌ
እንደሚታወቀው ያለን የተፈጥሮ ደን  ሀብት ከሞላ ጎደል የሚገኘው በደቡብ ምዕራብና በደቡብ ኢትዮጵያ የተወሰኑ ቦታዎች ብቻ የሚገኝ ነው። በክልል ደረጃ በጋምቤላ፤ በኦሮሚያና በደቡብ ክልል ውስጥ ማለት ነው።
የሥራ ዕድል መፍጠርና የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ መንግሥት ሊቆምለት የሚገባ ዓላማ ነውና ያንን ለማድረግ ሰፋፊ እርሻዎችን የሚያስፋፉ ባለሀብቶችን ማበረታቱ ተገቢ ነው። ግን ደን ካልተመነጠረ የሥራ ዕድል መፍጠር አይቻልም፤ የምግብ ዋስትናም ማረጋገጥ አይቻልም የተባለ ይመስል ሁለቱን ማጣረስ ግን ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም። 
ካላት ስፋት አንጻር በስፋት በተፈጥሮ ደን የተሸፈነችው ጋምቤላን ስንወስድ የህንድ ኩባንያ ሻይ፡ቅጠል ለማልማት ብሎ በጉማሬ ቀበሌ የወሰደው መሬት ጋር በተያያዘ  ያለውን ችግር እንደማሳያነት እንየው እስቲ። 
የጉማሬ ቀበሌ አስተዳዳሪ አቶ ታምሩ አምበሎና ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ደብዳቤ የጻፉበት፤ የአካባቢ ተቆርቋሪዎች መድረክ ጥናት ያደረገበት ይህ በጥበቃ ሥር የነበረ ከሦስት ሺህ ሄክታር በላይ የሆነ የተፈጥሮ ደን አደጋ ላይ ወድቋል።
አምና ታኅሣሥ አንድ ቀን የተጻፈው የፕሬዚዳንቱ  ደብዳቤ የዚህን የተፈጥሮ ደን ምንነትና ሌሎች ቁም ነገሮችን  ስለሚገልጽ ሙሉ ደብዳቤውን እንዲያነቡት እነሆ።የጉማሬ ቀበሌ አስተዳዳሪ፡ የወረዳው ነዋሪዎች ያቀረቡት አቤቱታ ወደ ጎን በመተው፤ ከወረዳ እስከ ፌደራል ያሉ የደን ባለሞያዎች ባላመኑበት ሁኔታ፤ በአካባቢ ጉዳይ ለዓመታት የሚታትሩት ፕሬዚዳንት የጻፉትን ደብዳቤ ግምት ውስጥ ሳያስገባ፤እንዲሁም የፌደራል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ማሳሰቢያም ችላ በማለት የግብርና ሚኒስቴር ደኑ ተመንጥሮ የሻይ ቅጠል እንዲለማበት አድርጓል።
ችግሩን መሪር የሚያደርገው ከመንግሥት ሹሞች የሚሰጠው ምላሽ ሲጀመር ገንቢና አመክኖያዊ አለመሆኑ ቢያሳስብ አይገርምም።
አምና አንድ የግብርና ሚኒስቴር ሹም  “የሻይ ቅጠል ልማትም ደን ማለት ነው።” ማለታቸው ሪፓርተር ሲዘግብ፤ በዛው ስም የሚጠሩ የልማት ባንክ ፕሬዚደንትም አሁን በቅርቡ ደን እየመነጠረ ላለ የህንድ ኩባንያ እንዴት ነው 89.5 ሚልዮን ብር ብድር  እንዲሰጠው  የምትፈቅዱት ተብለው ሲጠየቁ የሰጡት መልስ ያው ራሱ “የሻይ ቅጠል ልማትም ደን ማለት ነው።” የሚል መሆኑ ያሳዝናል። 
የግብርና ሚኒስትሩ ባለሥልጣንማ አንዴ ”ደኖችን ዝም ብለን ይዘን መቀመጥ አንችልም” ሲሉ እንደገና ቁጥቋጦ ነው ብለው ሲያጣጥሉ፤ እንደገና የአካባቢ ተጽእኖ ግምገማ ከተደረገ በኋላ ነው ልማቱ የሚካሄደው እያሉ የተዘበራረቀ ነገር እንደተናገሩ ተዘግቧል። የክልሉ ፕሬዚዳንት ሳይቀሩ ምንም አይነት ጉዳት በደኑ ላይ እንደማይደርስ በጥናት ተረጋግጧል ማለታቸው ከተዘገበ በኋላ ነው ችግሩ እየተፈጠረ ያለው። 
መንግሥት በአንድ በኩል ለካርቦን ስርየት የሚሆን ደን ላለማ ነው፤ካለውም የተፈጠሮ ደን ውስጥ በአዛላቂ መልኩ አስተዳድረዋለሁብሎ ገንዘብ ለማስገኛ ለውጪ መንግሥታት እያቀረባቸው ያለው ሰነዶች ይዘትና እና መሬት ላይ እየሆነ ያለው ነገር አለመጣጣሙ ለአገሪቱ ወደፊት የሚያስከፍላት ዋጋ ቀላል አይሆንም።
ዛሬ የሚታቀደው የምርት መጨመር፤ ዛሬ የሚገነባው መሠረተ ልማት በደቂቃዎች ውስጥ ሊወድም ይችላል - በተዛባ የአየር ሁኔታ። የአየር መዛባትንና የአንድ አገር ምርት መጨመርን አዛላቂ በሆነ መልኩ ለማሳካት ደግሞ የደን ጥበቃና ልማት ሥራ በተመለከተ በአፍ የሚባለው፤ በመጽሐፍ የሚጻፈውና በመዳፍ የሚሠራው አንድና ያው መሆን ይኖርበታል።
የደኑን መመንጠር የሚቃወሙት በሙሉ ልማቱን ለማደናቀፍ ሆን ብለው የሚሠሩ ኃይሎች ናቸው ብሎ መውሰድ አይገባምም አይቻልምም። በስህተት ወይም ከመንግሥት እውቅና ውጪ ችግር ቢፈጠር ኖሮ አንድ ነገር ነበር። በመንግሥት ባለስልጣናት አንዴ ችግሩ እንደሌለ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ማስቀረት የማይቻልና የግድ መሆን ያለበት ችግር አድርጎ ማቅረብ ግን የጤና አይደለም።
ፕሬዚዳንት ግርማ የዛሬ ስምንት ዓመት ያደረጉት ንግግር አሪፍ መዝጊያ ይሆናል ለዛሬ ጽሑፍ፡“ኢትዮጵያ አረንጓዴ መሆን አለባት ሲባል በንግግር ብቻ ሳይሆን በተግባርም መገለጥ አለበት።”

=======
አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: