Thursday, February 16, 2012

‘አረንጓዴ’ የሕንጻ ግንባታ

(ጌታቸው አሰፋ፤ የካቲት 3 ቀን  2004 ዓ.ም.) ባለፈው እትም ስለ ሕንጻዎቻችን በጀመርነው ጽሑፍ ማጠቃለያ ላይ የሚገነባው እያንዳንዱ ሕንጻ በተቻለ መጠን ከሦስት የአካባቢ ክፍሎች አንጻር እንከን የለሽ ሆኖ መሠራት አለበት ብለን ነበር የፈጸምነው።
የመጀመሪያውና ዋነኛው ከምቹ ስፍራ ልኬት ጋር የሚገናኘው የሕንጻው የውስጠኛው አካባቢ ነው ብለን በውስጥ ምቾት ስር ስለሚካተቱት በቂ ብርሃን፤ ንጹህ አየር፤ ምቹ ሙቀት፤ሽታ አልባ፤ ድምጽና ኬሚካላዊ ልቀት የለሽ ስፍራ ስለ መፍጠር አንሰተን ነበር ያበቃነው።  እስቲ ያዝ ካረግንበት እንልቀቀው።

በሁለተኛ ደረጃ ሕንጻው ለአጥቢያው ጤነኛ መሆን በጎ ወይም ገንቢ አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት። ለምሳሌ ሕንጻው ባረፈበት አካባቢ ያለ ወይም የነበረ የብዝኃ ሕይወት ሀብት መጠበቅ ወይም መበልጸግ እንዲችል ሆኖ ሊገነባ ይገባል።ከአይን-አጥፊ ንጽብራቄም ነጻ መሆን አለበት። በቦታው ያሉት የእጽዋት አይነትና ብዛት ሳይቀነሱና ሳይጠፉ ማቆየት ለሚያስችሉ (ሲሆን እንዲጨመሩ) የአቀማመጥና የዲዛይን አማራጮች ቅድሚያ መስጠትን ያካትታል። 
ሕንጻዎችና ሉላዊ ተጽእኖአቸው
ሦስተኛው ልኬት ሕንጻዎች በዓለም አቀፋዊው (ሉላዊ) አካባቢ ላይ ሊያሳድሩ የሚችሉትን ተጽእኖ መቀነስን የሚመለከተው ነው። አንድን ሕንጻ ለመሥራት የምንጠቀምባቸው የግንባታ እቃዎች (ብረት፤ ስሚንቶ፤ ጣውላ ወዘተ) ሲመረቱም ሲጓጓዙም የሚለቋቸው በካይ ጋዞች አሉ። ለግንባታ የምንጠቀምባቸው ማሽነሪዎችም የሚለቁት ብክለት አለ። ከተገነባ በኋላም ለመብራት ለማሞቂያ ይሁን፤ ማቀዝቀዣ ወዘተ የሚያስፈልገው ኃይል የራሱ የሆነ ተጽእኖ አለው (እንደ ማመንጫው አይነት)። ከልቀት ጋር የሚያያዘው ተጽእኖ በተለያየ መልኩ ሊገለጽ ይችላል። የአየር ንብረት ለውጥ አንዱ ነው። ሌላው መርዛማ ልቀቶች ጋር የሚያያዘው ነው። ከአደገኛ የጸሐይ ጨረር የሚታደገን የኦዞን ንጣፍ መሳሰትም ሌላው ነው። አሲዳማነት፤ የውኃማ አካላት ከመጠን በላይ መዳበር፤የምድር-ቀረብ ኦዞን መፈጠር ወዘተ ከሕንጻ ግንባታ እቃዎችና ከሕንጻው አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ሊከሰቱ የሚችሉ የአካባቢ ተጽእኖዎች ናቸው። 
ባለሚናዎቹና ሚናቸው
የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኅበርና መሰል ድርጅቶች በሞያቸውና እውቀታቸው ብቻ በመመራት መስራት እንዲችሉ የራሳቸውን አቅም ገንብተው ለባለሀብቶች ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጀምሮ ልዩ ልዩ የምምክር መርሐ ግብሮችን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል። በአገሪቱ የሕንጻ ግንባታ ኮድ የተቀመጠው ዝቅተኛው  መስፈርት መሟላቱን መከታተል ከመንግሥት ይጠበቃል። አርክቴክቶቻችንና መሐንዲሶቻችን ሲሆን ከዝቅተኛው መስፈርት የላቀ ሥራ መሥራት ቢያንስ ግን ያንኑ የሚያሟሉ ሕንጻዎችን በተገቢው ቦታ ቆመው እንድናይ ሊረዱን ይገባል። የሪል ስቴት ኩባንያዎች አንድ ላይ በመሰባሰብ አቅማቸውን አጣምረው ሕንጻዎቻችን ተረጋግተው የሚያረጋጉን እንዲሆኑ ተደርገው እንዲሠሩ የተቻላቸውን ሁሉ ማድረግ አለባቸው።
ዋና ዋና የሚባሉት ኩባንያዎች በሊዝ የወሰዱትን የመሬት ስፋት ምን አይነት ሕንጻ ይሰፍርበት ይሆን? በሰንሻይን ኮንስትራክሽንና በሌሎች ኩባንያዎች እጅ የገባው የ57.2 ሄክታር መሬት ላይ የሚገነቡት ሕንጻዎች ለአዲስ አበባ ገጽታ አዎንታዊም አሉታዊም ሚና ይኖራቸዋል - እንደየአሠራራቸው። በየክፍለ ከተማው ለቤት ግንባታ የተሰጠው ከ260 ሄክታር በላይ መሬት አዳዲስ ሕንጻዎችን ሲያስተናግድ በውዴታ ግዴታ ምን ያህል ዛፎች አብረው ይተከላሉ? - ተገቢ ጥያቄ። ወደ 11 ሄክታር የሚሸፍኑ 42 ህንጻዎች ላይ ትኩረት በመስጠት የተደረገው የአክሰስ ካፒታል ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ በካሬ ሜትር ለቢሮና ለንግድ የሚሆኑ ህንጻዎች ከ75 ብር እስከ 120 ብር ድረስ ይከራያሉ። ከዚህ ውስጥ በካሬ ሜትር የተወሰነ ሳንቲም እንዲመድቡ በማድረግ በአካባቢው ዛፍ ተክሎ እና አስተክሎ የከተማዋን ውበት በመጠበቅ የከተማዋን የከባቢ አየር ሙቀት ማለዘብ ይቻላል። በቅርቡ ከተሰጠውና እየተሰጠ ካለው መሬት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ የሚሆነው ለቢሮና ለንግድ ለሚሆኑ ሰማይ-ጠቀስ ሕንጻዎች የሚውል ነው ተብሏል። አዲስ የሚገነቡቱ ውጤታማ መፍትሔዎችን ከመጀመሪያው አብረው እንዲፈተሉ ለማድረግ መልካም እድልን ይፈጥራሉ። በአገራችን የሚሠሩት መስተዋት-ለበስ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች ከሞላ ጎደል ገንዘብ አውጥቶ የሚያሠራቸውም፤ ከተሠሩ በኋላም ባለቤት ሆኖ የሚያከራያቸው ወይም የሚጠቀምባቸው ያውና አንድ ሰው ወይም አካል ነው። ይህ ማለት ተከራይቶ የሚጠቀምባቸው ሰው ወይም አካል ሌላ ቢሆንም  እንኳን ከኪራዩ የሚጠቀመው ያው ያሠራውና ባለቤቱ ስለሆነ በትንሽ ጭማሪ ዋጋ ሕንጻው በጥሩ ሁኔታ እንዲገነባ ቢያደርግ ጥሩ ዋጋ የሚከፍል ተከራይ በማግኘት፤ የማስተዳደር ወጪውን በመቀነስ፤ በትንሽ ጥገና ለረጅም ዕድሜ እንዲቆይ በማድረግ ወዘተ ተጠቃሚ መሆን ይችላል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የላቀ የሕንጻ ግንባታ ተሞክሮን አዘጋጅተው በማሳተም ለተጠቀሚዎች ማዳረስ ቢችሉ ያምርባቸዋል። ብዙኃን መገናኛዎች አርአያ ለሆኑ ሕንጻዎችና ከነሱ ጀርባ ላሉ ባለሞያዎችና ባለሀብቶች ሰፊና ጥራት ያለው ሽፋን መስጠት ቢችሉ የራሳቸውን ድርሻ ተወጡ ማለት ይሆናል።
መደረግ ያለበት
የዲዛይንና ግንባታ አካሄዶችን ማስተካከል አንዱና ዋነኛው ነው።አዲስ አበባ ወደ ጎን እየሰፋች መሄድ እንደሌለባት አንድና ሁለት የለዉም። አዎ ወደ ላይ ነው ማደግ ያለባት። ለዚህ ደግሞ ሰማይ-ጠቀስ ሕንጻዎች ጉልህ ሚና አላቸው። በእነዚህ አይነት ሕንጻዎች ደግሞ ቀለል ያሉ (ክብደታቸው ዝቅ ያለ) የሕንጻ ግንባታ እቃዎች ወሳኞች ናቸው። መስተዋትና አሉሚኒየም የመሳሰሉትን እቃዎች ጥቅም ላይ ማዋል ሊያስፈልግ ይችላል። መቼም አንዱ ሕንጻ ከሌላው ሕንጻ የተለየ እንደሆነ ይታወቃል -  በአቀማመጥ ፤በግንባታ እቃው አይነት፤በሚጠይቀው አገልግሎት ወዘተ። ለሌላ አገር የሚሠራና የግድ የሆነ ነገር ለኛ የሚሠራ ላይሆን ይችላል። ለምሳሌ ካለንበት የአየር ንብረትና ሁኔታ አንጻር መስተዋትን አለመጠቀም ሊመረጥ ይችላል። መጠቀም ቢፈለግ እንኳን መዘዙን ለሕንጻው ተጠቃሚዎችም ሆነ ለከተማዋ በአጠቃላይ በሚጎዳ መልኩ እንዳይሆን አብረው የሚሄዱ ቴክኒካዊ መፍትሔዎች ያስፈልጋሉ። አዲስ አበባ በሕንጻዎችዋ ውስጥም ሆነ ውጪ ነዋሪዎችዋን በሙቀት የምትጠብስ ከተማ መሆን የለባትም። ገና ሕንጻዎቻችን በዲዛይን ጠረጴዛ ላይ ባሉበት ወቅት ካልታሰበበት በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ማቀዝቀዣም ሆነ ሌሎች መሳሪያዎችን ተጠቅመን ከሙቀት ቃጠሎ ራሳችንን ብናድንም እንኳን የአገሪቱን ኢኮኖሚ ሊቀር በሚችል ወጪ ማቃጠላችን የግድ ሊሆን ነው።    
በተቻለ መጠን በአካባቢው በሚገኝ ዕቃ መሥራት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። ብዙ ርቀት አጓጉዘን የምናስመጣውን ማስቀረትን ይጠይቃል - የግድ ካልሆነ።በአገር ውስጥ በሚገኙ የግንባታ እቃዎች የሚገነቡ ሕንጻዎች መበራከት ኢኮኖሚያዊውም አካባቢያዊውም ሆነ ማኅበራዊ ጠቀሜታው የጎላ ነው። አገራችን ሕንጻዎችን ለመሥራት የሚያስችሉ አበይት ጥሬ እቃዎች በስፋት የሚገኙባት አገር መሆኗን መሠረት ያደረገ የስነ ሕንጻ እንስቃሴ መታየት አለበት። የግንባታ እቃዎች በመንግሥት መረጃ መሠረት ከአምስት ዓመታት በፊት ከነበረው ዋጋ አንጻር በ125 ፐርሰንት ጭማሪ አሳይቷል። እንደ ስሚንቶ የመሳሰሉ ወሳኝ ግብአቶች ዋጋ ደግሞ እስከ 300 ፐርሰንት ጨምሯል። ልክ እንደስሚንቶው ሁሉ ሌሎች ግብዓቶችም በአገር ቤት ጥሬ ዕቃዎች በአገርቤት ብዙ ርቀት ሳይኬድ የሚመረቱና የሚሸጡ ቢሆኑ ዋጋ ከመቀነስና ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪን ከማስቀረት ብቻ ሳይሆን በአካባቢ ተጽእኖ ደረጃም ሁነኛ ቅነሳ ማምጣት ይቻላል። አገር ውስጥ ከሚገኙ ጥሬ ዕቃዎች የሚመረቱና ለመገጣጠም ዝግጁ የሆኑ ክፍለ-ሕንጻዎች የሚያመርቱ ድርጅቶች ጥሩ ጅምር እያሳዩ ነው። ከዚህ አንጻር ማግኒዥየም ቦርድ፤ አግሮ ስቶንና የመሳሰሉት ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃዎች የሚመረቱበት መንገድ መመቻቸት አለበት (ጅምሩ አለ)።  አሁንም ከቻይና ድረስ የሚመጣ የብረት ግብአት ለማስቀረት መጣር ያስፈልጋል። 
ሕንጻዎች ከሚሰሩበት አሠራር አንጻር ጋር በተያያዘ እንዲሁም ከጣራቸውና በአካባቢያቸው ከሚነጠፈው አስፋልት የተነሳ የከተሞች ሙቀት ከከተማ ውጪ ካሉት የገጠር አካባቢዎች አንጻር ከፍተኛ ሙቀት እንዳላቸው ይታወቃል። ይህ ልዩነት እስከ አምስት ዲግሪ ሴንትግሬድ ድረስ ሊሆን ይችላል።በርካታ ሰው በሚኖርባቸው እንደ አዲስ አበባ ባሉት ከተሞች የሚገነቡት ሕንጻዎች ጣራቸው ነጣ ያለ፤ግቢያቸው በዛፍና በውኃ ሽፋን የተከበበ ቢሆን የካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀትን መቀነስ ብቻ ሳይሆን የከተሞች ውስጥ የከባቢ አየር ሙቀትን መቀነስ እንደሚቻል ጥናቶች ያሳያሉ (እንዲያውም በበለጠ)።
የላቀ ብልጫ ምዘና፤ እውቅናና ምዝገባ ስርዓት መዘርጋት ሌላው ጠቃሚ ነገር ነው። ይህ አይነት ስርዓት በግልጽ የሚታወቅና ሳይንሳዊ መስፈርት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት።መስፈርቱ በግንባታ እቃ፤ በክፍለ-ሕንጻ እንዲሁም በሙሉ ሕንጻ ደረጃ መውጣት ይችላል። ለምሳሌ ለሕንጻ ግንባታ የሚሆን ብረት ከብረት ማዕድን ሲመረት ከፍተኛ የኃይል ፍጆታን ይጠይቃል። ይህ ሀቅ መስፈርቱ ውስጥ ከሚገቡት አንዱ መሆኑ ነው። ከሞላ ጎደል በአገር ውስጥ ምርት የሚጠቀሙ ሕንጻዎች ከፍ ያለ ነጥብ የሚያገኙበት ስርዓት ሊሆን ይችላል። ደረጃ አወጣጡ በገለልተኛ የባለሞያ ወገን መሠራት የሚገባው ሲሆን መንግሥት ደግሞ የላቀ ብልጫ ላሳዩ ማትጊያ መንገዶችን ማበጀት ይጠበቅበታል። ገበያውም የብልጫ ልዩነትን የሚያንጸባርቅ መሆን አለበት። አገራዊው ስርዓት በሌላው ዓለም ያሉትን ስርአቶች መነሻ ሊያደርግ ይችላል። ለምሳሌ በአዲስ አባባ የአሜሪካ ኤምባሲ ያስገነባው አዲስ ሕንጻ የተሰራው በቦታው ለበርካታ ዓመታት የነበሩት እጽዋትንና የዱር እንስሳትን ባሉበት እንዲቀጥሉ በሚያደርግ መልኩና አረንጓዴ የግንባታ ቴክኒኮችን በማዋሃድ የተሰራ በመሆኑ በሰሜን አሜሪካ በሥራ ላይ ባለውና LEED ተብሎ በሚታወቀው “በኃይልና በአካባቢ ዲዛይን መሪነት” የብልጫ ምዝና ስርዓት መሰረት እውቅና ተሰጥቶት የተመዘገበ ሕንጻ ነው። 
ሌላው በሥራ ላይ ያለውና አስራ ሰባት ዓመታት የሆነው የአገሪቱ የሕንጻ ግንባታ ኮድ በአግባቡ ጥቅም ላይ እየዋለ እንደሆነ ከመከታተል ጋር ኮዱ በመስኩ ላለው እድገት እንዲሁም ለአዳዲስ እውቀቶችና አማራጮች የሚመጥን ተደርጎ መሻሻል አለበት። በሕንጻ ባለሞያዎችና በባለሀብቶች ዘንድም የአስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልጋል።በሌላው ህይወታችን የሚንጸባረቀው ከምዕራብ አገሮች ወይም ከሌሎች የዓለማችን ክፍሎች የተገኘ አሠራር ወይም ቴክኖሎጂ በሕንጻዎቻችንም ቢታይ የሚጠበቅ ብቻ ሳይሆን በራሱ ችግር አይደለም። ችግሩ ያለው የተገቢነትና የጥሩነት ልኬታችን ለሌላ አይነት የአየር ንብረትና ሁኔታ፤ ለሌላ አይነት ዐውድና ዳራ የተበጀውን ልኬትና አሠራር በቀጥታ መገልበጣችን ላይ ነው። ሕንጻዎቻችንም ሆነ ሌሎች ነገሮቻችንን በዚህ ቀጥታ ግልበጣ ልማድ መሰረት መሥራታችን ነው ክፋቱ። ዶክተር ኤልሳቤጥ ጊዮርጊስ በዶክትሬት የምርምር ጽሁፋቸው ስለ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን በአጠቃላይ የጠቀሱት እዚህ ላይ ማንሳት ተገቢ ይሆናል። በግርድፉ ወደ አማርኛ ሲመለስ “የኢትዮጵያ ምሁራን ኢትዮጵያ እንደ አገር ቅኝ ተገዝታ የማታውቅ አገር መሆኗ ልዩ ያደርጋታል የሚለው ላይ አጽንኦት ይስጡ እንጂ የምዕራባዊያን የዘመናዊነትና ዘመናይነት ትርጓሜን ሁለንተናዊ አድርገው መቀበላቸው ምሁራዊ ቅኝ ተገዢ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው” ይላል። በስነ ሕንጻው መስክ የዚህ አባባል እውነታነት የሚያረጋግጡ ነገሮች ማየት ከባድ አይመስልም። ይህ ሲባል ግን ጭራስኑ ነባራዊና ተጨባጭ ሁኔታዎችን ያገናዘቡ የሕንጻ ሥራዎች አልተሠሩም፤አይሠሩም ማለት አይደለም። ወደዚህ አይነት ድምዳሜ እንዳንሄድ የሚያደርጉን የታወቁም፤ ያልታወቁም ሥራዎች አሉ፤ይኖራሉም። ለምሳሌ በርቀት ክትትል ላይ በመመስረት የነአርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስና የነአርክቴክ ሚሊዮን ሳሙኤልን ሥራዎችን መጥቀስ ይቻላል - ከምስጋናና እና ከአድናቆት ጋር።

የአርክቴክት ሚልዮን ሳሙኤል  ሥራ -  እናት ሕንጻ - ፒያሳ ፤አዲስ አበባ

የአርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ ሥራ:ጎንደር

=======
አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: