Friday, February 3, 2012

‘የአይበገሬውና የአረንጓዴው ኢኮኖሚ’ ሰነድ


(ጌታቸው አሰፋ፤ ታኅሣሥ 21 ቀን  2004 ዓ.ም.)ቅድመ ነገር፡ እንኳን ለአዲስ ጉዳይ አምስተኛ ዓመት አደረሳችሁ። አዘጋጆችም እንኳን ደስ ያላችሁ። ወደ ዛሬው ጉዳይ ስንመለስ…
በኅዳሩ የደርባን ደቡብ አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ወቅት ከተካሄዱት ነገሮች መካከል በኢትዮጵያ መንግሥት  “ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ” በሚል ርእስ የተዘጋጀው ሰነድ ምረቃ ነው። በዛሬው እትም ስለ ሰነዱ ማንሳት
እንጀምራለን።
በእጄ ያለው ሰነድ በእንግሊዝኛ የተዘጋጀ ነው። የአማርኛ ቅጂ መኖሩን እንጃ ካለም እጄ ውስጥ አልገባምና ስለእንግሊዝኛው እትም ነው የማነሳው። አንዱ ሰነድ ራዕይ ላይ የሚያተኩር ሲሆን  ወደ ሰላሳ ስድስ ገጽ ያለው ነው ሌላኛው ደግሞ ከመጀመሪያው ተለቅ ያለና ስልት ላይ የሚያተኩረው ነው። ከሀያ ዓመት በኋላ ማለትም እ.አ.አ በ2030 አገራችን በምጣኔ ሀብት ደረጃ መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ተርታ እንድትሰለፍ ለማድረግ ነው የሚለው የእድገትና ውልጠት እቅዱ የ2025 እ.አ.አ. ግብ ነው የስልቱም ምጣኔ ሀብታዊ መዘውር። ይህን እውን ለማድረግ ሁለት ነገሮች ታሳቢ መሆን አለባቸው። የመጀመሪያው የወትሮው ምጣኔ ሀብታዊ ‘ቀለም’ አያስኬድም ከሚል የሚነሳ ነው። ሁለተኛው ደግሞ የአገሪቱን የምጣኔ ሀብት አውታሮች እንዳልነበሩ የሚያደርግ የ’አየር ንብረት ለውጥ’ የሚባል ደንቃራም መመከት አለበት የሚል ነው። እነሆ እነዚህ ሁለት ነገሮች “ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ” የራዕይና የልስት ሰነዶችን ወለዱ። 
ዋናው የስልት ሰነድ ባለ ስድሳ አራት ገጾች ዋና ክፍል ይዞ በባለ መቶ ሠላሳ ገጾች አባሪ የታጀበ ነው። በሰነዱ መጀመሪያ ላይ እንደተጠቀሰው ራዕዩ በ2025 እ.አ.አ. አገሪቱን ባለመካከለኛ ገቢ ደረጃ የሚያደርሰው የምጣኔ ሀብት ክንውን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ በኩል የሚመጣ መሆን አለበት።
የኢትዮጵያ ትልቁ ተግዳሮትም የምጣኔ ሀብት እድገትን በአዛላቂ መንገድ ማምጣት እንደሆነ ያስቀምጣል።
ልማትንና አዛላቂነትን የሚያመጣ አረንጓዴ የእድገት ፈለግ መከተል ነው አስፈላጊው እቅድ ይላል ሰነዱ። የአረንጓዴው ኢኮኖሚ ግንባታ በአራት ምሰሶዎች ላይ የተመሠረተ ይሆናል። ከእነዚህ ሦስቱ ግብርና፤  የደን ልማትና የኃይል ማመንጫ ናቸው። አራተኛው ምሰሶ ብዙ ዘርፎች የታጨቁበት ነው። መጓጓዣ የኢንዱስትሪው ዘርፍና ህንጻዎችን ይይዛል። እነዚህ አንድ ላይ የተጨፈለቁት ራሳቸውን ችለው ቢቀመጡ እንደ መጀመሪያዎቹ ሦስት ምሰሶዎች የጎላ የካርበን ዳይኦክሳይድ አቻ ልቀት መጠን የላቸውም በሚል መነሻነት ይመስላል። በዚህ ጽሑፍ አራተኛውን ምሰሶ ‘ሌሎች’ በሚል የወል ርእስ እንይዘዋለን። 
የዛሬው ቀለም
አጠቃላይ በ2003/2004 ዓ.ም. የአገሪቱ የካርቦን ዳይኦክሳይድ የልቀት አቻ መጠን 150 ሚልዮን ቶን እንደሆነ ይጠቅሳል። ከዓለም አቀፍ የልቀት መጠን አንጻር በጣም ያነሰ ነው። የመጠኑን ትልቅ ወይም ትንሽ መሆን ለማነጻጸር ያህል በዓለም ትልልቅ ከሚባሉ የፖታሽ ማዕድን ክምችቶች አንዱ የሆነው የዳሎል ክምችት እስከ 150 ሚልዮን ቶን ፖታሽ ድረስ ይደርሳል።
የልቀት መጠኑ በነፍስ ወከፍ ሲሰላ ወደ አንድ ነጥብ ስምንት ቶን መሆኑ ነው። ኢትዮጵያ በህዝብ ብዛት ደረጃ የዓለም ድርሻዋ አንድ ነጥብ አንድ ፐርሰንት ሲሆን በዓለም የልቀት መጠን ድርሻዋ ደግሞ ወደ ዜሮ ነጥብ ሦስት ፐርሰንት ብቻ ነው ማለት ነው።  ሰማንያ አምስት ፐርሰንት የልቀቱ መጠን የሚመጣው ከግብርና ዘርፍና ከደን ዘርፍ ሲሆን የኃይል ማመንጫ ሦስት ፐርሰንት፤ መጓጓዣ ሦስት ፐርሰንት፤ ኢንዱስትሪ ሦስት ፐርሰንት፤ እንዲሁም ህንጻዎች ሦስት ፐርሰንት ያህል ያዋጣሉ።  በካርቦን ዳይኦክሳይድ የልቀት አቻ ስሌት ውስጥ የተካተቱት አየር ንብረት ለዋጭ ጋዞች ካርቦን ዳይኦክሳይድን(CO2) ጨምሮ በዋናነት ሚቴን(CH4) እና ናይትረስ ኦክሳይድ(N2O) ሲሆኑ እነ ሃይድሮፍሎሮካርበንስ(HFCs)፤ፐርፍሎሮካርበንስ(PFCs) እና ሰልፈር ሄክሳ ፍሎራይድ(SF6)  ወዘተ ለመካተታቸው እርግጠኛ መሆን አልቻልኩም። እስቲ በሰነዱ መሠረት እያንዳንዱን ዘርፍ እንመልከት።
ግብርና 
ለላቀ የምግብ ዋስትና የሚያግዝ የእርሻና የከብት ልማትን ማሻሻል፤ የገበሬ ገቢን መጨመርና የዘርፉን ልቀት መጠን መቀነስ ነው የተቀመጠለት ግብ።
በዚህ ዘርፍ ዋነኛው የልቀት ምንጭ የከብት ልማት ሲሆን የእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚም በተከታይነት ያዋጣል። የከብቶች የሚቴን ልቀት ከመኖ የማብላላት ሂደታቸው ጋር ሲያያዝ ከእበታቸው ጋር የሚያያዘው የናይትረስ ኦክሳይድ ልቀትም አስተዋጽኦ ያደርጋል። ከ150 ሚልዮን ቶኑ ውስጥ ወደ 65 ሚልዮን ቶን የሚሆነው ማለትም ወደ አርባ ፐርሰንት የሚሆነው ከከብቶች ጋር የተያያዘው ነው።  ይህ እንግዲህ ከሃምሳ ሚልዮን በላይ የሚሆኑት የአገሪቱ ከብቶች ወይም ወደ መቶ ሚልዮን የሚሆነው የእንስሳት ሀብታችን አሉታዊ አስተውጽኦ መሆኑ ነው። ወደ አስር ሚዮልዮን ቶን ልቀት ደግሞ በእርሻ የማዳበሪያ አጠቃቀም፤ ወደ ሦስት ሚልዮን ደግሞ ቃርሚያ ወደ አፈር ሲመለስ የሚፈጠር የናይትረስ ኦክሳይድ ልቀት ጋር የሚገናኝ ነው ይላል ሰነዱ። 
የደን ልማት 
ኢኮኖሚያዊና ስነምህዳራዊ አገልግሎት(የካርበን ዕቀባን ጨምሮ) ላይ ያተኮረ የደን ጥበቃና መልሶ ማልማት ነው እንደ ግብ የተያዘው። ይህ ዘርፍ የ55  ሚልዮን ቶን ልቀት ምንጭ  ነው። ለእርሻ መሬት ሲባል የሚመነጠር ደን የሃምሳ ፐርሰንት ድርሻ አለው። በማገዶ እንጨት ሰበብ የሚጨፈጨፈው ደን ወደ አርባ ስድስት ፐርሰንት ሲያዋጣ ፤መደበኛ ከሆነና መደበኛ ካልሆነ ከእንጨት ሥራ ጋር የተያያዘው የዛፎች ቆረጣ አራት ፐርሰንት ያህል አስተዋጽኦ ያደርጋል።
የኃይል ማመንጫ
በዚህ ሥር የተቀመጠው ግብ ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚሆንና ለክፍለ አህጉራዊ ገበያ የሚውል ከታዳሽ ምንጮ የሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስፋፋት የሚል ነው። ሲጀመር ይህ ዘርፍ ከካርቦን የጸዳ ሊባል የሚችል ነው። ምስጋና ወደ ዘጠና ፕርሰንት ለሚሆነው የውኃዊ ኃይል ማመንጫችን። እንደዛም ሆኖ ከማዕከላዊ ማሰራጫ ውጪ ያሉ መብራት ኃይል የሚያስተዳድራቸው የዲዝል ጀነሬተሮች ጋር በተያያዘ ወደ አምስት ሚልዮን ቶን አስተዋጽኦ ያደርጋል ይህ ዘርፍ። ወደ ሦስት ፐርሰንት የአገሪቱን አጠቃላይ የልቀት መጠን ይሸፍናል ማለት ነው።
ሌሎች 
ሌሎች በሚለው ሥር የተካተቱት እነ መጓጓዣ፤ ኢንዱስትሪና ህንጻዎች ሲሆኑ የተቀመጠላቸው ግብ ትኩረት የሚያደርገው ዘመናዊና ስሉጥ የኃይል አጠቃቀም ወዳላቸው ቴክኖሎጂዎች መፈናጠር ላይ ነው።  ከመጓጓዣው ክፍል የምድር መጓጓዣ ወደ 75 ፐርሰንቱን ሲይዝ የአየር ትራንስፖርት ደግሞ ወደ 23 ፐርሰንት ይዟል። ከአዲስ አበባ የመኪና መጨናነቅ አንጻር የሰው ማጓጓዣ መኪኖች የተመልካች ትኩረት የሚስቡ ናቸው። በሰነዱ መሠረት ግን ከፍተኛ ድርሻ የሚይዙት የህንጻ ግንባታ መኪኖችና የዕቃ ማጓጓዣ መኪኖች ናቸው። 
ኢንዱስትሪም ወደ አራት ሚልዮን ቶን ነው አስተዋጽኦ የሚያደርገው። የኢንዱስትሪ ልማት ወደፊት ያልገፋ ከመሆኑ አንጻር የልቀት አነስተኛ ድርሻው የሚጠበቅ ነው። ከዚሁ የልቀት መጠን ወደ ሃምሳ ፐርሰንቱ የስሚንቶ ኢንዱስትሪ የሚልቀው ነው። አንዳንድ ኢንዱስትሪዎች ልቀታቸው ከሚጠቀሙበት የኃይል ምንጭ ጋር የተያያዘ ነው። ለምሳሌ ቅሪታዊ ነዳጆች የምንላቸው እንደ ከሰል ድንጋይ፤ የተፈጥሮ ጋዝና የነዳጅ ዘይት የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች ልቀታቸውም የዛን ያህል ከፍ ያለ ነው። ስሚንቶ ግን ከሚመረትበት ሂደት ጋር ተያይዞም ካርቦን ዳይኦክሳይድን ይለቃል። በመቀጠል ወደ ሠላሳ ሁለት ድርሻ ያለው የማዕድን ሥራ ሲሆን የጨርቃ ጨርቃ ጨርቅና የቆዳው ዘርፍም ወደ አስራ ሰባት ፐርሰንት ድርሻ ይይዛል። ወደ ሁለት ፐርሰንት የሚሆነው ደግሞ የብረታ ብረት፤ የኬሚካል ፤ የምግብና የመሳሰስሉት ማምረቻዎች ድርሻ ነው። 
በህንጻዎች ሥር የተካተተው ልቀት ደግሞ ከደረቅና ከፈሳሽ ቆሻሻ ጋር የሚገናኘው ወደ ሦስት ሚልዮን ቶን ሲሆን በዲዝል ከሚሰሩ የግል የኃይል ማመንጫዎች ጋር ደግሞ ወደ ሁለት ሚልዮን ቶን በድምሩ አምስት ሚልዮን ቶን የሚሆነው ነው።
የወትሮው አካሄድ
የአየር ንብረት ለዋጭ ጋዞች በተመለከተ ምንም ነገር ሳይደረግ በተለመደው አሠራር ከተቀጠለ በሃያ ዓመት ውስጥ ማለትም በ2030 እ.አ.አ የአገሪቱ የልቀት መጠን በካርቦን ዳይኦክሳይድ አቻ ሲሰላ ወደ 400 ሚልዮን ቶን ይደርሳል - አሁን ካለው ከ150 ሚልዮን ቶን ላይ ወደ 250 ሚልዮን ቶን ጭማሪ ማለት ነው። በነፍስ ወከፍ ወደ ሦስት ቶን ይሆናል ማለት ነው። ለንንጽር ያህል ከላይ እንደተገለጸው ዛሬ ያለው የነፍስ ወከፍ ልቀት መጠን ወደ አንድ ነጥብ ስምንት ቶን ነው። ከፍተኛ ጭማሪ የሚያሳየው ዘርፍ ግብርናው ሲሆን ይሄውም ወደ 110 ሚልዮን ቶን ጭማሪ ያመጣል። በሁለተኛነትና በሦስተኛነት ደረጃ ኢንዱስትሪና የደን ዘርፍ ሲከተሉ እነሱም የ65ና የ35 ሚልዮን ቶን አዲስ ተጨማሪ ልቀት በቅደም ተከተል ይዘው ይመጣሉ።  የወትሮው አካሄድ የኢንዱስትሪ ልቀትን በአስራ ሁለት እጥፍ ሲያሳድግ ከመጓጓዣ ጋር የተያያዘውን ልቀትን ደግሞ በሰባት እጥፍ ያስድጋል። ዝቅተኛ እንደሆነ የሚቀጥለው ዘርፍ አሁንም የኃይል ማመንጫው ዘርፍ ነው። .
የታለመው ግብና መንገዱ
ከሀያ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ ከሃምሳ በላይ ባለሞያዎች ተሳትፈውበታል የተባለው ሰነድ የተዘጋጀው በሰባት ልዩ ልዩ ኮሜቴዎች እንደሆነ ተገልጿል። በየክልሉም ውይይት ተደርጎበታል ተብሏል። የታለመው ግብ ከሀያ ዓመት በኋላም የአገሪቱ የአየር ንብረት ለዋጭ ጋዞች የልቀት መጠን አሁን ባለበት ደረጃ ማለትም በ150 ሚልዮን ቶን መገደብ ነው። ከሚጨምር የሕዝብ ብዛትና ከሚያድግ ኢኮኖሚ ጋር ተጣጥሞ የሚሄድ ዜሮ የልቀት ጭማሪ ግብ ያሳካሉ የተባሉ ከስድሳ በላይ ሥራዎች ተለይተዋል። ከነዚህም ከፈጣን ትግበራ አንጻር አራት ሥራዎችን ቅድሚያ ተሰጥቷቸዋል። እነዚህም የውኃዊ ኃይል ሀብታችንን በስፋት መጠቀም፤  የበለጸጉ የገጠር የማብሰያ ቴክኖሎጂዎች በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል፤ የከብት ልማት የእሴት ሰንሰለትን ስልጠት ማሻሻልና ከደን ምንጠራና ጉስቁልና ጋር የተያያዘውን ልቀት መቀነስ የሚሉት ናቸው። እስካሁን ከሞላ ጎደል  ከእናንተ ጋር የቆየው የመንግሥት ሰነድ ነበር። እኔ ደግሞ በሚቀጥለው እትም እመለሳለሁ። መልካም የልደት በዓል።

=======
አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: