Monday, March 26, 2012

የአካባቢ ትምህርት ትላንትና ዛሬ


(ጌታቸው አሰፋ፤ መጋቢት 1 ቀን  2004 ዓ.ም.) ድሮ ድሮ በአጋጣሚ ካልሆነ በቀር ሆን ብሎ የአካባቢ ጉዳይን እንደ ትምህርት መስክ መርጦ መማር ብርቅ ነበር። እናም እኔ ወደ አካባቢ ጉዳይ መስክ  የገባሁት የሆነ አጋጣሚ በፈጠረው አጋጣሚ የተነሳ ነበር። ከአስራ ሰባት ዓመታት በፊት እንዲህ ሆነ….
ከአራተኛ ዓመት ወደ አምስተኛ ዓመት መሸጋገሪያ ክረምት ላይ። አምስት ኪሎ ኬሚካል ምህንድስና ትምህርት ክፍል። የክረምት ሥራ እየሠራሁ ነበር።  የምሠራው ሥራ የአንድ ኬሚካል የምርት ሂደት ላይ ያተኮረ የቤተ ሙከራ ሥራ ነበር። አጋጣሚ የኬሚካል ምህንድስና ተመራቂዎች እስከዛን ጊዜ ድረስ የሠርዋቸው የመመረቂያ ጽሑፎችን የማየት እድል ፈጠረልኝ። አዲስ አባባ ዩኒቨርስቲ ከዛ በፊት አምስት ወይም ስድስት ጊዜ ብቻ ነው ኬሚካል መሀንዲሶችን ያስመረቀው። እናም የማገላብጣቸው የምረቃ ጽሑፎች ያን ያህል ብዙ አልነበሩም። አንድ የምረቃ ጽሑፍ ከሌሎች ጽሑፎች ይበልጥ ቀልቤን ሳበው ብቻ ሳይሆን መጻኢ እድሌንም ወሰነ - በኋላ ሳስበው። ጸሐፊው በአሁኑ ሰዓት በተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ፕሮግራም የአፍሪካ ምክትል ኃላፊ ናቸው። ጽሑፉ ከኢንዱስትሪ የሚወጡ ቆሻሻ ፍሳሾች ላይ ያተኮረና ስለአካባቢ ጉዳዮጭ ያለኝ ግንዛቤ ከፍ ያደረገልኝ ነበር። እናም ያን ጊዜ ወሰነኩ - የመመረቂያ ጽሑፌ ከአካባቢ ጉዳዮች ጋር የሚያያዝ መሆን እንዳለበት። ችግሩ ክረምት ያሠሩኝ የነበሩት አስተማሪ ጊዜው ሲደርስም ክረምት እሠራው በነበረው ኬሚካል ዙሪያ እንደሠራ ፈለጉ ብቻ ሳይሆን ገፋፉኝ። እኔ መሥራት የምፈልገው በአካባቢ ጉዳይ ብቻ መሆኑን አጽንቼ ብነግራቸውምምን ላይ የሚያተኩር ነው?” እናያሰብከው አንድ ሰው ብቻ የሚሠራው አይደለምና ከማን ጋር ልትሠራ ነው?” በማለት ሃሳቤን እንድቀይር ገፉኝ። ልቤ ውስጥ የገባውን ነገር ሊያስተወኝ የተፈታተነኝ አብሮኝ የሚሠራ ተማሪ ማግኘቱ ነበር። ኬሚካል ምህንድስና ከሌሎች ምህንድስና ዘርፎች ጋር ሲተያይ አዲስ ስለነበር ተመርቆ ሥራ ማግኘት በወቅቱ ቀላል አልነበረም። በዛ ላይ መመረቂያ ጽሑፉ በምርቶች ዙሪያ ሳይሆን በአካባቢ ጉዳይ ከሆነ የሥራ እድሉ የበለጠ ጠባብ ይሆናል ከሚል አብሮኝ ለመሥራት ፈቃደኛ የሆነ ተማሪ የተገኘው ከብዙ ሙከራ በኋላ ነበር። የአዋሽ ቆዳ ፋብሪካ ቆሻሻ ፍሳሽ ጋር አብሮ የሚወጣውን ክሮሚየም የተባለውን ኬሚካል መልሶ መጠቀም የሚቻልበት ሂደትና ማሽን ዲዛይን አድርጎ የአካባቢ ብክለቱን  ከመቀነስ ጋር ለኬሚካሉ ግዢ የሚወጣውን ወጪ መቀነስ የሚያስችል ሥራ ነበር የሠራነው። 
ከዛ በኋላ ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ስቀጠር (ከፓሊ ቴክኒክነት ወደ ዩኒቨርስቲነት በሚሻገርበት ዋዜማየዲግሪ መርሐ ግብሩ ላይ በአካባቢ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ኮርስ ቀርጸን አስገብተን ማስተማር ጀመርን።
በባህር ዳር ከሁለት ዓመት በላይ ቆይታዬ በኋላ ለሁለተኛ ዲግሪ ለመማር የውጪ የትምህርት እድል ለማግኘት ስጥር በአንድ ጊዜ ሦስት እድሎች ተፈጠሩ። አንደኛው መንግሥት የሚሰጠኝ ህንድ አገር የመሄድ እድል። ሁለቱ ደግሞ በራሴ ተጻጽፌ ያገኘሁዋቸው ሲሆኑ አንደኛው ወደ ቤልጄም ሌላኛው ደግሞ ወደ ስዊድን ለመሄድ የሚያስችሉ ነበሩ። ጤናን (እዛ ሄደው የታመሙ ስለነበሩ) እና የገንዘብ ክፍያ መጠኑን ግንዛቤ ውስጥ ሲገባ ህንድ የመጀመሪያ ምርጫዬ አልሆነምና ተውኩት። ከቤልጀምና ከስዊድን አንዱን መወሰን ግን ከበደኝ። ቤልጄም ብሄድ የስኮላርሺፕ ክፍያው ከፍ ይላል። በዛ ላይ ደግሞ ለዶክትሬት ትምህርት ለመቀጠልም ከፍተኛ እድል ነበረው። ክፋቱ የትምህርቱ አይነት ከፍላጎቴ ጋር የሚሄድ አልነበረም። እኔ የምፈልገው የአካባቢ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር፤ ያገኘሁት የቤልጄም እድል ደግሞ ከምግብ ቴክኖሎጂ ጋር የሚያያዝ ነበር። ስዊድን ደግሞ የስኮላርሺፕ መጠኑ ከቤልጄም ያነሰና ለሦስተኛ ዲግሪ ለመቀጠል ደግሞ እድል የሌለው ነበር - በነበረኝ መረጃ መሠረት። የትምህርቱ አይነት ግን የአካባቢ ምህንድስናና አዛላቂ መሠረተ ልማት ላይ ስለነበር ከፍላጎቴ ጋር እጅጉን የሚጣጣም ነበር። መወሰን ሲያቅት ማማከር ጥሩ ነውና በወቅቱ እኔም የንስሀ አባቴን አማከርኩ። ያለውን ሁኔታ ካብራራሁላቸው በኋላ ለእሳቸው ምክር መስጠቱ ቀላል ነበር።ፍላጎትህን አስቀድም። ሌሎቹ ጉዳዮች ይደርሳሉ።አሉኝ። በዛ መሠረት ወደ ስዊድን ሄጄ ተማርኩ። የለም የተባለው እድልም አባቴ እንዳሉትደርሶተገኘና የዶክትሬት ትምህርቴንም እዛው ጨረስኩ።
አምስት ኪሎ ውስጥ የምረቃ ጽሑፍ ካነበበኩ የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርቴን እስከጨረስኩበት ድረስ ባሉት ዓመታት ውስጥ በአገራችን የዩኒቨርስቲ ቁጥር እየጨመረ ድኅረ ምረቃ ያልነበራቸው ዩኒቨርስቲዎችም አዳዲስ መርሐ ግብሮች እየከፈቱ ነበር። በአንዳንድ ቦታዎች የነበሩት የአካባቢ ጉዳይ ነጠላ ኮርሶችም ወደ ሙሉ የዲግሪ መርሐ ግብሮች የማደግ ደረጃ መድረስ ጀመሩ። 
ለምሳሌ በአዲስ አባባ ዩኒቨርስቲ አምስት ኪሎ የአካባቢ ምህንድስና መርሐ ግብር፤ በአራት ኪሎ የአካባቢ ሳይንስ መርሐ ግብር፤ በስድስት ኪሎ የአካባቢና ልማት የትምህርት መስክ ተጠቃሾች ናቸው።
በጂማ የአካባቢና ጤና መርሐ ግብር በመቀሌ የመሬት ሀብት አስተዳደርና የአካባቢ ጥበቃ መርሕ ግብር የመሳሰሉትም አሉበት። ሌሎችም አነሰም በዛምበመጀመሪያ ዲግሪም ሆነ በሁለተኛ ደግሪ ቢያንስ ግን በኮርስ ደረጃ ይሰጣሉ። ይህ ሁሉ መልካም ነው። 
እዚህ ላይ መነሳት ያለባቸው ነገሮች ግን አሉ። ከነዚህ ሁለቱን እስቲ ብድግ እናድርግ - ላዛሬ።
ችግር ፈቺነት
ትምህርቶች ሁሉ ከችግር መነሳት ባይኖርባቸውም አንዳንድ ትምህርቶች ግን ከችግር መነሳት ያለባቸው ወይም ከችግር ቢነሱ የበለጠ ትርጉም የሚሰጡ ናቸው። የአካባቢ ጉዳይ ትምህርትን እዚህ ውስጥ ልንመድበው እንችላለን። መነሻ የሚሆነው ችግር በገሀዱ ዓለም የተከሰተ ባይሆን እንኳን የመከሰት እድል ካለው እንደ ችግር ለመቆጠር በቂው ነው።
የአካባቢ ትምህርቶቻችን ይዘታቸውና አቀራረባቸው ዓለም አቀፋዊና ጥቅል ንደፈ ሃሳባዊ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ የሚፈጥሩ፤ አገራዊና አጥቢያዊ ጉዳዮች ላይ ደግሞ የሚያደማ እውቀት የሚያስጨብጡ መሆን አለባቸው።
አጥቢያዊ ጉዳዮች(ችግሮች ወይም ክስተቶች) እንደ ቤተ ሙከራ ወይም እንደ መስክ ሥራ ሆነው የዋናው ስርዓተ ትምህርት አካል ተደርገው መጠለፍ አለባቸው። ለችግሮች መፍትሔ ለማስገኘት፤ ሲገኝም በማስረጽና የማስፋፋት ስራ በመስራት በኩል ነባራዊ ጉዳዮች ወሳኞች ናቸው። ከምርምርና ስርጸት ጋር የተያያዘ ትምህርት የሚዘልቅ እውቀት የማስያዝ አቅሙ ከፍ ያለ ስለሆነ ችግር-ፈቺ ይዘትና አቀራረብ ዋናው ክፍል መሆን ይገባዋል። ምንም እንኳን አንድ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የሚማረው ተማሪ ከተለያያ አካባቢ የመጣ ቢሆንምና ተመርቆ የሚሠራበት ቦታም የተለያየ መሆኑ ቢታወቅም የመጣበት አካባቢና ዩኒቨርስቲው ያለበት አካባቢ ዙሪያ ያሉት አካባቢያዊ ጉዳዮች በሚማረው ትምህርት ውስጥ መካተት አለባቸው። ለምሳሌ እኔ የምሠራበት ዩኒቨርስቲ የሚገኝበት ክፍለ ግዛት በነዳጅ ዘይትና በተፈጥሮ ጋዝ የበለጸገ በመሆኑ ከነዚህ ሀብቶች ጋር የሚያይዙ የአካባቢ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ መርሐ ግብሮችና ትምህርቶች የዩኒቨርስቲው ዋና አካል ናቸው። ለምሳሌ የባህር ዳር ዩኒቨርስቲና የጎንደር ዪኒቨርስቲ ከጣና ሐይቅ ጋር የተያያዙ የአካባቢ ጉዳዮች ከሚያተኩሩባቸው አንዱ መሆን አለበት። አዲስ አባባ ዩኒቨርስቲ የደረቅ ቆሻሻ ሁለንተናዊ አያያዝን እንደ አንድ መስክ መያዝ አለበት። ጅማ ዩኒቨርስቲ ከቡና ተረፈ ምርት ጋር በተያያዘ ምርምርና ስርጸት እንዲያደርግ ብንጠበቅ አይበዛብንም። የመቀሌ ዩኒቨርስቲ የተራቆተ መሬት ዳግም ሕይወት ዘሪ የንድፈ ሀሳብና የተግባር ዘይቤዎች ማበልጸግን ማካተት አለበት። ወዘተ ዩኒቨርስቲም ወዘተ ጉዳይ ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት እያልን መቀጠል እንችላለን።
ተማሪው ከመጣበት አካባቢ ያለና የትምህርትና ምርምሩ አካል መሆን ያለበትን ጉዳይ መለየት ላይ የተማሪው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ የሚሰጠው ትምህርት ያንን እድል ለተማሪው የሚፈጥር መሆን አለበት። ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ በነበርኩበት ጊዜ በመቅረጽና ለአንድ ዓመት በማስተማር የተሳተፍኩበት ኮርስ ውስጥ በተማሪዎች እንዲሠሩ ካደረግኩዋቸው ፕሮጄክቶች መካከል ከየመጡበት አካባቢ ያሉ የአካባቢ ጉዳችን(ችግሮችን) መተንተን አንዱ ነበር። የአንዳንዶቹ መሳጭ ሥራዎች አሁንም ድረስ ፋይሌ ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
ዩኒቨርስቲው በሚገኝበት አካባቢ ያለው ችግር በመለየት ደገሞ የበለጠ እውቀት ያላቸው በከተማውና በአካባቢው ያለው ህዝብ፤ የመስተዳድር አካላትና ኢንዱስትሪዎች ናቸው። ዩኒቨርስቲው ከነዚህ ጋር በመቀናጀት አሉ የሚባሉ ችግሮችን ከአጣዳፊነትና ከክብደት አንጻር በቅደም ተከተል የማስቀመጥ ሥራ ማሠራት ይችላል። 
አደረጃጀት
የአካባቢ ጉዳዮች ከሞላ ጎደል ዘርፈ-ብዙ በመሆናቸው በነሱ ዙሪያ የሚሰጠው ትምህርትም በይዘት ስፋትና ጥልቀት ሚዛናዊና ሁለንተናዊ መሆን ይኖርበታል። የትምህርቱ አደረጃጀትም ይህንን ሀቅ የሚያንጸባርቅ መሆን አለበት። በተለይ በአንድ ከተማ ውስጥ ወይም ዙሪያ የሚገኙ የአካባቢ ጉዳይ ላይ የሚያተኩሩ የትምህርት መስኮች  ሀብት ቆጣቢና ስሉጥ የሆነ መንገድ በሚፈጥር መልኩ መቀናጀት አለባቸው። ለምሳሌ በአዲስ አባባ ዩኒቨርስቲ አምስት ኪሎ የሚገኘው የአካባቢ ምህንድስና መርሐ ግብር፤ በአራት ኪሎ የሚሰጠው የአካባቢ ሳይንስ መርሐ ግብር እና በስድስት ኪሎ ያለው የአካባቢና ልማት የትምህርት መስክ በጋራ የሚሠሩት ነገር መፍጠር ከቻሉ (ይቻላልም) ለተማሪዎቹም ለአስተማሪዎቹም ለዩኒቨርስቲውም ለአገሪቱም ጠቃሚ ይሆናል። ምክንያቱም የአካባቢ ጉዳይ የተፈጥሮ ሳይንስ፤ የምህንድስና እና የማኅበራዊ ሳይንስ እይታዎችና የጥናት ዘዴዎች ተቀናጅተው ሲሠሩበት የበለጠ ውጤት የማምጣት ባህርይ አለው።  ፍላጎቱ ካላቸውና የሚጠቅማቸው ከሆነ ተማሪዎቹ በአንድ ግቢ ውስጥ በሚሰጡ ኮርሶች ብቻ ሳይገደቡ የመረጡትን ኮርስ የሚወስዱበት ሁኔታ፤ የመመረቂያ ፕሮጄክቶች ላይ በጋራ የሚሠሩበት መንገድ መፍጠር ያስፈልጋል። በኮርስም ሆነ በፕሮግራም መልክ የሚሰጠው የአካባቢ ጉዳይ ትምህርት ቀልጣፋነትና እንደየሁኔታውና እንደየጊዜው መመቻቸት የሚችል ሆኖ ቢቀረጽ ጠቀሜታ አለው። 
=======
አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: