Monday, March 26, 2012

ማኅበራዊ አዛላቂነት

(ጌታቸው አሰፋ፤ መጋቢት 15 ቀን  2004 ዓ.ም.) አዛላቂነት ምጣኔ ሀብታዊ፤ አካባቢያዊና ማኅበራዊ አውታሮች አሉት። ማንኛውም ቴክኖሎጂ፤ ፕሮጄክት ፓሊሲ ወዘተ ከአዛላቂነት አንጻር ስንገመግመው ከእነዚህ ሦስት አውታሮች አኳያ በጎና ጎጂ ተፅዕኖውን ለይተን  አስቀመጥን ማለት ነው። የማኅበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ መስክ በጣም ጠቃሚ ግን በጣም አስቸጋሪ መስክ ነው። የማንኛውም ልማት ጥቅም የሚለካው ተደምሮ ተቀንሶ ለሰው ከሚሰጠው

ጥቅም ነውና የማኅበራዊ አዛላቂነት ግምገማ ወሳኝ ነው። አስቸጋሪነቱ ደግሞ ከመለካት ጋር የሚያያዘው ክፍሉ ነው። ማነው የሚለካው? እንዴት ነው የሚለካው? የሚሉትን ጥያቄዎች ይጨምራል። የምጣኔ ሀብታዊ ግምገማ ቢያንስ ስንት ወጪ ይደረጋል? ምን ገቢ ይደረጋል? ተብሎ ሊለካ የሚችል ነው። የአካባቢ ተፅዕኖም ቢሆን በተፈጥሮ ሳይንስ ዘዴዎች የሚለካና የሚጠና ነው። የማኅበራዊው ዘርፍ መለኪያ መሣሪያዎች ግን ለየት ባለ መልኩ ወሰብሰብ ይላሉ። ቃለ መጠይቅ በማድረግ፤ የመጠይቅ ቅጽ በማስሞላት፤ አብሮ በመሳተፍ ማጥናት የመሳሰሉትን ዘዴዎችን በመጠቀም መገምገም ይቻላል። በነዚህ መንገዶች የሚሰበሰበው አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ማኅበራዊ ተፅዕኖን ለመለካት የሚሰበሰብ መረጃ በተለይ በታዳጊ አገሮች ትክክለኛነቱ ለማረጋገጥ  አስቸጋሪ ነው። ከሚጠቀሱት ምክንያቶች መካከል አንዱ ለምሳሌ መጠይቁን የሚያስሞላው ክፍል እንኳ እውነተኛ መረጃ ለመስብሰብ ቢሰማራም የሚሞላው ሰው ወይም ለቃለ መጠይቁ መልስ የሚሰጠው ሰው ሆን ብሎ የተሳሳተ መልስ የመስጠት እድሉ ከፍተኛ መሆኑ ነው። ይህን የተሳሳተ መልስ የሚሰጠው በአንድ በኩል መጠይቁን የሚያስሞላው ሰው (ጠያቂው) ራሱ፤ ካልሆነም ከጠያቂው ጀርባ አለ ብሎ የሚያስበው አካል የሚፈልገው መልስ አስቀድሞ በመገመትና ይሄ መልስ ብሰጥበሰላም ያኖረኛልብሎ በማሰብ ሊሆን ይችላል። ይህ የሚሆነው በሰላም መኖርና አለመኖር የሚባሉት ሁነቶች በተጨባጭ ቢኖሩም ባይኖሩም ማለት ነው።  በሌላ በኩል ደግሞ መላሹ የምሰጠው መልስ ጥቅም ያስገኝልኛል ብሎ በሚያስበው መልክም ሊያስቀምጠው ይችላል። በተለይይቸግረሃል ወይ?’ አይነት ጥያቄዎች ለዚህ አይነት መልሶች ሳቢ ናቸው። በገሐዱ ዓለም ለመላሹ ከሚደረገው ቃለ መጠይቅ ጋር የሚያያዝ ጥቅም ቢኖርም ባይኖርም ማለት ነው - ይህ አይነት ስሌት ተሰልቶ መልስ የሚሰጠው።
በአንድ ወቅት ስለመሬት ይዞታ ለማጥናት ወደ አንድ ክልል የሄዱ አጥኚዎች ገበሬውን ሲጠይቁት ያጋጠማቸው ችግር የሚሰጣቸው መልስ ለመንግሥት አካል የሚሰጥ አይነት መልስ የሚመስል ሆኖ ነበር ያገኙት። የጥያቄውን መልስ ተአማኒነት ለመፈተሽ ሌሎች አባሪና ገባር ጥያቄዎች ሲጠይቁ ከሚያገኙት መልስ ጋር በጣም የተለያየ ነበር - ትክክለኛውን ስሜታቸውን ሀሳባቸውን ማወቅ እስኪቸገሩ ድረስ።
አካባቢያዊ ተፅዕኖ የሚጀምረው በገቢር ከተገለጸ ክስተት ጋር ተያይዞ ነው። ማኅበራዊ ተፅዕኖ መፈጠር የሚጀምረው ግን በመረጃ ደረጃ ካለ ነገርም ጭምር ነው።  
የማኅበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ ተለዋዋጮች በተለያየ ጊዜ የተጠኑ ሲሆን በቁጥር ወደ ሀያ ስምንት ይደርሳሉ። እነዚህም በተለያዩ ክፍሎች የሚከፈሉ ሲሆን ሕዝባዊ ተፅዕኖ፤ ተቋማዊ ሥርዓት ተፅዕኖ፤ የማኅበረሰብ ለውጥ ተፅዕኖ፤ ነፍስ ወከፋዊና ቤተሰባዊ ተፅዕኖ እና ማኅበራዊ መሠረተ ልማት ተፅዕኖ ተብለው ይታወቃሉ። በመጨረሻው ክፍል ስር ከሚገኙትና ከፕሮጄክት ዕቅድና ትገበራ አኳያ መጠናት ካለባቸው ተለዋዋጮች አንዱ በታወቁ ባህላዊ፤ ታሪካዊ፤መንፈሳዊና ስነ-ጥንታዊ ሀብቶች ላይ የሚደርሰውን ተፅዕኖ የሚመለከተው ነው። 
ለዛሬው ጽሑፌ መነሻ የሆነኝና ከዚህ መጠናት ካለበት ተለዋዋጭ አንጻር የሚታየው ሰሞኑን መንግሥት በወልቃይት መሥራት የጀመረው የሸንኮራ አገዳ ልማትና የስኳር ፋብሪካ ፕሮጄክት ነው። የማምረት አቅሙ ትልቅ ለሆነው ፋብሪካ በጥሬ እቃነት የሚጠቀመውን የሸንኮራ አገዳ ለማልማት የሚያስፈልገው ሰፊ መሬት እንዲሁም ከሞላ ጎደል በመስኖ የሚለማ ስለሆነ ለዛ የሚሆነውን ግድብ መስራትን ያካተተ ነው እናት ፕሮጄክቱ። በስኳር ራሷን ያልቻለችና ስኳር  ከውጪ ለምታስገባ አገር ስኳር ፋብሪካዎች በብዛት መቋቋም አለባቸው። አንድ ስኳር ፋብሪካ ሆን ተበሎ ከመጀመሪያው ታስቦበት ከተሠራ አልያም አስፈላጊ የማስፋፊያ ሥራ ከተደረገለት ሲፈለግ ስኳር፤ ሲፈለግ ነዳጅ አረቄ ማምረት ይችላል። ያም ማለት ስኳር በጣም ሲፈለግ (ገበያው ያንን ሲያመለክት) ስኳር ይመረትበታል። በሌላ ጊዜ ደግሞ ነዳጅ አረቄ በአገር ውስጥም በውጪም ተፈላጊነቱ ሲበዛና የሚያስገኘው ገቢ ከፍ ያለ ሲሆን ስኳሩን ቀንሶ ነዳጅ አረቄውን በገፍ ማምረት ይቻላል። የስኳር ፋብሪካዎች በየቦታው መሠራታቸው ደግሞ ለየተጠቃሚውና ለየገበያው ተመጣጣኝ ቅርበት ስለሚኖራቸው በጣም አስፈላጊ ነው። 
በወልቃይት የሚሠራው የስኳር ልማት ፕሮጄክት በመንግሥት በመታቀድ ብቸኛው አይደለም። በአገር ውስጥ የመወያያ ርዕስ በመሆን ግን ብቸኛው ይመስለኛል። ለወትሮው እንደነ ግልገል ግቤ ሦስት የመሳሰሉት ፕሮጄክቶች በአሉታዊ መልኩ ጉዳይ እየሆኑ የቆዩት በውጪው ዓለም በተለይም የተወሰኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ጥቅምና መብት እናስጠብቃለን በሚሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በኩል ነበር።
የወልቃይቱ ፕሮጄክት ጉዳይ የሆነው ግን ፕሮጄክቱ ለዋልድባ ገዳማት ካለውቅርበት-ርቀትአኳያ ነው። የዋልድባ ገዳማት ለቅርቡም ለሩቅም የኅብረተሰብ ክፍል የሚሰጡት ከፍተኛ ትርጉም አለ። ዋልድባ የት ነው? ምን ያህል ስፋት አለው? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎችን መመለስ የማይችለውም ሆነ የሚችለው ቢያንስ አርባ አራት ፐርሰንት የአገሪቱ ዜጋ በአንድነት ለቦታው መንፈሳዊነት የሚሰጠው ዋጋ ከፍ ያለ ነው።  በዚህ ምክንያትፕሮጄክቱ ራሱ ዋልዳባ ገዳም ክልል ውስጥ ላይ ነው፤ ዋልድባን እንዳለ ያጠፋል፤ ወደ ዋልድባ ቀጣና ገባ ብሏልየሚል መረጃ አለኝ የሚል ወገን አለ። በመንግሥት በኩልኧረ በፍጹም ዋልድባን አይነካም፤ፕሮጄክቱ ከገዳሙ ክልል ከአምስት እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ ራቅ ይላልየሚል ማብራሪያ አሁን ጽሑፌን ጨርሼ ልልክ ስል ሲሰጥ ሰምቼአለሁ። 
ከዚህ ውጪ ጽሑፌን መረጃ-ጠገብ ለማድረግ ላለፉት አስር ቀናት ሙሉና በቂ መረጃና ማስረጃ ሳፈላልግ ብቆይም አልተሳካልኝም። ሌላው ቀርቶ የገዳሙ ክልል ከየት እስከየት እንደሆነና ስፋቱ ምን ያህል እንደሆነ በአንድ በኩል፤ የፕሮጄክቱ ሙሉ ይዘትን ጨምሮ የሚሸፍነው ቦታ ከየት ጀምሮ የቱ እንደሚያቆም በሌላ በኩል የጠራ መረጃ ገና አላየሁም። ዋልድባ ገዳሙና ዋልድባ ቦታው ልዩነታቸውና አንድነታቸው ላይም እንዲሁ። ፕሮጄክቱ አሁን ከታስበበት ቦታ አንስቶ ሌላራቅያለ ቦታ መሥራት ይቻላል ወይስ አይቻልም የሚለውም ጭምር። 
አንድ ነገር ግን በርግጠኝነት መጻፍ ይቻላል። ፕሮጄክቱ ገና ከአሁኑ ማኅበራዊ ተጽእኖ መፍጠር ጀምሯል። ምክንያቱም ከላይ እንዳልነው የማኅበራዊ ተጽእኖ የሚጀምረው በጆሮ ነው።  የተሳሳተ መረጃም ትክክለኛ መረጃም አስተዋጽኦው (ተፅዕኖው ተብሎ ይነበብ) እኩል ነው። መንግሥት የፕሮጄክቱ ባለቤትና አስፈጻሚ እንደመሆኑ መጠን ባለድርሻ አካላትን በሙሉ ማሳተፍ አለበት። ማሳተፍ የሚጀመረው ደግሞ ተገቢውን መረጃን ተደራሽ ከማድረግ ጀምሮ ነው። 
ኅዳር 24 1995 .. የወጣው የአገሪቱ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ አዋጅ ስለ ሕዝብ ተሳትፎ በሚጠቅሰው ክፍሉ አንቀጽ 15  ቀጥር 1 ላይ “….ማንኛውም የአካባቢ ተፅዕኖ የጥናት ዘገባ ለሕዝብ ይፋ በማድረግ በዘገባው ላይ አስተያየት መጠየቅ አለበትይልና ቀጥርላይ ደግሞ “….በአጠቃላይ የሕዝብ በተለይም ደግሞ የፕሮጄክቱ አተገባበር ጉዳት ያስከትልባቸው ይሆናል ተብለው የሚገመቱ ማኅበረሰቦች አስተያየት፤ በአካባቢ ተፅዕኖ ጥናት ውስጥ መካተቱን እንደዚሁም ምርመራው በሚካሄድበት ወቅት መጤኑን መረጋገጥ አለበትይላል። በዚሁ አዋጅተፅዕኖበማኅበራዊና በባህላዊ ገጽታዎች ላይ የሚከሰት ተከታይ ለውጥን እንደሚያካትት አንቀጽ አንድ ቁጥር አራት ላይ ተመልክቷል።
በዚህ ምክንያት መንግሥትልሠራው ያሰብኩት ፕሮጄክት ይህን ይህን ይመስላል፤ በዚህ በዚህ ምክንያት አሁን የተመረጠው መንገድና ቦታ አስፈላጊና አይተኬ ሆኖ (ከሆነ) አግኝቼዋለሁ፤ ባደረግኩት ጥናት የሚያሳድረው አዎንታዊም አሉታዊም ተፅዕኖ ይህና ይህ ነው፤ ለአሉታዊው ተፅዕኖውም እንዲህ እንዲህ አይነት የመፍትሄ  መንገዶች አዘጋጅቼአለሁ፤ ባለድርሻዎች የምትሉት ካለ እነሆ፤ የተሻለ ሀሳብ ካለም ለመስማትና ለማየት ለመቀበልም ዝግጁ ነኝ ማለት አለበት።ይህ ደግሞ ከላይ በጠቀስኩት አዋጅ እንደተመለከተው በቆይታ በፕሮጄክቱ ምክንያት በቅርብ ርቀት በሚፈጠሩትከተሞች ተያያዥ ክስተቶች ምክንያት የገዳማውያኑ መደበኛ ኑሮ ቀጣይነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ተፅዕኖ ከተዳማሪነትና ለመመለስ ከመቻሉ ወይም ካለመቻሉ አኳያ መታየት አለበት። 
ባለድርሻውን ማሳተፍ ማለት በሥራው ሂደት ላይ ድርሻ የመውሰድ ያህል ኃላፊነትን ለባለድርሻው በማሸከም የጋራ የሆነ ሁለንተናዊ አገራዊ ጥቅምን ከማስጠበቅ አንጻር ባለድርሻው ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው እንዲገባበት ማድረግ ነው። የሚሳተፈው አካል ጥቅሙን እንዲያስጠብቅ እድል ከማግኘቱ ጋር ጥቅሙ በማይጠበቅበት ሁኔታ ራሱ እንኳ ሁኔታውን ተረድቶ እንዲቀበለው መንገድ ይክፍትለታል ማለት ነው። የማንኛውም ክፍል ተነጻጻሪ ጥቅም መለ(!)ካት ያለበት ደግሞ በራሱ መሆን አለበት። ይጠቅመዋል የተባለውም ነገር ራሱ ያለ ምንም ተጽእኖ ጥቅሜ ነው እንዲል ለማድረግ ማሳተፍ የግድ ነው። በማሳተፍ ሂደቱ ደጋፊ፤ አስረጂና ተንታኝ ሊሆን የሚችል አካል ይኖራል። ተደምሮ ተቀንሶ ግን ጥቅሙን የሚለካው ራሱ ተጠቃሚው  ብቻ መሆኑን በተግባር እውቅና መስጠቱ ለሁሉም አካላትና ለሥራውም ተፈጻሚነት የሚበጅ ይሆናል። ከወልቃይቱ ፕሮጄክት ጋር በተያያዘም ያለው ጉዳይ መንግሥት አሁን እንደሆነው መሬት ላይ ገና ሥራውን ሳይጀመር ተገቢውን መረጃ ከመስጠት ጀምሮ ኃላፊነቱን መወጣት ነበረበት። አሁንም ቢሆን ቢያንስ የራሱን የጥናት ሰነዶች ይፋ ማድረግ አለበት።
ከሰባት ዓመት በፊት ስዊድን ወስጥ ያደረግኩት አንድ ጥናት ውስጥ በአንድ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ነዋሪዎች ወደፊት በጥናት ላይ በነበሩና ወደፊት በተግባር ላይ ሊውሉ ስለሚችሉ አዳዲስ የኃይል ማመንጫ ቴክኖሎጂዎች በተመለከተ ያላቸው እውቀት፤ ፍርሀትና፤ ስሜት ከአዛላቂነት ግምገማ አኳያ የሚመለከት ነበር። ለዚህ ጥናት ይረዳኝ ዘንድ የመጠይቅ ቅጾች ላኩኝ - በነሲብ ንሞና ለተመረጡ ሰዎች። በአንድ ዙር ሞልተው የላኩ ሰዎች ነበሩ። ማስታወሻ ላኩኝ - ላልመለሱት። የተወሰኑት መለሱ። መጨረሻ ላይ ደግሞ በሁለት ዙር ላልመለሱት አንድ ጥያቄ ብቻ ያላት መጠይቅ ላኩኝ። በአጭሩ ለምን እንዳልመለሱ የምትጠይቅ (ከጊዜ እጥረት ነው? ወይስ ጥያቄዎቹ ግልጽ አይደሉም? ወዘተ የምትል) መጀመሪያ ዋናውን ጥያቄ ከመለሱትም ሆነ ከሌሎች መላሾች ይበልጥ ቀልቤን የሳበው በአንድ ሰው የተሰጠች መልስ ነበረች። እሷምመንግሥትም ሆነ ቴክኖሎጂ የሚፈጥሩትና የሚያበለጽጉት ሌሎች ክፍሎች ዜጎች እንደዜጎች ያለንን ሃሳብና ፍላጎት አካትተው አይሠሩም ብዬ ስለማምን ነው ያልመለስኩትየምትል ነበረች። ባደጉት አገሮችም ሆነ ይልቁንም በንደኛ አይነት አገሮች በዚህም ሆነ በዛ ምክንያት ዜጎች መንግሥትም ሆነ ሌሎች ውሳኔ ሰጪ አካላት ሃሳባችንንና ፍላጎታችንን ተግባራዊ ግንዛቤ ውስጥ አያካትትሉንም ብለው ተስፋ እስኪቆርጡ ድረስ የሚሰማ ጆሮ ማጣት የለባቸውም።
መቋጫዬ የመረጃ ረሀብ ቅነሳ መርሐ ግብር ይታወጅ ይተግበር የሚል ነው።
=======አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

2 comments:

Weyra said...

The conclusion is funny and yet annoying.

Berhanu said...

I admire and envy of your command of the language and the subject. A timely and enlightening new narrative; Indeed, you inject a new energy to an issue that has been muzzled and polarised .A seminal piece of work, I love it , in particular:
አዛላቂነት ምጣኔ ሀብታዊ፤ አካባቢያዊና ማኅበራዊ አውታሮች አሉት። ማንኛውም ቴክኖሎጂ፤ ፕሮጄክት ፓሊሲ ወዘተ ከአዛላቂነት አንጻር ስንገመግመው ከእነዚህ ሦስት አውታሮች አኳያ በጎና ጎጂ ተፅዕኖውን ለይተን አስቀመጥን ማለት ነው።
በወልቃይት የሚሠራው የስኳር ልማት ፕሮጄክት በመንግሥት በመታቀድ ብቸኛው አይደለም። በአገር ውስጥ የመወያያ ርዕስ በመሆን ግን ብቸኛው ይመስለኛል። ለወትሮው እንደነ ግልገል ግቤ ሦስት የመሳሰሉት ፕሮጄክቶች በአሉታዊ መልኩ ጉዳይ እየሆኑ የቆዩት በውጪው ዓለም በተለይም የተወሰኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ጥቅምና መብት እናስጠብቃለን በሚሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በኩል ነበር።
የወልቃይቱ ፕሮጄክት ጉዳይ የሆነው ግን ፕሮጄክቱ ለዋልድባ ገዳማት ካለው “ቅርበት-ርቀት” አኳያ ነው። የዋልድባ ገዳማት ለቅርቡም ለሩቅም የኅብረተሰብ ክፍል የሚሰጡት ከፍተኛ ትርጉም አለ።
Thank you