Saturday, April 28, 2012

ኑ መረጃን እንሰብስብ፤ ተደራሽም እናድርገው


(ጌታቸው አሰፋ፤ መጋቢት 29 ቀን  2004 ዓ.ም.) ሰሞኑን በዝቋላ አቦ ገዳም ዙሪያ ያለውና አንድ ለአካባቢው የሆነው (ለአንድ ለእናቱ እንዲሉ) ግርማ ሞገሳሙ ደን በአሳዛኝ ሁኔታ ሲቃጠል ነበር (በጎግል ኧርዝ ካርታ ላይ ደኑን ፍንትው ብሎ ብታዩት አንድ ለአካባቢው የመሆኑ ነገር እጅግ ያሳሳችኋል)።ብዙ ሰው ከአዲስ አበባም ከደብረዘይትም እየተጠራራ ሄዶ ተጋግዞ አጠፋው - በእግዚአብሔር ቸርነት። ይሄ ነገር ከአሁን በፊት የተደጋገመ ክስተት በመሆኑ ለወደፊትም አንድ ነገር ካልተደረገ እንደገና ኧረ ከዛም በላይ ላለመከሰቱ ምንም ዋስትና የለም። እንደገና እንዳይከሰት ለማድረግ የተለያዩ ነገሮች መደረግ እንዳለባቸው በየቦታው ያለ ሰው ሲወያይ ነበር።  
ስለወደፊቱ መረጃ-ጠገብ ውይይት የሚበረታታ ነገር ነው። እንደ አገር እንደ ማኅበረሰብ ዛሬና ነገ ማድረግ ያለብን ነገር ለመተንተንና በተግባር የሚጨበጥ ስራ ለመሥራት  ውይይቱ በጣም አስፈላጊ ነው። እስቲ ዝቋላ እንቆይና ለመሆኑ ትላንቱእሳት ምን ያህል የመሬት ስፋት ላይ የነበረ ደን ተቃጠለ? በቁጥር ምን ያህል ዛፎች ሙሉ በሙሉ ተቃጠሉ? ምን ያህሉ ከሰሉ? ምን ያህሉ ተለበለቡ? ምን ምን አይነት ዛፎች ናቸው የተቃጠሉት? ለመሆኑ ቅድመ-እሳት ምን ያህል ዛፎች በዝቋላ ደን ነበሩን? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ያስፈልጋል። መልሱ የጉዳቱ መጠን ለማወቅና በገንዝብም በካርቦንና በሌሎች የስነ ምህዳር አገልግሎች መሠረት ለመዘገብና ለማስላት ይጠቅማል። በዛ ላይ ደግሞ መልሰን መተካት ያለብን የትኛው እና በምን ያህል መጠን ነው የሚለውን መነሻ የሚሆን ቁጥር ይሰጠናል። ቁጥር ኖረንም አልኖረንም ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል - ግልጽ ነው። ለወደፊቱ ግን በተደጋጋሚ በሌሎች ጽሑፎች ላይ እንዳነሳሁት ትክክለኛ ቁጥር መጥራት ስንችል ትክክለኛ አያያዝ ለማበጀት ይቀለናል። ትክክለኛ ቁጥር ለመጥራት ደግሞ ጥያቄዎች መጠየቅን መልስ መሻት መጀመር አለብን።
በዚህ ሳምንት አንድ የምርምር ፕሮጄክት ዙሪያ ውይይት ለማድረግ ከአንድ ምርምሩን በገንዘብ መደገፍ ይችላል ከተባለ ድርጅት የመጣች ሰው ጋር ስብሰባ ተቀምጬ ነበር። ፕሮጄክቱ በካናዳ በተለይ ደግሞ የምሰራበት ዩኒቨርስቲ በሚገኝበት ክፍለ ግዛት ያለው የደን፤ የግብርና እና የካርቦናዊ ቆሻሻ ሀብቶችን እንደ ግብአት በመጠቀም የሚመረቱና ሊመረቱ የሚችሉት ምርቶችንና አገልግሎቶችን ከአካባቢያዊ ተጽእኖና ከኃይል ቁጠባ አንጻር የሚኖራቸው ደረጃ ማጥናት ላይ የሚያተኩር ነው። ለምሳሌ የደን ሀብትን ብንወስድ ከደኑ ከሚገኝ ጣውላና ጥሬ እቃዎች የሚሰሩትን የቤትና የቢሮ ቁሳ ቁሶች፤ የሕንጻ መገንቢያ ቁሶች፤ የወረቀትና የወረቀት ውጤቶች እንዲሁም ሙቀት አቃቢ ቁሶችን ወዘተ ሙሉ የምርት፤የአገልግሎትና የፍጻሜ-ሕይወት ሂደታቸውን በማጥናት አገሪቱ ወይም ክፍለ ግዛቱ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ዘርፍና ክፍለ-ዘርፍ ካለ የትኛው ነው የሚለውን ጥያቄን መመለስን ያካትታል - ፕሮጄክቱ።
መጠየቅ መጠየቅ አሁንም መጠየቅ
ታዲያ በንግግራችን መሐል የሚከተሉትን ወርቅ ወርቅ የቁጥር ጥያቄዎችን ጠየቀችኝ። በክፍለ ግዛቱ ወስጥ ያለው ደን ለመነሻ ያህል ወስደን በክፍለ ግዛቱ ውስጥ ምን ያህል ካርቦን አለ? በየዓመቱስን ምን ያህል ካርቦን ከከባቢ አየር በአጠቃላይ በደኑ ያታቀባል? ምን ያህል ካርቦንስ የደን መጋዘኑን ለቆ በየዓመቱ ከምርቶች ጋር ተያይዞ ይወጣል? የጥያቄዎቹን ወርቅነት የምለካው ከየት-ወዴት ለሚሉት ጠቋሚ መንታ ተጠየቆች በአግባቡ ምላሽ ለማስገኘት ካላቸው አቅም አኳያ ነው። ብሔራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶች፤ ሳይንሳዊ ምርምሮች፤ ትምህርታዊ ሥራዎች በሙሉ የተሰፈረ ነገር ላይ ሲመሰረቱ ውጤታቸው ስለሚያምር እንደዚህ አይነት ጥያቄዎችና መልሶች አስፈላጊ ናቸው። ሦስቱን ጥያቄዎች ለመመለስ ደግሞ የተለካ፤ የተቆጠረና የተሰላ መረጃን ከየቦታው ማዋሀድን ይጠይቃል። ያን ማድረግ ይቻላል ፤ይደረጋልም። በአገራችንም ስንት ነው? ስንት ነበር? ስንት ጎደለ? ስንት ተጨመረ? የሚለው በየቦታው በየጊዜው በሁሉም ሰው ዘንድ የሚጠየቅ መሆን አለበት። በአንድ ወቅት ሐዋሳ ውስጥ የሕጻናት መዝናኛ ማዕከል መክፈት ይፈልግ የነበረ ወዳጄ ጋር ከተማዋ ውስጥ በእግር እየዞርን እያወራን ሳለ ለብዙ ዓመታት የኖረባት ሐዋሳ ስንት ሰው እንደሚኖርባት እንደ ቀላል ነገር አድርጌ ጠየቅኩት። ከወዳጄ የተረዳሁት መልሱን አለማወቁ ብቻ ሳይሆን ጥያቄው ራሱ ጠይቆ አለማወቁ፤ ጭራሽኑም መጥቶለት አለማወቁ ነው። በተለይ የሕጻናት መዝናኛ እከፍታለሁ ካልክ አጠቃላይ የሕዝብ ብዛት ብቻ ሳይሆን ስንት ሕጻናት እንዳሉ፤በብዛት በየትኛው የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ እንደሆነ፤ በየዓመቱ ስንት እንደሚወለዱ ወዘተ ማወቅ እንደሚያስፈልግ አውርተን ስለ መጠየቅ አስፈላጊነት ማንሳታችን ትዝ ይለኛል።
መልስ እንኳን መስጠትም ማግኘትም የማንችልበት ቦታም ላይ ቢሆን ጥያቄው ሁል ጊዜ መፈጠር አለበት።  በእኛ ዘንድ ያለው ግን በብዛት ጥያቄው አይመጣልንም። ለምሳሌ የእኛ ሰዎችም ሆኑ ሌሎች የምዕራባዊያን ዜጎች ተወልደው ስላደጉበት ከተማ ወይም መንደር ሲያወሩ ወዲያው የሚጠየቁት ጥያቄ ስንት ሰው ይኖርባታል የሚል ቢሆን መልሳቸው ለየቅል ነው። ሌሎች ዜጎች ከሞላ ጎደል ቢያንስ ገምተው፤ ወይም በሆነ ወቅት ይህን ያህል ነበር ብለው በተወሰነ ደረጃም በንጽጽርም ቢሆን የሆነ ነገር ማለታቸው አይቀርም። የእኛ ሰዎች ግን ከሞላ ጎደል ኧረ እኔ እንጃ ከሚለው ጀምሮ ጥያቄን በጥያቄ መመለስን አካቶ ወይም በድፍኑትንሽ ነችትልቅ ነችወዘተ  ከማለት ውጪ መልስ አይኖራቸውም። ሲጀመር ጭራሽ ስንት ሊሆን እንደሚችል እንኳን ሃሳብ ሆኖብን የማያውቅ ነገር ነዋ። ስለዚህ ያቺን ከተማ ወይም መንደር በሕዝብ ብዛት ከሌላ ከተማ ወይም መንደር ታንሳለች ወይስ ትበልጣለች? ወደሚለው ጥያቄ ወይም አምሳ ሺህ ይሆናል? ወዘተ እያሉ መቀጠል ያስፈልጋል - የእኛን ሰው። እንደዛም ሆኖ ሁለት አብሮ አደጎች ራሱ ይሄን ጥያቄ የሚመልሱት በተለያየ መልኩ ነው። 
ስለ መረጃ እጥረትና ጥራት ዝቅተኛ መሆን ያው ከአሁን በፊት አንስተናል። መረጃው ባለበትም ቢሆን የማይጠይቅ ኅብረተሰብ ባለበት ቦታና ሁኔታ ያለ(!) መረጃ ከሌለ መረጃ ብዙም አይለይም - ቢያንስ ለዛ ኅብረተሰብ።
ጥራት ያለው መረጃ ጠያቂ ሲበዛ የሌለ መረጃም ካለመኖር ወደመኖር ይመጣል፤ጥራቱም ከፍ እያለ ይሄደል። ጥሩ መረጃ ጠያቂ በሌለበት ግን ከዕለታት አንድ ቀን ጠያቂ ሲመጣም የምር መልስ የሚሰጠው አያገኝም። በግምት የሚወራው ብቻ ነውመረጃሊሆን የሚችለው። ወደ ውጪ ስንወጣም ብዙም አንለወጥም። አሁን ባለሁበት ከተማ(ለሦስት ፈሪ ዓመት ነው የኖርኩት) ስለሚኖረው የእኛ ሰው ቁጥር በተመለከተ የምር ከሚጠይቀው ይበልጥ በአቦሰጥ የሚገምተው ሰው እጅግ ብዙ ሆኖ ነው ያገኘሁት። የሚጠ(!)ራው ቁጥር ከሦስት ሺህ እስከ አስራ አምስት ሺህ ይደርሳል። በአጠቃላይ አንድ ሚልዮን ህዝብ በሚኖርባት ከተማ በሁለቱ ቁጥሮች መካከል ያለው ልዩነት እጅግ ብዙ ነው። በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ማኅበርና የኢትዮጵያ ቆንስላ በካናዳ እዚህ ከተማ ስንት ነን ብዬ ጠይቄ መልስ ለማግኘት ያደረግኩት ሙከራ አልተሳካም(ይህ አባባል የሆነ ሬዲዮ ድምጽ አይመስልም?)  ቁጭ ብዬ ወደ ማስላት ገባሁ። አንዳንድ በነጻ የሚገኙ የአገሪቱም የከተማይቱም ይፋዊ የመንግሥት መረጃዎችን መሠረት አድርጌና ቁጥር ያጠረበት ቦታ ላይ ደግሞ እንዲህ ቢሆን እንዲህ ቢሆን ብዬ አስልቼ ያመጣሁት ቁጥር ከላይ ከጠቀስኩትና ሰዉ በግምት ከሚጠራው ዝቅተኛው ቁጥርም በታች ሆነ። ያንን ውጤቴን እዚህ ከተማ በምናሳትመው መጽሔት ላይ አሳትሜው በተወሰነ ደረጃ መወያያ ሆኖ ነበር። በነገራችን ላይ እንዲሁ ጥቅል የሆነስንት ነን?” ከሚል ጥያቄ ተነሳሁ እንጂ ለተሻለ ዓላማ ቁጥራችንን ማወቅ የሚፈልግና ገንዘብ ለመክፈል ፈቃደኛ ለሆነ ሰው መረጃው በካናዳ የስታቲስቲክስ ቢሮ ውስጥ የሚገኝ ነው።
ምን ይቆጠር ምን ይለካ
ሁሉም ነገር ይቆጠር ሁሉም ነገር ይለካ። ምሳሌዎችን ለመጥቀስ ያህል ግን አስቀድመን ከተነሳንበት የዝቋላ አቦ ጉዳይ ጋር ከሚያያዘው መጀመር ይቻላል። ለመሆኑ በየቦታው ምን ያህል የደን ስፋት ነው ያለን? በየቦታው በየመንደሩስ (በከተማም በገጠርም) ስንት የዛፍ ዝርያዎች አሉን? ከየዝርያው ስንት እግር ዛፎች በየሰፈሩ አሉ? ማወቅ፤መመዝገብና ማዳራስ አለብን።
በየመንደሩ በየሸንተሩ ስንት ወንዞችና ጅረቶች አሉ? ስንቶችን ንጹህ ናቸው? ስንቶቹ ዓመቱን ሙሉ ይፈሳሉ? ስንቶቹ ከደረቁ ቆዩ? ምን ያህል ርዝመት አላቸው? ምን ያህል ስፋት ነበራቸው? አላቸው?
የየወንዙና የየጅረቱ የፍሰት መጠን መረጃ በካርታ ተደግፎ በቀላሉ የሚገኝ መሆን አለበት።
በአንድ ወቅት በአንድ ቦታ የነበሩ ያሉ የመኖሪያም ሆኑ ሌሎች ሕንጻዎች ብዛትና አይነት ማን በነገረን? ማን መረጃውን ተደራሽ ባደረገልን
የመኪኖች ቁጥርና አይነትስ የመጨረሻውን ታርጋ ቁጥር ብቻ በማየት መቼ ይታወቃል? በየጊዜው ከጥቅም ውጪ የሚሆኑትን ማን መዘገባቸው? በየጊዜውና በየቦታው በሥራ ላይ ያሉት፤ በየአይነታቸው፤ በየሞዴላቸው፤ በየአገልግሎት ዘመናቸው፤ በየሚወስዱት ነዳጅ አይነት ወዘተ ተዘርዝረው የሚያሳይና የአንድ ወቅት ሳይሆን በየጊዜው የሚታደስ ወቅታዊ መረጃ የት ይሆን ያለው?
ከነዚህ እና ከሌሎች ብዙ ደርዘን ከሚሆኑት የመረጃ ጥያቄዎች መካከል የተወሰኑት መረጃውን ብሎ በመሰብሰብ የሚመለሱ ናቸው። በሌላ በኩል መረጃቸው በተወሰነ ደረጃና ጥራትም ቢሆን የሆነ ቦታ ያላቸው ይኖራሉ። ግን ወይ ተደራሽ አይደሉም፤ ወይም በየጊዜው የሚያታደሱ ባለመሆኑ ወቅታዊ አይደሉም። 
ማን ይሰብስብ? ማን ያዳርስ?
ጥራት ያለው መረጃን በመፍጠርም ሆነ ተደራሽ በማድረግ በኩል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የአንበሳውን ድርሻ መውሰድ ያለበት መንግሥት ነው። ቢያንስ በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ገጸ ድር ላይ ያለውን እንኳን መረጃ በቀላሉ የሚገኝ በቀላሉ የሚታይ ማድረግ ለመንግሥት ለማድረግ በጣም ቀላል ለተጠቃሚዎች የሚሰጠው ጥቅም ደግሞ በጣም ትልቅ ነበር (ሰሞኑን አለ የተባለ መረጃ ከገጸ ድሩ ለማግኘት ደጋግሜ ሞክሬ እምቢ ብሎኝ መተዌን እንዴት ልሸሽግ?) ግን ያም አልሆነም። መንግሥት ሆይ ቢያንስ ያሉትን መረጃዎች በቀላሉ እንድናገኛቸው አድርግልን። አስደርግልን። ወደታችን ስንወርድ ግን መረጃ በመሰብሰብም ሆነ ተደራሽ በማድረግ ከመንግሥት ማዕቀፍ ውጪ ያለነው የማኅበረሰብ ክፍሎችም ብዙ መስራት እንችላለን። በርካታ ማኅበራትና የትምህርት ቤት ክበቦች በየከተማው አሉ። ብዙም ከመስመራቸው ሳይወጡ ከአካባቢያቸው ሳይርቁ መሰብሰብ የሚችሉት መረጃ ቢያንስ አካባቢያቸው መንደራቸው ተሰፍራ፤ ተቆጥራና ተለክታ እንድትታወቅ ያደርጋል። በቦታው ያሉ የእምነት አደረጃጀቶች እድሮች ወዘተ ከአንደኛ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጋር በመተባበር የአካባቢውን ተማሪዎች በማሰማራት ሊሰሩትና ሊያሰሩት የሚችሉት ነገር ነው። በአንድ ትንሽ ከተማ ያለውን የሕዝብ ብዛት አንዴ ከታወቀ በኋላ ሲወልድና ሲሞት ደስታውንም ሐዘኑንም መካፈል የግድ ስለሆነ የልደትና የሞትን እንዲሁም የፍልሰት (ወደ ውስጥና ወደ ውጭ) ቁጥር በየጊዜው እየቆጠሩ በማስላት ቀጣይ ጥራት ያለው መረጃ  በመንደር ደረጃ ማበጀት ይችላላ። በየቦታው በየጊዜውከመኖር ወደአለመኖር  ‘ካለመኖር ወደ መኖርየሚመጡትን ነገሮች፤ ሰዎች፤ የቤትና የዱር እንስሳት፤ እጽዋት፤ ሕንጻዎች፤ መኪኖች ወዘተ በየመንደሩ በየሰፈሩ ለመመዘገብ ከባድ አይደለም። የተመዘገበውን ለሚፈልገው አካል ተደራሽ በማድረግ በኩል ደግሞ የብዙኃን መገናኛዎች፤የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፤ፓስታ ቤቶችና፤ ኢትዮ ቴሌኮም ወዘተ ጥሩ ድርሻ መጫወት ይችላሉ። ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሯቸውን ተማሪዎች ቢያንስ ጥሩ ጠያቂዎች፤ ጥሩ መልስ ፈላጊዎች ማድረግ አለባቸው። 
=======
አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: