Saturday, April 28, 2012

የት ፈጨሺው?

(ጌታቸው አሰፋ፤ ሚያዝያ 13 ቀን  2004 ዓ.ም.) በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በጾም ጊዜ የፍስክ ምግቦች ስም መጠራት የለበትም በሚል እሳቤ ላይ የተመሰረተ የልጆች (የወንድም የሴትም) ጨዋታ አለ። አንድ ልጅ ድንገት ተሳስቶ የፍስክ ምግብ ስም ከጠራ ሌሎች ልጆች ተሽቀዳድመው በቁንጥጫ ይይዙታል። ተቆንጣጩ ጾሙ ሲፈሰክ ለቆንጣጩ የሚሰጠውን የፍስክ ምግብ ጠርቶ ቃል ካልገባ አይለቀቅም። በዚህም ምክንያት ልጆቹ በጾም ወቅት ወሬ ሲያወሩ የፍስክ ነገር እንዳያነሱ መጠንቀቅ አለባቸው ማለት ነው። ይህን የፍስክም የጾምም ምግቦችን የሚያነሳው ጽሑፍ ለመጻፍ አስብ የነበረው ታላቁ የሁዳዴ ጾም ባለፈው ሳምንት ከመጠናቀቁ በፊት ነበር። ይሁንና የአንባቢያን ቁንጥጫ ፈርቼ ሳይሆን አዲስ ጉዳይ የቆየ ጉዳይን እየገፋብኝ ጾሙ ካለቀ በኋላ እነሆ ዛሬ ለመጻ(!) በቅቷል። እንቀጥል።

የራሳቸው የሆነ የሚበሉት ምግብ የሌላቸው ሚልዮኖች በአገራችን እንዳሉ ይታወቃል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ለሌሎች ሚልዮኖች የኑሮ ውድነቱ እጅግ ከባድ ጫና ሆኖባቸዋል። እንደዛም ሆኖ አነሰም በዛም መደበኛውን የሁዳዴን ጾምም ሆነ ሌሎች አጽዋማትን ሚልዮኖች ወደው ፈቅደው እየጾሙት ነው። በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሥጋዊና የመንፈሳዊ ሕግ ምንጭ የሆነው ፍትሐ ነገሥት ስለ ጾም በሚናገረው አንቀጹ ላይ ጾምበሕግ ውስጥ በታወቀው ጊዜ የሰው ከምግብ መከልከልመሆኑንናከእንስሳትም የሚገኘውን አለመብላትማለት እንደሆነ ይናገራል። 
ጾም መንፈሳዊ ተግባር ነውና ከመንፈሳዊ እይታ አንጻር ብቻ የሚታይ ነገር ነው ሊባል ይችላል። ይሁንና መንፈሳዊው ዓለም ሥጋዊው ዓለም ላይ የሚያጠላው የራሱ የሆነ ጥላ ስለሚኖረውና ስለሚገባውም ይህን መንፈሳዊ ሥራ ከአካባቢያዊ አዛላቂነት አኳያ እንመለከተዋለን። አስቀድመን እንዳየነው ጾም በዋናነት የሚገለጸው ከሚበላው የምግብ አይነትና ከሚበላበት ጊዜ አንጻር ነው። በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት መሰረት በዓመት ከሁለት መቶ በላይ የሚደርሱ የጾም ቀናት ያሉ ሲሆን በነዚህ ቀናት ጠዋት ቁርስ አይበላባቸውም - ቅዳሜ እና እሁድ ካልዋሉ። ምግብ በሚበላበት ጊዜም ማንኛውም አይነት ከእንስሳት ተዋጽኦ ውጪ የሆነ ምግብ ነው የሚበላባቸው። የሥጋና (የአሳም ጭምር) የወተት ውጤቶች በማንኛውም የጾም ወቅት አይበሉም። 
በምዕራቡ ዓለም ለተለየ ምክንያት መንፈሳዊ ያልሆኑ ሰዎችን ጨምሮ ከምግብ መታቀብ እንኳን ባይኖር የእንስሳት ተዋጽኦን በተለያየ ደረጅ ከምግብ ዝርዝራቸው እያወጡ የሚገኙ ሰዎች ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እየሄደ ይገኛል።
ጾምና አካባቢ
የተወሰኑት ሰዎች ሥጋና የሥጋ ውጤቶችን ያስወግዱና ወተትና የወተት ውጤቶችን የሚበሉና የሚጠጡ ናቸውቬጂቴሪያን  የሚባሉቱ።  ሌሎች ቬጋን የሚባሉት ደግሞ ሙሉ በሙሉ የወተት ውጤቶችንና የባህርም የየብስም እንስሳት ተዋጽኦን አይበሉም። ከነዚህ ሁለት ክፍሎች ውጪ አንድ ነገር የሚጨምሩ ወይም የሚቀንሱ ሰዎችም አሉ። አንዳንዶች ምግብ በተመለከተ ምን እንደሚበሉ እንደማይበሉ የሚወስኑት ከጤናቸው ጋር በተያያዘ፤ ለእንስሳት መብት መጠበቅ ካላቸው አመለካከት፤ ከሰውነትንጽህናጋር በማያያዝ ወይም ከእምነታቸው አንጻር ሊሆን ይችላል። በጣም ትንሽ የሆነው ክፍል ደግሞ ከአካባቢ ጥበቃ አንጻር የተሻለ ነው የሚሉትን ምግብ የሚመርጡ ሰዎችን ያካተተው ነው። 
ከአካባቢ አዛላቂነት አንጻር የምግብ አይነቶች በተናጠል ሲጠኑ ቆይቷል። በጅምላ ደግሞ የእጽዋት ተዋጽኦ ምግቦችና የእንስሳት ተዋጽኦ በአካባቢ ላይ የሚያደርሱት ተጽእኖ ማበላለጥም እንዲሁ ትኩረት ስቦ የሚገኝ ነው። ከመነሻችን ጋር እንዲያያዝልና የጾምና የፍስክ ምግብ እያልን እንቀጥላለን። 
ሁለቱን የምግብ አይነቶች ከአካባቢ ተጽእኖ አኳያ በተለያየ መልኩ ሊነጻጸሩ ይችላሉ። ለምሳሌ አንድ ኪሎ የጾምና አንድ ኪሎ የፍስክ ምግብ ልናነጻጽር እንችል ይሆናል። በሌላ መልኩ የመቶ ብር የጾም ምግብና የመቶ ብር የፍስክ ምግብም እንዲሁ የትኛው አነስተኛ የአካባቢ ተጽእኖ አለው ብሎ ማስላት ይቻል ይሆናል። በክብደትም ሆነ በዋጋ መሰረት ማነጻጸር የተሳሳተ ማጠቃለያ ላይ የማድረስ እድል አለው። ለምሳሌ ከምግቡ ዋጋ ጋር በተያያዘ የሚፈጠር ልዩነት ዋጋው የተወሰደው ከመቼና እና ከየት ነው የሚል ጥያቄን ስለሚፈጥር ከጊዜና ከቦታ ጋር የተቆራኘ ነው የሚሆነው። ምግብን የምንበላበት ዋነኛውን አላማ የማያገናዝብ ስሌትና ንጽጽር ነው ትክክለኛ የሚሆነው። ምግብን እንደ ምግቡ አይነት ኃይል ለማግኘት፤ ሰውነት ለመገንባት ወይም ከበሽታ ተከላካይ ንጥረ ነገሮችን እናገኝበት ዘንድ ነው የምንመገበው። የጾም ምግብና የፍስክ ምግብ እንደየ ንጥረ ነገሩ የሚሰጡት አይነትና መጠን አንድ አይነት የሚሆንበትም የሚለያይበትም ጊዜ አለ። 
የተሻለ ንጽጽር የሚሆነው ይህን ልዩነትና አንድነት ያገናዘበ ስሌት መከተል ነው። በዓመት ውስጥ ያሉትን የጾም ቀናት ውስጥ በስርአቱ መሰረት በመጾም ማሳለፍና ምንም ሳይጾሙ የፍስክ ምግብ እየበሉ በማሳለፍ የሚከተለው የአካባቢ ተጽእኖ ልዩነት ምን ያህል ነው የሚለው እይታ ትርጉም ያለው ይሆናል።
የፍስክ ምግብ ዋና አካል የሆነው ሥጋ ነው። ሥጋ (ቁርጥም ሆነ ቀይ ወጥ) የምግብ ጠረጴዛችን ደርሶ ለአቅመ-መበላት ከመብቃቱ በፊት ብዙ ሂደቶችን ያልፋል። ሥጋው የበሬ ነው እንበልና በሬው ለዓመታት ሲመገብም የተፈጥሮ ግዴታውን ሲወጣም በአካባቢ ላይ የሚያደርሰው ተጽእኖ ቀላል አይደለም። የኛ አገር በሬ ከሆነ የሚውለው መስክ፤ የሚያድረውም ከአውሬ መከላከል ላይ ብቻ ያነጣጠረ አገነባብ ያለው በረት ውስጥ ነውና - ተጽእኖው የሚካበድ ላይሆን ይችላል። በአንዳንድ ቦታዎች በብዛት ከብቶች በሚኖሩበትና የግጦሽ መሬት በሚያንስበት ወቅት ለከብቶቹ ግጦሽ ሲባል የሚጨፈጨፍ ደን ሲኖር መካበድ የማያስፈልገው ከባድ ይሆናል - ችግሩ።
በተቀራኒው በምዕራቡ ዓለም ያለው ለእርድ የሚሆኑ እንስሳት አመጋገብና አያያዝ በምናይበት ጊዜ በአካባቢ ላይ የሚያደርሱት ተጽእኖ እጅግ ከፍተኛ ሆኖ እናገኘዋለን። የፍስክ ምግብ ለማምረት ጥቅም ላይ የሚውለው የቅሪታዊ ነዳጅ መጠን የጾም ምግብ ለማምረት ከሚያስፈልገው ጋር ሲነጻጸር በአስር እጥፍ ይበልጣል። ለምሳሌ እያንዳንዷ የፍስክ ምግብ የአየር ንብረትን ለውጥን ከማምጣት አንጻር ከጾም ምግብ በአስር እጥፍ የባሰ ተጽእኖ አላት ማለት ነው። በአሜሪካ ብቻ ስናይ በአገሪቱ ከሚመረተው አጠቃላይ የቅሪታዊ ነዳጅ  ውስጥ ከአንድ ሦስተኛው በላይ የሚሆነው የሚውለው ለምግብ የሚሆኑ እንስሳትን ለማደለብ ነው።
በጾም ምግብና በፍስክ ምግብ መካከል ያለው ልዩነት ትርጉም በዓለም ደረጃ ሲታይ የላቀ ነው። 2050 .. የዓለም የህዝብ ብዛት ወደ ዘጠኝ ነጥብ አንድ ቢልዮን ይደርሳል ተብሎ ይገመታል። ያኔ የዓለም የሥጋ ፍጆታ በእጥፍ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ምግብና መኖ
በዓለም ከሚመረተው የምግብ ምርት ከግማሽ በላይ የሚሆነው ለእንስሳት መኖነት እየዋለ ይገኛል። ይህን የምግብ ምርት ለማምረት ደግሞ በግብአትነት የሚያስፈልገው ውኃ፤ ማዳበሪያም ሆነ ጸረ ተባይ ሁሉ የእንስሳት ተዋጽኦው ሸክም ነው።  በካሎሪ የሚለካውን የምግብ የኃይል መጠንን ስንወስድ ከአንድ እንስሳ መቶ ካሎሪ የምትሰጥ ሥጋ ለማግኘት ለእንስሳው እስከ ሰባት መቶ ካሎሪ የሚደርስ ኃይል የያዘ ለሰው ምግብ ሊሆን ይችል የነበረ ምርት ነው በመኖነት የሚሰጠው።
መኖውን ለማምረት ለማዘጋጀት፤ ከብቶችን በበጋም በክረምትም መዋያቸውንና ማደሪያቸውን ተገቢውን ሙቀት እንዲያገኝ ለማድረግ፤ ከዛ በጅምላ ወደሚታረዱበት ዘመናዊ ቄራ ለመውሰድ፤በቄራው ውስጥ ያሉትን ማሽኖች ለማንቀሳቀስ፤ ለማረድና ከዛም ነዳጅ-ጨራሽና በካይ በሆኑ ባለ አስራ ስምንት ጎማ የጭነት መኪኖች በመጠቀም ሥጋውን ወደየቦታው ለማዳረስ በሚደረገው ባለ ብዙ ክፍለ-ሂደት ሥርአት ወቅት ጥቅም ላይ የሚውለው የኃይል መጠንና የሚከተለው በካይ ልቀት ሊሳስበን ይገባል። 
የነዳጅ ቁጠባ፤ የብክለት ቅነሳ እና የአየር ንብረት ለውጥን የመግታት ሥራ ለመስራት የምንችለው በዓለም ደረጃ የምንመገበው የምግብ አይነት የመለወጥ አቅጣጫ ስንከተል ነው የሚሉ ድምጾች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጎልተው እየተሰሙ ነው።
በእርግጥ ሥጋ ከሚያስገኙልን የምርት ሂደቶች መካከል የተወሰኑትን የጾም ምግብም ብንጠቀም የግድ የሚኖሩ ናቸው። ይሁንና ኃይል ፈጂና በካይ የሆኑት የተወሰኑ ክፍለ-ሂደቶች ግን ከሥጋና መሰል የምግብ አይነቶች ጋር የበለጠ የሚያያዙ ናቸው።
ከጾም ምግብ ጋር ወደፊት
የዓለም ሕዝብ የሚመገበው ምግብ አይነት ለውጥ ቢያሳይ የሚሰጠው ጥቅም ትኩረት እንዲያገኝ ካደረጉት መካከል የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ የወጣው በተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ፕሮግራም ስር የሚገኘው የዓለም አቀፍ አዛላቂ የሀብት አስተዳደር ቡድን ያዘጋጀው ሪፖርት አንዱ ነው። ሪፓርቱ ዓለማችን ከእንስሳት ተዋጽኦ ምግብ ወደ ዕጽዋት ተዋጽኦ ምግብ መቀየር እንዳለባት ይመክራል። ከሪፓርቱ መውጣት አንድ ዓመት ቀደም ብሎ የቀድሞው የእንግሊዝ ሌበር-መራሽ መንግሥት አማካሪ የነበሩትና የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይን ከገንዘብ ስሌት ጋር በማቀናጀት የሚታወቁት ጌታ ኒኮላስ ስተርን ለምድራችን የሚበጀው የዕጽዋት ተዋጽኦ ምግብ ነው ብለው ነበር። በነገራችን ላይ  ጌታ ኒኮላስ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የዛሬ ሦስት ዓመት ለኮፐንሀገን ዝግጅት ሲባል አዲስ አበባ ተደርጎ በነበረ አንድ ስብሰባ ላይ ንግግር ሲያደርጉበአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች ዙሪያ ያስተማሩኝ ጥሩ ወዳጄ’  በማለት ያሞካሽዋቸውና በወቅቱ አፍሪካ የጋራ አቋም ለመያዝ  ታደርገው ከነበረው ጥረት በስተጀርባ ሆነው ሚና የተጫወቱ ናቸው። የተመዱ የአየር ንብረት ለውጥ የበይነ መንግሥታት የሳይንቲስቶች ስብስብ መሪ የሆኑት ራጀንድራ ፓቹዋሪም ስለ ካርቦን ልቀት ቅነሳ ሲባል በሳምንት አንድ ቀን ሥጋ-አልባ ምግብ በመብላት አስተዋጽኦ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበው ነበር።
የሥጋና የወተት ውጤቶች ግብርና ከዓለማችን የንጹህ ውሃ ፍጆታ ሰባ በመቶውን ይወስዳል። ከአጠቃላይ የዓለም የመሬት አጠቃቀም አኳያም ሲታይ ሰላሳ ስምንት በመቶውን ይሄው ዘርፍ የሚወስደው ሲሆን አስራ ዘጠኝ በመቶ የሚሆነውን የዓለማችን የአየር ንብረት ለዋጭ ጋዞች ልቀት ድርሻም ከነዚህ የፍስክ ምግቦች አቅርቦት ጋር የሚያያዝ ነው። 
የተመዱ አካል ምክር የምግብ ፍጆታን ወደተመጠነ ደረጃ ማውረድና እንደዛም ሆኖ የፍስክ ምግብን በተቻለ መጠን ማስወገድ ለአካባቢ ይጠቅማል የሚል ነው። በአጠቃላይ ሥጋዬን አድክሜ የነፍስ ፍላጎቴን አጎለብታለሁ ብሎ አምኖ የሚጾመው ሰው በዚህ ምድርም የተሰጠውን ምድርን የመጠበቅ (ከአካባቢ ብክለትም ጭምር) ኃላፊነትም ተወጣ ማለት ነው። የጾም ምግብ የመብላት ወይም የመጾም ጥቅም ሥጋና መሰል ምግቦች የሚያስከትሉትን ብክለት ብቻ በማስወገድ ላይ የታጠረ አይደለም (መንፈሳዊነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ) ለከብቶች መኖነት እየዋለ ያለው የዓለም የምግብ ምርትም በረሃብ የሚያልቁትን የተለያዩ አገር ወገኖችን ሕይወት ለመታደግ የራሱን ሚና እንዲጫወት ማድረግም ጭምር እንጂ። ይህ ብቻ አይደለም። ከጾሙ ጋር ተያይዞ የሚመጣው ለሌላው የማካፈል ሥራም በማኅበራዊ አዛላቂነት መነጽርነት ሲታይ ባላቸው ሰዎች ዘንድ የተከማቸውን ሀብት(ምግብን ጨምሮ) ለሌላቸው በመስጠት ማኅበራዊ ፍትህን በማስተካከል ደረጃ የራሱ የሆነ ድርሻ ይወጣል። ከላይ የጠቀስነው የፍትሐ ነገሥቱ የጾም አንቀጽጿሚው የረኃብን ችግር ያውቅ ዘንድ ለተራቡትም ለሚለምኑትም ይራራላቸውየሚለው ትእዛዝ ይህንን የሚያጎላ ነው። ይህ በተግባር ሲገለጽ ጿሚዎች ለቁርስ ያወጡት የነበረውን ገንዘብ በተደራጀ መልኩ ሰብስበው ለተለያዩ ወገኖች መርጃ እንዲሆን ማድረግን ያካትታል። ማኅበረ ቅዱሳን ይህን እንደሚያደርግ አውቃለሁ። ወዶ ፈቅዶ የሚጾመው ክፍል በማጣትና በኑሮ ውድነት ሳይፈልጉየሚጾሙትወገኖች የዕለት ጉርስና የዓመት ልብስ እንዲያገኙ ቢያደርግ የጾሙ አካባቢያዊና ማኅበራዊ አዛላቂነት የተጨበጠ ይሆናል። በአጭሩየትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪውየሚለው አባባል በምግብ-ነክ የአካባቢ ተጽእኖ ላይ አይሰራም።የት ፈጨሺው?’ የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት።
=======
አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org


1 comment:

Anonymous said...

አንዳንዴ ነገሮችን እንዲህ እንዳንተ ፈትፈት አድርጎ የሚያቀርብ ሲገኝ እንዴት የልብ ያደርሳል::
አሁን በአመት ውስጥ ያሉትን ጾሞች ለምጾም የሚያስችለኝን በቂ ምክኒያቶች አሳይተኽኛል::ምስጋና እያቀረብኩ ከጾም ጋር ወድፊት...