Sunday, August 14, 2011

የምር አቀንቃኞች


(ጌታቸው አሰፋ) በወቅቱ እሠራበት የነበረው የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ገና መጀመሩ ነበር - እንደ ዩኒቨርስቲ። ከመደበኛ ሥራዬ ውጪ የአካባቢና የተፈጥሮ ሀብት ጉዳይ የሚገደን ሰዎች ተሰባስበን ክልላዊ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ በማስጨበጥ ሥራዎች ላይ የሚያተኩር መንግሥታዊ ያልሆነ ማኅበር አቋቁመን መንቀሳቀስ ጀመርን።እኔ የማኅበሩ ጸሐፊ፤ በግብርና ቢሮ የሚሠራ ሌላ ባለሙያ ደግሞ ሰብሳቢ ሆነን ነበር።  በወቅቱ የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ለበርካታ ዓመታት በፓሊቴክኒክነት የቆየውን ግቢ ወደ ቴክኖሎጂ ፋኩልቲ ደረጃ ለማሳደግ አስፈላጊ የነበሩ ግንባታዎችን በስፋት እያጧጧፈ ነበር። ግቢው ቀድመውኑም ቢሆን በጣም ሰፊ ነበርና የቦታ ጥበት አልነበረውም። ይሁንና እስካሁን ድረስ በማይገባኝ ምክንያት ነባር ዛፎች እየተቆረጡ  የነበሩበት ቦታ ላይ ህንጻዎች መተካት ጀመሩ። አንዳንዶቹ ዛፎች የማስፋፋቱ ሥራ ከመጀመሩ ከሠላሳ አራት ዓመታት በፊት ከተቋቋመው ፓሊቴክኒክ ግቢ በላይ እድሜ-ጠገብ ነበሩ።
የትምህርት ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት ከሚገኝበት አዲስ አበባ ሆነው የማስፋፋቱን ሥራ ንድፍ የነደፉት ባለሙያዎች በአካል ሄደው እነዛን ዛፎች ስላለማየታቸው እንጂ ስለማየታቸው በወቅቱ መረጃ አልነበረኝም - ዛሬም የለኝም። በኛ አገር የመረጃ ሥራ ደግሞ የተወሰኑ ዛፎች ቀርቶ ትልልቅና እድሜ-ጠገብ ትክሎችን መዝግቦ የመያዙ ልምድ ባለመበልጸጉ በአካል በቦታው ተገኝተው፤ ስለ ጉዳዩ ከሚያውቁ ሰዎች ጋር ተማክረው ንድፉንም ሆነ ተከታይ የዲዛይንና የግንባታ ሥራዎችን ማስፈጸም ያስፈልጋቸው ነበር የሚል እምነት ነበረኝ። የሆነው ሆኖ እኛ ቢያንስ “ለምን ይሄ ይሆናል?” ብለን በማኅበራችን ስም ለምን አንጠይቅም በማለት ወደ ማኅበራችን ሰብሳቢ ደወልኩ። ዝም ከምንል ቢያንስ ተማሪዎችን አስተባብረን የግንባታ ሥራው ሳይገፋበት እንደገና እንዲታይ  እንዲደረግ፤ እስከዛ ድረስ ደግሞ የቆዩ ዛፎች ያሉበት አካባቢ የተጀመረው ግንባታ እንዲቆም ድምጻችንን እናሰማ የሚል ነበር - በቀጭኑ ሽቦ ያስተላለፍኳቸው ቃላት መልእክት አሁን እንደ አዲስ ሲቀናበር። ሰብሳቢው ያንን ጥያቄ ማቅረብ ከባድ እንደሆነ  እንዲያዉም ግንባታውን[የማስፋፋት ሥራውን] መቃወም ተደርጎ ሊወሰድብን እንደሚችል ወዘተ ነገረኝ - የመሰለውን። እኔም በዛ መልስ አምኜም ይሁን ተገድቤ - ብቻ  የምችለውን ነገር እንዳደረግኩ ራሴን አሳምኜ ቁጭ አልኩ(ራስን በራስ ማሳመን እንዴት ቀላል ቢሆን ነው ያኔ ለኔ?)። ዛፎችም ተቆረጡ። ፓሊም የባህርዳር ዩኒቨርስቲ የቴክኖሎጂ ፋኩልቲ ሆነ። እኔም የቆዩ ዛፎች በማይረባ ምክንያት ባስቆረጥኩበት ግቢ ውስጥ ስለ አካባቢ ጥበቃ አስተማርኩ - ምስኪን።
ስዊድን - የምሮቹ 
ለማኅበራችን ሰብሳቢ ስልክ በደወልኩ ዓመት ከምናምን ወራት በኋላ በአካባቢ ምህንድስናና በዘላቂ መሠረተ ልማት የትምህርት መስክ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ ሆኜ የስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም እምብርት ላይ አብሮውኝ ከሚማሩት ጋር ቆሜአለሁ።  የመስክ ጎብኝት በስነ-ምድር ፕሮፌሰራችን ቦ ኦሎፍሶን መሪነት።  ስቶክሆልም የተበሳሳው የሰዊዘርላንድ አይብ ነች እስክትባል ድረስ በምድር የውስጥ ለውስጥ ፍልፍል የባቡር መንገዶች የተሸነሸነች ከተማ ነች። ሦስቱ ዋና ዋና ፍልፍል የባቡር መንገዶች ከየአቅጣጫው መጥተው ሲያበቁ መሐል ከተማ ላይ የየራሳቸውን መስመር ጠብቀው ላይና ታች ሆነው ስለሚተላለፉ ወደታች ጥልቅ ሆኖ የተፈለፈለው አለታማው ምድር በጣም ረጅምና ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ  ከምድር በላይ እንጂ በታች ያለ አይመስልም። በዛ ላይ ከባለ ሦስቱ ድርብርብ  የምድር ውስጥ የባቡር ፍልፍል መስመር አናት ላይ ትልልቅ ሕንጻዎች ተሠርተውበታል። አሁን ያለነው ከዚሁ መሐል ከተማ ከሚገኘው የውስጠ-ምድር ባቡር ጣቢያ ከአንድ ኪሎሜትር ያነሰ ርቀት ላይ ከሚገኝ ንጉሣዊ ፓርክ ከተባለው ሌላ ጣቢያ አጠገብ ነው። ፕሮፌሰሩ አይኖቻችንን ወደ አንድ ዛፍ እንድናቀና እያመላከቱ ጠየቁን። ከወዳታችኛው የዛፉ ክፍል አካባቢ የቆየ ግዝግዝ ቀለበት ግልጽ ሆኖ ይታያል[ፎቶ -ግዝግዝ ]። 



የግዝግዙን ታሪክ አወሩልን። በ1960ቹ የባቡር ጣቢያውን ከመገንባት ጋር በተያያዘ በአካባቢው የነበሩ እድሜ-ጠገብ ዛፎችን መቁረጥ ተጀምሮ ነበር። ይሁንና “ሊቆረጡ አይገባም!” ባይ አቀንቃኞችና የከተማዋን መሠረተ-ልማት ለማስፋፋት ሲባል መቆረጣቸው የግድ ነው በሚለው የከተማ አስተዳደር መካከል እሰጥ-አገባ ተጀመረ። ይኸው አሰጥ-አገባ ውጤት አልባ በመሆኑ አቀንቃኞች ወደ ሰፊ ተቃውሞ አመሩና ግንቦት አራትና አምስት 1963 ዓ.ም.  የዛፍ አቃፊዎች ዘመቻ ተደረገ።  ብዙዎች  ራሳቸውን ከዛፎቹ ጋር በሰንሰለት አስረው ዛፎቹን አቅፈው “አናስነካም!” አሉ። የተወሰኑት ዛፎች ላይ ወጥተው “አንወድርም! ስትፈልጉ ቆርጣችሁ ከምትጥሉት ዛፍ ጋር አብራችሁ ጣሉን!” አሉ[ፎቶ -ሰልፉ]። 

ለካስ ፕሮፌሰር ቦ ኦሎፍሶን ከሀያ ስምንት ዓመት በፊት ለመቆረጥ ተገዝግዞ የነበረው ዛፍ ላይ ወጥተው አድረው ነበር። እሳቸውና ሌሎች የዛፍ-ማቀፍ አቀንቃኞች አሁን ግዝግዙ የምናየውን ዛፍ ብቻ ሳይሆን ሌሎች አስራ ሦስት ዛፎችን ከመቆረጥ አትርፈዋል። በነሱም ጥረት የባቡር ጣቢያው መግቢያዎች ከዛፎቹ በስተ ምሥራቅና በስተ ምዕራብ ራቅ ብለው እንዲገነቡ ተደረገ።
ፕሮፌሰሩ ለአንድ ሌሊት እላዩ ላይ ተጣብቀው አድረው ለዋሉት ውለታ ሜዳሊያቸው የሆነውን የዛፍ ግዝግዝ ጠባሳ እያሳዩን በነበረበት ጊዜ በኔ አእምሮ ይመላለስ የነበረው ከመገንደስ፤ ከመቆረጥና ከመነቀል ያላተርፉኳቸው የባህርዳር ዛፎች ጉዳይ ነበር።  የስቶኮሆልሞቹ ዛፎች ዛሬ ድረስ እዛ በቦታቸው በጎብኚዎች የሚጎበኙ ናቸው [ፎቶ -ዛፎቹ ዛሬ]።



 እነዚህን ዛፎች ለመታደግ የተደረገው የሁለት ቀን ዘመቻ 40ኛው ዓመት መታሰቢያ በዚህ ዓመት ከሁለት ወር በፊት በቦታው ተከብሯል።  የ14  ዛፎችን ሕይወት ያስቀጠለው በልሳነ ስዊድን “አልም-ስትሪደን”(የአልም ዛፎች ውጊያ) ተብሎ የሚታወቀው ይህ ዘመቻ በአውሮፓ ለዛፎችና ለደኖች ተቆርቋሪነት እንቅስቃሴ ጅማሮ ተደርገው ከሚወሰዱ ቀደምት ክስተቶች አንዱ ነው።
ካሴታችንን ትንሽ ወደፊት እናጠንጥን። ስዊድን ውስጥ ….ግን ሌላ ቦታ…. ሌላ ጊዜ… 
የብሮታ ደን አራት መቶ የእግር ኳስ ሜዳዎች የሚያክል የስዊድን ሁለተኛ ከተማ የሆነችው ጉተንበርግ አጠገብ የሚገኝ ነው። ቀደም ሲል አንድ ገዳም በባለቤትነት ይዞት ነበር። የተፈጥሮ እቀባዊ እሴቱ ከፍተኛ እንደሆነ  የሚነገርለት የዚህ ደን ሩብ ያህሉን ስፋት የሚሸፍኑት ዛፎች ተቆርጠው ለእንጨት ሥራ እንዲውሉ ተሸጡ - የካቲት 1994 ዓ.ም.።  ይህን በመቃወምና ደኑ ጥበቃ ሥር እንዲውል ለመጠየቅ የ”አረንጓዴ ሰላም” አቀንቃኞች ራሳቸውን ከዛፎቹ ጋር አሰሩ። ፓሊስ አስገድዶ አላቀቃቸው። ሀያ አቀንቃኞች ተያዙ። በተቃውሞው ምክንያት ለጊዜውም ቢሆን የዛፎቹ ቆረጣ ተቋረጠ። መስከረም 5 ቀን 1997 ዓ.ም. የዛፍ ቆረጣው እንደገና ሲጀመር አቀንቃኞች በጠቅላይ ግዛቱ ወደ ሚገኝ ፍርድ ቤት ሄደው የቆረጣ ውሳኔውን መገዳደር ያዙ - መንግሥትን በመክሰስ። ክሱም “የስዊድን መንግሥት የሕዝብ ሀብት የሆኑትን ደኖች ከመቶ ዓመታት በላይ በዝብዟል። በዚህ ብዝበዛ ምክንያት ደግሞ ጥንት ከነበረው የደን ብዝኃ ሕይወት አምስት ፐርሰንት ብቻ እንዲቀር አድርጓል።” የሚል መነሻ የያዘ ነበር (የክሱን መጨረሻ ለማወቅ ያደረግሁት ጥረት አልተሳካም)። 
ስዊድን የቆየ የዛፎችና የደን ጥበቃና እንክብካቤ አቀንቃኞች ልምድና እንቅስቃሴ ያላት አገር በመሆኗ ዛሬ የደን ሽፋኗ ከጠቅላላ ስፋቷ ወደ ግማሽ ገደማ ሲሆን ከአገሪቱ ወደ ውጪ ከሚላኩት ምርቶች በአጠቃላይ የደን ምርቶች አሥራ አምስት ፐርሰንት የሚሆነውን ድርሻ ይይዛሉ። የዛሬ ሰባት ዓመት የነበረውን መረጃ መሠረት ወደ ዘጠና ሺህ አንድ መቶ ሰዎች በደን ልማትና በደን ምርቶች ኢንዱስትሪ ተቀጥረው ይሠሩ ነበር። 
ኢትዮጵያ - የቆጡም የብብቱም
በስዊድን የዛፎችና የደን እንክብካቤ አቀንቃኞች ሚና የጎላ ከሆነ (ከፓሊሲ ቀረጻና አፈጻጸምና ከመሳሰሉት ጋር በመቀናጀት) በአገራችን አቀንቃኞች ሊጫወቱት የሚገባው ሚና ተመናምኖ እጅግ ዝቅተኛ ወደሆነ ደረጃ የወረደው የደን ሀብታችንን ከመታደግ አንጻር ጠቃሚነቱ አሌ የማይባል ነው። ድሆች ስለሆንን ብቻ ሁለመናችንን ገንዘብ ወደሚያስገኙ ነገሮች ብቻ ማዞር የለብንም- እንደ ማኅበረሰብ። ዛሬና ነገ ገንዘብ አስገኝተው ጠንቃቸው ግን ለትውልድ የሚተርፉ  የአካባቢ መጐሳቆልንና የተፈጥሮ ሀብት መመናመንን የሚያስከትሉ የልማት አቅጣጫዎችን በአግባቡ መፈተሽ ያሻል። መንግሥት ሲባል በተፈጥሮው የግዙፍና አርበ-ሰፊ መዋቅሮች ቋጠሮ በመሆኑ አንድ ቦታ፤አንድ ወቅትና አንድ አቅጣጫ ላይ አፍጥጦ ሊቀር ይችላል። ከሌላ አቅጣጫ መታየት የሚገባቸውና፤ ከሌላ ቦታና ከመጪው ጊዜ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በመንግሥት የቢሮክራሲ ወንበሮች መሐል እንዳይቀረቀሩና የቆጡም የብብቱም እንዳይወድቅ ለማድረግ አንድ ወይም ከአንድ በላይ የአካባቢና የተፈጥሮ ሀብት ጉዳዮችን ይዘው የሚጠቁሙ፤ የሚያሳዩ፤ የሚያሰሙና የሚሞግቱ አቀንቃኞች ያስፈልጉናል። ቀጥተኛ፤ለጉዳዩ የሚመጥኑ፤ ከገንቢ ውጤት ላይ የሚያደርሱና ሊፈጸም በታለመው ጉዳይ ልክ የተሰፉ አካሄዶችን የሚጠቀሙ አቀንቃኞች ለተገቢ ፓሊሲዎች ቀረጻና ለአፈጻጸማቸው(በተለይ) ወሳኝ ናቸው።  የአካባቢ ጉዳይ ፓርቲ-ዘለል፤ትውልድ-ተሻጋሪ  ጉዳይ ነው። የፓለቲካ የተጽእኖ አድማስ (በጊዜም በሥፍራም) ደግሞ ውሱን ነው።በአንድ ቦታና በሆነ ወቅት የሚገኝ የተፈጥሮ ሀብት በአግባብ መልማትም ይሁን መመናመን ግን ከቦታው ውጪና ከዛን ወቅት በላይ አዎንታዊም ይሁን አሉታዊ ግብረ-መልስ አለው። ለዚህም ነው የአካባቢና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ ጉዳይ የተለየ ፍላጎት ከማስፈጸም ጋር አጣምረው በሚሄዱ ክፍሎች ሳይሆን ከጉዳዩ ጋር በቆረቡና በጉዳዩ በተካኑ አቀንቃኞች መራመድ ያለበት።
በመንግሥት በኩል መረጃ-ጠገብ ለሆኑ ለእንደዚህ አይነት አቀንቃኞች እንቅስቃሴ ሰሚ ጆሮንና ተመልካች አይንን ባለመንፈግ የሚገለጽ ተገቢ ትኩረት በመስጠት ጥያቄዎችን የሚያቀርቡበት አገባብ፤ ካቀረቡም በኋላ ተመጣጣኝ ምላሽ ሳይዘገይ እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታን መፍጠር ይኖርበታል።  
====================
ሐምሌ  30  ቀን 2003 ዓ.ም. አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

3 comments:

Zereality said...

arife 'yegna-ena-yenesu' analysis....' የአካባቢ ጉዳይ ፓርቲ-ዘለል፤ትውልድ-ተሻጋሪ ጉዳይ ነው። የፓለቲካ የተጽእኖ አድማስ (በጊዜም በሥፍራም) ደግሞ ውሱን ነው።በአንድ ቦታና በሆነ ወቅት የሚገኝ የተፈጥሮ ሀብት በአግባብ መልማትም ይሁን መመናመን ግን ከቦታው ውጪና ከዛን ወቅት በላይ አዎንታዊም ይሁን አሉታዊ ግብረ-መልስ አለው።'....

Zereality said...

it would have been more better if you raised some of those benefits of forestry for Swedish economy or thier welfare system or anything else(means translated in to emibela ena emiteta)....beza beza newe yemigebane(meriwechachene yemigebachewe) beye newe enji....i got sense the whole point.....

Elias said...

Environmental assessment is still not implemented in many construction projects that is the case in many of the big projects. I believe one person can bring change, no need to surrender as the Swedish people have done. Thanks for sharing us your experience