Friday, December 21, 2012

ልቀቁልን እንጂ አትልቀቁብን - ዶሃ


(ጌታቸው አሰፋ፤ ኅዳር 29 ቀን  2005 ዓ.ም.) የአየር ንብረት ለውጥን እንደ ገዳይ በሽታ ብንቆጥረው ኖሮ ዓለም መታከምና መዳን አለባት የሚለው ላይ እንስማማና ወደ ተግባር እንሄድ ነበር። በዚህ እሳቤ የካርበን ልቀት በሽታ አምጪ ታህዋስያን ልቀት ተደርጎ ከታሰበ ልቀቱ ሲሆን ፈጽሞ እንዳይኖር ካልሆነም በእጅጉ እንዲቀንስ እናደርግ ነበር። ችግሩ ግን በነባራዊው ዓለም የአየር ንብረት ለዋጭ ጋዞች ልቀት ገንዘብ ለማስገኘት በሚደረግ ሂደት የጎንዮሽ ተጽእኖ ሆኖ መከሰቱ ነው። ሌላው ችግር ለቃቂዎች አቅም ያላቸው፤ የሚታመሙት ደግሞ አቅመ አናሳዎች። ቀመሩ ውስጥ ገንዘብና ኢኮኖሚ ባይኖሩበት ኖሮ ይህ ሁሉ የጉባኤ ጋጋታም አያስፈልግም ነበር። ይህ አልሆነምና ስብሰባም ጉባኤም አለ። እነሆ የዶሃው ጉባኤም እንደቀጠለ ነው (ይህ ጽሁፍ እስከተጻፈበት ጊዜ ድረስ)።

በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የነዳጅ ዘይትን ጨምሮ ቅሪታዊ ነዳጅ ሀብታቸውን በመሸጥና ጥቅም ላይ በማዋል ከሚታወቁት የመካከለኛ ምስራቅ አገሮች አንዷ የሆነቸው ካታር(ኳታር) ቀዘቀዝ ያለና በጣት ለመቆጠር የማይበቁ የአገር መሪዎች የሚገኙበትን ጉባኤ ሁለተኛው ሳምንት ተያይዛዋለች። መካከለኛው ምስራቅ አስራ ሰባት አገሮችን ሲያጠቃልል ወደ ሶስት መቶ ሰማንያ ሚልዮን የሚሆን ህዝብ ይኖርበታል (ከአሜሪካ ህዝብ ብዛት በሰባ ሦስት ሚልዮን የሚበልጥ)። እነዚህ አገሮች በህዝብ ብዛት ከትልቅ ወደ ትንሽ በቅደም ተከተል ሲቀመጡ ግብጽ፤ ኢራን፤ ቱርክ፤ ኢራቅ፤ሳውዲ አረቢያ፤ የመን፤ሶሪያ፤ ዩናይትድ አረብ ኢሚሬትስ፤ እስራኤል፤ዮርዳኖስ፤ሊባኖስ፤ ፍልስጤም(ገና አገር ባይሆኑም)፤ኦማን፤ኵዌት፤ካታር፤ባህሬንና ሳይፕረስ ናቸው።
የዘንድሮውን የዓለም የአየር ንብረት ጉባኤ አሰተናጋጅ ከተማ ዶሃ እንግዲህ ሁለት ሚልዮን ህዝብ ያላት ካታር ትልቋ ከተማ ነች። ካታር ዓለምን በሁለት መንገድ ትመራለች - በነፍስ ወከፍ ገቢና በነፍስ ወከፍ የካርቦን ልቀት መጠን ከፍተኛነት። ሁለቱንም መሪነት ያገኘችው ባላት የነዳጅ ዘይትና የተፈጥሮ ነዳጅ ሀብት ምክንያት ነው።
የዶሃው ጉባኤ የመጀመሪያው ሳምንት በኤክስፐርቶች ሲደረጉ የነበሩ ስብሰባዎች የበዙበት ነበር። ከዛሬ ማክሰኞ ጀምሮ ደግሞ በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት - በተለይ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስትሮችና ባለሥልጣናት በዋናነት የሚሳተፉበት ድርድር ነው። ቀሪው የጉባኤ ጊዜ በሁለት ዋና ዋና አወዛጋቢ ጉዳዮች ላይ ያነጣጥራል-  የኪዮቶ ፕሮቶኮል ቀጣይ እጣ ፈንታ (‘አትልቀቁብን’) እና ለታዳጊ አገሮች ቃል ስለተገባ ገንዘብ ጉዳይ (‘ልቀቁልን’)።  
አትልቀቁብን
ኪዮቶ ሁለት ከጃንዋሪ 1 2013 ጀምሮ የሚተገበር የኪዮቶ አንድ ቅጥያ ነው። ሂደቱም እስከ 2020 ኪዮቶን ማራዘም፤ ከዛም አስቀድሞ የተቀረጸና በ2015 የሚጸድቅ ዓለም አቀፍ ስምምነት ከ2020 ጀምሮ በስራ ላይ ማዋልን ይጨምራል። ዶሃ ላይ ብቅ ያለ ሌላም ጉዳይ አለ - ወደ አስራ ሦስት ቢልዮን ቶን ካርበን ዳይኦክሳይድ የሚደርስ ከመጀመሪያው ኪዮቶ ዙር የተረፈ የልቀት ፈቃድ መጠን። ይህ መጠን በኪዮቶ ፕሮቶኮል መሰረት አገሮች ከተሰጣቸው የልቀት መጠን ፈቃድ(ለአንዳንዶች መቀነስን ለሌሎች ደግሞ መጨመርን) አኳያ ጥቅም ላይ ያልዋለ የልቀት ፈቃድን የሚመለከት ነው። እነሆ አሁን የመጀመሪያው ኪዮቶ  ፕሮቶኮል በዚህ ወር መጨረሻ ሲያበቃና ወደ ሁለተኛው ዙር ሲገባ ጥቅም ላይ ያልዋለው የልቀት መጠን ወደ ሁለተኛው ዙር ተላልፎ የመልቀቅ መብታችን ይከበር የሚሉ እንደነ ፖላንድና ሩሲያ ያሉ አገሮች አሉ። ይህ  አቋም በታዳጊ አገሮች ዘንድ ምንም አይነት ተቀባይነት የለውም።
ኪዮቶ የበለጸጉ አገሮች ከፍተኛ መጠን ያለው ታሪካዊ ልቀትንና የታዳጊ አገሮች (ቻይና ህንድና ብራዚልን ጨምሮ) የነበራቸው ‘እዚህ ግባ የማይባል’ ልቀትን ያገናዘበ  ‘የጋራ ግን ተለይቶ የተመጠነ ሃላፊነት’ በሚል መርህ ላይ የተመሰረተ ነበር።  የኪዮቶ ሁለትም ሆነ የረጅም ጊዜው ስምምነት (ከ2020 በኋላ የሚኖረው ስምምነት) አሁንም እንደ ቀደመው  ‘የጋራ ግን ተለይቶ የተመጠነ ሃላፊነት’ በሚል መርህ ላይ እንዲመሰረት ነው የቻይናም የሌሎች ታዳጊ አገሮችም ፍላጎት። እንዲያውም መርሁን በማሻሻል ‘የጋራ ግን ተለይቶ የተመጠነ ሃላፊነትና ከተናጠል አቅም ጋር የሚሄድ’ እንዲባል ነው የቻይና አቋም።
ከመጀመሪያው ዙር ኪዮቶ አንድ ፌርማታ ሳትሄድ  ‘ወራጅ አለ!’ ብላ የወጣችው አሜሪካ ማንኛውም ስምምነት ውስጥ ይህ መርህ እንዲኖር አትፈልግም። እንዳዛ አይነት መርህ ላይ የሚመሰረት ማንኛውንም የልቀት ቅነሳ ስምምነት አልነካውም ባይ ነች። ‘በገሃዱ ዓለም ላይ ያለው እውነታ ላይ ተመስርቶ ለሚመለከት ክፍል እነቻይናም የብክለት መጠናቸው በእጅጉ ስለጨመረ ያንን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የልቀት ቅነሳው የሁሉም የጋራና እኩል ኃላፊነት መሆን አለበት‘ የሚለው የአሜሪካ አቋም በቻይና ዘንድ በ’ልማታዊ አይኗ’ ላይ የመምጣት ያህል ተደርጎ ተወስዶ በዚህ ሳምንት አሜሪካ ላይ ያነጣጠሩ ጠንካራ መልእክቶችን እያስተላለፈች ነው።
ልቀቁልን
ይህ ጉዳይ በዶሃው ጉባኤ በዋናነት የታዳጊ አገሮች አጀንዳ ነው። ካደጉት አገሮች የተለያዩ ምንጮች ተሰብስቦ ለአየር ንብረት ለውጥ ማስተሰሪያና ማጣጣሚያ የሚበጅ የቴክኖሎጂ ሽግግር (የታዳሽ ኃይልና የመሳሰሉት ) በታዳጊ አገሮች እንዲተገበር የሚያግዝ ገንዘብ ነው። ባለፈው ሳምንት ጽሑፍ እንደተገለጸው ጠንካራና ወደ ተግባር የሚሸጋገር የገንዘብ ፍሰት ይኖራል ብሎ አፍን ሞልቶ ለመናገር አይቻልም። እስካሁን ያለው የዶሃው ጉባኤ ሂደት ስንመለከትም።  የበለጸጉት አገሮች የበካይ ጋዝ ልቀትን ላለመቀነስ እና የገንዘብ ድጋፍ ልቀትን ደግሞ ላለመጨመር ድርቅ ብለዋል።
እንደዛም ሆኖ አንዳንድ አገሮች ታዳጊ አገሮችን አንረሳም እያሉ ነው። ለምሳሌ ታላቋ ብሪታንያ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ግንኙነት ላላቸውና በታዳጊ አገሮች ላይ ለሚተገበሩ ፕሮጄክቶች የሚሆን በአጠቃላይ ወደ ሃምሳ ስምንት ቢልዮን ብር የሚሆን ገንዘብ እለቃለሁ ብላለች - በዚህ ሳምንት በዶሃ።  ቻይናም እንዲሁ በሦስት ዓመታት ውስጥ የሚከፈል ወደ ሦስት ነጥብ ስድስት ቢልዮን የሚጠጋ ብር ለታዳጊ አገሮች (በተለይ ለአፍሪካና ለሌሎች ደሴታማ አገሮች) ‘እነሆ በረከት!’ ብላለች።
ታዳጊዎቹ ላደጉት አገሮች በካይ ጋዛችሁን አትልቀቁብን ገንዘቡ ግን ልቀቁልን ከሚለው ጥሪያቸው በተጨማሪ
በቀሪዎቹ የጉባኤው ቀናት መሆን አለባቸው ተብለው ከሚጠበቁት ጉዳዮች መካከል ከአሁን በፊት አስፈላጊነታቸው ላይ በሌሎች ጉባኤያት ስምምነት ለተደረሰባቸው አዳዲስ ዓለም አቀፍ ተቋማት ‘ጥርስ’ መስጠት ነው። ከነዚህ መካከል የአረንጓዴ የአየር ንብረት ፈንድ አንዱ ሲሆን የአየር ንብረት የቴክኖጂ ማዕከልና ትስስር ሌላው ነው።
አዲስ ጉዳይ ለህትመት ስትበቃ የዶሃው ጉባኤ ውጤት ይታወቅ ይሆናል። ይህ ጽሑፍ ግን ቀደም ብሎ መጻፍ ስላለበት ያኔ ያረጀ ሊሆን ይችላል።
አምና በደርባን የተደረሰው ስምምነት በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የሚደረገውን የተመድ የድርድር ሂደትን ከመበታተን በማዳን ላይ ብቻ የተወሰነ ነበር ማለት ይቻላል። የዶሃም እጣ ፈንታ እንደዛ ባይሆን ይበጃል። ወደ ዶሃ ከሄዱት የዓለም ጥቂት መሪዎች መካከል የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አቶ መለስን በመተካት የአፍሪካ የመራህያነ መንግሥትና ርዕሳነ ብሔር የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚቴ አስተባባሪ በመሆናቸው  ሰኞ ዕለት በዶሃ በተደረገው የአፍሪካ ተደራዳሪዎችና ልኡካን ስብሰባ ላይ በጉባኤው የሚኖረው የአፍሪካ አቋም በተመለከተ ባደረጉት ንግግር ስለ ገንዘብ ድጋፍ፤ ስለኪዮቶ ቀጣይነት እንዲሁም ከ2020 በኋላ መኖር ስለሚገባው ስምምነት አንስተዋል። እስከዚህ ዓመት መጨረሻ መሰጠት ስለነበረበት የ30 ቢልዮን ዶላርና በ2020 ወደ100 ቢልዮን ማደግ ስለሚኖርበት ዓመታዊ ድጋፍ በተመለከተ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ በየዓመቱ የበለጸጉት አገሮች የሚያዋጡት መጠን አፍሪካ መከታተል አለባት ብለዋል። በአቶ ኃይለማርያም የተንጸባረቀው ሌላኛው የአፍሪካ አቋም የዓለም የከባቢ አየር ሙቀት ጭማሪ ጣሪያ በያዝነው ክፍለ ዘመን ማብቂያ 1.5oC መሆን አለበት የሚለው ነው። ይህ ጭማሪ ከኢንዱስትሪ አብዮት በፊት ከነበረው የከባቢ አየር ሙቀት ጋር ሲነጻጸር ማለት ነው። በበለጸጉት አገሮች በኩል ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ሊመጡ የሚችሉ መጠነ ሰፊና አይነት ብዙ ጥፋቶች እንዳይከሰቱ ለማድረግ ቀይ መስመር ተደርጎ እየተወሰደ ያለው የሙቀት ጭማሪው 2oC በላይ እንዳይሆን ማድረግ የሚል ነው።
የደርባኑ ጉባኤ ሁሉን አቀፍ አስገዳጅ የቅነሳ ስምምነትን ወደ 2020 እንዲገፋ በማድረጉ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረቱት የቅነሳ ቃል ኪዳኖች ሲሰሉ የከባቢ አየር ሙቀት ጭማሪ ከ1.5oCም ከ2oC ም በልጦ ከ3-4 ዲግሪ ሊደርስ እንደሚችል ነው የሚያሳዩት።  ሳምንት የዶሃን ውጤት እንገመግማለን። ደሞ ለመገምገም!
 =======
አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: