Friday, December 21, 2012

ለመስማማት መስማማት?


(ጌታቸው አሰፋ፤ ታኅሣሥ 6 ቀን  2005 ዓ.ም.)  የዶሃው የአየር ንብረት ጉባኤ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ተጠናቋል። በጉባኤው ላይ ተስፋ አልነበረኝም። ከተጠናቀቀ በኋላም የሚያስደስት ነገር አላገኘሁበትም። ውሳኔዎች ግን ተላልፈዋል - ጥርስ ይኑራቸው አይኑራቸው በጊዜ የምናያቸው። ከውሳኔዎቹ ጥቂት የማይባሉት ከአሁን በፊት በነበሩት ጉባኤያትም የተላለፉ ነበሩ። ስላልተገበሩ ግን አሁንም ‘እናረጋግጣለን’ እና ‘እናጠናክራለን’ ወዘተ የሚል ተጨምሮባቸው ተመልሰው መጥተዋል።  እስቲ የውሳኔውን ዋና ይዘት እንየው።

የመጀመሪያው ዙር ህይወቱ ሊያበቃ ከሦስት ሳምንታት ያልበለጠ እድሜ የቀረው የኪዮቶ ፕሮቶኮል ከ’መሞት’ ተርፎ - ከአዲሱ የአውሮፓዊያን ዓመት ጀምሮ ለስምንት ዓመታት እንዲቀጥል ተደርጓል። የዶሃውን ጨምሮ እስካሁን የተደረጉ 18 ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ድርድሮችና ጉባኤያት የሚያጠነጥኑት በዚሁ በኪዮቶ ፕሮቶኮል ዙሪያ ነበር። ከአሁን በፊት እንዳየነው የኪዮቶ ፕሮቶኮል ባለ 28 አንቀጽና 2 አባሪዎች ስምምነት ሲሆን ጃፓን በሚገኘው የኪዮቶ ከተማ ታህሳስ 2 1990 ዓ.ም. የጸደቀ ነበር። ስምምነቱ ላደጉት አገሮች  አሳሪ የልቀት ቅነሳ/ገደብ ይዞ ነበር። በፕሮቶኮሉ የተካተቱት አየር ንብረት ለዋጭ ጋዞች ከኃይል ማመንጫዎች፤ ከመጓጓዣ አገልግሎት፤ከከባድ ኢንዱስትሪዎችና ከግብርና ዘርፍ ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ ናቸው። እነዚህ ዘርፎች ደግሞ በአንድ አገር የምጣኔ ሀብት እድገት ላይ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ።  በዚህ ምክንያት የልቀት መጠን ቅነሳ ቢያንስ በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ ምጣኔ ሀብት እድገት ላይ ትርጉም ያለው ተጽእኖ  ይፈጥራል አይፈጥርም በሚል የሚነሳ ክርክር አለ። ዘርፈ ብዙ አቅም በሌላቸው አገሮች ላይ የሚኖረው ተጽእኖ ግን ግልጽ ነው። ይህ አንድምታ ከስራ እድልና አጥነት ጋር ቀጥተኛ ዝምድና ስላለው በስልጣን ላይ ላሉ ፖለቲከኞች በመራጭ ዘንድ እንዲኖራቸው ለሚፈልጉትና ለሚጠብቁት ተቀባይነት አሉታዊ ትርጉም ስለሚሰጥ ፕሮቶኮሉ በመጀመሪያው ዙር ሕይወቱ መልካም ዘመን አላሰለፈም።  የኪዮቶ ፕሮቶኮል የልቀት ቅነሳ ወይም ገደብ የሚጥለው ‘ቅጥያ 1’ ተብለው በሚጠሩት አገሮች ላይ ነው ። የ’ቅጥያ 1’ አገሮች ዝርዝር ወደ 40 የሚደርስ ሲሆን የአውሮፓ አገሮች፤ አሜሪካ፤ካናዳ፤አውስትራልያንና ራሺያን ይጨምራል። ቅጥያ 2 ተብለው የተዘረዘሩት አገሮች ደግሞ በማደግ ላይ ላሉ አገሮች የፋይናንስ ድጋፍና የቴክኖሎጂ ሽግግር የማድረግ ኃላፊነት የተሸከሙ ሲሆን ወደ 23 አገሮችን ያቅፋል። ከቅጥያ 1 ውጪ ያሉ አገሮች አገራችንን ጨምሮ እነቻይና ፤ብራዚል፤ ሕንድና ደቡብ አፍሪካ የሚገኙበት ሲሆን የኪዮቶ ፕሮቶኮል ያጸደቁ፤ የተቀበሉና የፈረሙ ናቸው። ይሁን እንጂ እስካሁን ባለው ሁኔታ የልቀት ቅነሳም ይሁን ገደብ አልተጣለባቸውም። የኪዮቶ ፕሮቶኮል አንቀጽ 23 በ1990 እ.አ.አ. ከነበረው የልቀት መጠን ቢያንስ 55 ፕርሰንቱን የሚሸፍኑ የቅጥያ አንድ አገሮችን ጨምሮ ቢያንስ በ55 አገሮች ከጸደቀ በኋላ በ90ኛው ቀን በሥራ ላይ መዋል እንዳለበት ይገልጻል።  በነገራችን ላይ የልቀት መጥኑም የሚሰላው ለቅጥያ አንድ አገሮች እንጂ ለመላው ዓለም አይደለም።  በዚህ አንቀጽ መሰረት ራሺያ በየካቲት 9 ቀን 1997 ዓ.ም. ስታጸድቀው  ፕሮቶኮሉ ወደ ሥራ ገብቷል። አሜሪካ ፕሮቶኮሉ ለፊርማ ክፍት በሆነ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ብትፈርምበትም ወደ አገሪቱ ሕግ አውጪ አካል ወስዳ ማጸደቅ በሚጠበቅባት ጊዜ የቢል ክሊንተን የሥልጣን ዘመን አብቅቶ የአየር ንብረት ለዋጭ ጋዞች ዋና ምንጭ በሆነው የነዳጅ ዘይት ዘርፍ ባለሀብቶች የሚደገፉትና የዘርፉን ጥቅም አስጠባቂ የሆኑት ጆርጅ ቡሽ ስልጣን የወጡበት ወቅት በመምጣቱ የኪዮቶ ፕሮቶኮል በአሜሪካ ሳይጸድቅ ቀረ።
ከ1990 እ.አ.አ. ልቀታቸው ጋር ሲነጻጸር ከ2008-2012 እ.አ.አ. ያለው ዓመታዊ የልቀት ቅነሳ መጠን የአውሮፓ ህብረት - በ8 ፐርሰንት፤ አሜሪካ - በ7 ፐርሰንት ፤ ካናዳ፤ ፖላንድ፤ ሀንጋሪና ጃፓን -በ6 ፐርሰንት  ሲሆኑ   ክሮሺያ ደግሞ በ5 ፐርሰንት ናቸው።  የልቀታቸው ልዩነት ዜሮ እንዲሆን የሚጠበቅባቸው  ኒውዝላንድ፤ ራሺያና፤ ዩክሬን ናቸው። በገደብ መጨመር የሚችሉት ደግሞ በ8 ፐርሰንት አውስትራልያ፤በ1 ፐርሰንት ኖርዌይና በ10 ፐርሰንት አይስላንድ ናቸው። ይህ ስሌት ታሪካዊ ልቀታቸውን መነሻ ያደረገ ነው። የአውሮፓ ህብረት በጋራ የተሰጠውን 8 ፐርሰንት የመቀነስ ኢላማ ለአባል አገሮቹ ያከፋፈለ ሲሆን የተወሰኑት አገሮች እንዲጨምሩ የተወሰኑት እንዲቀንሱ ሆኖ ተሰጥቶዋቸዋል። ለምሳሌ በስሌቱ መሰረት ስዊድን በ4 ፐርሰንት እንድትጨምር ሲፈቀድላት ጀርመን ደግሞ በ21 ፐርሰንት እንድትቀንስ ትገደድ ነበር።
በያዝነው ዲሴምበር ወር መጨረሻ ላይ የፕሮቶኮሉ የሥራ ጊዜ ስለሚያበቃ በሌላ ስምምነት መተካት ይኖርበታል ተብሎ ላለፉት ዓመታት ጉባኤ በጉባኤ ሲደረግ ነበር። በተዳከመ መልኩም ቢሆን ‘ዳግም ሕይወት ይኑረው’ የሚለውንና ‘በነበር አይቀር’ የሚለው ውሳኔ በዶሃውን ጉባኤ የተወሰነውም ለዚህ ነው።
አገሮች የልቀት ቅነሳ ወይም ገደብ ኢላማቸውን ለማሳካት በዋናነት ብሔራዊ መፍትሔዎችን ያዘሉ መርሐግብሮችን መቅረጽ ቢጠበቅባቸውም የኪዮቶ ፕሮቶኮል ሦስት ተጨማሪ ስልቶችን ይፈቅዳል። አንደኛው የልቀት ንግድ የሚባለው ነው። የልቀት ንግድ ማለት ልቀት ተፈቅዶላቸው ግን የተፈቀደላቸውን መጠን መጠቀም የማያስፈልጋቸው አገሮች፤ ከተፈቀደላቸው ጣራ በላይ ልቀት ላለባቸው ሌሎች አገሮች መሸጥ የሚችሉበት መንገድ ነው። ሁለተኛው የማይበክል የእድገት ክንውንውታ ሲሆን ይህም በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ተቀርጸው የሚተገበሩ ልቀት ቀናሽ ፕሮጆክቶችን ያካትታል።  ለምሳሌ በወላይታ የሚገኘው የሁምቦ ደን ልማት ፕሮጄክት በዚህ ስር የሚጠቀስ ነው። ሦስተኛው የኪዮቶ ፕሮቶኮል ስልት ደግሞ የጋራ ትግበራ የሚባለው ነው።  አንድ የልቀት ቅነሳ ወይም ገደብ ያለበት አገር ሌላ ቅነሳ ወይም ገደብ ያለበት አገር ሄዶ የቅነሳ ፕሮጄክት እንዲፈጽም የሚያስችለው መንገድ ነው። ተቀባይ አገር የውጪ ኢንቨስትመንትና ቴክኖሎጂ በማግኘቱ ሲጠቀም ፈጻሚ አገር ደግሞ ፕሮጄክቱ የሚያስመዘግበው የልቀት ቅነሳ መጠን ለራሱ ያደርጋል ማለት ነው። በሦስቱም መንገዶች ማለትም በልቀት ንግድ፤በማይበክል የእድገት ክንውንውታ እና በጋራ ትግበራ የልቀት ቅነሳ መጠን እንደመደበኛ ሸቀጥ ለገበያ የሚውል ሲሆን እያንዳንዱ የልቀት ቅነሳ መጠን አንድ ቶን ካርቦን ዳይኦክሳይድ ያህል ነው።
በሌላ በኩል በዝቅተኛ የእድገት ደረጃ  ያሉ አገሮች (የእኛን ጨምሮ) የአየር ንብረት ለውጥ በአገራቸው ሊያስከትለው የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችሉ ስራዎችን የሚያካትት ብሔራዊ የማጣጣሚያ መርሐግብር መቅረጽ ይጠበቅባቸዋል። እነዚህ አገሮች ለዚህ መርሐግብር ቀረጻ ይረዳቸው ዘንድ በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ከሚያደርገው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ከቅጥያ ሁለት አገሮች የገንዘብ ድጋፍ ያገኛሉ። የቀረጹትን መርሐ ግብር ለሚመለከተው የተመድ አካል ማስረከብ አለባቸው። የተለያዩ አገሮች ከማጣጣሚያ ስልት በተጨማሪ የልቀት ስርየት ስልትም በመቅረጽና በመተገበር ላይ ናቸው።
ኪዮቶ ፕሮቶኮል ከላይ ከተጠቀሱት ሦስት ስልቶቹ ጋር ለሚቀጥሉት ስምንት ዓመታት ትንፋሽ እንዲያገኝ መደረጉ ለምልክት ያህልም ቢሆን ስምምነት የሚባል ነገር መኖሩ ራሱ በጎ ነውና በጎ ነው።
እፍርታሞቹ አገሮች እነ አሜሪካ፤ ራሺያ ካናዳና ጃፓን ከመጀመሪያው ኪዮቶ ስለወጡ ኪዮቶ ለዳግም ሕይወት ሲበቃ የአውሮፓ አገሮች ብቻ ጉልኮስ የሚሰጡት ህመምተኛ ሆኖ ነው። ይህም የሆነው በኪዮቶ መቃብር ላይ የሚቆም ዓለም አቀፍ አሳሪ የልቀት ቅነሳ ስምምነት ሀውልት ለመቅረጽ ጊዜ ለማግኘት ነው።  ቋሚው ስምምነት እስከ 2015 እ.አ.አ. እንዲጸድቅና  ከ2020 ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል ይደረጋል ተብሏል።
ለአየር ንብረት ለውጥ ማስተሰሪያና ማጣጣሚያ የሚበጅ የቴክኖሎጂ ሽግግር በታዳጊ አገሮች እንዲተገበር የሚያግዘው ገንዘብ በተመለከተ እንግሊዝ፤ ጀርመን፤ ዴንማርክ፤ ፈረንሳይ፤ ስዊድንና የአውሮፓ ኮሚሽን እስከ 2015 እ.አ.አ. ወደ ስድስት ቢልዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ለታዳጊ አገሮች ለመስጠት ቃል ገብተዋል። የአረንጓዴ የአየር ንብረት ፈንድ አካል ስለሆነውና በ2020 ወደ100 ቢልዮን ማደግ ስለሚኖርበት ዓመታዊ ድጋፍ እና የአየር ንብረት የቴክኖጂ ማዕከልና ትስስር መቋቋም ጉዳይም የ’ይጀመር’ ውሳኔ ተሰጥቶበታል - በዶሃ።
አዲስ ውሳኔም ነበር። እስካሁን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በታዳጊ አገሮችና በትንንሽ ደሴታማ አገሮች ለደረሰ ‘ኪሳራና ጉዳት’ ካደጉት አገሮች ካሳ መከፈል አለበት ወደ ሚል ሊያመራ የሚችል ውሳኔ ተላልፏል - አሜሪካ ‘ካሳ’ የሚለውን ባትቃወም ኖሮና ህጋዊ ጉልበት የሌለው ‘ስምምነት’ ብቻ ባይሆን ኖሮ ጥሩ ነበር። ስምምነት ለመስማማት የሚስማማ ለመተግበር ግን የማይስማማ ጉባኤ እስከመቼ? እንጃ! ለማንኛውም በሚቀጥለው ዓመት ዋርሶ ፖላንድ ጉባኤው ይቀጥላል።
 =======
አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: