Tuesday, January 8, 2013

ከጤንነት የሚሻል ሕክምና የለም

(ጌታቸው አሰፋ፤ ታኅሣሥ 20 ቀን  2005 ዓ.ም.)  ዛሬ የምጽፍበት ጉዳይ ከአረንጓዴ ጉዳይ ጋር ምን አገናኘው ለምትሉ አስቀድሜ መልስ ልስጥ። በአካባቢ ጥበቃም ሆነ በኃይል አቅርቦትና ፍጆታ ዙሪያ በአገሪቱ መዋዕለ ንዋይ ፈሶባቸው የሚሰሩ ስራዎች ወጪ ቆጣቢ ሆነው ውጤታማ እንዲሆኑ ካስፈለገ ከእውቀት አኳያ አንዱን ሳይጥል ሌላውን ሳያንጠለጥል መሆን አለበት። ከዚህ በላይ ደግሞ የማንኛውም አገር ልማታዊ ጉዞ በእውቀት ላይ መመስረት አለበት። በዚህ ሁሉም ሰው ከሞላ ጎደል ይስማማል። እውቀት ደግሞ ከመማር ይገኛል። በዚህም ብዙ ልዩነት አይኖርም። ጥያቄ የሚነሳው ግን ‘መማር ምን ማለት ነው?’ ‘ሰው የትና ከማን ይማራል?’ ‘ከየትና ከማንስ መማር አለበት?’ በሚሉት ዙሪያ ላይ ነው። በአገራችን በየእርከኑ መደበኛ ትምህርት ቤትና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ገብቶ የሚማረው ሰው ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ይገኛል። ለፈጣንና አዛላቂ እድገት የተማረ ሰው ቁጥር መጨመሩ አስፈላጊ ነውና ደግ ነው።


ይሁንና በየደረጃው ያለው ስርአተ ትምህርት ከይዘትና ከጥራት አንጻር መገምገም አለበት። ለጥራቱ መሻሻል አስፈላጊ ግብአቶች መሟላት አለባቸው። የትምህርት መሳሪያዎች የምንላቸው እንደ መጻሕፍትና የቤተ ሙከራ እቃዎችና የመሳሰሉት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። ከሁሉም በላይ ግን ብቃት ያለውና በራሱ የሚተማመን የአስተማሪ ሰራዊት ይፈለጋል። ጥራትን ማስጠብቀም ሆነ ማስቀጠል የሚቻለው ይህ ሰራዊት በሚገባ የታጠቀ ከሆነ  ነው።
ሰራዊቱን ከማስታጠቅ አንጻር ባህላዊና ዘመናዊ የእውቀት ምንጮች እንደየአስፈላጊነቱ በየፊናቸው ተገቢውን ሚና መጫወታቸው ጠቃሚ ነው።
ባህላዊ እውቀት ስንል ሰናዩን ከእኩዩ ለይተን ሰናዩን ማስፋፋትና ማጉላት በሂደትም ውጤት የሚያመጣውን መሸለምና ማበረታት የሚቻልበት ሁኔታ ማመቻቸት ማለታችን ነው። ባህላችን ውኃና ኃይል የመሳሰሉትን ሀብታት በአግባቡ ከመጠቀም አንጻር በጎ መሆን አለመሆኑን ማጥናት አለብን። የተለያዩ ነገሮችን ቆጥቦ መጠቀም እንደመቸገር የሚያይ አመለካከት ካለን (ሳይኖረን ይቀራል?) ጎጂ ነው። የደን የውኃና የአፈር ጥበቃ መንግሥት ከላይ ወደ ታችን የሚያወርደው ነገር ብቻ ሆኖ ሳይቀር ስር የሰደደ መሠረት ያለው ስራ ሆኖ እንዲቀጥል ባህል ወሳኝ ነው። መራባት ያለበት ባህላዊ እውቀት መራባትና መስፋፋት አለበት። ለምሳሌ እንደሚታወቀው የኮንሶ ብሔረሰብ ከአፈር አያያዝ አኳያ ዓለምአቀፍ እውቅና የተሰጠው እውቀት አለው። ይህ እውቀት ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ምን ያህል ሊስፋፋ የሚችል ነው? የእውቀቱ መነሻና ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍበት ትውፊታዊ መንገድ ምን ይመስላል? ለእነዚህ ጥያቄዎች የምንሰጠው መልስ ባህላዊው ገመድ ከዘመናዊ ጋር አንድ ላይ ተፈትሎ ጠንካራ ገመድ የሚሆንበትን መንገድ ለማበጀት ይመቻል። በሌላ አባባል ባህላዊውና ዘመናዊው እውቀት በድርና ማግነት ሲቀናበሩ አሟቂ የልማት ጋቢ ሊወጣቸው ይችላል።
ከዘመናዊ እውቀት አኳያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መስፋፋት በጎ ነው። የተቋማቱ፤ የተማሪዎቻቸውና የተመራቂዎቻቸውን ቁጥር በብቸኝነት እንደ ስኬት መለኪያ ማየት ግን ስህተት ነው። የአገሪቱ የኢኮኖሚ ምጣድ ተገቢና ተፈላጊ ግለት ላይ ሆኖ እንጀራዉን በተከታታይና በቀጣይነት በሚፈለገው ጥራትና ብዛት እንዲያበስል ይጠበቃል። ይህን ለማድረግ ደግሞ በዋናነት የተማረ የሰው ኃይል ያስፈልጋል። የተማረው የሰው ኃይል እንደ ምጣድ(የኢኮኖሚው) ሰሪ፤ እንደ ምጣድ ገጣሚ፤ እንደ ምጣድ ጠጋኝ ወዘተ ይሰራል። የዚህ ኃይል እውቀት ደግሞ እንደ ነዳጅ በተመጠነና በተስማማ ጥራት መግባት አለበት - ወደ ምጣዱ። አገራዊው የኢኮኖሚ ምጣድ እንደ አንድ ትልቅ ምጣድ የምናየውን ያህል እንደተለያዩ ምጣዶች ስብስብም ማየት እንችላለን። ኢኮኖሚው እንደ ነዳጅ የሚጠቀምበት የምሩቃኑ ብዛትና ጥራት(የእውቀታቸው) ምጣኔ ቁልፍ ነገር ነው።
‘በአጭር በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ስንት ምሩቃን በምን መስክ ያስፈልጉናል?’ ብቻ ሳይሆን ‘ባለን አቅም በጥራት ማስመረቅ የምንችለው ምን ያህል ነው?’ ብለን መጠየቅና መመለስ አለብን - እንደ አገር። በእንደዚህ አይነት አካሄድ ሄደን ነው የከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን ቁጥርና አይነት መወሰን ያለብን።
እርግጥ ነው የተመረቀው ሁሉ ስራ ማግኘት ላይኖርበት ይችላል - በማንኛውም አገር። እንደዛም ሆኖ ግን በአገራችን ሁኔታ በርካታ ተመራቂዎች ስራ የማያገኙበት ሁኔታ ካለ ወይም መስራት በሚገባቸው መስክ ሳይሆን በሌላ መስክ ላይ የሚሰሩ ከሆነ እንደ አገር ቆም ብለን እንድናስብ ሊያደርገን ይገባል። በአገራችን ሁኔታ የሚለውን እንየው። አገራችን ‘ስኮላርሺፕ’ ሰጥታ ነው ተማሪዎችዋን የምታስተምረው። ወጪ መጋራት ከተጀመረ በኋላም ቢሆን ለትምህርቱ ተገቢ ክፍያ አለማስከፈሏ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም መለኪያ በብዙ አገሮች(ድኃ አገሮችን ጨምሮ) የማይደረግ ምግብና መጠለያ ሰጥታ ነው  የምታስተምረው። ምግብና መጠለያ አቅርባና የትምህርት ክፍያም ሳታስከፍል ያስመረቀቸው ተማሪ በኢኮኖሚው ውስጥ በተመረቀበት መስክ ተሰማርቶ ተጠቅሞ የማይጠቅማት ከሆነ አገራዊው ኪሳራ እጅግ ከፍተኛ ነው። በዛ ላይ ደግሞ በግለሰብና በቤተሰብ ደረጃ የስራ አጡ ቁጥር መበራከት የራሱ የሆነ ጎጂ ተጽእኖ አለው።
ከዚህ አንጻር ነው የመንግሥት ባለሥልጣናት በዚህ ዙሪያ የሚሰጡት መግለጫና መከራከሪያ ከችግሩ የባሰ ችግር እንዳለ የሚያሳይ ሆኖ የሚገኘው። መከራከሪያው የሚገናኘው ከስራ ባህል ጋር ነው።
አገራችን ውስጥ ስራን የመናቅ ችግር ነበረ አለ። ክብር ምን ማለት እንደሆነ ግራ እስኪገባ ድረስ አለመስራት ያህል ክብር አዋራጅ ነገር እያለ ስራን ከአይነቱ ጋር አያይዞ መናቅ ክብርን እንደማስጠበቅ አድርጎ መቁጠርም ነበር አለም። እንደዚህ አይነት የአመለካከት ችግርን ደግሞ መንግሥት መዋጋት አለበት። ይህ ማለት ግን በመንግሥት እንደሚነገረው በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ብዙ አገራዊና ቤተሰባዊ ሀብት ፈሶባቸው የተማሩ ሰዎች ስራ አጥተው ሲያበቁ በግዴታ ቢበዛ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ብቻ የሚበቃው ስራ ላይ ሲሰማሩ ስራ ላለመናቅ ማስረጃ አይሆንም። እነዚህ ሰዎች የመንግሥት የሥራው ውጤቶች ናቸው። ኮብል የሚጠርቡት ወገኖች ሲጀመር መንግሥት ያስተማራቸው ኮብል ስቶን እንዲጠርቡ አይደለም። ለኮብል ስቶን ጠረባ የሚሆን ትምህርትና ዝግጅት አድርገው በዛው ቢሰማሩ ደስ የሚያሰኝ ነገር እንጂ የሚያሳዝን ነገር አይኖረውም ነበር። ይሁንና እነሱም ሲማሩ መንግሥትም ‘በድጎማ’ በመጀመሪያ ዲግሪና በሁለተኛ ዲግሪ እንዲማሩ ሲያደርግ በመስካቸው ሥራ ሰርተው ራሳቸውን ጠቅመው በሂደቱ ደግሞ አገሪቱን እንደሚጠቅሙ ታሳቢ ተደርጎ ነው። የተማሩት ትምህርትና ያጠፉት ጊዜ እንደመነሻም እንደ መድረሻም ከሚሰሩት ስራ ወይም እንዲሰሩ ከተገደዱበት ስራ ጋር ግንኙነት እስከሌለው ድረስ ጎሽ የሚያሰኝ ነገር የለውም።
ወደው ሳይሆን ተገደው የገቡበትን ስራም እንደስራ አለመናቅ ተደርጎ መወሰዱ ትክክል አይደለም። የማይፈልገውን ነገር ለማድረግ የተገደደ ሰው ተገዶ የሚሰራው ስራ እንደ ስኬት ሊቆጠርለት አይገባምና። ከተመረቁበት መስክ ውጪ ተገደው የገቡበት ስራ ከፍተኛ ገንዘብ ሊያስገኝላቸው ይችላል እያስገኘላቸውም ነው። እናም ከዛ ተነስተው ሊወዱት ይችላሉ - እነሱ። በእውነትም ‘እንኳንም በሞያዬ አልሰራሁ’ ሊሉ ይችላሉ። ደስታቸውም ሆነ እርካታቸው በአገርና በቤተሰብ ሀብት የከፍተኛ ትምህርት መከታተላቸውን ትክክለኛነት አያረጋግጥም። ለዛም ነው መንግሥት በዚህ የማይፈለግ ውጤት ዙሪያ የሚያቀርበው መከራከሪያ አሳማኝ የማይሆነው።  ለአንድ ሰው የምንመኝለት አለመታመምን ነው። መመኘት ብቻ አይደለም ሰውየው መረዳት ያለበትም እንዳይታመም ነው። ከቁጥጥር ውጪ በሆነ መልኩ ከታመመ ግን የሚያገኘው ህክምና ቢበዛ ጥሩ ነው እየረዳው ነው ልንል እንችላለን እንጂ ጤናማ ከመሆን የሚሻል ህመም ያለ ይመስል ተገዶ ከታመመ በኋላ የሚያገኘውን ህክምና ለማብራራት መሞከር አይገባም። ከዚህ ጋር የሚያያዝ ሌላው ነጥብ አሜሪካም ሆነ ሌሎች አገሮች ያለውና ከሞያው ውጪ የሚሰራው የተማረው ኢትዮጵያዊ ዙሪያ የሚነሳው ነው። ይህም እስከ ፒ.ኤች.ዲ ተምረው ሲያበቁ ማንኛውም ስራ እየሰሩ ለምን ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን ተመሳሳይ ሁኔታ እንደ ጉድ ይወራል የሚለው የመንግሥት ባለሥልጣናት መከራከሪያ ነው።  ይህም ቢሆን ወዶ ፈቅዶና ስራ መናቅ የለብኝም ብሎ ሳይሆን ተገዶ ገቢ ማግኘት ስላለበትና ኑሮውን ማሸነፍ ስላለበት ነው።  እነዚህ አገሮች ደግሞ በየመስኩ ተምረው በተመረቁበት መስክ የሚሰሩ ሰዎች ያሉባቸው ብቻ ሳይሆኑ ከሞያቸው ውጪ በሚሰሩ ሰዎች (የውጪ አገር ሰዎችን ጨምሮ) የሚቆጩ እንጂ እንደ ስኬት የሚቆጥሩ አይደሉም። እነዚህ ከሞያቸውና ከትምህርታቸው ውጪ በሆነ መስክ ተሰማርተው የሚገኙ ወገኖች እድሉን ቢያገኙ ያንን ስራ ይሰሩታል ወይ ብለን ብንጠይቅ መልሱ አይሰሩትም የሚል ነው።
መንግሥት ሆን ብሎ አይደለም ያንን ያመጣው። ለዚህም ነው ሆን ብሎ ያላመጣውን ነገር ይልቁንም እንደ ጎንዮሽ ጉዳት የመጣውን ነገር አላስፈላጊና ተቀባይነት የሌለውን ማብራሪያ በመስጠት ‘መልክ ለማስያዝ’ ከመልፋት ይልቅ  ኃላፊነቱን መውሰድ አለበት -መንግሥት። ‘ያላሰብነው ነው የሆነው’ ብሎ ወደማስተካከል መሄድ አለበት። ለኢኮኖሚያዊ ምጣድ የሚያስፈልገው ብዛትና አይነት ነዳጅ የጫነ ምሩቅ ከየተቋማቱ እንዲወጣ ማድረግ አለበት።
=======

አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.orgNo comments: