Tuesday, January 22, 2013

ዋልያዎች ለዋልያዎች - ዘኳስ ለዘሜዳ

(ጌታቸው አሰፋ፤ ጥር 11 ቀን  2005 ዓ.ም.) ለዛሬ ስለ ሁለት ዋልያዎች እንጽፋለን - የኢትዮጵያችን የብቻዋ ስለሆነ እንስሳው ዋልያና ዋልያ ተብሎ ስለሚጠራው ብሔራዊው የእግር ኳስ ቡድናችን። በተለይ ስለ ሁለተኛው ዋልያ ለመጻፍ ወይም መጻፍ ለመጀመር ዛሬ ምቹ ነው። ብሔራዊ ቡድናችን የያዘውን መጠሪያ ስም ያገኘው ከብርቅየው እንስሳ ‘ዋልያ አይቤክስ’ ስም ነው። የአሰያየም ሂደቱ በተመለከተ ዝርዝር መረጃ የለኝም (እነ ደጉ፤ አዳነና ጀማልም አናውቀውም ሲሉ ሰምቻለሁ)። ዋልያ አይቤክስ የኢትዮጵያ ከኢትዮጵያ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሊሆን እንደሚችል ግን መገመት ይቻላል። ስለ ሁለቱም ዋልያዎች (ዋልያ ዘሜዳና ዋልያ ዘኳስ) በተራበ ተራ (አሁን ባይርበኝ ኖሮ ‘በተራ በተራ’ ብዬ እጽፈው ነበር) እናነሳና ከዛም መልሰን እናገናኛቸዋለን።


ዋልያ ዘሜዳ (ተራራ ላይ ሜዳ ካለ?)

መጀመሪያ ስለ ዱር እንስሳው ዋልያ እናወጋለን።ሙሉ ስሙ ዋልያ አይቤክስ ተብሎ የሚጠራው ይህ እንስሳ የዘር ሀረጉ የሚመመዘዘው አይቤክስ ተብለው ከሚጠሩ ዝርያዎች ነው። ከምድረ ገጽ ለመጥፋት በአደጋ ላይ ካሉት ዝርያዎች የሚመደበው ዋልያ በስሜን ተራራሮች ይገኛል። የምቹ ስፍራ መመናመንና የህገ-ወጥ አደንና ስርቆት ጥቃት ሰለባ መሆን ዋልያዎችን  በ2004 እ.አ.አ. በቁጥር ወደ 500 አካባቢ እንዲወርዱ አድርጓቸዋል።እርግጥ ዋልያዎቹ መራባት እንኳ ቢችሉ አሁን ያሉበት የስሜን ተራሮች ምቹ ስፍራ መሸከም የሚችለው  2 000 ያህል ዋልያዎችን  ብቻ ነው - ድሮ ድሮ እዚህ ቦታ ከዚህ በላይ በብዛት ይገኙ እንዳልነበር። ይሁንና በሃያኛው ክፍለ ዘመን ቁጥራቸው በጣም ቀንሶ 1994-1996 እ.አ.አ. አካባቢ 200–250 ብቻ ሆነው ነበር። በዋልያዎች ሰፈር የሰዎች በዙሪያቸው መስፈር፤ የከብቶች ግጦሽ ቦታና እርሻ ቦታ መስፋፋት ፈታኝ ሁኔታዎችን ይፈጥራሉ፤ የመንገድ ግንባታም ስፍራቸውን ሊሸነሽንባቸው ይችላል። እርግጥ በ1969 እ.አ.አ. የተቋቋመውና 27200 ኳስ ሜዳዎች የሚያህል ስፋት ያለው የስሜን ብሔራዊ ፓርክ ለተቀሩት ዋልያዎች ተገን ሆናቸዋል።
ዋልያዎች በሰው ስራሽ ማኅደረ-እንስሳ (zoo) የሚገኙ ስላልሆኑ ዘራቸው እንዳይጠፋ ካለው ስጋት አኳያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ላይ የሚሰራው IUCN የተባለው የተመድ ድርጅት የተወሰኑ ዋልያዎች ወደ ማኅደረ-እንስሳ ተወስደው ራሳቸውን እንዲተኩ መደረግ አለበት ይላል።  በሌላ አጠራር ሀበሻው አይቤክስ ተብሎ የሚታወቀው ዋልያ አይቤክስ የፍየል የቅርብ ቤተ-እንስሳ (ቤተ-ሰብ እንዲሉ) ነው።ከአይቤክሶች ሁሉ የደቡቡ የእኛው ዋልያ አይቤክስ ነው። ባለፉት አስርተ ዓመታት የዋልያ አይቤክሶች ቁጥር በእጅጉ መቀነስ ‘በጣም የመጥፋት አደጋ ላይ የደረሱ’ ከሚባሉት ዝርያዎች መካከል እንዲመደብ አድርጎታል።ዋልያዎች እንደየ እድሜያቸው የሌሊት ሲሳይ የሚያደርጓቸው እንስሳት አሉ።ለአቅመ-ዋልያ የደረሱ ዋልያዎች የጅብ ሲሳይ ሲሆኑ ግልገል ዋልያዎች ደግሞ ለቀበሮዎችና ለዱር ድመቶች መና ናቸው። ዋልያ አይቤክሶች አብዛኛው ቆዳቸው ከቼኮሊታዊ ቡናማ እስከ በስሱ የተቆላ ቡናማ ቀለም አለው። ግራጫማዊ ቡናማ አፍ፤ ነጫማ ግራጫ አይንና እግር ፤ እግራቸው ከውስጥ በኩልና ሆዳቸው ነጭ ሲሆን እግራቸው ላይ የነጭና የጥቁር ስብጥርም ሊኖር ይችላል። ወንድና ሴት ዋልያዎች በመጠንም በቀለምም ይለያያሉ። ሴቶቹ አነስ ያሉና ቀለል ያለ የቆዳ ቀለም ያላቸው ናቸው። በክብደት ከ80 ኪሎ(ሴት) እስከ 125 ኪሎ (ወንድ) የሚደርሱ ሲሆን ወደ ኋላ የዞረና እስከ 1 ሜትር ከ10 ሴንቲሜትር የሚደርሱ ትልልቅ ቀንዶች አሏቸው። ቀንዶቹ በዋልያዎች መካከል ለሚደረግ የጉልቤዎች ክንቻ ላይ ጥቅም ላይ ይውላሉ። ወንዶቹ አንዲት ሴት (ቆንጆ? የተማረች? ባለሞያ?) ዋልያ በእጃቸው ለማስገባት በቀንዶቻቸው በኃይለኛው ይፋለጣሉ። ሴቶቹም ቢሆኑ ቀንድ አላቸው - እንደ ወንዶቹ ደረቅና ጠንካራ ሆነው አጠርና ቀጠን ያሉ። ዋልያዎች ጭራቸው ከ20-25 ሴ. ሜ.፤ ቁመታቸው ከ140-170 ሴ.ሜ. ከፍታቸው ከ90-110ሴ.ሜ ይደርሳል። ርዝመቱ እንደ ዋልያው እድሜ የሚለያይ ጥቁር ጺም አላቸው - ወንድ ዋልያዎች። ለትልቆቹ - ረዘምና በዛ ያለ። ዋልያ አይቤክሶች የመንጋ እንስሳት ሲሆኑ በየመንጋው ከአምስት እስከ ሃያ የሚደርሱ አባላት ሊኖሩ ይችላሉ። የዋልያ መንጋ ከግማሽ እስከ ሁለት ኪ.ሜ. በቀን ሊጓዝ ይችላል።  እድሜያቸው የገፋ ወንድ ዋልያዎች ብቸኝነት የሚያበዙ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ከዋናው መንጋ በአጭር ርቀት ሆነው ይቆዩና የተራክቦ ወራት ሲደርስ ቀሪውን መንጋ ይቀላቀላሉ። ዋልያዎች ለአቅመ-ተራክቦ የሚደርሱት በአንድ ዓመታቸው ነው። እስከ 15 ዓመትም መኖር ይችላሉ። የተራክቦ ወራት የሚባለው በአብዛኛው ከመጋቢት እስከ ግንቦት አካባቢ ሲሆን ልጆች የሚወለዱት ደግሞ መስከረምና ጥቅምት ላይ ነው። ዋልያዎች በአንድ ጊዜ አንድ ወይም ሁለት ልጅ ነው የሚወልዱት። ወንዶች ለብቻ በቡድን ያሳልፋሉ። ሴቶች ደግሞ በቡድን ከልጆቻቸው ጋር። የዋልያ የእርግዝና ወራት ከ150 እስከ 165 ቀናት ነው(ለንጽጽር፡ የሰው 285 ቀናት)።  ዋልያ አይቤክሶች  ከባህር ጠለል በላይ ከ2,500 ሜትር እስከ 4,500 ሜትር  የሚደርስ ተራራማ፤ አለታማና  አፋፋማ ቦታዎች የሚኖሩ ናቸው። እጽዋት በሊታ ሲሆኑ መኖሪያቸው የተራራ ላይ ደን፤ሳራማና ቁጥቋጣማ ስፍራዎች ናቸው። ከፍ ያለ ዛፍ ላይ ያለ ቀንበጥ ለመብላት ሲፈልጉ የፊት እግራቸውን ወደላይ ዘርግተው በኋላኛው  እግራቸው ይቆማሉ። ዋልያዎች ጠዋትና ማታ በንቃትና በብቃት ሲያሳልፉ በፀሐይ ጊዜ የሆነ አለት ላይ በማረፍ ያሳልፋሉ።
ዋልያ ዘኳስ
ስለሁለተኛው ዋልያ ደግሞ እስቲ የተወሰነ እንበል።አገራችን ለመጨረሻ ጊዜ ለአፍሪካ ዋንጫ ባለፈችበት ጊዜ የዘጠኝ ዓመት ልጅ የነበርኩ ልሁን እንጂ ቴሌቪዥን በቤታችን ብቻ ሳይሆን በስምም ይሁን በመልክ በማውቀው ሰው ቤት ውስጥ የነበረ አይመስለኝም። እናም ያ ጊዜ የኔ ጊዜ አልነበረም - ከብሔራዊ ቡድናችን አኳያ። ኳስ አይቼ ማድነቅ በምችልበት (በአይነ ስጋም ሆነ በአይነ ስክሪን ለማየት በምችልበት) እድሜ የብሔራዊ ቡድናችን እነ ገብረመድኅን ኃይሌን፤ ሙሉጌታ ከበደን፤ ሙሉጌታ ወልደየስንና ዳኛቸው ደምሴን ያቀፈበት ጊዜ ነበር - ሙሉ በሙሉ የአገር በቀሎች ስብስብ።  ዛሬ ዋልያዎች ውጪ ተወልደው ያደጉና እዛው ውጪ የሚጫወቱ እንደ ዩሱፍ ሳላህ እና ኢትዮጵያ ተገኝተው ለውጪ ክለብ ለመጫወት የበቁ እንደነሳላዲን የመሳሰሉ ያሉበት ነው - ከነገብሬ ጊዜ በተለየ። እግር ኳስ በተመለከተ የመረጃ መግበስበስ ካልሆነ እጥረት የሌለበት ዘመንና አገር ነው ዛሬ ዋልያዎች የሚወክሉት - ከነሙሌዎች ዘመን በተለየ። ብዙኃን መገናኛዎችና ባለሀብቶች በጅማሬ ደረጃም ቢሆን በጎ ሚና የሚጫወቱበት ዘመን ላይ ነው ዋልያዎች የሚጫወቱት - ከነዳኙ ጊዜ በተለየ። ድሮም ዘንድሮም አንድና ያው የሆነና እነገብሬ፤ ሙሌዎችና ዳኙም የሚያውቁት አንድ ነገር ግን አለ። ልቡ እስኪወልቅ ድረስ ቡዱኑን የሚደግፍ - ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ጨዋታ አልፎ ለብራዚልና ለባርሳ ጨዋታ የሚመጥን ደጋፊ። የተጫዋቾች ትውልድና ሁኔታ ተቀይሯል - መቀየርም ስላለበት። ደጋፊው ግን በትውልድም በሁኔታም አልተቀየርም። አሁንም ከልቡ፤ አሁንም ከአንጀቱ ይደግፋል። ሲቀናን ይቦርቃል፤ ሳይሳካልን ይሳቀቃል።
ዘኳስ ለዘሜዳ
ህዝብና መንግሥት ለዋልያዎቻችን ምስጋናም ማበረታችም (ቀብድ ብጤ?) የሚሆን ክብር ገላጭ ነገሮችን እያደረጉ ነው። ይገባቸዋል! የዋልያ ቡድን አባላት ስም በየሰዉ ጓዳ እየገባ ነው። ታዋቂ እየሆኑ ነው። ደስ ይላል። ተገቶ ከተሰራ የአርሴናሉ አሰልጣኝ በቅርቡ በስም ለማወቅ ይቸግራል ያሉት የዋልያ ምርጥ ተጫዋቾች ስም በዓለም መድረክም እየታወቀ የማይመጣበት ምክንያት የለም። እስከዛ ግን በአገር ውስጥ ያለውን ታዋቂነታቸውን በመጠቀም ተጨማሪ አገራዊ ጠቀሜታ ያለው ነገር መስራት አለባቸው ባይ ነኝ። ለምሳሌ የመለያ ስማቸውን ያገኙበት ብርቅዬ እንስሳ ዋልያ አይቤክስ በቁጥር አሁን ካለበት የሚጨመርበትንና ከመጥፋት የሚድንበትን በዘመቻ መልክ ተጀምሮ በአዛላቂነት የሚቀጥል ስራ በስማቸው ማስጀመር አለባቸው። ይህ ስራ በአገር ውስጥ ባለሞያዎች የሚደገፍ፤ ለስራው የሚሆን የገንዘብ እገዛ ደግሞ ከውስጥም ከውጪም መንግሥታዊ ከሆኑና ካልሆኑ አካላት የሚገኝ ተደርጎ ሊቀረጽ ይችላል። እንዲህ አይነት ከስማቸውም ከክብራቸውም ጋር የሚሄድ ስራ ለመስራት ከነሱ የሚፈለገው ታዋቂነታቸውና ስማቸውን መጠቀምና የማስተማር ስራ ላይ ማገዝ ብቻ ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ ቢያንስ አንድ ጊዜ ወደ ስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ሄደው ከአማናዊዎቹ ዋልያዎች ጋር ‘መተዋወቅ’ አለባቸው። ዋልያዎች ዘኳስ ይህንን ስራ ሰርተው የዋልያዎች ዘሜዳ ቁጥር በከፍተኛ መጠን ጨምሮ ለማየት ካበቁን ‘ዋልያዎች ለዋልያዎች’ በመስራታቸው ‘ዋልያ’ የብርቅዬ ሕያው እንሳሳም የብርቅዬ ሕያው ብሔራዊ ቡድንም ስም ሆኖ ይቀጥላል ማለት ነው ። በድቡብ አፍሪካ እንዲሆን የምመኘው - ዋልያዎች የዙር ጨዋታዎችን አልፈው አስገራሚ የደረጃ ውጤት ሲያመጡ ማየት። ለመስማት የማልመኘው  (ከማይሆን የሽንፈት ዜና በተጨማሪ)- ‘ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ዋልያዎች ስለዋልያ አይቤክስ ተጠይቀው ‘እኔ እንጃ’ አሉ’ መባልን መስማት። ድል ለዋልያዎች!
=======

አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: