Tuesday, January 22, 2013

እነሱ ከእኛ ወይስ እኛ ከነሱ?

(ጌታቸው አሰፋ፤ ጥር 4 ቀን  2005 ዓ.ም.) በውጪው ዓለም ገና እና አዲስ ዓመት በስድስት ቀናት ልዩነት የሚከሰቱ ሁለት በዓላት ሲሆን መዘዛቸው ደግሞ እጅግ ከፍተኛ ነው። በምዕራቡ ዓለም የገና በዓል ከጊዜ ወደ ጊዜ ትርጉሙም ሚናውም እየተቀየረ መምጣቱን ማየት ይቻላል። እዚህ ካናዳ ውስጥ በአንድ ትምህርት ቤት ህጻናት ከቤተሰቦቻቸው ለተለያያ ትውልድ የገና በዓል የሚሰጠው ትርጉም ምን እንደነበር ጠይቀው እንዲጽፉ የቤት ስራ ይሰጣቸዋል። አንዱ ቅድመ አያቱን አያቱንና አባቱን ጠይቆ መጣ። ሴቷ ቅድመ አያቱ በዘመናቸው ጊዜ የነበረውንና የገና ብስኩት ላይ ስለሚቀባው ክሬም አንስተው ለዛን ዘመን ውድ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ለገና ብቻ ተቀብቶ ስለሚበሉት እንዴት በጉጉት ይጠብቁት እንደነበርና ያኔ የሰፈር ሰዎች አንድ ላይ ሆነው ያከብሩ እንደነበር አጫወቱት። አባታቸው ሚንስተር የነበሩት አያቱ ደግሞ የገና በዓል ለሳቸው ዘመን ሰዎች ጎዳና ተዳዳሪዎችን የመርጃ፤ ቤተ ክርስቲያን ሄደው ዝማሬ ማቅረቢያና ጎረቤታሞች ምግብና ደስታ የሚጋሩበት እርስ በርስ እየተደጋገፉ የሚያከብሩበት በዓል እንደነበር ነገሩት። አባቱን ሲጠይቅ ያገኘው መልስ ደግሞ የገና በዓል አከባበር ሌላ ቅርጽና ይዘት መምጣቱን ማየት የሚያስችል ነበር። አባትዬው ስለ አሻንጉሊቶችና ትልልቅ የፕላስቲክ መጫዎቻዎች እንደስጦታ መስጠት ዋነኛው የበዓሉ መገለጫ እየሆኑ መምጣታቸውንና ከዚህም ጋር በተያያዘ  ወላጆች ስጦታዎችን ለመግዛት አቅም በሚያጡበት ጊዜ እንዴት ጫናም ሀዘንም ይሰማቸው እንደነበር አጫወቱት።

አዎ በውጪው ዓለም የገና በዓል ትርጉምና አከባበር ተቀይሯል - ለዚያውም በፍጥነት። ገና ወይም ልደት ከጌታችን ልደት ጋር ያለው ግንኙነት በጣም ከመላላቱ የተነሳ የጌታ መወለድ ከገና በዓለ ማክበርና አለማክበር ጋር የሚያገኛነው ሰው ቁጥር እጅግ እያነሰ መምጣቱን ማየት ይቻላል - ለምሳሌ በአውሮፓ። 
አሁን በምዕራቡ ዓለም የገና በዓል አከባበር ከገና ዛፍና ከገና ስጦታ ጋር ብቻ ተሳስሮ ቀርቷል። የስጦታ ነገር ከተነሳ  የገና ካርዶች ዋና ተጠቃሾች ናቸው።  የገና ካርድ ላይ የሚኖር ማንኛውም ስእል/ምስል ከጌታ ልደት ጋር የሚያያዝ እንዲሆን የሚጠበቅ ነው። ሐቁ ግን አሁን አሁን የገና ካርድ ምስሎችም የጌታ ልደት ማሳያነታቸው እየቀረ ነው። እርግጥ ለሽያጭ የቀረበው የዓለም የመጀመሪያው የገና ካርድ በ1843 ሲታተምም ይዞት የወጣው ስዕል ቤተሰቦች ሲበሉ ሲጠጡ የሚያሳይ እንጂ የጌታን ልደት ጋር የሚገናኝ አልነበረም። ከዛ በኋላ ግን የገና ካርዶች የሚታወቁት ከትክክለኛው የበዓሉ መነሻ ጋር በሚያያዝ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ ጠቋሚነታቸው ነበር። በቅርቡ በእንግሊዝ አገር በተደረገ ጥናት ከተካተቱት 6 576 የገና ካርዶች ውስጥ 36 ላይ ብቻ ጌታ በከብቶች በረት፤ መላእከት እና የመሳስሉት ስእሎችን የያዙ ነበሩ። የተቀሩት 6 540 ከጌታ ልደት ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ግንኙነት የሌላቸው ሆነው ተገኝተዋል።
በአብዛኛው በገና ህጻናት ናቸው በስጦታ የሚንበሸበሹት።  በዓለም ወደ ሁለት ቢልዮን ህጻናት አሉ።  ከነዚህ ውስጥ ከሙስሊም፤ ሂንዱ፤ አይሁዶችና ኢአማንያን ወላጆች የተገኙ ህጻናት የገና ስጦታ አያገኙም ተብሎ እንኳን ቢታሰብና ቁጥራቸውን ብንቀንሰው ወደ ሰባት መቶ ሚልዮን ክርስቲያን ህጻናት ይኖራሉ። ለስሌት ሲባል በገና ስጦታ የማያገኙትን በርካታ የእኛ አገር ህጻናትን ለጊዜው ትተናቸው ማለት ነው።
እያንዳንዱ ህጻን የሚያገኘው ስጦታ በአማካይ ስድስት መቶ ሃምሳ ዘጠኝ ግራም የሚመዝን መጫወቻ ነው ተብሎ ቢታሰብ አጠቃላይ የስጦታ እቃዎች ክብደት 461 300 ቶን ይሆናል ማለት። ለንጽጽር ያህል ስጦታው ግዙፉ አውሮፕላን ቦይንግ 747 ከሚጭነው የሰው ብዛት ሻንጣና ነዳጅ ጋር ሲተያይ ወደ 2000 እንደዚህ አይነት አውሮፕላኖች የሚያስፈልጉት ነው - ለማጓጓዝ። የእቃዎች ማምረቻ ማጓጓዛ አካባቢን በመበከል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። ከበዓሉ ጋር ተያይዞ የሚፈጠረው ቆሻሻ አይነትና ብዛት ማዘጋጃ ቤት ይቁጠረው።

የገና ዛፍ ህያው አረንጓዴ የጽድ ዛፍ በሚጠቀሙ አገሮች ቀላል ያልሆነ የዛፍ መጨፍጨፍን ያስከትላል። እርግጥ እያንዳንዱ ቤት ሆን ብሎ አስቦ የሚያደርግበት የ‘መተካካት’ መንገድ ካበጀ ደገኛ ዛፎች ከጭፍጨፋ ይድናሉ። የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ እቤታችን የገና ዛፍ ነበረን። ቤታችን የጽድ አጥር ያለው ስለነበር በየዓመቱ ከጽዶች መሀል የማትከረከም አንዲት ጽድ ትኖራለች። ይህች ጽድ ለሚቀጥለው ዓመት የገና ዛፍ ለመሆን ነው የማትከረከመው። እሷ ተቆርጣ ጥቅም ላይ ስትውል ተረኛ የሆነች ሌላ ጽድ ትለቀቃለች። ያኔ ብርቅ ሊሆን የሚችልው ይህ መልካም አሰራር የትጉው አባቴ አሰራር ነበር። በምዕራቡ ዓለም ሰው ሰራሽ የፕላስቲክ ገና ዛፍ  ከሞላ ጎደል ጥቅም ላይ ይውላል። በአገራችንም በጥቂት በጥቂቱ እየገባ ነው። ፕላስቲክ ሲጀመር ከነዳጅ ዘይት የሚሰራ በመሆኑ ከአካባቢ ደኅንነት አንጻር በጎ አይደለም። በዛ ላይ ደግሞ በመበስበስ ንጥረ ነገሮቹ ወደ አፈር በቀላሉ ስለማይዋሃዱ ወደጥንተ ተፈጥሮው ለመመለስ አስቸጋሪ ነው። በተለይ የገና ዛፍ ፕላስቲኮች ደግሞ በአብዛኛው ከሌላ ውህድ ጋር ተሰባጥረው ስለሚሰሩ በዳግም ሕይወት ለሌላ ቁስ መስሪያነት መልሶ ለመጠቀምም አይበጁም። እርግጥ አንድ የገና ዛፍ መልሶ መላልሶ በየዓመቱ ለመጠቀም ይቻላል። ይህ በጎ ጎኑ ነው ከለምለም ዛፍ ጋር ሲነጻጸር ማለት ነው።
በምዕራቡ ዓለምም ቢሆን አሁን ድረስ የምር አማናዊው የገና ዛፍ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ነው - በዋጋም ውድ ነው። በዛፍ የበለጸጉ እንደ ካናዳ አይነት አገሮች ‘ትኩስ ቁርጥ’ የገና ዛፍ ወደ ውጪ አገር እየላኩ ይቸበችባሉ። ለምሳሌ ካናዳ ባለፈው ዓመት 1 738 212 የሚሆኑ የገና ዛፎችን ወደ ውጪ ልካለች። ወደ 1.6 ሚልዮን የሚሆኑት የሄዱት ወደ አሜሪካ ሲሆን ከኩባ እስከ ዩናይትድ አረብ ኢሚሬተስ ፈረንሳይ ታይላንድ ወዘተ ድረስም ልካ ሸጣለች። በዋጋ ደረጃ ጠቅላላ የተላከው ዛፍ 28.2 ሚልዮን ዶላር የሚያወጣ ነው። 25.8 ሚልዮን ዶላር ያህሉ የተገኘው ለጎረቤት አገር አሜሪካ ከተደረገው ሽያጭ ነው። በነገራችን ላይ አሜሪካም  ወደ 5 ሚልዮን ዶላር የሚያወጡ ትኩስ-ቁርጦችን ወደ ካናዳ አስገብታለች በዛው ዓመት።   ለአምና ገና በካናዳ ጥቅም ላይ የዋሉት ትኩስ-ቁርጥ የገና ዛፎች ዋጋ ወደ 51.3 ሚልዮን ዶላር ይሆናል። ከተለያዩ አገሮች ወደ ካናዳ የገቡ ሰው ሰራሽ የገና ዛፎች ዋጋ በአንጻሩ ደግሞ ወደ 47 ሚልዮን ዶላር ሲሆን ከዚህ ውስጥ ወደ 46 ሚልዮን ገደማው ከቻይና ነው። የተቀረውን አንድ ሚልዮን ዶላር የሚጋሩት ታይላንድ አሜሪካ ሜክሲኮና ቬትናም ናቸው። ቻይና መቸም ለበዓል አከባበርም ሆነ ለፈለገው ነገር አገሮች ለሆነ ምርት ፍላጎት ካላቸው ያንን ነገር አምርታ ማቅረብን ተክናበታለች - እኛ አገር የዛሬ አምስት ዓመት ሚልኒየም ሲከበር የሚልኒየሙ አርማ ያለበት ባንዲራ ከወርቅ-ቅብ መቆሚያው ጋር አምርታ እንዳቀረበችው ማለት ነው። ቻይና የዓለም ፋብሪካ በመባል መታወቋ ትክክል ነው። በነገራችን ላይ እነዚህ ትኩስ-ቁርጦች ከመደበኛ ደን እየተቆረጡ የሚገኙ አይደለም - ለዚህ ጉዳይ ሆን ተብሎ ከሚለማ የገና ዛፍ ልማት እንጂ። በካናዳ የገና ዛፍ የልማት ቦታዎች በቁጥር ወደ 2 381 ይደርሳሉ። በመጠንም በቁጥርም እየቀነሱ የመጡት እነዚህ ቦታዎች በአሁኑ ውቅት ወደ 28 315 ሄክታር ስፋትን ይሸፍናኑ።  በእንግሊዝም የአማናዊው ገና ዛፍ አምራቾች ማህበር በየዓመቱ ወደ ስምንት ሚልዮን የሚሆን የምር ገና ዛፎችን ይሸጣሉ።
በአጠቃላይ ገና በተለያዩ አገሮች ያለው ኢኮኖሚያዊ ድርሻ ከፍተኛ ነው። በዩናይትድ ኪንግደም ለምሳሌ ወደ ሃያ ቢልዮን ፓውንድ ያህል ገንዘብ የሚወጣ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ወደ አንድ ነጥብ ስድስት ቢልዮኑ ከምግብና መጠጥ ጋር ተያይዞ የሚወጣ ነው። አዎ የፈረንጆች ገና አከባበር ወጪው ብዙ ነው። ለአብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ከገና በኋላና ተከትሎት በሚመጣው አዲስ ዓመት ማግስት የሚጠብቀው ባዶ ካዝና ነው - ገንዘቡ ሁሉ ለተለያዩ ስጦታዎች ግዢና በመብላት በመጠጣት ስለሚያልቅ።
የገናና የአዲስ ዓመት ሰሞን በምዕራቡ ዓለም ከአቅም በላይ በሚወጣው ወጪ ምክንያትና እስከ እዳ መግባት ድረስ የሚያበቃ ጫና ምክንያት የተለያዩ ማኅበራዊ ቀውሶች ይከሰታሉ። ለምሳሌ የጃንዋሪ መጀመሪያው ሳምንት ላይ ከፍተኛ የፍቺ ቁጥር ይታያል። ከወጪ ጋር በተያያዘም የአአምሮ ህመም ሰለባ የሚሆኑ ሰዎች ቁጥር እንዲሁ ከፍ ይላል- ከነዚህ በዓላት በኋላ። ስለበዓል ከተነሳ እነሱ ከእኛ ወይስ እኛ ከነሱ እንማር? ቢያንስ ገናን በተመለከተ ሲሆን እናስተምራለን። ቢያንስ ግን ከነሱ አንማርም።
=======

አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: