Friday, December 21, 2012

የዶሃው ጉባኤ

(ጌታቸው አሰፋ፤ ኅዳር 22  ቀን  2005 ዓ.ም.) ከዚህ ሳምንት ሰኞ ጀምሮ በካታር ዶሃ የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ አስራ ስምንተኛው የባለድርሻዎች ጉባኤ በመካሄድ ላይ ይገኛል። አምና በደርባን ደቡብ አፍሪካ ተደርጎ የነበረው ጉባኤ ቀጣይ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥርስ ያለው ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስፈልጉ ነገሮች ሳይንስና ፓለቲካ ናቸው። ሳይንሱ አሁንም በመረጃ እየደለበ እየሄደ ነው። እንዲያውም መሬት ላይ የሚታየው የአየር ንብረት ለውጥ አመልካች ክስተቶች ሳይንስ ይሆናል ካለው ፈጥነው በርክተውና ጎልብተው እየታዩ ነው። በአሜሪካ የኸሪከን ሳንዲ የድርቅ ክስተት፤ የሰሚናዊ ዋልታዊ የበረዶ ግግሮች ከልክ በላይ መቅለጥ፤ የባህር ጠለል ከፍ ማለት፤ የህንድ በኃይለኛ ጎርፍ መጥለቅለቅ፤ የሳህል አገሮች በከፍተኛ ድርቅ መመታት ወዘተ።

እንደዛም ሆኖ ፓለቲካው እንደ ግመል ሽንት ወደኃላ እየሄደ ነው። ለአጭር ጊዜና ለተወሰነ የህዝብ ቁጥር በተወሰነ የህዝብ ቁጥር የሚመረጡት ፓለቲከኞች በዛሬ አጀንዳዎች ተጠምደውዋል። የአገር መሪዎች አበረታች ሁኔታ የሰፈነበት ጊዜ ስልጣን ላይ የሚወጡበት ጊዜ በትልልቅ ዓለም አቀፍና ዘላቂ አጀንዳዎች የመያዝ እድላቸው ሰፊ ነው። የአገራቸው ህዝብ በስራ አጥነት በሚቸገርበት ሁኔታና ምጣኔ ሀብታዊ ምልከታዎች በጎ ባልሆኑበት ጊዜ ስልጣን ሲይዙ ደግሞ አጀንዳ የሚያደርጓቸው ነገሮች የአጭር ጊዜና በቀጥታ የአገራቸውን ህዝብ የሚመለከተው ጉዳዮች ላይ የሚታኩሩ ናቸው።
ዓለም አቀፍ ስምምነትን የመቅረጽ፤ የማጽደቅ፤ የማጸደቅ፤የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ያላቸው አገሮች መሪዎች ስልጣን በሚይዙበት ወቅት ያለው የአገራቸውና በአቅም አቻዎቻቸው የሆኑ አገሮች ምጣኔ ሀብታዊ ሁኔታ በተለየ መልኩ ወሳኝ ነው። ወሳኝነቱ በቀጥታና በአጭር ጊዜ ኢኮኖሚን ለማከም ለማያስችል የአየር ንብረት ለውጥ ዓለም አቀፍ ስምምነት የሚሰጡትን ትኩረት ከፍም ዝቅም ያለ እንዲሆን በማድረጉ ነው። 
የአየር ንብረት ለውጥ በአውሮፓም በአሜሪካም ታሞ ለሚገኘው ኢኮኖሚ ስቃይ ቀናሽ ክኒን አይደለም፤ ህይወት ዘሪ ጉሉኮስም አይደለም፤ መርዝ አብካኝ መድኃኒትም አይደለም፤ ህምም አልባ ፈዋሽ ቀዶ ጥገናም አይሆንም - ቢያንስ በአጭር ጊዜ። የአውሮፓና የአሜሪካ ኢኮኖሚ ጤናማ ባልሆነበት ሁኔታ ከሚካሄድ ጉባኤ የአየር ንብረት ለውጥ አምጪ ጋዞች ልቀት ቅነሳ ዙሪያ የሚደረግ ተተግባሪ ስምምነት መጠበቅ እጅግ አስቸጋሪ ነው።  አሜሪካ ታማም ሆነ ድና ከኪዮቶው ስምምነት ውጪ በነበረችበት ጊዜ የአውሮፓ ጤናማ መሆን ዓለም ወደ ተሻለ ነገር ባያሸጋግር እንኳ ወደባሰ አዘቅት እንዳትገባ ረድቷት ነበር። አሁን ግን የአውሮፓ ብልቶች የሆኑ አገሮች ታላቅ የኢኮኖሚ ድቀት ላይ ይገኛሉ። ሁነኛ የሚባሉት የአውሮፓ አገሮችም እነዚህን በኢኮኖሚ የነቀዙ አገሮችን ለማትረፍ እና ነቀዙ ሌሎችንም እንዳይበላ ለማድረግ እየባተሉ በሚገኙበት ወቅት ነው የዶሃው ጉባኤ ለሁለት ሳምንታት የሚካሄደው።
ያደጉት አገሮች የዓለም አማካይ የከባቢ አየር ሙቀት እስከያዝነው ክፍለ ዘመን ማብቂያ ድረስ በአንድ ነጥብ አምስት ዲግሪ ሴንት ግሬድ ጭማሪ ላይ እንዲወሰን የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረስ እንዳይቻል አድርገው ሲያበቁ  እሺ ይሁን መቼስ በሁለት ዲግሪም እንስማማ ከተባለ በኋላ እሱም የሚቻል አይመስልም - በተያዘው አካሄድ። በዚህ ምክንያት የአፍሪካም ሆነ ሌሎች ስብስቦች አዲስ ነገር ይዘው አልሄዱም ወደ ዶሃ። አውሮፓ ወደ ደርባን ሲትሄድ የውስጥ ልዩነቷን አቻችላ በተሻለ ጠንካራ አቋም ነበር። ወደ ዶሃ የሚትሄደ ግን በውስጥ ያለው ልዩነት ሰፍቶ ብቻ ሳይሆን የበለጠ በተዳክመበት ሁኔታ ነው። ወደ አውሮፓ የሚደረጉ ከአውሮፓም ከአውሮፓ ውጪም የተነሱ በረራዎች የካርቦን ብክለት ግብር እንዲከፍሉ ለማድረግ እየገፋችበት የነበረው አሰራር ከአውሮፓ ውጪ ባሉት አገሮች ተቃውሞ ምክንያት ቢያንስ ለጊዜው ትቼዋለሁ እንድትል ተደርጋለች።  የዚህ የግብር ክፍያ መነሻው የአየር ጉዞዎች በከፍተኛ ደረጃ በካይነታቸው ከመታወቃቸው ጋር የተያያዘ ነበር። በአጠቃላይ አውሮፓ የተለመደው አዲስ ስምምነት እንዲጸድቅ የማድረግ መሪ ሚናዋን ለመጫወት አቅም ይዛ አይደለም ወደ ዶሃ የምትጓዘው።
የዶሃው ጉባኤ የብዙኃን መገናኛም ሆነ የህዝብ ትኩረት አላገኘም። ከሦስት ዓመታት በፊት ከፍተኛ ትኩረት አግኝቶ ከነበረው የኮፐንሃገኑ ጉባኤ ወዲህ ከተካሄዱት ሁለት ጉባኤያት የመጨረሻው ዝቅተኛ ግምት የተሰጠው ጉባኤ ነው ማለት ይቻላል።

የዶሃው ጉባኤ የሚፈለገው በአገሮች መካከል የሚደረግ ሁሉን አቃፊ ውኃ የሚቋጥር ዓለም አቀፍ  ስምምነት ያስከትላል ባይባልም መካሄዱ ግን ለሌሎች በጎ ስራዎች ማከናወኛ የሚሆኑ ስብስቦችን ለመፈጠር መልካም መድረክ ይሆናል። በዚህ ምክንያት በአገሮች የሁለትዮሽና ከዛም በላይ ቁም ነገር ያላቸው መሰባሰቦች ይፈጠራሉ ብለን እንጠብቃለን። በተለይ መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት (የተለያዩ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ተዋናዮች ጨምሮ) በቴክኖሎጂና በመሳሰሉት መስኮች ዙሪያ በመሰባሰብ የሚያደማ ስራ የመስራት እድል ይሰጣቸዋል የዶሃው ጉባኤ።
ይህ ሲሆን ብቻ ነው ከተለያየ የዓለማችን ማዕዝናት ወደዛ ያመሩት የልኡካን ቡድን አባላት በአውሮፕላን ጉዞአቸው የለቀቁትን በካይ ጋዝ የሚያክም ስራ ሰሩ ማለት የምንችለው።
ከደርባን ጋርና እስካሁን ከተደረጉት በርካታ ጉባኤያት ጋር ሲነጻጸር የዶሃው የሚለይበት አንዱ ምክንያት በሁለት ኃይላተ ግብር እየተመራ በሁለት መም ሲካሄድ የነበረው ድርድር በአንድ ወጥ ኃይለ ግብር ስር ሆኖ የሚካሄድ መሆኑ ነው።
አምና ከዋናዎቹ የደርባን አጀንዳዎች መካከል አንዱ የነበረው የኪዮቶ ፕሮቶኮል ቀጣይ እጣ ፈንታ የዶሃም ዋነኛ አጀንዳ ነው። የጃፓን ከተማ በሆነችው የኪዮቶ ከተማ ታኅሳስ 2 1990 ዓ.ም. የጸደቀው የኪዮቶ ፕሮቶኮል ተብሎ የሚጠራው ስምምነት ዓለም አቀፍ የልቅት ቅነሳና ገደብ መጠንን የደነገገ ስምምነት ነበር። የኪዮቶ ፕሮቶኮል የቅጥያ አንድ ተብለው የሚጠሩት ሰላሳ ሰባት የበለጸጉ አገሮችና የአውሮፓ ህብረት የሚገኝበት ስብስብ የልቀት መጠን በአማካይ በአምስት ፕርሰንት እንዲቀንሱ ያስገድዳል።  የኪዮቶ አሳሪነት ለቅጥያ አንድ አገሮች ብቻ እንዲሆን የተደረገውና በነሱ መካከልም በተለያየ መጠን እንዲከፋፈሉት የተደረገው ያለፉት 150 ዓመታት ታሪካዊ ልቀት-ጠገብ የኢንዱስትራሊያዊ እድገታቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ነበር። ከቅጥያ አንድ ውጪ ያሉት ቻይና ፤ብራዚል፤ ሕንድና ደቡብ አፍሪካ የሚገኙበት ስብስብ የኪዮቶ ፕሮቶኮል አካል ቢሆኑም በፕሮቶኮሉ የመጀመሪያ ዙር የልቀት ቅነሳም ይሁን ገደብ አልተጣለባቸውም ነበር።
የደርባኑ ጉባኤ የኪዮቶን ቀጣይ ህይወት በበጎ መልኩ ሊወስን አልቻለም ነበር። እንዲያውም በዛው ወራት ካናዳ፤ ጃፓን፤ ኒውዚላንድ፤ ራሺያ በኪዮቶ ቀጣይ ዙር ቀርቶ ማብቂያው ከተቃረበው የመጀመሪያው ዙርም ባለቀ ሰዓት ‘ወራጅ አለ’ ብለዋል። አሜሪካ ከመጀመሪያው ዙርም ውስጥ እንዳልነበረች ሁሉ ቀጣይ ዙር ውስጥ ለመግባትም ጉጉት የላትም።
ሌላው የአረንጓዴ የአየር ንብረት ለውጥ ፈንድ ተብሎ የሚጠራው ነገረ-ገንዘብ እንደአምናው ሁሉ ዘንድሮም አጀንዳ ነው።  በሚቀጥሉት ስምንት ዓመታት እያደገ መጥቶ ከ2020 አ.አ..አ ጀምሮ ወደ መቶ ቢልዮን ዶላር በዓመት የሚደርሰው ፈንድ ለታዳጊ አገሮች የማጣጣሚያና የስርየት ሥራዎች ትግበራ የሚውል ነው። በታዳጊ አገሮች በኩል ፈንዱ እስካሁን በሌላ ስም ለተረጂ አገሮች ሲሰጥ የቆየውን ገንዘብ አሁን አዲስ የስም መጠቅለያ ብቻ በመቀየር የሚሰጥ እንዳይሆን ስጋት አለ። ይህን ስጋት ከሚያስወግዱት መካከል ገንዘቡ በከፊል ከዓለም አቀፍ የባህር ትራንዚት፤ከአየር ጉዞ ቲኬትና ፤ ከገንዝብ ልውውጥ አገልግሎት በፐርሰንት መሰበስብ ከሚያስችል አዲስ ምንጭ ይገኛል መባሉ ነው። የዚህን ፈንድ እውን መሆንና ተግባራዊነት በተመለከተ ጠቃሚ ውሳኔ ቢተላለፍ ትልቅ ስኬት ይሆናል። እስካሁን በታየው ግን ታሪካዊ የብክለት ኮሮጆ ተሸካሚ ላልሆኑ ታዳጊ አገሮች የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ የሚያስችል የገንዘብ ደጋፍ ለመስጠት ይህ ነው የሚባል የተግባር እንቅስቃሴ አይታይም - ባዶ ቃል ከመግባትና የገቡትን ቃል ከማደስ የዘለለ።
ብዙ ጉባኤዎችን በማስተናገድ የምትታወቀው ዶሃ የዓለም የንግድ ድርጅት ድርድርም የተካሄደባት ከተማ ነች። ዶሃ አሁን እያስተናገደችው የምትገኘው ድርድር የመሳካት እድሉ ዝቅተኛ ነው። ዶሃ ተሳክቶላት የስኬት ድኃ ከመሆን ተርፋ የኔና የመሰሎቼ ግምቶች ተሳስተው ለማየት ያብቃን።
 =======
አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: