Sunday, November 25, 2012

በሌለ በሬ ማረስ?


(ጌታቸው አሰፋ፤ ኅዳር 15  ቀን  2004 ዓ.ም.)ስለ ‘ያ ትውልድ’ና ‘ይሄ ትውልድ’ ከመጻፍ አስቀድሞ ‘ያ ትውልድ እና ይሄ ትውልድ ስንል ምን ማለታችን ነው?’ የሚለውን ጥያቄ መመለስ ተገቢ ነው። በተለመደው አባባል በ1960ቹ መጀመሪያ አጋማሽ ውስጥ ይካሄዱ በነበሩት የተማሪዎች እንቅስቃሴዎች ወቅት እድሜያቸው ቢያንስ ለአቅመ-መሳተፍ የደረሱ ሰዎች ስብስብን ነው ‘ያ ትውልድ’ የምንለው።
ላላ ስናደርገው ….የእድሜ መስፈርቱ እንዳለ ሆኖ ቀጥሎ ያለውን አይነት ግጥም የሚገጥም ሰው ወይም እንዲህ ተብሎ የተጻፈ ግጥምን ማንበብ አሁን ድረስ የሚመስጠው ሰው አባል የሆነበት ትውልድ ማለት ነው ልንልም እንችላለን።
“. . . ምን ነካው ይህ ትውልድ ፈሰሰ ሞቱ
     ምነው ከዳው ወኔ ያት ቅድመያቱ
     ሜን ብሎ መኖር ተሸክሞ ቀንበር
     ልነበረም ልምዱ ትውልድ ይመስክር ። ” [‘ያ ትውልድ ይመስክር’ በሚል ርዕስ በኢሕአፓ ገጸ ድር ከተለጠፈ ግጥም የተወሰደ ነው።]
በተማሪዎች እንቅስቃሴ ወቅት አካባቢ የተወለደውም ሆነ በወቅቱ ይደረግ የነበሩት ነገሮች ትንሽ ትንሽ ትዝ የሚለውና ከዛም በኋላ የምድረ ኢትዮጵያን በረከት ለመካፈል ወደዚህ ዓለም የተቀላቀለው ሁሉ የ’ይሄ ትውልድ’ አባል ተደርጎ ተወስዷል - በዚህ ጽሁፍ።
የዛሬ አስራ አራት ዓመት አካባቢ አውሮፓ ውስጥ እማርበት ከነበረው ዩኒቨርስቲ አንድ አሁን ጡረታ የወጣ ነጭ ፕሮፌሰር ነበር። ተዋወቅን። ከኢትዮጵያ መሆኔን ስነግረው “ኢሕአፓ ነህ ወይስ መኢሶን?” ሲለኝ ክው አልኩ። ከመቅጽበት ስረጋጋና ገና የዛ ትውልድ አባል አለመሆኔንና ስለሁለቱም ብዙም የማውቀው ነገር እንደሌለ ከመናገሬ የከነከነኝ አንድ ጥያቄ ቢኖር ‘ከሁለቱ አንዱ ውስጥ አባል መሆንን እንደ መደበኛ የወሰደ አጠያየቅ ከየት አመጣው?’ የሚለው ነበር። በኋላ የተረዳሁት ‘ያ ትውልድ’ ወይም ቢያንስ ከፕሮፌሰር ዲክ ኡርባን ቬስትብሮ ጋር ለመገናኘት እድል የገጠማቸው የ’ያ ትውልድ’ አባላት የዛሬ አርባ ዓመታት በፊት ሳይቀር የፓለቲካ ጎራዎች አባልነታቸውን ከአገር ውጪ ጭምር እስከምን ድረስ ያጦዙት እንደነበር ነው።
ለኔ ‘ያ ትውልድ’ ከሰራው በጎ ስራ ይበልጥ ያጠፋውና እያጠፋው ያለው ይበልጣል - ከሞላ ጎደል።  ጥቂት የዛ ትውልድ አርአያ የሚሆኑ አባላት በጎ ስራና አስተሳሰብ የትውልዱ ልዩ ሁኔታዎች ናቸው እንጂ መደበኛው አይደሉም - የምናወራው ግን ስለ መደበኛው አባላት ነው።
በኢዩቤልዩ ቤተ መንግሥት የሚፈጸም የአረንጓዴ ሽልማት ስነስርዓት ተገኝቼ ነበር - ከግማሽ ደርዘን ዓመታት በፊት። አካባቢን የሚመለከት ድራማ ቀረበ። አንድ የታወቁ ሰው ተነሱ (አሁን በሕይወት የሉምና ነፍሳቸውን ይማር)። ድራማው የቀደመውን ትውልድ(ከያ ትውልድ በፊት የነበረውን ማለታቸው ሳይሆን ይቀራል?) የሚተች ሆኖ ስላገኙት ማዘናቸውንና ተያያዥ ጉዳዮችን አነሱ። እርግጥ የዛኑ በታዳማዊ ፊት ሃሳቤን መስጠት ዳድቶኝ ነበር። ይሁንና እስከ’ ቅልቅሉ’ ሰዓት ጠብቄ ለብቻ አግኝቼ አነጋገርኳቸው። ሃሳቤ ለጽሑፍ በሚሆን መልኩ ሲመቻመች እንዲህ የሚል ነበር “አይወቀስ፤ አይተች የሚባለው ትውልድ ምን ስለሰራ ነው የማይወቀሰውና የማይተቸው? መስራት ሲገባው ያልሰራውን መልካም ነገር ስናይ፤ ማድረግ ሳይገባው ያደረገውን ኢመልካም ነገር ስንመለከት መወቀስና መተቸት ይነሰው ወይ? የሞራል የበላይነት ይኑረውም አይኑረውም ሳይጠይቅና ሳይጠየቅ መውቀስ እንጂ መወቀስ ያለበት የማይመስለው፤ መተቸት እንጂ መተ(!)ቸት ያለበት የማይመስለው ሆኖ የሚቀጥለው እስከመቼ ነው?.....”  ። እውነት ግን ለያ ትውልድም ሆነ ከሱ አንድ ቀደም ላለው ትውልድ (የአገር ዳር ድንበር ያስከበሩትን አይጨምርም) የማይደፈር የማይገሰስ ‘መወቀስን አስቀድሞ በመውቀስ የመሻር መብት’ ማን ነው የሰጠው?
የያ ትውልድ ሰዎች ጠላት በማፍራትና እስከወዲያኛው ጠላት አድርጎ በማቆየት የሚችላቸው የለም።
“ጠላት” የሚሉትንም ክፍል ‘ልክ ለማስገባት’ የማይፈነቅሉት ድንጋይ (እነሱ ራሳቸው የቆሙበት ድንጋይም ሳይቀር) የለም።
ከሦስት ዓመታት በፊት ነው። አንድ ስልክ ተደወለ። የ’ያ ትውልድ’ ሰው ነው። መንግሥትን አሁን ድረስ በሁለገብ ትግል አወርዳለሁ የሚል ስብስብ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ አለው። የደወለልኝ ከሙያዬ አንጻር እንደሆነ ነገረኝ። ይሁንና ዋና ዓላማው ሌላ ነበር። ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በኮፐንሀገኑ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ጊዜ የአፍሪካ አፈ ቀላጤ ሆነው የሚጫወቱትን ሚና መቃወም ነው የፈለጉት - እሱና ስብስቡ። ለዚህ ተቃውሞ የሚሆናቸው ‘ሙያዊ’ ድጋፍ እንዲያገኙ እንዳግዛቸው ፈልገው እንደሆን ነገረኝ። እነዚህ ሰዎች መልካም የሚልዋቸውን አጋጣሚዎች ወይም ሁኔታዎች ሲመጡ ጠላታቸውን “ልክ የማስገባት” አካሄድ በመከተል ይታወቃሉና አልገረመኝም። የደዋዩ ጥያቄና የኔ መልስ (ቃል በቃል እንደዚህ ላይሆን ይችላል ያልኩት - ሀሳቡ ግን እንደዛ ነው- ዋናው ቁምነገሩስ ሃሳቡ አይደል?!) “የኢትዮጵያ መንግሥት በአካባቢ ጉዳይ ላይ በቂ ስራ እየሰራ ነው ብለው ያስባሉ?” “በቂ ስራማ እየሰራ አይደለም።” “እኛም ከዚህ አንጻር ነው በኮፐንሀገን የሚደረገው ጉባኤ ላይ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የአካባቢ ጥበቃ ችግሮችና ጉድለቶች በቁጥር አስደግፈን ለመቃወም ያሰብነው? እና ምን ይላሉ?” “እኔማ የምለው አስቀድሜ እንዳልኩት መንግሥት በቂ ስራ ባይሰራበትም እንኳን፤ በቂ ስራ ቢሰራበትም ኖሮ ችግር ሆነው የሚቀጥሉ ነገሮች እንዳሉ ሁሉ መንግሥት በቂ ስራ ባልሰራበትና በማይሰራበት ጊዜም እንደዜጎች ሰርተን ማረም፤ ማሻሻልና ማስተካከል ያለብን አለ ብዬ አምናለሁ። እናም ከመቃወም ይልቅ ጥያቄየ አንተም ሆንክ እኔ የድርሻችንን ምን ያህል ተወጥተናል? በተለይም የአገሪቱ የገጠር ክፍል ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የምናየውን የአካባቢ ጉስቁልና ዙሪያ መንግሥት ሰራም አልሰራም በተወሰነ ደረጃ  የድርሻችንን አልተወጣንም ብቻ ሳይሆን አልሞከርነውም።    ወዘተ ወዘተ ነገር አልኩት። ለጊዜው “በዚህ መልኩ አላየሁትም ነበር። አመሰግናለሁ” ብሎኝ ተለያየን። ያው በተቃውሞውም ቀጠሉ።
በድሮ በሬ ቀርቶ በዘንድሮ በሬ ራሱ ማረስ ቀላል አይደለም። ‘ያ ትውልድ’ ግን አሁንም በድሮ በሬ ማረስ ነው የሚፈልገውና የሚመኘው። በዘንድሮ በሬ አርሰን በምግብ ራሳችንን መቻል ካቃተን በሌለ በሬ አርሰን የት እንደርሳለን?
ለክብርና ለጥቅም መሞት ሊለያይም አንድም ሊሆን ይችላል። ‘ለክብራችንና ለጥቅማችን ስንል አሳልፈን የምንሰጠው ነገር ምንድነው?’ ነው ዋናው ቁም ነገሩ። የአንድ ማኅበረሰብ ታላቅ የእድገት ደረጃ  ላይ መድረስ አለመድረስ በተለያየ መልኩ መገለጽ ቢችልም ዋናው ቀለሙ የሚያያዘው ግን ልዩነት ማስተናገድ ከመቻሉና ካለመቻሉ ላይ ነው ብዬ አምናለሁ። ስለ መገንጠል በአገራችንና እና አካባቢያችን ዙሪያ ይወራል ብቻ ሳይሆን ይህ ጥያቄ ለብዙዎች ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል። ከዛም አልፎ በአገራችን ‘አንቀጽ 39’ ሆኖ ተቀርጿል። በአንድ በኩል ለዚህ አንቀጽ መጸነስ እስከ መወለድና የሃያ አንድ ዓመት ወጣት እንዲሆን ለማድረግ፤ በሌላ በኩል ይህ አንቀጽ እንዳይጸነስ፤ እንዳይወለድና በአጭሩ እንዲቀጭ ለማድረግ አምርረው የተሰለፉና ለመቃወም የተጋደሉ ሚልዮኖች የ’ያ ትውልድ’ ወገኖች አሉ። የመገንጠል አይነት የማይበጅ ሃሳብ በእኛ አገር ብቻ የሚነሳ አይደለም። ካናዳ ውስጥ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ የሆነችው የኵቤክ ግዛትን ለመገንጠል ሌት ተቀን የሚሰሩ ግዛቲቱን የሚያስተዳድሩ ፓርቲና አባላቱ አሉ። በቅርቡ ደግሞ የባራክ ኦባማ ዳግም መመረጥ አልዋጥ ያላቸው ቴክሳስንና የመሳሰሉትን የደቡብ ዩኤስ አሜሪካ ግዛቶችን መገንጠል አለብን ብሎው የተነሱና ‘አብርሃም ሊንከን የታላቋ አሜሪካ ታላቅ አባት ሳይሆን ደቡብን በጦር አስገብሮ የአሜሪካ አካል ያደረገ ጦረኛ(ጦርነት ናፋቂ) ነው’ እያሉ ድምጻቸውን እያሰሙ ነው። በካናዳም ይሁን በአሜሪካ ይችን ወይም ያችን እንገንጥል ይበሉ እንጂ ጦር ወደመማዘዝ ግን አልሄዱም፤ አይሄዱም። ሃሳብን በጉልበት ማሸነፍ አይቻልማ! በሁለቱም ጫፍ ያለው ‘ያ ትውልድ’ ግን በዚህ ዙሪያ አሁንም ‘ነቄ’ አላለም።
 የኅብረተሰብ ‘እውነታዎች’ በየጊዜውና በየዘመኑ ግልጽና ፈጣን እንዲሁም ድብቅና አዝጋሚ ድርድር እየተደረገባቸው የሚቀረጹና የሚጠፈጠፉ ናቸው። ከአቀራረጽና ከአጠፋጠፍ ጋር ተያይዞ እንኳ የተበላሸ ነገር ቢኖር ሂደቱ ካለ አሁንም በድርድር የሚሰተካከል ነው።
‘ያ ትውልድ’ ግን ኅብረተሰባዊ እውነታ ግትርና በጊዜም በቦታም የማይለወጥ አንድ ቦታ ላይ ቆሞ የቀረ ያህል አድርጎ የወሰደ ይመስላል። ጊዜም ትውልድም እየሸሸው ሲሄድም እንኳን ከመባንን ይልቅ ‘ባለበት ሂድ’ን መርጦ ለመቀጠል እስከ ጥግ ድረስ የመሄድ አባዜ የተጠናወተው ይመስላል። ችግሩ  ያለው ‘ያ ትውልድ’ ችግሩን በዘር ወደ ትውልድ የሚተላለፍ እንዲሆን አድርጎ ለመቅረጽ መስራቱ ላይ ነው።
በአብዛኛው የተለመደው ያ ትውልድ ይሄን ትውልድ ሲወቅስ ማየት ነበር። እስቲ እሱም ዛሬ ይወቀስ በሚል ይህ ጽሑፍ ተጽፏል። ትውልድ ተሻጋሪ እንቁዎች በዛም ትውልድ ውስጥ እንዳሉ እና እንደበሩ ግን በድጋሚ ማንሳት የግድ ይላል። ምስጋና ለነሱ።


 =======

አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

6 comments:

Anonymous said...

Ya Tiwld wist yeresahew ale. EPRDF is part of YA TIWLD. Meles, Esayas all are part of YA TIWLD. Minew enersu altenesum Gech????

Akababi said...

annoymsha....lik new.... Ya Twilid wusT wana tewanayoch mekakel yeTeqeskachew/shachew alubet...

"ሃሳብን በጉልበት ማሸነፍ አይቻልማ! በሁለቱም ጫፍ ያለው ‘ያ ትውልድ’ ግን በዚህ ዙሪያ አሁንም ‘ነቄ’ አላለም።" yalkutim leza new...

lela bota layim ከዛም አልፎ በአገራችን ‘አንቀጽ 39’ ሆኖ ተቀርጿል። በአንድ በኩል ለዚህ አንቀጽ መጸነስ እስከ መወለድና የሃያ አንድ ዓመት ወጣት እንዲሆን ለማድረግ፤ በሌላ በኩል ይህ አንቀጽ እንዳይጸነስ፤ እንዳይወለድና በአጭሩ እንዲቀጭ ለማድረግ አምርረው የተሰለፉና ለመቃወም የተጋደሉ ሚልዮኖች የ’ያ ትውልድ’ ወገኖች አሉ። yemilewun enesun yemiChemir new...
kezih belay lemanisat..... ye-tsihufu meTenm alamam ayfeqdim neber...

environmental geTegn new.... andi hulet sim albawoch yanesahut....

Anonymous said...

ያ ትውልድ ምንም አልሰራም!!!!!!!!!!!!!!! አሁን እኔ ማወቅም መስማትም የምፈልገው ይሄ ትውልድ የሠራውን ሥራ ነው እስቲ አሳዩና፡፡

Anonymous said...

ለኔ ‘ያ ትውልድ’ ከሰራው በጎ ስራ ይበልጥ ያጠፋውና እያጠፋው ያለው ይበልጣል - ከሞላ ጎደል። ጥቂት የዛ ትውልድ አርአያ የሚሆኑ አባላት በጎ ስራና አስተሳሰብ የትውልዱ ልዩ ሁኔታዎች ናቸው እንጂ መደበኛው አይደሉም - የምናወራው ግን ስለ መደበኛው አባላት ነው።

ምናአልባትም ቀጥቂቶቹ ይቆጠሩ ከሆነ!!!!!!!!!! እናንተን ሀ ሁ አስቆጥሮ አሁን ካላችሁበት ያደረሰ ያ አጥፊ ትውልድ ይመስለኛል

Anonymous said...

The truth is, we make a mistake when we think that generations can be separated. The truth is you need me so that I have shoulders you can stand on, and we need you because you have shoulders somebody else can stand on. We are one.
Maya Angelou

Anonymous said...

በሁለቱም ጫፍ ያለው ‘ያ ትውልድ’ ግን በዚህ ዙሪያ አሁንም ‘ነቄ’ አላለም።