Sunday, November 25, 2012

አረንጓዴ ኮከቦች
(ጌታቸው አሰፋ፤ ሰኔ 9 ቀን  2004 ዓ.ም.)   ኢትዮጵያ የሚሰሩትን የሚያውቁ አብሪዎች በየመስኩ ያስፈልጋታል ብለን ጀምረን ነበር ባለፈው እትም። የሚሰሩትን የሚያውቁ ማለት በመረጡት ጉዳይ ላይና ዙሪያ ከልብ በልብ ለመስራት ልባቸውን ከአእምሮአቸው ጋር አዋህደው የሚሰሩ ማለት ነው ብለን ነበር። እንደነዚህ አይነት አብሪዎች ውሎ አድሮ ቢያንስ አይን ላላቸውና ብርሃንን ለሚወዱ ሁሉ የሚያበሩ አብሪዎች ናቸው ብለን ከድርጅቶች ሁለት አንስተናል። በአካባቢና በኃይል ጉዳይ ዙሪያ ብዙ ናቸው ባይባሉም አረንጓዴ አብሪ ግለሰቦችም አሉ። የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ከልማትና ከእድገት ጋር እንደሚጣረስ ተደርጎ በሚቀርብባቸው የእኛ አይነት አገሮች ውስጥ አረንጓዴ አብሪዎች እጅግ ውድ ናቸውና ለዛሬ ሁለት ግለሰቦችን በአረንጓዴ ኮከብነታቸው ብርሃናቸውን እዘክራለሁ።
ዶ/ር ተወልደ ብርሃን  
የጋሽ ስብሐት ወንድም ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር ከሃያ ዓመታት ገደማ ጀምሮ  የፌደራል አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ኃላፊ ሆነው እያለገለገሉ ነው። ዶክተር ተወልደ አማራጭ የኖቤል ሽልማት ተብሎ የሚታወቀው ራይት ላይቭሊሁድ ሽልማት ለመሸለም ስዊድን አገር በመጡበት ጊዜ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው ወዳጄ ዶክተር አግዘው ጋር በስዊድን ፓርላማ ህንጻ በሚደረገው የሽልማት ስነስርዓት ተገኝቼ ነበር። የእሳቸው፤ የእንግሊዛዊቷ ባለቤታቸውና ከእንግሊዝ አገር የመጣችው ልጃቸውም የአገር ባህል ልብስ ድምቀት ሰጪ ነበር።
ድምጻቸውን ከኢትዮጵያ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአፍሪካ አገሮችን ጨምሮ ቡድን ሰባ ሰባት እና ቻይና ተብሎ የሚታወቀው የበርካታ አገሮች ስብሰብ አፈ ቀላጤ ሆነው ሰርተዋል። የደኅንነተ-ሕይወት ዋና ተደራዳሪ ሆነው ለአርሶ አደርና አርብቶ አደር ማኀበረሰቦች የሕያዋን ባለቤትነት መብትና አዛላቂ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ጉዳይ ዙሪያ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ተከራክረዋል።
በይፋም ባይሆን ውስጥ ውስጡን የሦስተኛው ዓለም ክፍል ሰዎች (ምንም ቢማሩ፩) የራሳቸው የሆነ ጠንካራና ረቺ የሆነ የመደራደሪያ ሃሳብ አያቀርቡም የሚል እብሪት በበለጸጉት አገሮች ተደራዳሪዎች ዘንድ ነበረና በዶር ተወልደ ዋና መሪነት ይቀርብ የነበረው የድርድር ሃሳብ ይዘትን በኃይለ ሃሳብ መምታት ሳይችሉ ሲቀሩ ሌላ ሞራል የሚነካ የሚመስላቸው ነገር ያደርጉ ነበር። ለምሳሌ በአንድ የድርድር ዙር በእሳቸው ቡድን የሚቀርበው ሃሳብ አረንጓዴ ሰላም በተሰኘ ዓለም አቀፍ የአካባቢ ጉዳይ አቀንቃኝ ድርጅት ተሰርቶ የተሰጣቸው እንጂ የራሳቸው እንዳልሆነ (ለማዘጋጀት ብቃቱ አይኖራቸውም ከሚል ንቀት) ሲነገራቸው እጅግ የተበሳጩበት ሁኔታ እንደ ነበር ስዊድን መጥተው የተናገሩትን አስታውሳለሁ። ድርድሮች በተወሰነ ጊዜ መቋጨት ያለባቸው ጉዳዮች ተይዞ ስለሆነ የሚጀመረው ብዙ ጊዜ የጊዜ እጥረት ስለሚያጋጥም ቀን ከሌሊት መደራደርን ይጠይቃል። ያደጉት አገሮች ብዙ ተደራዳሪዎች ይዘው ስለሚሄዱ የተወሰነው ሲደራደር ሌላው ያርፋል (እስከ መተኛት ድረስ)። እኛንና መሰለ አገሮችን ወክለው የሚሄዱት እነ ዶር ተወልደ ግን በስድሳ ዓመታቸው (በዛን ወቅት) በዛ ላይ የአስም በሽተኛ ሆነው ሌት ተቀን ከጎረምሶቹ ጋር ይደራደሩ በነበረበት ሁኔታ ነው የእብሪት ንግግሩንም ይሸከሙ የነበሩት። እናም በሳቸው አባባል ምንም እንኳን ሰው ለመምታት ለመጨረሻ ጊዜ እጃቸውን ያነሱት የአስራ ሁለት ዓመት የነበሩ ጊዜ ቢሆንም ሞራል-ነኪ የሆነው የ’ብቃት-የላችሁም’ አባባል ግን ሊቋቋሙት ስላልቻሉ ‘ለመማታት’ ተጋብዘው ነበር።
ይህ ሁሉ ሲሆን ከምዕራቡ ዓለም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተጽእኖ ይደረግባቸው የነበረ ከመድርከም ውጪ በሆነ ሁኔታ ነበር። የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም እርዳታ ጉዳይ እሳቸውን ዝም ከማሰኘት ጋር አቆራኝተው እያቀረቡ የሚያመጥቡት ጊዜና ሁኔታም ነበር። የግብርና ሚኒስትር ባለሥልጣናት በኩልም ሳይቀር ‘ለምን አትተውም’ ተብለው እንደነበር ተነግሯል። ያልተወደደላቸው አቋም በጥናተ ስረት ምህንድስና መሰረት የሚፈበረኩ ልዉጥ ሕያዋን ከአንድ ዙር በላይ ተዘርተው የማይበቅሉ የሰብል ዘሮች ስርጭት በተመለከተ ያላቸው አቋም አንዱ ነበር። በሕያዋን ፍጥረቶች (ለምሳሌ ሰብሎችና ሌሎች እጽዋቶች) የባለቤትነት (ከባለአእምሮ ንብረትነት ጋር በተያያዘ) የምዕራቡ ዓለም አገሮች በትልልቅ አትራፊ ኩባንያዎች ግፊት የሚያራምዱት አደገኛ አቋም በመቃወምና ሌሎች በርካታ አገሮችንና ስብስቦችን በማስተባበር የትም እንዳይደርስ ለማድረግ የወሰዱት እርምጃ ሌላው ነው። የእሳቸው አቋም የነዚህ ሕያዋን ባለቤትና ዋና ተጠቃሚ እታች ያለው የማኅበረሰቡ ክፍል - ገበሬው - ነው የሚል ነው።
ተራ ወደ ሆነና ስብሰባ እንዳይሳትፉ ለማድረክ ቪዛ ወደመከልከል አካሄድም ተሞክሮ ነበር - በካናዳ። የዛሬ ሰባት ዓመት ነው። የተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ በካናዳ ሞንትሬያል ከተማ ይካሄድ ነበር።  ሞንትሬያል የተመድ ብዝኃ ሕይወት ጽ/ቤት መቀመጫ ነች። የዶ/ር ተወልደ አቋም በካናዳ መንግሥት ዘንድ ያልተወደደ ስለነበር  ቪዛ በማገድ ከስብስባ ሊያስቀራቸው ሞከረ። ብዙ ዓለም አቀፍ መጠየቂያዎች ተሞልተው የበርካታ አገር ምሁራንና አቀንቃኖች- ካናዳዊያንን ጨምሮ - ተቃውሟቸውን አሰሙ -  ቪዛውም እንደገና እንዲያገኙ ተደረገ።
ቪዛውን ካገኙ በኋላ የሚከተለውን ኢ-ሜይል ለደጋፊዎቻቸው ልከው ነበር።
ውድ ጓደኞቼ
ዛሬ ሜይ 24 ነው። ወደ አመሻሹ። ወደ ካናዳ ለመግባት እነሆ ቪዛዬን አግኚቼአለሁ። ስለዚህ ብዙዎቻችሁን ሞንትሬያል አገኛችኋለሁ። የጉዞ ዝግጅቶቼ ሁሉ እንደታቀዱት ከተሳኩ ሜይ 26 ማታ ላይ ሞንትሬያል እደርሳለሁ። ጉዳትና ካሳ ላይ የሚታኩረው የመጨረሻው ቀን ላይ እቀላቀላችኋለሁ። የወደፊቱ ዓለም አቀፍ የጉዳትና ካሳ ጉዳይ ላይ የሚኖረን አካሄድ ቅርጽ ለሁላችሁም በሚታይበት ደረጃ ላይ ሲሆን እደርሳሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ስቀላቀላችሁ በተሻለ ደረጃ የሚታይበት ሁኔታ ለመፍጠር የቻልኩትን በማድረግ እረዳለሁ። ከዚህ ስብሰባ በኋላ በአንድ ወይም በሁለት ስብሰባዎች አሰራሩን በጽኑ መሰረት ላይ አቁመን ኃላፊነት ከጎደለው የህያውን ምህንድስና እንዲታደገን እናደርጋለን የሚል ተስፋ አለኝ።
ስለ ትልቅ ድጋፋችሁ ሁላችሁንም አመሰግናለሁ። ብዙ አገሮችን ለአንድ ዓላማ እንዲሰሩ የማድረግ ዘይቤ በመንግሥት ደረጃ ሌላ ምት አስተናግዷል። ነገር ግን በማኅበረሰቦች ስብስብ ደረጃ ያለውና እናንተ አካል የሆናችሁበት አብሮ የመስራት ኃይል አሸናፊ ሆኗል።
መንግሥታዊ እብሪትን ለመቆጣጠር ምናልባት በማኅበረሰቦች ስብስብ ደረጃ ያለው አብሮ የመስራት ሂደት ይዘን መግፋት አለብን።
እስቲ አስቡበት። እኔም አስብበታለሁ። በዚህ ጉዳይ ላይ እመለሳለሁ።
የማኅበረሰብ ሉላዊነት ለዘላለም ይኑር!
በጣም አመስጋኙ ጓደኛችሁ
ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር
ዶክተር ተወልደ ብርሃን የተመድ የአካባቢ ፕሮግራም የ2006 ሻምፒዮንስ ኦፍ ዘኧርዝ አሸናፊ ሲሆኑ የዓለም የወደፊት ምክር ቤትም አባል ናቸው።
ጋሼ አበራ ሞላ
በሙዚቃዊ ድራማው ገጸባህሪ ስሙ ጋሼ አበራ ሞላ - የሚጠራበት ስሙ ስለሺ ደምሴ ሲጀመር አስተማሪ ነበር በሙያው። ከሐረር የመምህራን ማሰልጠኛ ሰልጥኖ እንደወጣ ከላሊበላ እስከ ሰቆጣ ያስተማረው ስለሺ ደምሴ መጀመሪያ ወደ ጅቡቲ ከዛ ወደ ፈረንሳይ እና መጨረሻ ላይ ወደ አሜሪካ አቀና።
የጃን ሜዳው ልጅ አዲስ አበባን ለማጽዳት የታተረው ከሃያ ስድስት ዓመታት የአሜሪካ ቆይታው በኋላ በባህል አምባሳደርነት ከመጣ በኋላና ወደ ሸገር በቋሚነት ከተመለሰ በኋላ ነው።
ወጣቶችን ፤ አጥቢያዊ ማኅበረሰቦች እና የአጥቢያ አስተዳደሮችን በማንቃትና በማስተባበር ንጹህና ጤናማ አካባቢን ከመፍጠር አኳያ ሌሎች አርአያውን ለመከተል እስኪቋሙጡ ድረስ ማነሳሳት የቻለ አብሪ ስራ ሰርቷል - ጋሼ አበራ ሞላ። አንዳንድ ሰዎች የሚሰሩት ስራ - ምንም በጎ ቢሆን - በቀላሉ የማይታይ ወይም በአጭር ጊዜ ውስጥ የማይታይበት አጋጣሚ አለ። የጋሼ አበራ ሞላ አብሪ ስራ ግን የከተሞቻችን የአደባባይ ምስጢር ሆኗል።
ቆሻሻ-ጠገብ ጥጋጥጎችን በአረንጓዴ መስኮች፤ የዝንቦች ማንዣበብን በንቦች መርበብ መተካት ማለት ግሩም ነው።
ይህ ስራው የአገር ውስጥም የውጪም ሽልማቶች ባለቤት አድርጎታል።
ሁለቱ ድርጅቶችና ወገኖች በአጥቢያችንና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰሩና የሚያበሩ አብሪዎቻችንን ሁሉ ይወክላሉ ብዬ አምናለሁ። አብሪ ግለሰቦች ባይኖሩ አዲስ ነገርን አሰራር መፍጠር ይቸግር እንደነበረው ሁሉ ድርጅቶች ባይኖሩ ደግሞ ዘላቂና ዘመን ተሻጋሪ ስራ መስራት አይቻልምና አብሪዎች ይኑሩ!

 =======

አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: