Sunday, November 25, 2012

በ2004 ዓ.ም.ጣራ ስር


(ጌታቸው አሰፋ፤ መስከረም 11  ቀን  2004 ዓ.ም.) እነሆ 2004 ዓ.ም. አለቀ።  ዓመቱን ከኢትዮጵያና ከዓለም የኃይልና የአካባቢ ጉዳዮች አኳያ በግርድፉ እንቃኘው።
የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ሰልት
የአገራችን “ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ” ሰነድ የተመረቀው በዚህ ዓመት ኅዳር ላይ ነው። አንዱ የሰነዱ ጥራዝ ራዕይ ላይ የሚያተኩር ሲሆን ሁለተኛው ስልት ላይ የሚያተኩረው ነው። ሰነዱ የወትሮው ምጣኔ ሀብታዊ ‘ቀለም’ መቀየርንና የአገሪቱን የምጣኔ ሀብት አውታሮች እንዳልነበሩ የሚያደርግ የ’አየር ንብረት ለውጥን’  መመከት እንደ መነሻ ይዟል። የስልት ሰነዱ ባለ 64 ገጾች ዋና ክፍል ይዞ በባለ130 ገጾች አባሪ የታጀበ ነው። በሰነዱ መጀመሪያ ላይ እንደተጠቀሰው ራዕዩ በ2030 እ.አ.አ. አገሪቱን ባለመካከለኛ ገቢ ደረጃ የሚያደርሰው የምጣኔ ሀብት ክንውን እውን የሚሆነው ልማትንና አዛላቂነትን የሚያመጣ አረንጓዴ የእድገት ፈለግ በመከተል ነው። የአረንጓዴው ኢኮኖሚ ግንባታ በአራት ምሰሶዎች ላይ የተመሠረተ ይሆናል። ከእነዚህ ሦስቱ ግብርና፤  የደን ልማትና የኃይል ማመንጫ ናቸው። አራተኛው ምሰሶ እነ መጓጓዣ የኢንዱስትሪው ዘርፍና ህንጻዎች የታጨቁበት ‘ሌሎች’ ክፍል ነው። አጠቃላይ በ2003/2004 ዓ.ም. የአገሪቱ የካርቦን ዳይኦክሳይድ የልቀት አቻ መጠን 150 ሚልዮን ቶን እንደሆነ ይጠቅሳል። ሰማንያ አምስት ፐርሰንት የልቀቱ መጠን የሚመጣው ከግብርና ዘርፍና ከደን ዘርፍ ሲሆን የኃይል ማመንጫ ሦስት ፐርሰንት፤ መጓጓዣ ሦስት ፐርሰንት፤ ኢንዱስትሪ ሦስት ፐርሰንት፤ እንዲሁም ህንጻዎች ሦስት ፐርሰንት ያህል ያዋጣሉ።  በተለመደው አሠራር ከተቀጠለ በሃያ ዓመት ውስጥ ማለትም በ2030 እ.አ.አ የአገሪቱ የልቀት መጠን በካርቦን ዳይኦክሳይድ አቻ ሲሰላ ወደ 400 ሚልዮን ቶን ይደርሳል - አሁን ካለው ወደ 250 ሚልዮን ቶን ጭማሪ ማለት ነው። ከሚጨምር የሕዝብ ብዛትና ከሚያድግ ኢኮኖሚ ጋር ተጣጥሞ የሚሄድ ዜሮ የልቀት ጭማሪ ግብ ያሳካሉ የተባሉ ከስድሳ በላይ ሥራዎች ተለይተዋል። ከነዚህም ከፈጣን ትግበራ አንጻር አራት ሥራዎች ቅድሚያ ተሰጥቷቸዋል። እነዚህም የውኃዊ ኃይል ሀብታችንን በስፋት መጠቀም፤  የበለጸጉ የገጠር የማብሰያ ቴክኖሎጂዎች በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል፤ የከብት ልማት የእሴት ሰንሰለትን ስልጠት ማሻሻልና ከደን ምንጠራና ጉስቁልና ጋር የተያያዘውን ልቀት መቀነስ የሚሉት ናቸው።
የደርባኑ ጉባኤ
የደርባኑ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የተካሄደውም በዚህ ዓመት ነው። ከኅዳር 18 ጀምሮ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እስከ ኅዳር 29 ቀጥሎ ባለ 200 ገጽ ዋና ዋና የውሳኔ ሀሳቦችን የያዘ የስምምነት ሰነድ ይዞ ወጣ።
የመጨረሻው ስምምነት ዋናው አካል የሆነው የወደፊት ዓለም አቀፍ የልቀት ቅነሳ ስምምነትን የሚመለከተው ስምምነት ነበር። ይህ የወደፊት ስምምነት ይዘቱ አሁን አይታወቅም። ይዘቱን የሚወስነው ድርድር የሚጀመረው በሚቀጥለው ዓመት(2012 እ.እ.አ.) ሲሆን የሚጠናቀቀው ደግሞ በ2015 እ.አ.አ. ነው። የወደፊቱ ስምምነት ከ2020 እ.አ.አ. ጀምሮ ነው ተግባራዊ የሚሆነው። ከኪዮቶ ፕሮቶኮል በተለየ መልኩ የወደፊቱ ስምምነት እነ ቻይና፤ ህንድ፤ ብራዚልና ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ ሁሉንም አገሮች እንዲያካትት ነው ደርባን ላይ ስምምነት የተደረሰው።  ‘እስከ 2020 እ.አ.አ. ባሉት ዓመታትስ ምን ይደረግ?’ ለሚለው ጥያቄ ደርባን የሰጠችው መልስ የአውሮፓ ኅብረት የፍኖተ-ካርታ ሀሳብ  መሠረት የኪዮቶ ፕሮቶኮል በሁለተኛው ዙር እንዲቀጥል የሚል ነው - በተወሰኑ አገሮች ብቻም ቢሆን።  የአረንጓዴ አየር ንብረት ፈንድ ሥራ እንዲጀምር ከመወሰን ባለፈ ገንዘቡ ከየት፤ እንዴት፤ በምን መጠን እንደሚመጣ ደርባን ይሄ ነው የሚባል ውሳኔ አላሳለፈም። ቀደም ብሎ የነበረው ስምምነት ከ2010 እስከ 2012 እ.አ.አ. ድረስ ለመነሻ የሚሆን 30 ቢልዮን ዶላር እንዲኖር ከ2020 እ.አ.አ. ጀምሮ ደግሞ በዓመት 100 ቢዮልን ዶላር የሚደርስ መጠን እንዲሆን ነበር። እስካሁን የተጀመረ ነገር ለመኖሩ ምንም ምልክት የለም። ታዳጊ አገሮች ወደ ደርባን የሄዱት ፈንዱ በአፋጣኝ ገንዘብ ያለው እንዲሆን፤ ከገንዘቡም ግማሽ በግማሽ ለስርየትና ለማጣጣሚያ ሥራዎች የሚውል ሆኖ እንዲዋቀር ለማስደረግ ነበር። ይልቁንም በደርባን ስምምነት ፈንዱ ለግል ኩባንያዎች ብሔራዊ፤ ክልላዊና ዓለም አቀፋዊ የስርየትና የማጣጣሚያ ፕሮጄክቶችን እንዲፈጽሙ የሚያስችል ተደርጎ መዋቀሩ የፈንዱን ገንዘብ የምዕራባዊያኑ ትልልቅ ኩባንያዎች ሲሳይ እንዲሆን ሊያደርገው ይችላል የሚል ስጋት አለ። የቴክኖሎጂ ክንውንታም ሌላው የደርባኑ ስምምነት አካል ነው። የአየር ንብረት ቴክኖሎጂ ማዕከልና መረቦች ማቋቋም አንዱና ዋናው ሥራ ሲሆን የማዕከሉ አላማም ለታዳጊ አገሮች የሚሆኑ የስርየትና የማጣጣሚያ ቴክኖሎጂዎችን ማልማት፤ ማስፋፋትና ጥቅም ላይ ማዋል ነው። የተመዱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ማዕቀፍ ጽ/ቤት የማዕከሉን መቀመጫ ለመወሰን የሚረዳውን ሁኔታ ለማመቻቸት በሁለት ወር ውስጥ የመቀመጫ ሀሳቦችን መቀበል እንዲጀምር በደርባን ተወስኗል። የማጣጣሚያ ኮሚቴም ተቋቁሟል። የደን ምንጣሮን ለመቀነስ የሚያስችሉ ፕሮጄክቶችንም ለመደገፍና  በተቻለ መጠን ለመምራት ከስምምነት ላይ ተደርሷል። የካርበን ማስወገጃና ዕቀባ ፕሮጀክቶችም የኪዮቶ ፕሮቶኮል አንዱ አካል በሆነውና ‘የማይበክል የእድገት ክንውንውታ’ ተብሎ በሚጠራው ስልት ውስጥ እንዲጨመር ተደርጓል- በደርባን ። ተደምሮ ተቀንሶ በደርባን የተደረሰበት ስምምነት በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የሚደረገውን የተመድ የድርድር ሂደትን ከመበታተን አድኖታል። የዓለም የከባቢ አየር ሙቀት እየጨመረ እንዳይሄድ የሚታደግ ስምምነት ግን አይደለም። ሳይንሱ እንደሚያሳየው ከሁለት ዲግሪ ሴንት ግሪድ የጭማሪ ጣራ በታች ለመሆን ውኃ የሚቋጥር የቅነሳ ሥራ መሠራት ያለበት ቅድመ 2020 እ.አ.አ. ነው። ደርባን ግን ሁሉን አቀፍ አስገዳጅ የቅነሳ ሥራን ወደ 2020 እንዲገፋ ነው ያደረገው። በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረቱት የቅነሳ ቃል ኪዳኖች ላይ መሠረት ያደረጉት ስሌቶች የሚያሳዩት ደግሞ የከባቢ አየር ሙቀት ጭማሪ ከሁለት ዲግሪ በታች መሆኑ ቀርቶ ከሦስት እስከ አራት ሴንቲ ግሬድ ሊደርስ እንደሚችል ነው።  ‘ሁለት ዲግሪ ራሱ በዛ፤ አንድ ነጥብ አምስት ዲግሪ ነው መሆን ያለበት’ እያሉ ሲጮሁ ለነበሩት የትናንሽ ደሴታዊ አገሮች ስብስብና አፍሪካን ለመሳሰሉት የአየር ንብረት ለውጥ ተጠቂ ክፍለ ዓለሞች የደርባኑ ስምምነት ይዘት አልባ ነው። ከሁለት ዓመታት በኋላ የተመዱ የበይነ-መንግሥታት የአየር ንብረት ሳይንቲስቶች ቡድን ማለትም አይ.ፒ.ሲ.ሲ. አምስተኛው ሪፓርቱን ሲያቀርብ የቀጣይ ድርድሮች አካሄድና የወደፊቱ ስምምነት ይዘት ላይ የሚያደርሰው በጎ ተጽእኖ ይኖራል ተብሎ ተስፋ ይደረጋል።
ሌሎችና አሳዛኙ ክስተት
በዓለም አቀፍ ደረጃ በብራዚል 189 አገሮች የተወከሉበት የተመድ ሪዮ-ፕላስ-ሃያ ስብሰባ “የምንፈልገው መጪው ጊዜ” የሚል ስም ያለው ባለ 53 ገጽ ሰነድ ያወጣው ሰኔ ላይ ነበር። ሰነዱ ከአዛላቂ ልማት ጋር የተያያዙ የዓለማችን አካባቢያዊ፤ ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮች ይዘረዝራል፤ መፍትሔ የሚላቸውንና የሚያበረታታቸውንም ሀሳቦች አካቷል።283 አንቀጾች የያዘውና አሳሪና አስገዳጅ ሀረግ አልቦ የሆነው ሰነድ ወደ ስድሳ ጊዜ ያህል “ዳግም እናረጋግጣለን” ይላል። እርግጥ በሰነዱ ውስጥ አንዱ ሁለት አዳዲስ ነገሮች አልጠፉም -ብዙ ውኃ የሚቋጥሩ ናቸው ባይባልም። በአገራችን ከአካባቢና ከኃይል ጋር የሚያያዙ ሌሎች የተለያዩ ትንንሽም ትልልቅ የተከናወኑ ነገሮች አሉ።  ወደ 6000 MW የማመንጨት አቅም ያለው የኅዳሴው ግድብ ስራ ከተጀመረ አንድ ዓመት የሞላው በዚህ ዓመት ነው።  በተለምዶ ቆሼ ተብሎ ከሚጣረው የአዲስ አበባ ጥራጊዎች መካነ መቃብር ሆኖ ለ50 ዓመታት ሲያገልግል ከቆየው ቦታ 50 MW ኃይል የማመንጨት ስራ የሚሆንና፤ ወደኬኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል መሸጥ እንድንችል የሚያደርገን የማሰራጫ መስመር ለመስራት የሚያስችል ገንዘብ የተገኘው በዚህ ዓመት ነው። ዓመቱ ከመጠናቀቁ በፊት የሆነው ዋናው ክስተት ግን አሳዛኝ ነው። በአኅጉር ደረጃም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአካባቢ ጉዳዮች ዙሪያ ተደማጭ እና ተጽእኖ ፈጣሪ እንዲሁም ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀንድና በዙሪያ በኤሌክትሪክ ኃይል ‘ልዕለ ኃያል’ ለማድረግ ይሰሩ የነበሩት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሞት ተለይተውናል። አዲስ አዲስ ዓመት ለአካባቢና ለኃይል አቅርቦታችን!

 =======

አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: