Sunday, November 25, 2012

ስለኛ - አውደ ርእይ


(ጌታቸው አሰፋ፤ ሐምሌ 21  ቀን  2004 ዓ.ም.)ባለፈው ሳምንት የጀመርነው የቆሻሻ ጉዳይ በይክረም አቆይተን ለዛሬ ወቅታዊ ጉዳይ እናነሳለን። የፎቶ አውደ ርእይ በብሔራዊ ሙዚየም - እስከ ሐምሌ 17 ቀን ድረስ ይቆያል። አውደ ርእዩ ስለዛፍ፤ ስለውኃ፤ ስለአፈር፤ ስለሕይወት ነው። በአጭሩ ስለኛ። የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የአካባቢ ቀንን በማስመልከት በአካባቢ ጉዳዮችና በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ንቃተ ህሊናን ከፍ ማድረግ እንደ ዓላማ ይዟል።

ውኃማ አካላት ተካተዋል። በተለያየ መልኩ የባለሞያው ካሜራዊ አይን የዳሳሰቸው ሐይቆች አሉ።  የዝዋይ ሐይቅ
የአቢያታ ሐይቅ ከመድረቅ አንጻር በካሜራው እይታ ውስጥ የገቡ ናቸው። ድሮ ውሃ ጠገብ የነበሩት የሐይቆቹ ክፍሎች ደርቀው በሐይቅ ተሸፍነው የነበሩ አይመስሉም።  መኪና የሚነዳባቸው  ቦታዎች ወደመሆን መቀየራቸውን የሚያሳዩ ፎቶዎች አሉ። የጣና ሐይቅና የአዋሳ ሐይቅም በፎቶነት አሉ።  ከወንዞቻችንም የአባይ ወንዝ - በጢስ አባይነት- እና የአዋሽ ወንዝም ይገኙበታል።
የአዋሽ ወንዝ ጥቅጥቅ ባለ የውኃ አረም ንጣፍ ተሸፍኖ ጠመዝማዛው የወንዝ ውኃ መስመር አረንጓዴ ቀለም የተቀባ የአስፋልት ንጣፍ ይመስላል። ይህ በጎ መሳይ ንጣፍ ወደ አዋሽ ወንዝ በቀጥታና በገባሮቹ በኩል ከዓመት እስከዓመት የሚለቀቅበት የኢንዱስትሪ፤ የመኖሪያና የግብርና ዝቃጮች ድምር ሂሳብ ውጤት አንዱ መገለጫ ነው። ይህ የውኃውን የውስጥ ክፍል ሕይወት አልባ የሚያደርግ ንጣፍ የወንዙ የግርጌ ተጠቃሚዎች በቂ መጠንና ተገቢ ጥራት ያለው ውኃ እንዳያገኙ ያደርጋል። ከአበባ ምርት ጋር በተያያዘ የሚፈጠር ብክለት ደግሞ ከሁለት በላይ በሆኑ ፎቶዎች ተወክሏል። 
በአውደ ርእዩ ውስጥ ከቀረቡት ፎቶዎች መካከል በጣም ጉልበት ያለው መልእክት የሚያስተላልፉ አሉበት። የአንዱ ፎቶ ድባብ ግን ከሁሉም ልቆብኛል። ለጸሎት ያቀረቀሩ የሚመስሉ አዛውንቶች ይታያሉ። አንዱ ችግኝ በእጃቸው ይዘዋል።  ከፎቶው ይዘት ባልተናነሰ ከስሩ የተጻፈው መግለጫ ብዙ ይላል - “ጌታ ሆይ ይችን ችግኝ የእኔ እድሜ ያህል እንድትኖር ባርካት።” (የእንግሊዝኛው መግለጫ ወደ አማርኛ ሲመለስ)። የእድሜ ባለጸጋ ዛፎች እጥረት የወለደው ጸሎት። የመትከል ችግር በሌለበት የማጽደቅ፤ የማሳደግና የመጠበቅ ጥብቅና ተከታታይ ስራ ግን ባጠረበት ሁኔታ የተገለጸ ናፍቆት።  ከዛ ታልፎ ከሚታዩት ፎቶዎች ላይ ደግሞ ‘የዛፍ ያለህ!’ የሚሉ ደረቅ ቦታዎች ይታያሉ። የህጻናት የእናቶችና የአዛውንቶች የሕይወት ሸክም የሚያሳዩ ፎቶዎችም ይገኛሉ።
በአንዱ ፎቶ ‘የምጠላጠልበትና የምቀመጥበት ዛፍ ከሌለ የላስቲክ ወንበራችሁን ልጋራ’ የምትል የምትመስል ዝንጀሮም ቁጢጥ ብላ ትታያለች - ተደርደረው ከተቀመጡት የላስቲክ ወንበሮች አንዱ ላይ።
አውደ ርእዩ በምድር ቤትና ከላይ ባለው ክፍል በየግድግዳው ከተሰቀሉት ፎቶዎች በተጨማሪ በቁስና በድርጊት የሚገለጹ መልእክት አስተላላፊ ርእዮችም አሉት። ለምሳሌ ባህር ዛፍ በየበቀለበት አካባቢ ላይ የሚያሳድረው ምንጮችንና የከርሰ ምድር ውኃን የማድረቅ መዘዝ ላይ የተንተራሰና  ‘ከእነመጥረቢያው ወደ መቃብር መውረድ አለበት!’ ከሚል እምነት ጋር የሚተሳሰር የሚመስል ድርጊት አንዱ ነው። ለዚህም ገርበብ ተደርጎ የተቀመጠ የሬሳ ሳጥን ውስጥ የባህር ዛፍ ቅርንጫፎች ተቀምጠዋል። ትእይንቱ ምልክታዊ ኃይል አለው። ከእንጦጦ የመጡ የተለያዩ የዛፍ መቁረጫ መሳሪያዎችን የያዙ ዛፍ በመቁረጥ የሚተዳደሩ ወገኖችን የሚወክሉ ነበሩ። ጠርሙሶችና ቆርኪዎች የተንጠለጠለባቸው የሸንበቆና የአገዳ ሽርጦችና ተደራቢዎች የለበሱ ሴቶችም ነበሩ።
በአውደ ርዕዩ የሚታየው ነገር ሁሉ ጨለማማ ብቻ አይደለም። ያማሩ ለም ስፍራዎችንና  ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎችን የሚያሳዩ ፎቶዎችም አሉ። የአርሲ ነገሌ ፏፏቴን የሚያሳዩት ፎቶዎች እዚህ ውስጥ ይመደባሉ። ሌላው ‘ጽድት ያለ ነገር መስራት ይቻላል!’ እያለ አሰምቶ የሚናገረው የአዲስ አበባ ቄራን ‘የድሮና የዘንድሮ’ ምስልን በንጽጽር የሚያሳየው ፎቶ ነው። የአውደ ርእዩ አዘጋጅና ፎቶዎች አንሺው ባለሞያ ቢንያም ስለፎቶዎቹና ስለሚያስተላልፉት መልእክትና ስለሚያነሷቸው ችግሮች ሲናገር በስሜት ነው።  
‘የጠቀስካቸው ችግሮች ሁሉ አንድ ነገር በማድረግ ይፈታሉ ብለን ብናምን ያ ነገር ምንድነው?’ ብዬ ጠየቅኩት።
‘ዛፍ’ ሲል በአጭሩ መለሰልኝ። ዛፍ ከሌለ ውሃ የለም ነው ዋናው መልእክቱ። ዛፍ ከሌለ የምንሰራቸው ስራዎች ፍሬ አያፈሩም፤ ቢያፈሩም አይዘልቁም ነው። በርካታ አገራዊ ሀብት እየፈሰሰበት ያለውና ዘርፈ ብዙ አንድምታ ያለው የታላቁ ግድብም ቢሆን ግንባታው ከማለቁ በደለል የመሞላቱ ጉዳይ አይቀርም የሚል ስጋት አለው - ዛፍ ካልተተከለ።
‘እየተተከለ አይደለም እንዴ?’ ብዬ አስከተልኩ። ‘እዚህ አገር ዛፍ ይቀበራል እንጂ አይተከልም’ አለኝ በአጽንኦት።
አሳሳቢ ጉዳዮች በበዙበት አገር ውስጥ ሌላ አሳሳቢ ነገር መጨመር ከባድ እንደሆነ ግልጽ ነው። የሕይወታችን ድርና ማግ ስለሆኑት አፈርና ውኃ ማንሳት ግን ሌላ ተጨማሪ ማስፈራሪያ ወደ ችግር መዘርዝራችን ውስጥ መደመር ሳይሆን ያሉን ችግሮች ጭራቸው የት እንደሆነ የመጠቆም ያህል ነው። የፎቶ ባለሞያውን ቀልብ የሳቡት ችግሮች መነሻ በማድረግ ዝርዝር ጥናቶችና ምርምሮች ለሚያስፈልጋቸው ተገቢውን ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል። አስቸኳይ መፍትሔ የሚያስፈልጋቸውም እንዲሁ ተግባራዊና ተመጣጣኝ ምላሽ ሊያገኙ ይገባል። ከአሁን በፊት በሌላ ጽሑፍ እንዳነሳሁት ‘ዛፍ አይቆረጥ’  አይነትና መሰል ‘መፍትሔዎች’ ላይ ብቻ ሳንወሰን አማራጭና አዋጪ የኃይል ምንጮችን  አልምቶ ማዳረስ ያስፈልጋል። በዛፍ ቆረጣና በተያያዥ ስራዎች ለሚተዳደሩ ወገኖችም አማራጭና ቢያንስ ተመጣጣኝ ገቢ የሚያገኙባቸው መንገዶች እንዲኖራቸው ማድረግ ይጠበቅብናል - እንደ አገር።
የተለያዩ ጉዳዮችን የሚያነሱት የአውደ ርእዩ ፎቶዎች ጥሪ የሚያደርጉት ለተለያዩ ባለድርሻዎች ነው። ለባለሀብቶች፤ ለምሁራን፤ ለቴክኒክ ሰዎች፤ ለቤተሰቦችና ለጠቅላላው ህዝብ ‘አቤት’ የሚሉ በርካቶች ናቸው። ሁሉም ግን ጠንካራ የትድግና መልእክታቸውን የሚያስተላልፉት ለመንግሥት ነው።
ይህ አውደ ርእይ በፎቶ ጥበብ አድራሽነት የአካባቢ ጉዳይን ትኩረት የሚያሻው አጀንዳ  አድርጎ በማንሳት ወደ ተመልካቾች ማድረሱ ግሩም ነገር ነው። በአጠቃላይ ወደ መቶ የሚሆኑት ፎቶዎች ውስጥ የተሸፈኑት ጉዳዮች አይነትና ብዛትም ደስ ይላል። እንደማንኛውም ስራ ሊሻሻሉ የሚገባቸው ነገሮችም አሉ።  የአንዳንዶቹ  ፎቶዎች የአቀማመጥ ቅደም ተከተል ሳይዘበራረቅ በተሻለ ሁኔታ - ለምሳሌ ከሚያነሱት ጉዳይ አንጻር - ቢደረደሩ ይበልጥ ወጥና ሙሉ ‘ታሪክ’ የመናገር ኃይል ያገኙ ነበር የሚል እምነት አለኝ።  አንዳንዶቹ ፎቶዎች ከአውደ ርእዩ ዋና ማጠንጠኛ ርዕስ ጋር ለመገናኘታቸው እርግጠኛ መሆን ያልቻልኩባቸው ናቸው።
የፎቶዎቹ መግለጫዎች ሲሆን በአማርኛም ጭምር ቢደረጉ ጥሩ ነበር። ካልሆነም አሁን እንዳለው በእንግሊዝኛ ሆኖ የፎቶዎቹ መቼት (ጊዜና ቦታ)  የመሳሰሉትን ጨምሮ ተገቢ የጽሑፍ ማብራሪያ ቢኖራቸው ጥሩ ነበር። ፎቶዎቹ ውስጥ የሚታየው ቦታ አልፎ አልፎ ተጠቅሷል። የሌላቸው ግን ጥቂት አይደሉም (ለምሳሌ ድፍርስ ሆኖ ግን እጅግ ከመጉደሉ የተነሳ የክረምቱ ጢስ አባይ ያልመሰለንና ጠይቀን እሱ መሆኑን የተነገረን ፏፏቴ)። የተነሳበት ጊዜ መቼ እንደሆነ የሚሳይ ያለው ግን አላየሁም።  አውደ ርእዩ በቀጣይነት ወደፊት ሲታይ ፎቶዎቹ ቦታና ጊዜ የሚጠቅሱ እንዲሁም በተቻለ መጠን “በፊትና አሁን” የሚል አይነት አቀራረብ ቢኖራቸው የበለጠ ይሆናል። እነዚህ አስተያየቶች የፎቶ ባለሞያው የሚተጋለትን ተልእኮ የበለጠ ከማጠናከርና ውጤታማ ከማድረግ አንጻር የቀረቡ ናቸው።
አውደ ርእዩ በተመሳሳይ ርእስ ለሁለተኛ ጊዜ መቅረቡ የአካባቢ ጉዳይ ከአንድ ሰሞን ዘመቻ ማጠንጠኛ ከማድረግና ለህዝብ ግንኙነት ፍጆታ ከማዋል የዘለለና ወደ መፍትሔ የሚያመራ ስራ የመስራት ጅማሮ ምልክት ነውና ምስጋና ለባለሞያው። ነባራዊው ሁኔታ ‘የአካባቢ ጉዳይ ቅንጦት ነው’ የሚል ሃሳብና በፓለቲካዊ ፕሮፖጋንዳነት አይን የሚያይ አመለካከት በአንድ በኩል፤ ጉዳዩን ወደ ጥግ ወስዶ ‘አለቀ ደቀቀ’ ከሚል አቅጣጫ ብቻ የሚገኝ መረጃ ላይ የሚመሰረት አካሄድ በሌላ በኩል ጎልተው የሚታዩበት ነው።  ‘አዲስ ጉዳይ’ና ሌሎች ስፓንሶር ያደረጉት የፎቶ አውደ ርእይ ሁላችንም አዎንታዊ ሚና የምንጫወትበት ሜዳ ከመጥረግ አኳያ ጠቃሚ ነው። እስቲ አምስት ኪሎ ከሚገኘው ብሔራዊ ሙዚየም ብቅ ይበሉና ከአውደ ርእዩ ይቋደሱ።

 =======

አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: