Sunday, November 25, 2012

ተግባቦት

(ጌታቸው አሰፋ፤ ሰኔ 23 ቀን  2004 ዓ.ም.)   ባደጉት አገሮች ያሉት የከተማ ነዋሪዎች በከተማቸው ውስጥ ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ ለመንቀሳቀስ መኪና ባይኖር ይፈጅባቸው የነበረው ጊዜና በመኪና ሲጠቀሙ የሚፈጅባቸው ጊዜ ተቀራራቢ ሆኖ ነው የተገኘው - በአንዳንድ አገሮች የተደረጉ ጥናቶችን ስንመለከት። ለምን ቢባል በየመንገዱ ያለው በመኪና ብዛት የሚፈጠረው መጨናነቅና በየመብራቱ መቆም በመኪና መሄድ ሊያመጣው ይችልና ይገባ የነበረው በፍጥነት መድረስን ዋጋ ስላሳጣው ነው።
ስልክ ባልነበረብት ዘመን፤ ኢንተርኔት ባልነበረበት ዘመን፤ ኢንተርኔት ላይ መሰረት ያደረጉ የድምጽ ወምስል ቴክኖሎጂዎች ባልነበሩበት ዘመን ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ መጓጓዝ የግድ ነበር። በተለይ ቦታው ርቀት ካለው ብቸኛው አማራጭ ነበር - በአካል መንቀሳቀስ። አሁን ያለነው ደግሞ ሌላ ጊዜ ላይ ነው።  ሰው ካለበት ቦታ ሆኖ ባህርና ውቅያኖስ አቋርጦ ከሚገኝ ሌላ ቦታ የሚካሄድ ስብሰባን መካፈል የሚችልበት ነው - በአካለ ሥጋ መገኘት ሳያስፈልገው ። መምህራን እንዲሁ በአንድ ክፍለ ዓለም ሆኖ በሌሎች ክፍለ ዓለማት ለሚገኙ ተማሪዎች በቀጥታ በመተያየትና በመሰማማት ማስተማር የሚችሉበትም ነው።
እነዚህ አስቻይ ቴክኖሎጂዎች የትምህርታዊ መረጃ ልውውጥም ሆነ የቴክኖሎጂ ዕውቀት ዝውውርን በኃይለኛው እንዲካሄድ ለማድረግ ምክንያት ሆኗል። ዛሬና እዚህ በአካል ተገኝተን ከምናድርጋቸው ስብሰባዎችና ከምንሰጣቸው  ስልጠናዎች በቁጥርም ሆነ በጥራት የማይተናነሰው ክፍል የሚካሄደው በእነዚህ ኢንተርኔትን መሰረት ባደረጉ ቴክኖሎጅዎች ነው። አገራችን በዚህ ዘርፍ ገና ጀማሪ ትሁን እንጂ አነሰም በዛም የጥቅሙ ተካፋይ መሆን ጀምራለች። አገር ቤት ካሉ ተማሪዎች ቢያንስ እንደነ ስካይፒ በመሳሰሉ መሳሪያዎች የሚገናኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መምህራንና  አገር ውስጥ ከሚኖሩ ሸሪኮቻቸው ጋር በመሆን በዚህ መንገድ ጉዳዮችን የሚያሳልጡ በውጪ አገር የሚገኙ የቢዝነስ ሰዎች አሉ።
ከሰው ልጅ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ጋር የሚያይዘው የአካባቢ ተጽእኖ በደምሳሳው ስናየው በሁለት መልኩ ሊቀነስ ይችላል። አንደኛው ከእያንዳንዱ የምጣኔ ሀብት ዘርፍና እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘውን ልቀት የነጠላ መጠን መቀነስ ነው። ለምሳሌ የኃይል ማመንጫ ዘርፍ ቴክኖሎጂውን በመቀየር ወይም የኃይል ምንጩን በመለወጥ የነጠላ ልቀቱን መቀነስ ይቻላል። ሁለተኛው መንገድ ደግሞ እንቅስቃሴውን ማስቀረት ወይም በሌላ መተካት ነው። ለዚህኛው መንገድ ዋና ምሳሌ የሚሆነንና የዛሬ ጽሑፍ ዋና ፍሬ ነገር ማጠንጠኛ የሆነው የጉዞና ተግባቦት ጉዳይ ነው።  ከጉዞ ጋር የሚቆራኘው የአካባቢ ብክለት አላስፈላጊ ጉዞን በመቀነስና በማስወገድ ፤ አስፈላጊዎችንም  በመተካት ልንቀንሰው ወይም ልናስቀረው እንችላለን።
ከተግባቦት ጋር ስለሚገናኙት አስፈላጊ ስለሆኑ ጉዞዎችን እናንሳ። በዚህ ስር ስብሰባ ለመሳተፍ፤ በአንድ ስብሰባ ላይ ንግግር ለማድረግ መጓዝ፤ ወይም መደበኛ በአንድ ኩባንያ ቅርንጫፎች መካከል የሚደረግ ስብሰባ ለማካሄድ፤ ወይም አስተማሪዎች በሌላ ቦታ ከሚገኙ ተማሪዎቹ ጋር ለማስተማርም ሆነ ምርምር ለመምራት የሚያደርጉት ተግባቦት ሁሉ ይካተታል። ከአካባቢ ብክለት ቅነሳ አንጻር አንድ ሰው በቅርብ በሚገኝ ቦታ (500 ኪሎ ሜትር በታች) የሚደረግ ስብሰባ መካፈል ካለበት ሲሆን በባቡር ካልሆነም በአውቶብስ አለበለዚያ በመኪናም ቢጓዝ በአካባቢ ላይ የሚያደረሰው ተጽእኖ ከጉዞው አስፈላጊነት አንጻር ቅቡል ሊሆን ይችላል። ርቀቱ በጣም በጨመረ ቁጥር ግን ለምሳሌ ከአሜሪካም ሆነ ከአውሮፓ ወደ ኢትዮጵያ ለስብሰባም ሆነ ለማስተማር የሚደረግ ጉዞ በድምጽና በምስል ቴክኖሎጂዎች ዕገዛ ማስቀረት ከተቻለ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር መሆን አለበት።
በአገራችን ከትምህርት አኳያ በስፋት የተጀመረውን የከፍተኛ ትምህርት መስፋፋት የተጋረጠበት የጥራት ችግር አንዱ የሚያያዘው  ከመምህራን ብቃትና ብዛት ጋር ነው። ይህንን ችግር መሰረታዊ በሆነ መልኩም ባይሆን የአገር ውስጥ አቅም እስኪጎለብት ድረስ በውጪ ያሉ ፍላጎቱና ችሎታው ያላቸው ወገኖች የሚጫወቱት ሚና ቀላል አይሆንም።  እነዚህ ሰዎች ግን አገር ቤት ያሉ ተማሪዎችን ለማስተማርም ሆነ ወይም ደግሞ የአስተማሪዎችን አቅም ለመገንባት የግድ ውቅያኖስ አቋርጠው መጓዝ የለባቸውም። ሲጀመር እነዚህ ሰዎች ሲጓዙ የሚቆዩበት ወቅት ብቻ አይደለም በመደበኛ ስራቸውና ህይወታቸው ላይ ክፍተት የሚፈጥረው። በደርሶ መልስ ጉዞና ለጉዞው ዝግጅት የሚጠፋ ጊዜ አለ። ከጉዞው በኋላም ወደ መደበኛው ስራቸው ለመመለስ ጊዜ ይወስድባቸዋል። በተቃራኒው ደግሞ መጓዝ ሳያስፈልጋቸው ባሉበት ቦታ ሆነው መደበኛ ስራቸውና ህይወታቸው ላይ ያን ያህል ተጽእኖ ሳይፈጥርባቸው የድርሻቸውን መወጣት ይችላሉ። ከአካባቢ ብክለት አኳያ ከታየ ደግሞ የረጅም ርቀት ጉዞዎች የሚደረጉት በጄት አውሮፕላኖች ከመሆኑ አንጻር የጉዞ መኖርና አለመኖር ጉዳይ ትኩረት ሳቢ ነው። ከተለያዩ  የመጓጓዣ መንገዶች አንዱ የሆነው የአውሮፕላን ጉዞ በጣም በካይ ከሚባሉት መንገዶች አንዱ ነው። ስለዚህ እያንዳንዷን የአውሮፕላን ጉዞ ባስቀረን ቁጥር ከፍተኛ የአካባቢ ብክለት ቀነስን ማለት ነው።
እስካሁን ያየነው የኢንተርኔት መረብ የሚጠቀሙ የድምጽ ወምስል ቴክኖሎጂዎች ጉዙን በማስቀረት ከአካባቢ ብክለት ቅነሳና ለተጓዥ ተሰብሳቢና አስተማሪ የሚያስገኙትን ጥቅም ነው። ግን የጉዞው መቅረት ወይም መቀነስ ረብ በዚህ ብቻ የሚወሰን አይደለም። ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅምም አለው። አንድ ሰው ለማስተማር ሲሄድ ከሞላ ጎደል አገሪቱ የምታወጣው ወጪ አለ - የተጓዡን ወጪ ከመሸፈን አንጻር - ይህ አንዳንዴ እንደ ሁኔታው ቢሆንም።  ጉዞው ቀረ ማለት ይህም ወጪ ቀረ ማለት ነው። ቢያንስ ይቀንሳል።
የረጅም ርቀት ጉዞ አስቀርተን ግን በጉዞው ሊመጣ ይችል የነበረውን ጥቅም ሲሆን በእኩል ደረጃ ቢያንስ ግን ተቀራራቢ ጥራትና መጠን ያለው የተግባቦት አገልግሎት ከድምጽ ወምስሉ የቴክኖሎጂ አማራጭ መገኘት አለበት። ለዚህ ደግሞ ተደራሽነት፤ ፍጥነትና ጥራት ወሳኞች ናቸው።
እዚህ በምርምር አማካሪነት ከማስተምራቸውና ከማሰራቸው የዶክትሬት ተማሪዎች መካከል አንዱ እኔ ካለሁበት ከተማ በመኪና የሦስት ሰዓት መንገድ ላይ የሚኖርና የሚሰራ የቤተሰብ ኃላፊ ነው። ይህ ተማሪ መጀመሪያ ኮርሶች ለመውሰድ ወደ ዩኒቨርስቲው በሳምንት ለሁለትና ለሶስት ቀናት አንዳንዴም ለሳምንት ይመጣ ነበር። ከዛ እኔ እሰጠው በነበረው ኮርስ ግን ለተማሪው የስራና የቤተሰብ ጫና (በተወሰነ መልኩም ለአካባቢ ብክለት ቅነሳ ስንል) ተግባቦታችንን በስካይፒ አደረግነው። ከዛ ቀጥሎ በየሁለት ሳምንቱ አንድ ጊዜ የምርምር ስራው ምን ያህል እንደሄደ ለመገምገም በስካይፒ እንገናኛለን። ይህ መሆን የቻለው ስካይፒን ጨምሮ በኢንተርኔት ሊሰጡ የሚችሉ የድምጽ ወምስል አገልግሎቶች ጥራት ያላቸው በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን ህጋዊም በመሆናቸው ነው።
ሰሞኑን በሁሉም አቅጣጫ ያሉት ወገኖችን ሲያወያይ የከረመው በኢትዮጵያ መንግሥት በቅርብ ጊዜ ያወጣው አዋጅ እንደዚህ አይነት አገልግሎቶችን ህገወጥ የሚያደርግ በመሆኑ ከላይ ከጠቀስናቸው ነጥቦች አኳያ ስናየው ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ አለው። መንግሥት ይህን አዋጅ ያወጣበት ምክንያት ለራሱ ትተነው ሦስት ክፍልና አስራ ስምንት አንቀጽ አዘሉ አዋጅ ውስጥ በቀጥታ በፊደልና በተዘዋዋሪ በትርጓሜ ከትምህርታዊ መረጃ ልውውጥ፤ ከቴክኖሎጂ ዕውቀት ዝውውር፤ ከአካባቢ ተጽእኖና ከምጣኔ ሀብታዊ ጥቅም አንጻር አሉታዊ ሚና የሚጫወት ክፍል እንዳለው ግልጽ ነው - ከድምጽ ወምስል መረጃ ልውውጥ ጋር የሚያያዘው ክፍል።
ሲሆን በተቃራኒው ጠቃሚ መረጃ በስፋትና በጥራት የሚተላለፍበትን መንገድ ለማመቻቸት ተገቢ የቴክኖሎጂ ብቃት ያለው የምስል ወድምጽ ማስተላለፊያ ስርዓት አጠናክሮ መዘርጋት ይጠበቅበታል - መንግሥት።
ከላይ በጠቀስኩት መልክ በአገር ቤት ከሚገኝ ተማሪ ጋር በስካይፒ የትምህርትና የምርምር ውይይት ለማድረግ ያደረግነው  ተደጋጋሚ ሙከራ ከኢንተርኔቱ ፍጥነት ጋር ተያይዞ በተፈጠረ የጥራት ችግር ልንቀጥልበት አልቻልንም። ይህ አይነት ችግር ቢያንስ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ እንደ ዋና ችግር ታይቶ ተገቢውን ትኩረት ማግኘት አለበት። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አይነት ጠንቅ ያለው አዋጅ ከማውጣት በፊትም አጠቃላይ የተጽእኖ ግምገማ ማድረግ ይጠበቃል። አሁንም ጊዜው አልዘገየም -  በእንደዚህ አይነት ሁሉን አቀፍ ግምገማ ላይ የተመሰረተ አሰራር ለመዘርጋት። በሚቀጥለው እትም በዚህ ሳምንት በብራዚል ስለተጀመረው ስለ ተመድ ስብሰባ ከሸገር ይጻፋል - እድሜና ጤና ይስጠንና።


 =======

አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: