Sunday, November 25, 2012

ስብሰባ ቅዳ ስብሰባ መልስ!


(ጌታቸው አሰፋ፤ ሐምሌ 7  ቀን  2004 ዓ.ም.)  ባለፈው ቅዳሜ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት አካባቢ አዲስ አበባ ስገባ በጭጋጋማውና እርጥበታማው ማለዳ ከቦይንጉ መውጫ በር ላይ ቆሜ ከከተማይቱ ገላ በቅጽበት መቃኘት የምችለውን ያህል በስስት ስቃኝ የሆነ በተስፋ የረሰረሰ ደስታ ተሰማኝ - ከማውቃት በላይ ከምጠብቃት በላይ አረንጓዴ የሆነች መሰለኝ። የታየኝ ለውጥ በክረምቱ ምክንያት የተፈጠረ? ወይስ የመውረጃ መማው የሰጠኝ የሸገር ከፊል ቁንጮ የተገደበ እይታ? ወይስ የምር አዲስ አበባችን ለመለመች?

ከሁለት ቀን በኋላ እነዚህን ጥያቄዎች እያሰላሰልኩ ደስታም ተስፋም አልቦ ሆኖ ስላለቀውና ባለፈው ሳምንት ብራዚል ሪዮ ዴ ጄኔሮ ከተማ ስለተደረገው የተመድ ስብሰባ ለመጻፍ ተቀመጥኩ። ከሃያ ዓመት በፊት በዛች ከተማ ተሰባስበው የነበሩት የዓለም መሪዎች የተነጋገሩበትንና የወሰኑትን ቁም ነገር እንደ ማስፈንጠሪያ ተጠቅሞ የወደፊቱን ነገር ከምር ለመነጋገር ያላስቻለ ስብሰባ - የያኔውን ስብሰባ ‘ከማሰብ’ የዘለለ ቁም ነገር ያላስገኘ። የዓለም ቀልብ በአውሮፓ አገሮች የምጣኔ ሀብታዊ ድቀት በተያዘበት ወቅት የተደረገውና መክነው ከቀሩት ስብሰባዎች ስለሚመደበው ይህ ስብሰባ ወደ በኋላ እመለስበታለሁ።  እርግጥ ነው አውሮፓ የአሜሪካ፤ የካናዳ፤ የጃፓንና የቻይና ትድግና በእጅጉ በምትፈልግበት በዚህ ወቅት የአዛላቂ ልማት ጉዳይ ቅድሚያ ባይሰጠው አይገርምም። እንኳን ዛሬ ዓለም በምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ መናጥ ብርቋ ባልሆነበት ዘመን ቀርቶ በደጉ ዘመንም ቢሆን የአዛላቂ ልማት ጉዳይ በአካባቢያዊ አዛላቂነት መነጽር ከማየት ይበልጥ ደምሮ ቀንሶ በምጣኔ ሀብታዊ ዓይን ማየት የዓለማችን ገዢ ሃሳብ ነበር። የእነ ግሪክ ከጨዋታ መሆንና ግሪኮች የእለት ጉርስ ሳይቀር በእርዳታ ለማግኘት በአደባባይ እየተጋፉ ወረፋ በሚይዙበት ወቅት የአካባቢ ፋይል ወደ ታች መቀበሩ አይደንቅም።
የዛሬ ሃያ ዓመት በብራዚል ሪዮ የተደረገው ስብስብ የተሳካ ነበር - በርካታና ዋና ዋና መሪዎች የተገኙበት። ዝርዝር ስምምነቶች የተደረሱበትና ለመፈረም የበቁበት ነው። የበረሃማነት መስፋፋትን ማስቆም ላይ ያነጣጠረ አንድ ስምምነት፤ ብዝኃ ሕይወት ላይ የሚያተኩር ሌላ ሰነድ፤ ለእነ ኪዮቶ ስምምነትና ከዛም በኋላ ላሉትና ለሚኖሩት ስምምነቶችና ድርድሮች እናት የሆነው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ማእቀፍም የተቀረጸው በሪዮው ስብሰባ ነበር።  አዛላቂ ልማትን ከንድፈ ሃሳብ በዘለለ በከተሞች ወይም በማንኛውም የአጥቢያ አስተዳደራዊ ነቁጥ ደረጃ ለመተግበር ምን ምን መደረግ አለበት የሚተነትን አጀንዳ 21 የተባለ ሰነድም ውልደቱ በሪዮ ከተማ በዛው ዓመት ነበር።
አርጩሜና ካሮት
ለአንድ ዓለም አቀፋዊ ስብሰባ ስኬት ወሳኙ ነገር የስብሰባው ጉዳይ ዙሪያ ተሰብሳቢዎች ቅድመ ስብሰባ በነበረው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ መነሻነት ጭነውት የሚመጡት የመረጃ፤ የመነሳሳትና የቁርጠኝነት ወዘተ ነዳጅ መጠን ነው። ይህ ነዳጅ መጠኑ ከስብሰባው በኋላም ወደ ውሳኔዎች ትግበራ ሲገባ የሚበቃ መሆን አለበት። ትግበራው ላይ ሜዳና ቁልቁለት እንዳለ ሁሉ ‘ወይ ፍንክች!’ የሚል ዳገትም አለ። ወደ ሪዮ ሲኬድ የተያዘው ነዳጅ ጥሩ ጥሩ ስምምነቶች፤ ጥሩ ጥሩ ሰነዶችን ለማስገኘት በቂ ነበር። ከዛ በኋላ ግን ብዙ ሊያስኬድ አልቻለም።  አንዳንድ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ከሌሎች በተለየ ተሰብሳቢዎች ወደ ስብሰባው ሲሄዱ በየአገራቸው ወይም በየአካባቢያቸው ወይም በዓለማችን ደረጃ የተገተረ ዳገት አልፈው የሚሆንበት ጊዜ አለ። ዳገቱ ጭራሽ እንዳይሄዱም ያደርጋቸዋል። ቢሄዱም ‘ግንባር ለማስመታት’ ብቻ ሊሆን ይችላል። የዚህ አይነት ስብሰባዎች ሲጀመር እንዲጨነግፉ የተፈረደባቸው ናቸውና ስምምነት ቢኖርም ባይኖርም ብዙም ለውጥ የለውም። የያኔው ሪዮ ከነዚህ ጭንግፎች የተለየ የነበረ ቢሆንም የተወለዱት ስምምነቶች ግን ለአቅመ ትግበራ አልበቁም። ሊያድጉ አልቻሉም። የተግባር ወግ ማዕረግ ለማየት አልታደሉም።  ሁሉ በእጃቸው ሁሉ በደጃቸው የሚባሉት የዓለም መሪዎች ሸንቆጥ አድራጊ አርጩሜና ወደፊት የሚስባቸው ካሮት ያስፈልጋቸዋል- እንደሌሎቻችን ሁሉ።  ወደፊት መሄድ የሚጠበቅበት ግን ባለበት የሚቆም አልያም ወደኃላ ለመሄድ የሚዳዳ አህያ በሁለት መንገዶች ወደፊት የማስኬድ ጥበብ የቆየ ነው። ከኋላ በአርጩሜ ሸንቆጥ ማድረግ እና ከፊት ለፊቱ ደግሞ ሲንቀሳቀስ አብሮት የሚንቀሳቀስና ‘ልድረስበት ልድረስበት’ የሚያሰኘው ለምለም ካሮት በገመድ ማንጠልጠል። እነዚህ ገፊና ሳቢ መንገዶች ለግል ዘርፉም ይሁን ለመንግሥታዊ ወሳኔ ሰጪ አካላት የሚያስፈልጉ ናቸው - ለዜጎችም። 
የዓለም መሪዎች  በስልጣናቸውና በአገራቸው ላይ የመጣ ግልጽና ተጨባጭ ተግዳሮት (በመራጮች የምርጫ ካርድ ንፍገትና ቅጣት በኩል የሚገለጽ) መሸንቆጫ ሽመል ያስፈልጋቸዋል - ዘላቂና ተግባራዊ መፍትሄ የሚያመጣ ስብስባ ላይ ተሯሯጠው ለመገኘት፤ከልብ ለመወያየትና ጥርስ ያላቸው ስምምነቶች ላይ ለመድረስ። ሽንቆጣው ቀጣይ ስራን የሚያስራ ክትትልን የግድ የሚያደርግ ኃይል ሲኖረው ‘አሸወይና’ ይሆናል። ይህ ብቻ አይደለም። ዓለም አቀፋዊው የፓለቲካ አህያ ሽንቆጣው እንዲንቀሳቀስ ግን ባለበት እንዲዞር ሊያደርገው ይችላል። ወደፊት እንዲሄድ የሚስበው የምጣኔ ሀብታዊ፤ የህዝብ ግንኙነትና የዜጎች ይሁንታ የማግኘት ካሮት ያስፈልገዋል። በብዙ ወሳኝ አገሮች የዚህ አጋሰስ ጉዞ በአራትና አምስት ዓመት ሲበዛ በስምንትና አስር ዓመት የተገደበ ነው። በመሆኑ ሽንቆጣውና ካሮቱ በዚህ የጊዜ ርዝመት ክልል ውስጥ የሚፈለገው ያህል ርቀት የሚያስኬድ አቅም ሲኖረው ነው ጥቅም የሚሰጠው። ተተኪው ኃይል ለእሱ በአይነትም በመጠንም የተቀረጸ አርጩሜና ካሮት ካላገኘ የተጀመረውን ጉዞ ሊያቆመው ይባስ ብሎም ወደኋላ ሊመልሰው ይችላል (የዲሞክራሲ የጎንዮሽ ጉዳት ይሏል ይህ ነው)። ሁሌ በሁሉ ቦታ ደግሞ በስልጣን ላይ ላለው ኃይል የሚመጥን ተስፍሮ የተለካ መሸንቆጫና ካሮት አይገኝም።  ለዚህም አይደል በየጊዜው በየቦታው ስብሰባ እየተደረገ፤ ስምምነት እየተፈረመ፤ በሰነድ ላይ ሰነድ እየተደረደረ፤ ጉዳዩን ሁሉ ‘ጨዋታ ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ’ አድርገነው ሌላ ዙር ስብሰባ፤ ስምምነትና ሰነድ ውስጥ የምንገባው?
ሃያ ዓመት ወደኋላ?
በሪዮ ከዛሬ ሃያ ዓመት የተደረገው ስብሰባ ተከታይ በመሆኑ የዘንድሮው ሪዮ ፕላስ ሃያ ተብሎ ይጠራል። ከያኔው አኳያ ሲታይ የባለፈው ሳምንቱ በተሳታፊ ብዛትም በይዘትም እዚህ ግባ የማይባል በአንዳንዶች ዘንድ ‘ሪዮ ማይነስ ሃያ’ አልያም ‘ሪዮ ፕላስ ሃይ ማይነስ አርባ’ እያሉ እስኪተቹት ድረስ ዓለምን ወደፊት ከመውሰድ ይልቅ ወደኋላ የመለሰ ሆኖ ተገኝቷል። መቶ ርእሳነ ብሔርና መራህያነ መንግሥት የተገኙበት ስብሰባ የአሜሪካው ኦባማ፤ የእንግሊዙ ካሜሩን፤ የጀርመኗ መርኬል፤ የካናዳው ሃርፐር ላለመገኘት የወሰኑበት ሆኗል።  በዘጠኝ ቀናት ቆይታው ከ 45,000 በላይ ተሳታፊዎችን አስተናግዷል። 189 አገሮች የተወከሉበት ስብሰባ ሲጠናቀቅ “የምንፈልገው መጪው ጊዜ” የሚል ስም ያለው ባለ 53 ገጽ ሰነድ አውጥቷል። ሰነዱ ከአዛላቂ ልማት ጋር የተያያዙ የዓለማችን አካባቢያዊ፤ ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮች ይዘረዝራል፤ መፍትሔ የሚላቸውንና የሚያበረታታቸውንም ሀሳቦች አካቷል። የዛሬ አርባ አመት በስቶክሆልም የዛሬ ሀያ አመት በሪዮ እንዲሁም የዛሬ አስር ዓመት በጆሃንስበርግ ግንዛቤ የተወሰደባቸውና ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮችን እውቅና እንደሚሰጥ ያትታል። 283 አንቀጾች የያዘውና አሳሪና አስገዳጅ ሀረግ አልቦ የሆነው ሰነድ ወደ ስድሳ ጊዜ ያህል “ዳግም እናረጋግጣለን” ይላል። እርግጥ በሰነዱ ውስጥ አንዱ ሁለት አዳዲስ ነገሮች አልጠፉም -ብዙ ውኃ የሚቋጥሩ ናቸው ባይባልም።አንደኛው እስካሁን የነበረው የተመድ የአዛላቂ ልማት ኮሚሽንን ቀስ በቀስ እንዲተካው ተደርጎ የሚዋቀር ‘ሁለንተናዊና ከፍተኛ የበይነ-መንግሥታት የፓለቲካ መድረክ’  መቋቋም በተመለከተ የሚጠቅሰው ክፍል ነው። ሁለተኛው ደግሞ ከሥራ ውጪ ለመሆን ከሦስት ዓመት ያነሰ ጊዜ የቀራቸው ‘የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች’ን በ’አዛላቂ ልማት ግቦች’ እንዲተኩ የሚያደርገው ክፍል ነው። ከምር ለሚያስብና ከእንደዚህ አይነት ስብስብ ተጨባጭ ውጤት ለሚጠብቅ ተቆርቋሪ  ‘ከአንድ እስከ አራት አስርት ዓመታት በፊት ያልነውን ነገር ‘ዛሬም እንለዋለን!’ ለማለት ብቻ አካባቢን የሚበክሉ ረጃጅም የአውሮፕላን ጉዞዎች አድርጎ ሪዮ ድረስ መሄድ ለምን አስፈለገ?’ ያሰኛል። የ‘ስብሰባ ቅዳ ስብሰባ መልስ!’ አካሄድስ የሚቀረው መቼ ይሁን?

 =======

አዲስ አበባ ላይ ገበያ ላይ በዋለው  “አዲስ ጉዳይ”  መጽሔት  ላይ  መደበኛው   “የአረንጓዴ ጉዳይ” ዓምዴ ላይ  ታትሞ  የወጣ ጽሁፍ።  www.akababi.org

No comments: